>
2:20 am - Saturday November 27, 2021

''እምዬ'' የሚለውን ስም በተግባር የኖሩ ንጉሥ (ጳውሎስ ኞኞ)

…..የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በምትሰራበት ወቅት ሰው በመግደል የተከሰሰ አንድ ወንጀለኛ በምኒልክ ችሎት ፊት ቀረበ፡፡ ተከሳሹም ወንጀሉን በመፈፀሙ የሞት ፍርድ ተላለፍበት፡፡ በዘመኑም በነበረው የፍርድ ስርዓት መሰረት በገዳይ ላይ ውሳኔው ከመፈጸሙ በፊት የተበዳይ ወገኖች “ወንጀለኛው መገደሉ ቀርቶ ለተገደለው ዘመዳቹ የደም ካሳ የሚሆን ገንዘብ ትቀበላላቹ ወይ?” ተብለው ተጠየቁ፡፡ እነርሱም ” አይ የወንድማችን ገዳይ ይገደልልን እንጂ ካሳ አንቀበልም፡፡” በማለት መለሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍርድ የተላለፈበት ተካሳሽ ድምጹን ከፍ አርጎ “ጃንሆይ በሥራዬ ነውና መገደሉንስ ልገደል፡፡ ግን የዚችን የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን መጨረሻ እስካይ ዕድሜ ይሰጠኝና ልገደል” ሲል ጠየቀ፡፡ ይህን የሰሙት አጼ ምኒልክ ከዙፋናቸው ተነስተው ወንጀለኞች ከሚቆሙበት ቦታ ሄደው በመቆም ከፊታቸው ላሉት መኳንንት “ከሟች ወገኖች አስማሙኝ፡፡ ካሳውን እኔ ራሴ ከግምጃ ቤቴ እከፍላለው ይህን ሰው ግን እንድታስምሩልኝ እማፀናለው፡፡” በማለት የንግሥና ኩራት ሳይዛቸው ከወገባቸው ጎንበስ ብለው ጠየቁ ፡፡ በዚህ ጊዜ ወንጀለኛው ይገደልልን ብለው የነበሩት የሟች ቤተሰቦች በምኒልክ እግር ስር ወድቀው እያለቀሱ “ምረነዋል ለእርስዎ ስንል ምረነዋል ካሳውንም አንቀበልም” አሉ፡፡ ምኒልክም መልሰው “ነፍሱን ማሩልኝ አልኩ እንጂ ካሳውንማ መተው ፍርድ ማጓደል ነው” ብለው ገንዘቡን ከፈሉ፡፡.

…ምኒልክ ምንጊዜም ከማይረሱት ልማዳቸው አንዱ፣ ሠራዊታቸው ምግብ ሳይበላ እሳቸው አይበሉም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከዳጃች ውቤ ቤት ተጋብዘው ሄዱ፡፡ ደጃች ውቤም አማታቸውን ምኒልክን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ቤት እንዲገቡ ቢጠይቋቸው፣ “በፊት አሽከሮቼን አስገባና አብላልኝ” ብለው እምቢ አሉ፡፡ አሽከሮቹ ለግብር ሲገቡ የምኒልክንና የየመኳንንቱን በቅሎዎች የያዙ አሽከሮች ቀሩ፡፡ ይህን ያዩት ምኒልክ በቅሎአቸውን “ወዲህ አምጣት” ሲሉ፣ አሽከሮች እየሮጡ በቅሎአቸውን አቀረቡላቸው፡፡ አብረዋቸው ያሉት መኳንንት፣

“ወዴት ሊሄዱ ነው?” እያሉ ሲጠይቁ ምኒልክ የበቅሎዋን መሳቢያ ለኮ ከአሽከራቸው ተቀብለው፣ “ሂድ ግባና ምሳህን ብላ” አሉት፡፡ ሁሉም ደነገጡ፡፡ ምኒልክም አሽከሮቻቸውን ተቈጥተው ወደ ግብር እንዲገቡ ሲያደርጉ፣ እፊታቸው የነበሩት ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ከምኒልክ እጅ በቅሎዋን ለመቀበል፣ “ይስጡኝ እኔ ልያዛት” አሏቸው፡፡ ምኒልክም፣ “የኔን ተውልኝና ያንተን ካንተ አሽከር ተቀበል” አሏቸው፡፡ ከዚህ በኋላ መኳንንቱ ሁሉ ከአሽከሩ በቅሎውን እየተቀበለ ሲይዝ አሽከር ምሳውን ሊበላ ወደ ግብር ገባ፡፡ ምኒልክ ከአንዲት የኮክ ዛፍ ሥር በቅሎአቸውን ይዘው ቆመው አሽከሮቻቸው በልተው እስቲወጡ ድረስ ጠጅ እየጠጡ ይጠብቁ ጀመር፡፡“እምዬ ምኒልክ” የሚለውን ስም እንደኖሩት ይህ አንድ ማረጋገጫ መሆን ይችላል፡፡

ምንጭ፦ጳውሎስ ኞኞ፤አጤ ምኒልክ፣ 

 

Filed in: Amharic