>

የቀይ ኮከብ ዘመቻ (ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

የኤርትራ አማጺያንን ለማጥፋት ከተደረጉ ዘመቻዎች መካከል ብዙ የተባለለት ነው- የቀይ ኮከብ ዘመቻ፡፡ ታዋቂ የጦር ጠበብት እየደጋገሙ አውስተውታል፡፡ በጋዜጣና በሬድዮ ብዙ ተለፍፎለታል፡፡ አጀማመሩም ሆነ አፈጻጸሙ ትንግርተኛ መሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ዘመቻው የተካሄደበት ለየት ያለ ድባብና በርሱ ሳቢያ የተፈጠረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ “ኦሮማይ” የተሰኘው ተወዳጅ ድርሰት እንዲጻፍ ምክንያት ሆኗል፡፡

ያ ዘመቻ በኦፊሴል “የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ” ተብሎ ነበር የተሰየመው፡፡ የዘመቻው ዓላማዎችም ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ሻዕቢያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ነው፡፡ ሁለተኛው በጦርነቱ የፈራረሱ መሰረተ-ልማቶችን መገንባት ነው፡፡ ለዘመቻው “ቀይ ኮከብ” የሚል ስም የተሰጠው ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ-ማሪያም የአሜሪካ ባህር ሀይል “ብሩህ ኮከብ” (Bright Star) በሚል ስም በቀይ ባህር ላይ ላደረገው ወታደራዊ ልምምድ ምላሽ መሆን አለበት በማለት ባደረጉት ውሳኔ መሰረት እንደሆነ በወቅቱ የኤርትራ ክፍለ-ሀገር ኢሠፓአኮ ተጠሪ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “ቀይ እምባ” (Red Tears) በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡

የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ይፋ የተደረገው በሀገር አቀፍ ደረጃ በታወጀ ልዩ አዋጅ ነው፡፡ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስፈጽም ከፍተኛ ስልጣን የተሰጠው ሀገር አቀፍ ምክር ቤት ተቋቁሞለታል፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ሲሆኑ ዋና ጸሓፊው ኤርትራዊው አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል ነበሩ፡፡ የሀገሪቱ ምርጥ ምሁራን የተሳተፉበትና ድርጅታዊ ሀይሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላለት የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤትም አስመራ ላይ ተሰይሞም ነበር፡፡ ለዘመቻው ማስፈጸሚያ ከሁለት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ (በዛሬው የምንዛሬ ተመን ወደ ሀያ ቢሊዮን ብር ያህል የሚሆን) በጀት ተመድቦለታል፡፡ ዘመቻውን ለማስፈጸም በሚልም ከሊቀመንበር መንግሥቱ ጀምሮ ሀገሪቷ ያሏት ከፍተኛ ወታደራዊና የሲቪል ባለስልጣናት አስመራ ላይ ከትመዋል፡፡

የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ በይፋ የተከፈተው ጥር 17/1974 ነበር፡፡ የዘመቻውን መከፈት በሚያበስረው ጉባኤ ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሙያተኞች፣ መለዮ ለባሾች፣ የገበሬ ተወካዮች ወዘተ.. ተሳትፈዋል፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ጉባኤውን የከፈቱበት ንግግር በሬዲዮ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ተላልፏል፡፡ የአስራ አራቱ ክፍለ ሀገር ተወካዮችም በጉባኤው ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡ ጉባኤው ጥር 23/1974 ሲጠናቀቅ ሰባት ነጥቦች ያሉት “የአስመራ ማኒፌስቶ” በአቋም መግለጫ መልክ ይፋ ተደርጓል፡፡

የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጉባኤ በተከፈተበት ማግስት በቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው “ጉርጉሱም” የተባለች ሰርጥ ላይ የተዘጋጀው የምጽዋ ኤክስፖ በሊቀመንበር መንግሥቱ ተመርቋል፡፡ ዶጋሊ ላይ ሊገነባ ለታቀደው የራስ አሉላ መታሰቢያ ሀውልት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡትም ሊቀመንበር መንግሥቱ ነበሩ፡፡ በምጽዋ ከተማ በሚገኘው “አጼ ካሌብ አዳራሽ” ታሪካዊው የምጽዋ ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡ በአስመራና በምጽዋ ከተሞች የሚገኙ በርካታ ፋብሪካዎችም ተጠግነው የማምረት ተግባራቸውን እንዲጀምሩ ተደርገዋል፡፡ ከምጽዋ-አቆርዳት የተዘረጋው የባቡር መስመርም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህ ሁሉ ከተገባደደ በኋላ ነው ወታደራዊው ዘመቻ የተካሄደው፡፡
*****
የቀይ ኮከብ ወታደራዊ ዘመቻ በአራት ግንባሮች ነበር የተከናወነው፡፡
1. በብርጋዴር ጄኔራል አበራ አበበ የሚታዘዘው ውቃው እዝ በአልጌና በኩል (በሰሜናዊ ቀይ ባሕር ጠረፍ፣ ከናቅፋ ጀርባ እንዲያጠቃ)
2. በብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ የሚታዘዘው ናደው እዝ ከከረን ጀርባ ወደ ናቅፋ በር በከርከበት ግንባር (ከናቅፋ ደቡባዊ ምሥራቅ በኩል) እንዲያጠቃ
3. በብርጋዴር ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ የሚታዘዘው መብረቅ እዝ በቃሮራ ግንባር (ከናቅፋ ሰሜን ምዕራብ) እንዲያጠቃና የሻዕቢያን መውጫ እንዲዘጋ
4. በብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ጋሼ የሚታዘዘው መክት እዝ የአስመራን ዙሪያ እንዲያጥር የሚል ትዕዛዝ ተቀብለው ለውጊያ ዝግጁ ሆኑ፡፡

የካቲት 8/1974 ጎህ ከመቅደዱ በፊት በሁሉም ግንባሮች ወደ ናቅፋ የመጠጋት እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ የናቅፋ ተራሮች በቢ.ኤም. እና በሞርታር ተደበደቡ፡፡ ከሰማይ በሚወርዱ የአውሮፕላን ቦንቦች ታረሱ፡፡ ሮኬቶችና ካሊበሮች ተወናጨፉ፡፡ ናቅፋ እሳተ ጎመራ የፈነዳባት መሰለች፡፡ ሻዕቢያ መጥፊያው የተቃረበ መሆኑን ገምቶ ከናቅፋ ምሽጉ ሊወጣ ሲሰናዳ በሁሉም አቅጣጫዎች ዝግ ሆነበት፡፡ ስለዚህ ተራሮቹን የሙጥኝ ብሎ መከላከሉን ቀጠለ፡፡

የእግረኛና ሜካናይዝድ ውጊያ እንዲጀምር የታዘዘው በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የተሰለፈው መብረቅ እዝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እዙ በታቀደለት ሰዓት ባለመንቀሳቀሱ ሻዕቢያ በርቀት ያሉ ሀይሎቹን እንዲያሰባስብ ጊዜ ሰጠው፡፡ በሌላ በኩል ለዚሁ የመብረቅ እዝ ግንባር ቀደም ሆኖ የማጥቃት ግዳጅ የተሰጠው 21ኛ ተራራ ክፍለጦር በብቃቱ እንደተጠበቀው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ክፍለ-ጦሩ በተያዘለት እቅድ መሰረት ወደ ናቅፋ ተራሮች ምዕራባዊ ክፍል ተጠግቶ ሻዕቢያን ማባረር አቃተው፡፡ ይባስ ብሎም ጠላት በሰራለት ቀለበት ውስጥ ገብቶ ተከበበ፡፡ ሻዕቢያም ባለ በሌለ ኃይሉ ተረባረበበት፡፡ የተራራ ክፍለ ጦርም ተፍረከረከ፡፡ ሺዎች በሜዳ ላይ እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡

የውቃው እና የናደው እዞች የተሻለ ጀግንነት አሳይተው ከናቅፋ ስምንት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ደረሱ፡፡ ይሁንና ባልታወቀ ምክንያት በተሰጠ ትዕዛዝ እንቅስቃሴአቸው ተገታ፡፡ ከዚያ በኋላ እንንቀሳቀስ ቢሉ የማይቻል ነገር ሆነ፡፡ ሻዕቢያ ተዋጊዎቹን ከያሉበት አሰባስቦ ወደ ኋላ ይገፋቸው ጀመር፡፡ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው መልሶ ማጥቃት በአፋቤት (ከርከበት) ግንባር በዘመተው ናደው እዝ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፡፡ ሺዎች ሙትና ቁስለኛ ሆኑ፡፡ በትልቅ ሞራልና የድል ጉጉት የተጀመረው የቀይ ኮከብ ዘመቻም በከፍተኛ ሽንፈት ተፈጸመ፡፡
*****

የውቃውና የናደው እዞች ከናቅፋ አጠገብ ደርሰው እንዲቆሙ የተደረገበት ምክንያት እስከዛሬ ድረስ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ሻለቃ ጌታቸው የሮም በጻፉት መፅሐፍ “አንድ ከፍተኛ የኢሠፓ ባለስልጣን ሻዕቢያ እያዘናጋችሁ ሊፈጃችሁ ስለተዘጋጀ መቆም አለባችሁ’ የሚል ትዕዛዝ ስለሰጠ ነው” ይላሉ፡፡ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው “የጦር ሀይሎቹ መዋጋት ያቆሙት ናቅፋን የመያዙ ተግባር ሊቀመንበር መንግሥቱ ረጅም ዕድሜአቸውን ባሳለፉበት አንበሳው ሶስተኛ ክፍለ ጦር እንዲፈጸም ስለተፈለገ ነው” በማለት ጽፈዋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ግን ይህንን አባባል በከፍተኛ ቁጣ አስተባብለዋል፡፡ “ከሁሉም ጦሮች ቀድሞ ናቅፋ የደረሰውና ያለቀው ሶስተኛ ክፍለጦር ነው” በማለትም ተከራክረዋል፡፡

ለዘመቻው አጠቃላይ ውድቀት መንስኤ የሆነው ምክንያትም በታሪክ ጸሐፊዎችና በወታደራዊ ጠበብቶች ስምምነት አልተደረገበትም፡፡ ይሁንና አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) በጻፉት “ነበር” የተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ የሰነዘሯቸው ነጥቦች ብዙዎችን የሚያስማሙ ይመስላሉ፡፡ እነርሱም

1. የመብረቅ እዝ በተሰጠው ሰዓት መሰረት ግዳጁን አለመፈጸሙ
2. ለኤርትራ መሬት እንግዳና ባዳ የሆነውና በቅርብ ጊዜ ከማሰልጠኛ የወጡ ሀይሎች የተሰባሰቡበት 21ኛው ተራራ ክፍለጦር ግንባር ቀደም መቺ ሀይል ሆኖ ወደ ናቅፋ እንዲዘምት መደረጉ
3. ሊቀመንበር መንግሥቱ ለድል በመቸኮላቸው የውጊያው እቅድ ሲከለስ ከወታደራዊ አዛዦች የተሰጡትን የእርማትና የማሻሻያ ሐሳቦች ጨርሶ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው (ለምሳሌ ጄኔራል አበራ አበበ 21ኛው ተራራ ክፍለጦር አስተማማኝ ባለመሆኑ ግዳጁ ለሌላ ጠንካራ ክፍለ ጦር እንዲሰጥ ያቀረቡትን ሐሳብ ጨርሶ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው)፡፡
4. የእዞቹ አዛዦች በእቅዱ ሳያምኑበት ወደ ውጊያ የገቡ መሆናቸውና ሌሎችም ምክንያቶች ናቸው፡፡

የቀይ ኮከብ ዘመቻ በውድቀት ከጨነገፈ በኋላ የውድቀቱ መንስኤ ተጠንቶ ለውሳኔ እንዲቀርብ ታዘዘ፡፡ በዘመቻው የውጊያ ኢኒስፔክሽን መምሪያ ሃላፊ የሚመራ ቡድን የመብረቅ እዝ ወደ ሚገኝበት ቃሮራ ግንባር ተላከ፡፡ ቡድኑ ማጣራቱን ካከናወነ በኋላ የ21ኛው ተራራ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ውብሸት ማሞ እና የክፍለጦሩ 47ኛው ብርጌድ አዛዥ የሆኑት ሌ/ኮ/ል ስለሺ አስፋው የውድቀቱ ተጠያቂዎች ናቸው ተባሉ፡፡ ሁለቱ መኮንኖች በልዩ ትዕዛዝ ከተቋቋመ የጦር ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው በተላለፈባቸው ፍርድ መሰረት ኮ/ል ውብሸት ማሞ ተረሸኑ፡፡ ሌ/ኮ/ል ስለሺ አስፋው ደግሞ ማዕረጋቸውን ተገፍፈው ወህኒ ወረዱ፡፡ የመብረቅ እዝ ዋና አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ ወደ አስመራ ተጠርተው በቁም እስረኛነት ለረጅም ጊዜ ተቀመጡ፡፡
*****

አንድ ዓመት ሙሉ ዝግጅት የተደረገበት የቀይ ኮከብ ዘመቻ በዚሁ መልክ ነበር የተደመደመው፡፡ ሁለት ቢሊዮን ብር በሁለት ወር ተንኖ ውስጥ ተንኖ ቀርቷል፡፡ ታዲያ ሊቀመንበር መንግሥቱ የባሰ እልህ ይዞአቸው “ቀይ ኮከብ ሁለት” እና “ቀይ ኮከብ ሶስት” የተሰኙ ዘመቻዎችን ሞክረው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን ሊሰምርላቸው አልቻለም፡፡ በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት ኮ/ል መንግሥቱ ዘመቻው እንዳበቃ የናደውና የውቃው እዞች የናቅፋን ዙሪያ አጥረው እንዲቆዩ ቢደረግና ለኤርትራ ችግር ሰላማዊ መፍትሔ ወደ ማፈላለጉ ቢሄዱ ኖሮ ጥሩ ውጤት በተገኘ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዘመቻው ሻዕቢያንም ክፉኛ ያደከመ በመሆኑ ምናልባት አማጺው ሀይል ሰላማዊውን አማራጭ ይቀበል ነበር ተብሎ ይታሰብ ነበርና፡፡

የቀይ ኮከብ ዘመቻ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ነው ያለፈው፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት በዘመቻው ማብቂያ ላይ ባጋጠመው ውድቀት ክፉኛ ተናግቷል፡፡ የወታደሮቹ ስነ-ልቦናም በጣም ተቃውሷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የጦር ሀይል ወደ ናቅፋ መጠጋት ይፈራ ነበር፡፡ ዘማቾች “ናቅፋ” ከተባለ “ሞት” ብቻ ነበር የሚታያቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ለሻዕቢያ ሀይሎች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ሆኖአቸዋል፡፡ “17,000 ሆነን ከ150,000 የሚልቅ፣ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና በአውሮፕላንና በቢ.ኤም የተጠናከረ ግዙፍ ሰራዊት ድል አድርገናል” በማለት እንዲኩራሩ አድርጎአቸዋል፡፡ ናቅፋንም “ምልክት ጽናትና” (የጽናታችን ምልክት) በማለት እንዲጠሯት መንስኤ የሆናቸው ይኸው ነው፡፡

—–

ምንጮች
1. Dawit Wolde-Giorgis, “Red Tears”: Famine, War and Revolution in Ethiopia, Red Sea Press, New York 1989
2. David Lamb, “Evil Days: Thirty Years of War and Famine in Ethiopia (1961-1991), Africa Watch Group, New York, 1991
3. Paul B. Henze, “Eritrea’s War”, Shama Books, Addis Ababa, 2002
4. ገነት አየለ፣ “የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች”፣ አዲስ አበባ፣ 1994
5. ጌታቸው ሀይሉ፡ “ቀያይ ተራሮች”፣ አዲስ አበባ፣ 1993
6. ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ፣ “አይ ምጽዋ”፣ አዲስ አበባ፤ 1997
7. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር”፣ አዲስ አበባ፣ 1996
8. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር 2”፣ አዲስ አበባ፣ 2001
9. ጌታቸው የሮም፣ “ፍረጂ ኢትዮጵያ”፣ አዲስ አበባ፣ 1993

Filed in: Amharic