>
4:38 pm - Sunday December 2, 3032

ኢሕአዴግን ጨምሮ፣የፖለቲካ ፓርቲ አለን? (ውብሸት ሙላት)

የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለፖለቲካዊ መብቶች፤
የምርጫ ሥርዓቱ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ፀርነቱ፤
ኢሕአዴግን ጨምሮ፣የፖለቲካ ፓርቲ አለን?

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እና በመጀመሪያ ሃያ አንድ (ከዚያ አስራ ምናምን) አገር አቀፍ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየት ወይንም መደራደር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በመካከልም የተወሰኑ አጀንዳዎችን በሚመለከት ከኢሕአዴግ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉ ፓርቲዎች ከውይይቱ ወይንም ከድርድሩ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወቃል፡፡

ይህ ውይይት/ድርድር የሚከናወነው በገዥው እና በሌሎች በየትኛውም ደረጃ በሚገኝ ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ በሌላቸው ፓርቲዎች መካከል ነው፡፡ የኢሕአዴግ አጋር የሆኑትን ጨምሮ የክልል ፓርቲዎች የዚህ ሒደት አካል አይደሉም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ ፓርቲዎች የሚወያዩት ስለ ዜጎች ፖለቲካዊ መብቶች አከባበር እና አተገባበር ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዝርዝር ሲተነተኑ በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዋና ግባቸው የዜጎችን ፖለቲካዊ መብቶች በተገቢው ሁኔታ እንዲተገበሩ ማድረግ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ ጽሑፍ የሚያጠነጥነውም በጥቅሉ ስለ አገራችን የፖለቲካ መብት እና ነጻነት ጉዳይ ሆኖ፤ እነዚህ መብቶች ስላሉበት ሁኔታ፣መብቶቹን ለመተግበር የፓርቲዎች ሚና፣እነዚህን መብቶች በፓርቲ አማካይነት ሥራ ላይ ለማዋል ፈተና ሊሆኑ የሚችሉትን ሁኔታዎች መዳሰስ ላይ ያተኩራል፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ መብቶች ያሉበት ሁኔታ፣መብቶቹ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉት የፓርቲ ተግባራት ውስጥ የተወሰኑትን እና ቀደም ሲል አገሪቱ ትከተላቸው የነበሩ አሠራር እና የምርጫ ሥርዓቱም ከፖለቲካ መብቶች ጋር የሚኖራቸውን ትሥሥር ቅኝት ይደረግበታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው ዴሞክራሲያዊ የመሆን ሕገመንግሥታዊ ግዴታ ግን ለጊዜው በዚህ ጽሑፍ አልተካተተም፡፡

የፖለቲካ መብቶች ሲባል፤

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ይሁን በሌሎች ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ ዕውቅና ያገኙ በርካታ የፖለቲካ መብቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካዊ መብቶች ደግሞ ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ብቻ ያገኛቸው ስለሆኑ ሰብኣዊ መብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በመንግሥት ወይንም በሌላ አካል ችሮታ የተገኙ አይደለም ማለት ነው፡፡

ከሕገ መንግሥቱ የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ማንም ሰው የመሠለውን አመለካከት የመያዝ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣የመደራጀት፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ በተለያዩ ድርጅቶች ውሥጥ አባል የመሆን፣የመምረጥና የመመረጥ መብቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ መብቶች ፖለቲካዊ አመለካከትን ወይንም ሐሳብንም ጭምር የሚያካትቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ስለሆነም፣ ማንም ሰው የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት መያዝ ይችላል፡፡ በመያዝ ብቻ ሳይገደብ በነጻነት በመግልጽ ለሌሎች ሰዎች ማከፍል፣ከሌላም መቀበል ይችላል፡፡ የያዛቸውን ሐሳቦች ሥራ ላይ ለማዋልም የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶችን ሊያቋቁም ይችላል፡፡ ለሐሳቡ ድጋፍ ለማገኘትም ወደ ሕዝብ ለማስረጽም በተለያዩ ሚዲያዎች ማስተላለፍን ጨምሮ ሰልፍና ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል፡፡ እነዚህን ተግባራት በቀላሉ እውን ማድረግ ከሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዋነኛው ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች አማካይነት ነው፡፡

እነዚህ የፖለቲካ መብቶች ከሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ሁሉን አቀፍ የሰብኣዊ መብት መግለጫ እና ዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ስምምነትን ጨምሮ በተለያዩ የሰብኣዊ መብት ሰነዶችም ጭምር ዋስትና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ፖለቲካዊ መብቶች ከፖለቲካዊ ነጻነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ሲሆኑ ሁለተኛው በበኩሉ ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ጋር የተዛመደ ጉዳይ ነው፡፡ ተሳትፎ በበኩሉ ምርኩዙ ወይንም መቆሚያው ሥልጣኑ የተገደበ ኃላፊነቱ የታወቀ ብቻ ሳይሆን ቅቡልነት ያለው መንግሥት መኖርን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት መኖርን ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነት የሚሠማው መሆን እና የሌላን ሰው መብት ማክበር፣ፍትሐዊነት እና ተሳታፊው አካል ለሚያደርጋቸው ተግባረት አንፃራዊ ነጻነት መኖርንም ጭምር ይፈልጋል፡፡ ተሳትፎ፣ እንደ መብት ለሌላ መብት ግብ ማስፈጸሚያነት ብቻ የሚውል ሳይሆን በራሱም ዋጋ ያለው፤በራሱ ግብ የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡

ለተሳትፎ ዋጋ የሚሠጥ መንግሥት ለግለሰብና ለቡድን መብት ጥበቃ ያደርጋል፤ያከብራል፤ እንዲተገበሩም ያደርጋል፡፡ ፖለቲካዊ መብቶች ሕዝባዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ መሳተፍ የሚያስችሉ መብቶችንም ይመለከታል፡፡ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ዜጎች የማይሳተፉ፣ የሚከለከሉ፣ ከሆነ ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም፡፡

ፖለቲካዊ መብቶች በኢትዮጵያ ያሉበት ሁኔታ፤

የፖለቲካ መብት ከሚተገበርባቸውም መንገዶች አንዱ በሕዝባዊ ውሳኔዎች ላይ የዜጎች ተሳትፎ መኖር ነው፡፡ ተሳትፎ ከማስፈጸሚያነት ባለፈም በራሱም መብት ስለሆነ ማለት ነው፡፡ የሕዝብን ተሳትፎ በተመለከተ በቅርቡ ‘የኢፌዲሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም’ ያወጣውን ሪፖርት እንኳን ብንወስድ መብቱ ባለመከበር ያለበትን ደረጃ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሌሎች መብቶችን በተመለከተ ደግሞ የተለያዩ ተቋማት ያወጧቸውን ሪፖርት እንመልከት፡፡

በመጀመሪያ ‘ፍሪደም ሃውስ’ የተባለው ተቋም ኢትዮጵያን በተመለከተ ይፋ ያደረገውን የጥናት ውጤት ወይንም ደረጃ እንውሰድ፡፡ ተቋሙ ፖለቲካዊ መብቶች እና ዴሞክራሲ ስላሉበት ሁኔታ በየዓመቱ ለአገራት ደረጃ ያወጣል፡፡ የሚሰጣቸውም ደረጃዎች በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ነጻ፣ከፊል ነጻ እና ነጻ ያልሆኑ አገራት በማለት ይመድባቸዋል፡፡

ለአገራቱ ከአንድ እስከ ሰባት ነጥብ በመሥጠት አንድ ካገኘ በጣም ነጻ የሆነ ማለት ሲሆን፤ ሰባት ካገኘ ደግሞ ነጻ ባለመሆን ዝቅተኛ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ተቋሙ ለኢትዮጵያ እ.አ.አ ለ2010 ለፖለቲካዊም ይሁን ለሲቪል መብቶች ይዞታዋ አምስት ነጥብ ሰጥቷታል፡፡ ደረጃዋም “በከፊል ነጻ” የሆነች ብሏታል፡፡ ከ2011 ጀምሮ ግን ሰባት ወይንም ስድስት በማግኘት “ነጻ ያለሆነች” አገር አድርጓታል፡፡ ለ2016ም ሰባት ነጥብ ሰጥቷታል፤ወይንም አግኝታለች፡፡

መለኪያ ያደረጋቸው ነጥቦች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ፣ርእሰ መንግሥቱ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲመረጡ የሕዝብ ተሳትፎ፣የምርጫ ነጻነት፣የፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ እኩል ዕድል መኖር እና ምርጫ ማድረግ ብሎም ነጻ ቆጠራ ማከናወን፣የሕዝብ እንደራሴዎች የእውነት ሥልጣን መሆን፣ሕዝብ በፓርቲ የመደራጀት መብት የሕግም በገቢርም መረጋገጥ፣ጠንካራና ተገዳዳሪ ፓርቲዎች መኖር (ሕዝብን ማሳተፍ እና ማንቀሳቀስ የቻሉ)፣ የሕዝቡ ከመከላከያ፣ከፖሊስ፣ ከጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች፣ ከውጭ ኃይል፣ ከጠቅላይ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት እና በጥቂቶች እጅ ሥር ከሆኑ የኢኮኖሚ ተቋማት ተጽእኖ ሥር አለመሆን፣ ወይንም በሌላ ጉልበተኛ አካላት መዳፍ አለመውደቅ፣ የተለያዩ አናሳ ቡድኖች ያላቸው በራስ ጉዳይ የመወሰን ነጻነት፣ ናቸው፡፡ ተቋሙ ለእነዚህ መለኪያዎች ለኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ነጥብ ከሰጣት በኋላ ያከናወነችውን ምርጫ የይስሙላ እንደሆነ በመውሰድ ምርጫ እንደሌለ ወስዶታል፡፡

መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው ‘ኢኮኖሚክ ኢንተሊጀንስ ዩኒት’ የተባለው ተቋምም በ2016 ዓ.ም. ለአገራት የዴሞክራሲ ሁኔታ የሰጠው ደረጃ ከላይ ከተመለከትነው ብዙ ልዩነት የለውም፡፡ ጥናቱ ካካተታቸው 167 አገራት መካከል 125ኛ ደረጃን አግታለች፡፡ ከአስሩ በተያዘ ነጥብ ለምርጫ ሁኔታና መድበለ ፓርቲነት ዜሮ፣ መንግሥታዊ አሠራር 3.57፣ የፖለቲካ ተሳትፎ 5.56፣ ለፖለቲካ ባህል መዳበር 5.63፣ በአገሪቱ ላለው ነጻነት 3.24 በመስጠት አፋኝ (Authoritarian) የሆነ መንግሥት ያለባት አገር አድርጓታል፡፡

አፋኝ ያላቸው፣ የፖለቲካ ብዙኃነት የሌለበት ወይንም የነጠፈበት፣መንግሥታቱም አምባገነን፣ ለስም ብቻ የዴሞክራሲ ተቋማት ያሉባቸው፣ የሲቪል እና የፖለቲካ ነጻነት የሚጣስባቸው፣ምርጫ ቢኖርም ነጻና ፍትሐዊ ያልሆኑባቸው፣ ሚዲያው በመንግሥት (በገዥ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር) የሆኑባቸው ወይንም በጫና ውስጥ የሆኑባቸው፣ ነጻ ዳኝነት የሌለባቸው በማለት ተርጉሟቸዋል፡፡

ፓርቲዎች ፖለቲካዊ መብቶችን ለመተግበር፤

ፓርቲዎች በመርህ ደረጃ መራጮችን ከመንግሥት ጋር ለማገናኘት የሚፈጠሩ ድልድይ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ዕድል ይንቀሳቀሱ እና ይጠቀሙ ዘንድ የሕግ ከለላ እና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕጎቹም ሊያሟሏቸው የሚገቧቸው ዝቅተኛ መሥፈርቶችን ወይንም የሕጎቹ ግቦች ምን መሆን እንዳለባቸው የተለያዩ መለኪያዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ የሕጎቹን ግቦች በሦስት ማጠቃለል እንደሚቻል የዘርፉ ተመራማሪዎች ይስማማሉ፡፡ እነዚህም ፍትሐዊነት (Equitable)፣ ነጻነት (Free) እና ሚዛናዊነት (Fair) የሚሉ መለኪያዎች ናቸው፡፡ ሕጎቹ እነዚህን መሥፈርት ሲያሟሉ ፓርቲዎቹን ተወዳዳሪዎች ሊያደርጓቸው ይችላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

የምርጫ ዴሞክራሲ ነጻና ግልጽ የሆኑ ውድድሮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ውድድሮቹም አማራጮችን ለማግኘት ይረዳሉ፡፡ አማራጮች የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የተለያዩ ተቃራኒ ሐሳቦች/ፖሊሲዎች፣ ተመራጮች፣የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖርንም ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡም፣ ከእነዚህ መካከል ያሰኘውን ሊመርጥ ይችላል፡፡ የፓርቲዎችን አሠራር የሚቀይዱ ሕጎች ሲኖሩ እነዚህ አማራጮች አይኖሩም ማለት ነው፡፡ አማራጮቹ ከሌሉ ደግሞ ዜጎች ፍላጎቶቻቸውን ማንጠር እና መጠየቅ አይችሉም፤ ምርጫዎቻቸውንም አይገልጹም፤ገዥዎቻቸውን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ሥርዓት አይኖርም፤ማለት ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ሕጎቹ ፓርቲዎችን በእኩልነት የሚያዩ መሆን አለባቸው፡፡ የሚያዳሉ እና ልዩነት የሚፈጥሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ፓርቲዎች በሚከተሉት ፍልስፍና፣ርእዮተ ዓለም፣ፕሮግራም፣መርህ ወዘተ ምክንያት በማድረግ የሚገድቡ ወይንም የሚለያዩ መሆን የለባቸውም፡፡

ይሁን እንጂ አገራት ሥራ ላይ የሚያውሏቸው ፓርቲዎች የሚተዳደሩበትን ሕግ በሦስት የሚከፍሏቸው አሉ፡፡ የመጀመሪያው ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ፣ተቃዋሚዎችን እና የተለየ ሐሳብ ያላቸውን የሚያገልሉ፣አንድ ፓርቲ ብቻ እንዲኖር የሚያደርጉ ‘ሞኖፖሊስቲክ’ ሕጎች ናቸው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በጥቅሉ የሰብአዊ መብትን የሚያከብሩ ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማያንቀሳቅሱ፣ገዥ ፓርቲን በተለይም በፓርላማ እንዲጠቀም የሚስችሉ፣ተቃዋሚዎች ገንዘብ የሚያገኙበትን የሚከለክል እና ሥልጣን ላይ የሆነውን የሚጠቅሙ ሕጎች ደግሞ ሌላው ዓይነት ናቸው፡፡

ሦስተኛው፣ አፋኝ እና ቀያጅ ሕግ እምብዛም የሌለባቸው፣ፓርቲዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲ በእኩልነት የሚወዳደሩበት ሕጎች የሚከተሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ፓርቲዎችን የሚመለከቱ ሕጎችን በመገምገም ከላይ ካሉት ውስጥ ወደየትኛው እንደሚያዘነብሉ ማወቅ ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሁኔታ፤

በኢትዮጵያ የነበሩትንም ይሁን አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ብሔር ዘለል የሆኑ በማለት፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረጉት የኢሕአዴግ አባል እና አጋር የሆኑት ገዥ ፓርቲዎች እንዲሁም የተወሰኑ ተቃዋሚዎችንም ይጨምራል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሠረት ደግሞ የክልል እና የአገር አቀፍ በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ ለነገሩ ምንም እንኳን ሕጉ በአገር አቀፍ እና በክልል ገለጻቸው እንጂ በወረዳ፣ በዞን እና በቀበሌ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም መኖራቸውንም ልብ ይሏል፡፡

ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር) ደግሞ ገዥ፣ አጋር እና ተቃዋሚ በማለት ለሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣አጋሮቹ እና ተቃዋሚ የሆኑ የብሔር ፓርቲዎች ሲኖሩ ተቃዋሚዎች ደግሞ ብሔር ዘለል የሆኑ አሉ፡፡ ከላይ በተገለጸው እና በሌላም መልኩ ቢሆን የአደረጃጀታቸው ሁኔታ በራሱ ፖለቲካዊ መብቶችን ለመተግበር በራሱ በጎም አሉታዊም ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲና ርእዮተ ዓለም፤

ተለያዩ የፖለቲካ መብቶችን እና ፍላጎቶችን የሰብኣዊ መብት ሰነዶቹ እና ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡትን ለመተግበር ፈተና ሊሆን ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ የተራራቀ ርእዮተ ዓለምን መከተል ነው፡፡ የፈተናው ክብደት የሚጸናው ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ፖለሲውን እና ርእዮተ ዓለሙን ለማስፈጸም የሚያመቹትን ተቋማት ከመሠረተ ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ እንቅፋት ሊሆን የመቻሉ ነገር ነው፡፡ ቢመጡም ከእንደገና እንደ አዲስ ተቋማትን ማፍረስና ማቋቋም ይከተላል፡፡ ከእዚህ አንፃር የልማታዊ መንግሥትን እና ሊበራል ዴሞክራሲን መውሰድ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ አንዲት አገር ልማታዊ መንግሥት ከሆነችና በዚሁ አካሔድ ለውጥ አመጣለሁ ብላ ቆርጣ ከተነሳች ሥልጣን የያዘውም የፖለቲካ ፓርቲ ማንም ይሁን ማን የመንግሥት ሚና ላይ ስምምነት ሊደረስ ግድ ይላል፡፡ አልበለዚያ የዥዋዥዌ ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላ ርእዮተ ዓለም ከሆነ እንደዚሁ፡፡

ለአብነት፣ ኢሕአዴግ በልማታዊ መንግሥት መርሕ ሲመራ እነዚህን የሚያሳልጡ ሕጎች አውጥቷል፤ተቋማትን መሥርቷል እንበል፤ኤዴፓ ወይንም ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ ከፕሮግራማቸው መገንዝብ እንደሚቻለው የሊብራሊዝም ርእዮተ ዓለም ተከታይ ናቸው፡፡ ኢዴፓ ወይንም ሰማያዊ ፓርቲ አገሪቱን መምራት ቢችሉ እጅግ ብዙ ሕጎች ይሻራሉ፤የመንግሥት ኢኮኖሚውን የሚዘውርበት እጁ በእጅጉ እንዲያጥር ይደርጋሉ፡፡ የትምህርት ተቋማት፣ የሲቪል ሰርቪሱ አወቃቀር ሳይቀር ግልብጥብጡ ይወጣል፡፡ ተመልሶ ኢሕአዴግ ሥልጣን ቢይዝ ደግሞ ድጋሜ ወደልማታዊ መንግሥት ሊመለስ ነው፡፡ የፓርቲዎቹም ደጋፊዎችም ከሚያስማማቸው እና ከሚያቀራርባቸው ይልቅ የሚያለያያቸው እና የሚያራርቃቸው ይበዛል፡፡ ወይንም አይቀንስም፡፡

የተራራቀ ርእዮተ ዓለም መከተል ገዥ የሆነው ፓርቲ ለራሱ የሚጠቅም አሠራርን እንዲከተል ሊያበረታታው ይችላል ብለናል፡፡ ከዚህ አንጻር ኢሕአዴግን እንውሰድ፡፡ ፓርቲው ልማታዊ መንግሥት ጋር የሚጣጣም የፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር ስለፈለገ የአውራ ፓርቲ ሥርዓትን ለመከተል መርጧል፡፡

ልማታዊ መንግሥት መሸጋገሪያነቱ እስከሚያከትም ወይንም በሚፈለገው መጠን ልማት እስኪመጣ ድረስ ለረጅም ዓመታት ሥልጣን ላይ መቆየት የሚያስችለውን አካሄድ ይከተላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ልማታዊ መንግሥት ለአውራ ፓርቲ ሥርዓት መፈጠር ምክንያት ሆነ ማለት ነው፡፡

በአንድ አውራ ፓርቲ መመራት ልማድ ባደረገ አገር ውስጥ የባህል ልዩነትና ብዝሃነት እንጂ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነትም ይሁን ብዝኃነት መኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተራው የፖለቲካ መብቶች እንዳይጎለብቱ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ከላይ የተገለጹት ተቋማት ስለዴሞክራሲ እና የፖለቲካ መብቶች ሁኔታ ደረጃ ሲያወጡ የኢትዮጵያ በዚህ መጠን ዝቅ ለማለቱ የመንግሥትነት ሥልጣን ያለው ፓርቲ ከሚከተለው ርእዮተ ዓለም ሊመነጭ እንደሚችልም የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ኢሕአዴግ ስለፖለቲካ ፓርቲ፤

ኢሕአዴግ ስለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በ1994 ዓ.ም. ባወጣው ‘በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች’ በሚለው ሰነዱ አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ እንደ ኢሕአዴግ የወቅቱ ግምገማ በአገሪቱ ካላው ተጨባጭ ሁኔታ እና በታሪክም እንደታየው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአርሶ አደር እና አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ዘንድ ጠንካራ ድጋፍ፣መዋቅር እና እንቅስቃሴ ሊኖራቸው አይችልም፡፡

የትራንስፖርት እና የመገናኛ ዘዴዎች ሽፋን ደካማ በሆነበት አገር ፓርቲዎች በአገሪቱ በሙሉ ተንቀሳቅሰው አርብቶ እና አርሶ አደሩን ማንቀሳቀስ አይችሉም፤በገበሬው ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ፓርቲ ካለ በድጋሜ ሌላ ጠንካራና ሊፎካከር የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ ሊኖር እንደማይችል ገምግሟል፡፡

አርብቶ አደሩ ደግሞ ማኅበራዊ መዋቅሩ በጎሳ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ጎሳዊ ትስስሩን እና አስተዳደሩን እስካልተወ ድረስ የእውነት ፖለቲካ ፓርቲ ሊኖረው አይችልም፡፡ገበሬን ዘመናዊ አርሶ አደር ማድረግ፣ አርብቶ አደሩን ደግሞ ማስፈር ብሎም የልማት በተለይም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት ለዴሞክራሲ ወሳኝ ናቸው፡፡

እንደ ኢሕአዴግ ግምገማ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ ማለት የሚንድ፣የሚያፈርስ ወዘተ ተደርጎ ሊወሰድ የመቻሉ ጉዳይ እንደ ሥጋት ወስዶታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲዳብሩ ለማገዝ ዝግጁ ያልሆኑ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ ታማኝ ተቃዋሚ በመሆን የፖሊሲ አማራጭ እንጂ ሥርዓትን የሚንድ ሐሳብና ተግባር የሌላቸው መሆን እንደሌለባቸው፣በፖሊሲው ላይ አስቀምጧል፡፡

ሌላው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት በፓርቲ መወዳደር እና መፎካከር ከዘራፊዎች ውድድር የሚለይ አይደለም የሚል አስተያየትም አለው፡፡ ለዚህ ማጠቃለያ እንደ መነሻ የወሰደው ደግሞ በፓርቲ ተደራጅቶ መንግሥታዊ ሥልጣንን መቆናጠጥ የሃብት ምንጭ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የፓርቲው አቋም ነው፡፡ ይህም በራሱ በፓርቲ ሥርዓትም ሆነ በፖለቲካዊ መብቶች ላይ የራሱ ተጽእኖ ሊኖረው መቻሉን በቀላሉ መረዳት አይከብድም፡፡

ፓርቲ እና ምርጫ፤
በ1923ቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ለሕግ መምሪያው ተወካዮች የሚመረጡት በመኳንንቱና በሹማምንቱ ነበር፡፡ ሕዝቡ ምርጫ ምን እንደነበር፣ተመራጮች ምን እንደሚሠሩ ወዘተ ስላላወቁ ወይንም ስላልለመዱ የአካባቢው መኳንንትና ሹማምንት ስለ ሕዝቡ ሆነው “በአደራ መራጭነት” እየመረጡ ይልኩ ነበር፡፡

ነገሩ ሕዝቡ መምረጥ እስኪችል ድረስ የሕዝቡ ሞግዚት ሆነው ይመርጣሉ ማለት ነው፡፡ ልክ አንድ ሕጻን ልጅ ለአቅመ-አዳም/ሔዋን እስከሚደርስ ድረስ በሞግዚት እንደሚወከለው መሆኑ ነው፡፡ በፖለቲካ ሳይንስ “Tutelary Democracy” ይባላል፡፡ በእርግጥ ብዙ ሰው አሁንም ቢሆን ምርጫ ሲመጣ መምረጡን እንጂ ለምን እደሚመርጥ፣ ተመራጮች ምን እንደሚሠሩ የማያውቅ ሞልቷል፡፡

ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ሕዝቡ ለአቅመ-ምርጫ ስለደረሰና “ከአደራ መራጭነት” ነጻ ስለወጣ በቀጥታ መምረጥ ጀመረ፡፡ ውድድሩ በግለሰቦች ብቻ የነበረ ሲሆን የ50 ሰው ድጋፍና 500 ብር ማስያዝ ግን ግድ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ለሕግ መምሪያ አባልነት ለመወዳደር ነው፡፡ ተወዳዳሪውም ለደጋፊዎቹ ምን ምን ሊስፈጽምላቸው እንዳሰበ በቅስቀሳ ወቅት ይገልጻል፡፡ ሥልጣን የሚያዘው ወይንም ፖለቲካዊ መብቶችን ሥራ ላይ የሚዉሉት በፓርቲ አማካይነት ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ነበር ማለት ነው፡፡

የደርግን ስናይ ደግሞ እስከ 1979 ድረስ ምርጫ የሚባል ነገር ፈጽሞ አልነበረም፡፡ የኢሕዲሪ ሕገመንግሥት ሲጸድቅ ግን 800 አካባቢ አባላት ያሉት፣ የኢሠፓ አባላት የሆኑ ወይንም የኢሠፓን ይሁንታ ያገኙ በየምርጫ ጣቢያው የዝሆን፣ የጎሽና የአጋዘን ምልክት በማንገብ ሦስት ሦስት ሆነው ለውድድር በመቅረብ ሕዝቡ የዝሆን ምልክት ያለውን እንዲያጸድቅ ተደረግ፡፡ አካታችነቱ ከቅርጽ አንጻር ሰፋ ያለ ነበር፡፡ ከሃይማኖት፣ ከብሔር፣ ከአርሶአደር ወዘተ አኳያ ለማለት ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ፈጽሞ የፖለቲካና ሐሳብ ብዝኃነት ስላልነበረ ብዙም ለንጽጽር አይሆንም፡፡

በሽግግሩ ወቅት የነበረው ደግሞ ያው ጊዜው ሽግግር በመሆኑ ውዥንብር የበዛበት ስለሆነ በወቅቱ የነበሩት ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው ሥልጣን ቢከፋፈሉም ቅሉ ከፓርቲ ብዛትና የተለያየ ሐሳብ ካለቸው ቡድኖች ተሳትፎ አኳያ ግን እንደሽግግር መንግሥቱ ያለ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን ተፈጥሮ አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ እነኢሠፓ፣መኢሶን፣ኢህአፓ ባይወከሉም፣እነ ኦነግ ጥለው ቢወጡም እነ መአሐድ በመገለላቸው ጎደሎ ቢሆንም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ፤

የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱ እና ዋነኛው ምርጫ ነው፡፡ የምርጫ ሥርዓቱና እና የአመራረጥ ሁኔታውም ቢሆን እነዚህን መብቶች ለመተግበር እና በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ የራሳቸው ተጽእኖ ሊኖራቸው መቻሉ አያጠራጥርም፡፡

በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 9 እንደተገለጸው ሥልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ ነው፡፡ የምርጫ መርሆችን በተመለከተ ደግሞ በሕገመንግሥቱ በአንቀጽ 38 ላይ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ሁሉንአቀፍ፣ ምሥጢራዊ መሆን፣ በየጊዜው መካሔድ እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ የምርጫ ሥርዓቱን ደግሞ አንደኛ-አላፊ የሚባለውን ሥርዓት (First-Past-The-Post) እንድንከተል በሕገመንግሥት ተወስኗል፡፡

አንደኛ-አላፊ የምርጫ ሥርዓት መራጩ የፈለገውን ሰው ይመርጣል፡፡ በዛ ያለ ድምፅ ያገኘ ያልፋል፡፡ ፓርላማም ላይ አብላጫ ወንበር ያገኘ አስፈጻሚውን በብቸኛነት ስለሚያደራጅ ብዙ ጊዜ ጥምር መንግሥት አያስፈልገውም፡፡ የፓርቲዎች ፕሮግራምና ርእዮተ ዓለም በጣም ተራርቆ እየተፈራረቁ ሥልጣን የሚይዙ ከሆነ የቀድሞውን ፓርቲ ፓሊሲዎችና ሕጎች፣ እንዲያም ሲል ሕገመንግሥቱን ማሻሻልንና መሻርን ያስከትላል፡፡ቀድሞ የነበረው ፓርቲ ወደሥልጣን ሲመለስ ድጋሜ የመሻርና የማጽደቅ ዥዋዥዌ ውስጥ በመግባት ሕዝብን ማደናገርና ሀብትንም እንዲባክን ያደርጋል፡፡

በአንጻሩ በተመጣጣኝ ውክልና ተወዳደሪዎች የፓርቲ አባላት ብቻ ሆነው (ግለሰብ በግል አይወዳደርም) መራጮች በአብዝኃኛው ድምፅ የሚሰጡት ለፓርቲው ነው፡፡ ምርጫው ለማዕካለዊው መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሆነ፣ መራጮች የሰጡት ድምፅ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተደመረ በኋላ ፓርቲዎች ባገኙት ምጣኔ/ፐርሰንት ልክ፣ ብዙ የድምፅ ብክነት ሳይኖር፣ ወደ ፓርላማ ይገባሉ፡፡

ከየምርጫ ጣቢያው ምንም ማሸነፍ የማይችል ብዙ የፓርላማ ወምበር ሊያገኝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ ሲደረግ በድምሩ ኢሕአዴግ 48%፣ መድረክ 30%፣ አረና 6%፣ ኦብኮ 6%፣ ሰማያዊ 6%፣ መኢአድ 4% ድምጽ ቢያገኙ ፓርላማም ላይ የ550ን (የእኛ የሕዝብ ተወካዮች ብዛት ነው፡፡) በየፐርሰንታቸው እያባዙ ፓርቲዎቹ ይወክላሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ ስሌት ስንሔድ ኢሕአዴግ 264(550×48%)፣ መድረክ 165፣አረና 33፣ኦብኮ 33፣ ሰማያዊ 33፣ መኢአድ 22 ወንበር ይጋራሉ ማለት ነው፡፡

በብዙ አገራት አስፈጻሚውም ውስጥም (ሚኒስትሮች ምክር ቤት) ፓርላማ ላይ ባገኙት መጠን የሚኒስትርነትም ሥልጣን ስለሚሰጣቸው እንዲሁ ይካፈላሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ፓርቲ ፓርላማውንም አስፈጻሚውንም ጠራርጎ የመውሰድ አጋጣሚው ዝቅተኛ ነው፡፡

ሕጎችና ፖሊሲዎች በሚጸድቁበት ጊዜ አብላጫ ድምፅ በቀላሉ ማግኘት ስለሚያስቸግረው ጥልቅ ውይይት እየተካሔደ መተማመንና መግባባት ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ አልበለዚያ ሕጎች ላይጸድቁ ይችላሉ፡፡በተመጣጣኝ ውክልና ግን በዚህ ምሳሌ እንዳየነው ኢሕአዴግ መቼም ቢሆን ሁሉንም ወምበር መውሰድ አይችልም፡፡ ጥምር መንግሥት መመሥረት አለበት፡፡ ሚኒስትሮችንም ከየፓርቲዎቹ ማካተት አለበት፡፡

ስለሆነም ፓርላማም ላይ ሕግን ለማጽደቅ ጥልቅ ውይይት ማድረግና ማሳመንን ይጠይቃል፡፡ ውይይትንና ቀናነትን በእጅጉ ያበረታታል፡፡ ተቀራራቢ ርእዮተዓለም እንዲኖርና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠርም ይረዳል፡፡ድምፅም አይባክንም፡፡ የአሸናፊ ፓርቲንም በሕዝብና በተሸናፊ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖር ያበረታታል፡፡ አናሳዎች ከሕዝብ ተወካዮችና ከካቢኔም አይገለሉም፡፡ በተለይ ደግሞ ለዝርው (ተበታትነው ለሚኖሩ) ብሔረሰቦች ድምፃቸው ባክኖ እንዳይቀርና እንዲሰበሰብ ብሎም ዋጋ እንዲኖረው ይረዳል፡፡

የምርጫ ሥርዓቱ ፓርቲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን የዜጎች መብትን ሊያቀጭጭ የሚችልበት ሁኔታ አለ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የዜጎችን የፖለቲካ መብት የሚያሰፋ እና የሚያስጠብቅ የምርጫ ሥርዓትን ማስፈን ግድ ነው፡፡

በአጠቃላይ አሁን ባለው ሕገመንግሥትም ይሁን በዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ሰነዶች ዕውቅና ያገኙ በርካታ የፖለቲካ መብቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በተገቢው ሁኔታ ሥራ ላይ እየዋሉ ነው ለማለት ግን የተለያዩ ተቋማት ከሚሰጧቸው መረጃ ባሻገር መንግሥትም ጭምር ያውቀዋል፡፡ ለእነዚህ መብቶች መተግበር ደግሞ ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ከሚከተሏቸው ርእዮተ ዓለም ጀምሮ በርካታ ጉዳዮች ፍተሻ ያስፈልጋቸዋል፡፡

(በፓርቲዎቹ ውይይት ላይ ግን ኢሕአዴግ የምርጫ ሥርዓቱ ወደ ቅይጥ ትይዩ (Mixed-Parallel) እንጂ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና አይቀየርም ስላለ፤ያው ከልምድ እንደምንገምተው ኢሕአዴግ ያለው ስለሚጸድቅ ስለዚህ የምርጫ ሥርዓት ምንነት፣ባሕርያት፣ጥቅምና ጉዳት በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡)

Filed in: Amharic