>
12:52 pm - Wednesday December 1, 2021

ኢትዮጵያዬ! (ዘ-ሕሊና)

እንጀራ አ’ርጎ ሠርቶሽ
መጠቅለል የሚያውቁ እየቆራረሱሽ
ጠቅልለው ጠቅልለው ጠቅልለው ጎረሱሽ።

እናት ዓለም!

ቆጮ አድርጎ ሠርቶሽ
መክተፍን የሚያውቁ ለከተፉት ክትፎ ማባያ አደረጉሽ።

አንባሻ አ’ርጎ ፈጥሮሽ
መሸንሸን የሚያውቁ – በስለት ሸንሽነው
ሸንሽነው ሸንሽነው – ሆዶች ተካፈሉሽ።

እናቴ!

ገንፎ አድርጎ ፈጥሮሽ
መውጋትን የሚያውቁ – ማንኪያ እየሰኩብሽ
ወጋግተው ሰካክተው – በጥርስ አስነከሱሽ።

ኢትዮጵያዬ!

ማንጎ አድርጎ ፈጥሮሽ
ማሞቅሞቅ የሚያውቁ – ማሟሟት የሚያውቁ
ክንዶች አሞቅሙቀው – ክንዶች አሟሙተውሽ
ጨርሰው መጠጡሽ።

ገብስ አድርጎ ፈጥሮሽ
ማሸትን የሚያውቁ – አሽተውሽ አሽተውሽ
አሽተውሽ አኘኩሽ።

ሀገሬ!

አምቾ አ’ርጎ ፈጥሮሽ
እንሰትሽ ተንጋሎ
ሥርሽ ተፈንቅሎ
ውስጥሽ ተቀቅሎ
ጎምደው ሰለቀጡሽ።

ኢትዮጵያዬ!

ሲፈጥርሽ…

አ’ርጎሽ ዳቦ ቆሎ
እየቆነጠሩ
እየቆረጠሙ
ቃሙሽ ቶሎ ቶሎ

ሲሠራሽ…

አርጎሽ ፍራፍሬ
ልጣጭሽን ልጦ
ውስጥሽን ቆራርጦ
በላሽ ምድረ-ጥሬ።

ሲወጥንሽ…

አርጎሽ ጥሬ ሥጋ
ሚጥሚጣ እያስነካ
አዋዜ እያስነካ
ዳታ እያስነካ
ዋጠሽ ከርሰ-መንጋ።

ሲጀምርሽ…

ለጥጆቹ ብሎ – አ’ርጎሽ ትኩስ ወተት
በዕቃ ‘ሚያልብሽ እንጂ – ‘ሚያስጠባ ጠፋበት።

ሲጀምርሽ…

አርጎሽ ትኩስ ወተት
የሚንጥሽ እንጂ – ‘ሚያረጋሽ ጠፋበት።

ሲያበጃጅሽ….

አርጎሽ ሱፍ አበባ
የሚቀስምሽ እንጂ – ማር ‘ሚሰጥ የት ገባ?

ኢትዮጵያዬ!

ሀላዋ አ’ርጎ ፈጥሮሽ
ጭብጦ አ’ርጎ ፈጥሮሽ
ባቅላባ አ’ርጎ ፈጥሮሽ
ቅቤ አድርጎ ፈጥሮሽ
አሬራ አ’ርጎ ፈጥሮሽ
እርጎ አድርጎ ፈጥሮሽ

ፈጥሮሽ-ፈጥሮሽ-ፈጥሮሽ

ምግብነትሽን ያየም – በልቶሽ-በልቶሽ-በልቶሽ
ሲነሣ የዋጠሽ

ቋምጦሽ-ቋምጦሽ-ቋምጦሽ
ሲመጣ የጎመጀሽ

…እየ..ታ..ኘ..ክሽ አለቅሽ።

ሀገሬ!

ጠጅ አድርጎ ሠርቶሽ
አረቄ አ’ርጎ ሠርቶሽ
ጠላ አድርጎ ሠርቶሽ

ሠርቶሽ-ሠርቶሽ-ሠርቶሽ

ይህንንም ያየ – እንዳገኘሽ ቀድቶሽ

ጅው አ’ርጎ እየጠጣ
በስካር መንፈሱ እላይ እየወጣ
የሚያወርደው ታጣ
አይ የስካር ጣጣ።

እምዬ!

ለነዳያን ሲሣይ ምግብ አ’ርጎ ሠርቶሽ
ቁንጣንን ‘ማይፈሩ በአዳፋ እጃቸው እያግበሰበሱሽ
ስንት ዘመን ተበላሽ?
ስንት ዘመን ተጠጣሽ?
ስንትስ ዘመን ታገስሽ?

ዋ ኋላ…

ርኀብተኛ ሕዝብ – ምግብነትሽን ያጣ
በጾም ማደር ካራ – አንጀቱ የተበጣ
በኮስታራ ሆዱ – “ዋ” ሲል ከተቆጣ
የጎረሰሽ ሁሉ – ያገኘዋል ጣጣ
የመጎረስ ዕድል – የመበላት ዕጣ።

ርኀብተኛ ሕዝብ – ምግብነትሽን ያጣ
በጾም ማደር ካራ – አንጀቱ የተበጣ
በማዛጋት ብሒል – “ሀ” ብሎ ካማጠ
አኝኮ የዋጠሽ – ታኝኮ ተዋጠ!
©ዘሕሊና

Filed in: Amharic