>
5:16 pm - Thursday May 23, 8126

መስቀል በጉራጌ ~ ቤተንዳ ጉራጌ! (ጌጡ ተመስገን)

ኢትዮጵያ:- መስቀል በጉራጌ ሲታሰብ ከመስከረም 13 እስከ መስከረም 24 ያሉ ቀናቶች ትርጉም አላቸው፡፡

መስከረም 13 
ወሬት ያህና ወይም እንቅልፍ ነሺ ቀን ይሉታል

በዚህ ቀን እንቅልፍ የሚታጣው ሁሉም ቤተሰብ መስቀልን ‹‹እንዴት አሳልፈው ይሆን?›› ብሎ ስለሚያስብ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዋች ቀኑን የበዓሉ መክፈቻ ይሉታል።

***
መስከረም 14 
ይፍት ወይም የዕርድ ዋዜማ

ቀን ሴቶቹ የቤቱን ጣራና ግድግዳ ካጸዱ በኋላ መሸት ሲል ለቤቱ ወለል የተሰሩት ምንጣፎች ይነጠፋሉ፡፡ የቤት ዕቃዋችና ጌጣጌጦች ግድግዳ ላይ ይሰቀላሉ፡፡ ቆጮው በተለየ መልኩ በእንፋሎት ብቻ እንዲበስል ይደረጋል፡፡ ይህም ‹‹ዳቡዬ›› በሚል ይታወቃል ፡፡

***
መስከረም 15
ወኀምያ ወይም የእርድ በዓል ተብሎ ይጠራል፡፡

ወኀምያ ደስታና ሰላም ማለት ነው፡፡ እለቱ በአንዳንድ አካባቢዋች ‹‹የጨርቆስ ማይ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ እለት ጨርቆስን ያመለክታል፡፡ በዚህ ቀን ለእርድ የተዘጋጁ ከብቶች በየቤቱ በራፍ ይታረዳሉ፡፡ ከበሬው የሚፈሰው ደም በቃጫ ተነክሮ የቤቱ ደጃፍ መቃንና ምሶሶ ይቀባል፡፡ ከበሬው የተገፈፈው ሞራም እስከ መጪው ዓመት ድረስ የቤት ምሶሶ ላይ ይሰቀላል፡፡

የማረድ ግዴታ ያለባቸውና የሌለባቸው ሰዋች እንዳሉም መታወቅ አለበት፡፡ የማረድ ልምድ ያለባቸው ሰዎች የወሸምያ ዕለት ካላረዱ ወሸምያ ይገድላቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በየዓመቱ ከሚያርዱበት የተወሰነ ቦታ ፈቀቅ ለማለት እንኳን አይሞክሩም፡፡ ልማድ የሌላቸው ሰዋች ግን ስጋም ገዝተው በዓሉን ማክበር ይችላሉ፡፡

የማረድ ልማድ ያለባቸው ልምዱን ለመሰረዝ ከፈለጉ የሚከተለውን ህግጋት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ በየዓመቱ በሬ የሚያርድ ሰው በቀጣዩ ዓመት ጥጃ ያርዳል፡፡ በሁለተኛው ዓመት ፍየል ያርዳል፡፡ በሦስተኛው ዓመትም ፍየል ያርዳል፡፡ በአራተኛው ዓመት ዶሮ አርዶ በአምስተኛው ዓመት ምንም ባያርድ ወሽምያ ስለሚረሳ ችግር አይመጣበትም ፡፡ አሪፍ የማካካሻ ስልት ናት ፡፡

***
መስከረም 16
ምግይር ወይም ደመራ ነው፡፡

ደመራው በየቤቱ ደጃፍ የሚተከለው የልጆች ደመራና የአባቶች ደመራ ተብሎ ይታወቃል፡፡ በየበራፉ የሚተከለውን ደመራ ጠዋት ወይም ማታ ማቀጣጠል ይቻላል፡፡ የአባቶች ደመራ የሚለኮሰው ግን ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ በዚሁ ግዜ አባ ተዘር /ክረምትና በጋ/ የተባለውን ጨዋታ ልጆች ይጫወታሉ፡፡

በደመራ እለትም ሆነ በሌሎች የመስቀል ቀናት ከብቶች ውጪ አይወጡም ፡፡ የተዘጋጀላቸውን ምግብ ከቤት ይበላሉ፤ አይታለቡም ፡፡

***
መስከረም 17
ንቅባር ወይም ትልቁ በዓል ይባላል፡፡

በዚህ ቀን ቤተዘመዶች፣ በቡና የሚገናኙ ጎረቤቶች ተሰብስበው ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አዛውንቶች አናታቸው ላይ ቅቤ ይደረግላቸዋል፡፡ የከብቱ ሻኛም የሚበላው በዚህ ቀን ነው ፡፡

አንድ ሰው እናት፣ አባት፣ ታላቅ ወንድም ወይም አያቱ እያለ የመስቀል ሻኛን ለብቻ አይበላም፡፡ ዘመድ ከሌለው እንኳን በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ጋ ይዞ በመሄድ ማስመረቅ ይኖርበታል፡፡ ይሄ ሁሉ ለሻኛ ካላችሁ ሻኛ በሰባት ቤት ጉራጌ የበስር ንጉስ ወይም የስጋ ንጉስ መባሉን ማወቅ ያስፈልጋል።

**,*
መስከረም 19- 23 
የጀወጀ ወይም የመተያያ ቀን ይባላል፡፡

ከመስከረም 18 በኃላ ያሉትን ቀናት የሚያመለክት ሲሆን ለአንድ ሳምንት ያህል ባሉት ቀናት ባልና ሚስት ወገኖቻቸውን በተለይም እናት አባቶቻቸውን ስጦታ በመያዝ የሚጠይቁበት ነው፡፡ የሙየቶቸም ጭፈራ ይከናወናል፡፡ ሙየት ማለት በእናቶችና ሴቶች የሚዘፈን ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡
ዘመዳሞች ይጠያየቃሉ፣ ይመራረቃሉ፡፡

***
መስከረም 24
አዳብና ወይም መሰነባበቻ በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡

በአንዳንድ በተ ጉራጌዋች ዘንድ ከጀወጀ በተለየ መልኩ አሁንም ድረስ በድምቀቱ የሚታወቅ ሲሆን ለወጣቶችና ልጃገረዶች የተለየ የጭፈራ አጋጣሚ ነው፡፡

ጭፈራው ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ጥቅምት ድረስ ይዘልቃል፡፡ የአዳብና ጭፈራ በገበያዋች ላይ የሚከወን ሲሆን ድንቅ ባህላዊ አልባሳትና የውዝዋዜ ትዕይንቶች ይታዩበታል፡፡

በነገራችን ላይ ‹መንጠየ› የቋንጣ ክትፎ የሚበላበት የመጨረሻ ስነ ስርዓት ማሳረጊያ ነው፡፡ ይህ በዓል በአንዳንድ አካባቢዋች እስከ ጥቅምት 5 ሊቆይ ይችላል ፡፡

***
ቤተንዳ ጉራጌ ~ ዝ!

Filed in: Amharic