>
3:53 am - Wednesday February 1, 2023

አይቀሬው የለውጥ ማዕበል በኢትዮጵያ እና የህወሀት/ኢህአዴግ የቁልቁለት መንገድ! (ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት

ኢትዮጵያ ሐገራችን አሁን ላለችበት ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍትፌው ምን መሆን አለበት በሚለው አስተሳሰብ ላይ በገዥው ቡድንና በለውጥ ኃይሉ ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሮቹ በተጨባጭ መኖራቸውን በመረዳት በኩል ግን በገዥውም ሆነ በለውጥ ፈላጊዎች መካከል ብዙም ልዩነት ስለሌለ ስለሚደርሰው ግፍ፣ ግድያ፣ አፈናና ሌሎች ቀውሶችን መተንተን አሁን ላይ ብዙም አስፈላጊ ሆኖ ስላልታዬኝ በለውጥ አይቀሬነት፣ የለውጥ ስልቶችና ውጤቱ ላይ አተኩራለሁ፡፡
ለውጥ ተፈጥሯዊ ነው፣ማንኛውም ነገር ይለወጣል፡፡ የሰው ልጅም ይወለዳል ያድጋል ይሞታል፡፡ስልጣኔም ይፈጠራል፣ያብባል ከዚያም ያረጅና በሌላ ስልጣኔ ይተካል፡፡ አገዛዝም የተለያዩ ማደናገሪያዎችንና አስተሳሰቦችን ይዞ በስልጣን ላይ ይቆያል፡፡ ያለውን አመለካከትና አገዛዝ የማይሸከም ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ሲፈጠር በስብሶ ይወድቃል፣ በሌላ ሰርዓት ይተካል፡፡
ስለዚህም ህወሀት/ኢህአዴግ ወደደም ጠላም እኛ ተንቀረፈፍንም ፈጠንም በራሱ በተፈጥሮ ህግም ቢሆን ለውጥ አይቀሬ ነው፡፡ የእኛ ሚና ሊሆን የሚችለው ለውጡን በራሱ በተፈጥሮ ከሚሆነው ይልቅ እግዚዓብሄር በሰጠን አዕምሮ ተጠቅመን በታቀደና በተጠና መልኩ በአነስተኛ ወጭና ጊዜ ወደ ተሻለና አስቀድሞ ውጤቱ ወደታወቀ መንገድ መምራት ነው፡፡ ይህንን ካለደረግን ተፈጥሮ በራሱ ለውጥ የሚያደርግብን እንጅ በራሳችን ነገሮችን የምንለውጥ ወይም የመጡ ለውጦችን የምንቆጣጠር ሰብዓዊ ፍጡሮች መሆናችን ይቀርና ደመነፍሳዊ እንስሳ ወደ መሆን እንጠጋለን፡፡ ይህንን ካልኩ በኋል አሁን በሃገራች ያለውን የለውጥ ማዕበል በተመለከተ በሶስት ክፍሎች በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

1. የለውጡ ሁኔታና የህወሀት/ኢህአዴግ የሁኔታዎች ትንተና
2. ለውጡ ሊመጣ/ሊፋጠን/ የሚችልባቸው አመራጮች
3. የሚመጣውን ለውጥ እንዴት ወደ ተሻለ ሁኔታ መምራት እንቻላለን በሚሉ መሰረታዊ ሃሳቦች እይታዬን አቀርባለሁ፡፡

1. የለውጡ ሁኔታና የህወሀት/ኢህአዴግ የሁኔታዎች ትንተና
ህወሀት/ኢህአዴግ አሁን ያለውን የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ሲገመግም “የጠባብና የትምክህት አመለካከቶች ለስርዓቱ አደጋ መሆናቸውንና ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ተጨምሮበት የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ባለማጠናቀቃችን የህዝብ ቅሬታ ተፈጥሯል፡፡በዚህ ቅሬታ ምክንያት ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሮ ሌሎች ሃይሎች ለፖለቲካ መጠቀሚያ አድርገውታል” የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፈራ ተባ እያለም ቢሆን የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የብሄራዊ ደህንነት አጀንዳ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ህወሀት/ኢህአዴግ የተፈጠረውን ችግር ከላይ በተገለፀው ሁኔታ ከተነተነ በኋላ ችግሮቹን ለማስወገድ እንደ መፍትሔ ያቀረበው ሐሳብ “በመጀመሪያ የተፈጠረውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ማዋል፤ ለዚህም የእስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ፤ ቀጥሎም በጥልቅ የድርጅት ግምገማ የትምክህትና የጠባብ ሃይሎችን መምታት፣የድርጅትን የማስፈፀም አቅም በማሳደግ ለህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ መስጠት ከዚህም በተጨማሪ የፓርላማ ወንበሮችን ሙሉ በሙሉ በማሸነፋችን ተቃዋሚ ሃይሎች ባለመደመጣቸው ስለሆነ የምርጫ አዋጁን ከተቃዋሚዎች ጋር በማሻሻል በቀጣዩ ዙር ምርጫ ተቃዋሚዎች መጠነኛ ወንበር እንዲያገኙ በማድረግ የህወሀት/ኢህአዴግን የተራዘመ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ” የሚል ነው፡፡
ህወሀት/ኢህአዴግ የወቅቱ የሀገሪቱ ችግሮች እነዚህ ናቸው ይበል እንጅ የነገሮችን እድገትና የችግሮችን ዋና ምንጭ በውል ለመገንዘብ አልቻለም/አልፈለገም፡፡ ህወሀት/ኢህአዴግ እንደ ችግር የተቀበላቸውን ሀሳቦች እንደመነሻ ብንወስድ ትምክህትና ጥበት እንዴት ሊፈጠር ይችላል? ወቅታዊ ችግር ነው ወይስ በየደረጃው እያደገ የመጣ ችግር? ትምክህትና ጠባብነት እንደ ችግር እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ የችግሩን ምንጭ ሳይገነዘቡ እና የመፍትሄ ሃሳብ ሳያስቀምጡ በድርጅታዊ ግምገማ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል በግልፅ አላስቀመጠም ወይም ለማስቀመጥ አልፈገም፡፡ በተጨማሪም ዴሞክራሲና ልማት ጥያቄ አለመመለስ የብሔራዊ ደህንነት አደጋዎች ናቸው ብሎ ቢናገርም የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ በኢትዮጵያ እንዴት የህዝቡን ፍላጎት በሚመጥን ሁኔታ እውን ማድረግ እንደሚቻል ሳያሳይ የዴሞክራሲ መሰረታዊ ተቋማት እንዴት እንደሚገነቡ እና የዴሞክራሲና የልማት ጥልቅ ትስስርን ሳይገነዘብ ችግሩን ለማለፍ ብቻ በማድበስበስ እነደ ጊዜ መግዣ መንገድ እየተተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ስለሆነም በሕወሀት/ኢሕአዴግ የተሳሳተ የነባራዊ ሁኔታዎች ግምገማ ላይ ተመርኩዞ የሚሰጥ የመፍትሄ ሀሳብ ውጤታማ ስለማይሆን የለውጡን አይቀሬነት ያመላክታል፡፡
በእኔ እምነት ህወሀት/ኢህአዴግ እንደሚለው ሀገሪቱ አሁን ላለችበት ችግር መሰረቱ ጠባብነትና ትምክት ያመጣው ነው የሚለውን ብንቀበል እልኳን ጠባብነትና ትምክህት ላለፉት 26 ዓመታት ሕወሀት/ኢህአዴግ ውሃ እያጠጣና እየኮተኮተ በየደረጃው እያሳደጋቸው የመጡ ችግሮች እንጅ በድንገት የተፈጠሩ ስላልሆኑ የተፈጥሮ እድገታቸውን ጨርሰው የሚያደርሱትን ጥፋት አድርሰው ይከስማሉ እንጅ በድርጅት ግምገማ ሊጠፉ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ህወሀት በባህሪውና የተመሰረተበትን የቆመበትን የማነነት ፖለቲካ እስካልቀየረ ድረስ የራሱ የችግር መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህትን መዋጋት አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ለማታለልም ቢሆን በማንነት ላይ ተመርኩዞ ራስን ለማስተዳደር በህገ መንግስት የተፈቀደው መብት በክልሎች ዘንድ እያደገ ስለሚሄድና ከህወሃት ተፈጥሯዊ የጠቅላይነት ባህሪ ጋር በፅኑ ስለሚቃረን የውስጥ ሽኩቻውን ከጊዜ ጋር እያጠናከረው ይሄዳል፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ህወሃት አሁን በያዘወ የችግር አፈታት ዘዴ ከጊዜ ጋር በተቃራኒው መንገድ ስለሚሄድ ጊዜ በጨመረ ቁጥር የማንነት ጥያቄዎችና ሽኩቻዎች እያደጉ ድርጅቱ እራሱን በራሱ እየበላ ወደማይቀረው ሞት አፋፍ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም ለውጥ አይቀሬ ይሆናል፡፡
ዴሞክራሲ በመሰረቱ ለአብላጫ ድምፅ በመገዛት የአናሳውን መብት ማክበር ሲሆን በዚህ መሰረት ከህዝብ መካከል በህዝብ የተመረጠ እና ለህዝብ የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ አንፃር ህወሃት/ኢህአዴግን ስናየው ድርጅቱ እጅግ የጠበቀ ማዕከላዊነት ያለውና ጥቂቶቹ ብዙኃኑን እንደፈለጉ የሚገዙበት ስልጣንና ተዕዛዝ ከላይ ወደ ታች የሚወርድብት ከዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ በተፃራሪ የተፈጠረ ድርጅት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ህወሃትና ዴሞክራሲ አይተዋወቁ ወይም በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም፡፡ የህወሃትና የዴሞክራሲን ዝምድና በጨለማና በብርሃን መመሰል ይቻላል፡፡ ብርሃን ካለ ጨለማ የለም፤ ጨለማ ካለ ብርሃን የለም፡፡ ጨለማና ብርሃን አንዱ ሌላውን ካላጠፋ በስተቀር በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም፡፡ ህወሃትና ዴሞክራሲም እንዲሁ ናቸው፡፡ ህወሃት ካለ ዴሞክራሲ የለም፤ ዴሞክራሲ ካለ ህወሃት የለም፡፡ በተፈጥሮ ባህሪያቸው አንዱ ሌላውን ካላጠፋ በስተቀር በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም፡፡
በአጠቃላይ ህወሃት/ኢህአዴግ አሁን በያዘው የችግር መፍቻ መንገድና ከላይ በተነሱት ትንተናዎች መሰረት ትምክህትንና ጠባብነትን ታግሎ አመጣዋለሁ የሚለው ዴሚክራሲ እንደ ጊዜ መግዣና ማታለያ አድርጎ ስልጣኑን ለማስቀጠል የያዘው የመፍትሔ መንገድ በመሰረቱ የተሳሳተ የችግር ግምገማና መፍትሄ ላይ የተንጠለጠለ ስለሆነ የለውጡን ሂደት በእጅጉ ያፋጥነዋል፡፡ ለውጡንም አይቀሬ ያደርገዋል፡፡

2. ለውጡ ሊመጣ/ሊፋጠን/ የሚችልባቸው አማራጮች
ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን ከላይ ያነሳኋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ገዥውም ቡድን ቢሆን ለውጥ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ጥገናዊም ቢሆን ለውጥ ሳያደርግ ሊቀጥል እንደማይቻል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ለውጡ በምን ይመጣል በሚለው ላይ ግን የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ እይታዎች እንዷላቸው በማሰብ የለውጡን ማዕበል ሊያፋጥኑ ለለውጥም ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ አማራጭ የትግል ስልቶች መካከል፡-
ምርጫ
የትጥቅ ትግል
በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ
በህወሃት/ኢህአዴግ የሚወሰድ የማሻሸያ እርምጃ
መፈንቅለ መንግስት
ህዝባዊ እምቢተኝነት
የእርስ በእርስ ጦርነት እና የሐገር መፍረስ አደጋ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ አማራጭ መንገዶች ለውጡን ለማምጣት ያላቸውን እድል ለመለየት እያንዳንዱን መንገድ ያለውን መልካም ዕድል ወይም ችግር በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡

1ኛ. በምርጫ ለውጥ ማምጣት፡- ምርጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥን ሊያመጣ ይችላል ወይም አይችልም ከማለቴ በፊት ምርጫ በባሕሪው ከምንም አስቀድሞ ነፃነትን የሚሻና መራጩ የሚፈልገውን ለመምረጥ አማራጮች በእኩልነት የሚቀርቡበት መንገድ ነው፡፡ ለኢህአዴግ ምርጫ ማለት ዛሬ የሰው ልጅ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ልዕልና አንፃር ቢያንስ ቢያንስ ያለማስመሰያ ምረጫ በገዥነት መቀመጥ ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብና የኢህአዴግ ቁንጮ የሆነው ሕወሃት የአናሳ ቡድን ተወካይ በመሆኑ ብዙሃኑን ሁልጊዜ በኃይል አፍኖ ለመግዛት የማይችል መሆኑን ስለተረዳ የሚጠቀምበት የማታለያ ስልት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድርገው ወደስልጣን ያመጡትን ምዕራባውያን አሁን በደረሱበት የስነ መንግስት አወቃቀር ስልጣንን በምርጫ መለወጥ መርህአቸው እያደረጉት በመምጣታቸው ድጋፍ የሚደርጉላቸው አናሳ ቡድኖች ምርጫ እንዲያደርጉ ስለሚያስገድዱ የእነሱን ፍላጎት ለሟሟላት ብቻ ለይስሙላ የሚጠቀምበት ስልት እንጅ ዜጎች በነፃ ምርጫ የሚፈልጉት የሚያወጡበትና ያልፈለጉትን የሚያወርዱበት መንገድ እንዲሆን ስለሚፈልግ አይደለም፡፡ በነፃ ምርጫ የሚወለድ ዲሞክራሲ መሰረታዊ ባህሪው በብዙሃን ድምፅ መገዛትን እና የአናሳዎችን መብት ማክበር ነው፡፡ ሁለቱም መሰረታዊ ሃሳቦች ማለትም ነፃነትና ዲሞክራሲ ስለሌሉና የሕወሃት አፈጣጠር ከነዚህ በተቃርኖ የቆመ ስለሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ነፃነት ለዲሞክራሲዊ አስተዳደር ቅድመ ሁኔታ ነው፤ነፃነትና ዲሞክራሲ በሌሉባት ኢትዮጵያ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም፡፡

2ኛ. በትጥቅ ትግል ለውጥ ማምጣት፡-
ዓለም በካፒታሊዝምና ኮሚዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም ጎራ ተከፍላ ስትናጥበት የነበረው ዘመን የኮሚንይዝሙ ጎራ ተዳክሞ ከተፈረካከሰ በኋላ ዓለም በብቸኝነት በምዕራቡ የካፒታሊዝም ተፅዕኖ ስር ወድቃለች፡፡ የሁለቱ ጎራዎች ፉክክር በተመጣጣኝ ደረጃ በነበረት ወቅት በአንድ ጎራ የተቀመጠን ስርዓት ማውረድ የፈለጉ አካላት ከተቃራኒው ጎራ በሚያገኙት ድጋፍ መንግስታትን በትጥቅ ትግል ሲለዋውጡ አይተናል፡፡ ነገር ግን የኮሚንይዝሙ ጎራ ተዳክሞ ከተፈረካከሰ በኋላና ዓለም በምዕራቡ ዓለም የአስተሳሰብ ዕዝ ስር ከወደቀ በኋላ በስልጣን ላይ የተቀመጡ አምባገነኖችን በትጥቅ ለማውረድ የሚሞክሩ ለውጥ ፈላጊዎች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ የሚሰጣቸው ኃይል ባለመኖሩ በዚህ ስልት አምባገነኖችን ለመቀየር እየከበደ እንደመጣ የኮምኒይዝሙ ዓለም ከፈረሰበት ካለፉት 28 ዓመታት ወዲህ በጠመንጃ የተቀየረ አምባገነን ስርዓት ዓለሞኖሩ ግልፅ ማሳያ ነው፡፡ እዚህ ላይ የኮንጎንና የሊቢያ አምባገነኖች ከኮምኒዝም ጎራ መፈረካከስ በኋላ በጠመንጃ ኃይል የተገረሰሱ አምባገነኖች በመሆናቸው እንደመከራከሪያ ሊቀርቡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሁለቱ ሐገራት ላይ በትጥቅ ትግል ለውጥ የመጣበትን መንገድ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ኮንጎ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት መዝረፍ የፈለጉ ኃይሎች ያለ ኃፍረት የካቢላን ኃይሎች በቀጥታ በማስታቅና በመርዳት ስድስት ወር ባልሞለ ጊዜ ውስጥ ወትሮም ደካማና በሙስና የላሸቀውን የዛየር መንግስት ማውረዳቸው ከጀርባው የሚፈልጉትን ቡድን ወደስልጣን በማውጣት እሱን ተጠግተው የተፈጥሮ ሐብቷን ለመዝረፍ የፈለጉ ሰፍሳፋ የውጭ ኃይሎች የነበራቸውን ሚና በተለዬ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፡፡ የሊቢያውን አምባገነን ኮሌኔል ሞአመር ጋዳፊን ለማውረድ ምዕራባውያን በቀጥታ በዓየርና በምድር ጥቃት በማድረስ የሊቢያ ለውጥ ፈላጊዎች ጋዳፊን ለማውረድ ካደረጉት እንቅስቃሴ ጀርባ ምዕራባውያን የነበራቸው ጣልቃ ገብነት እጅግ ያፈጠጠ ስለነበረ በትጥቅ ትግል ለውጥ መጥቶበታል ለሚባል መከራከሪያ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ በዚህም መሰረት በኮንጎና በሊቢያ በትጥቅ የተደረጉ ለውጦች ምን ያህል በውጭ ኃይሎች ፍላጎት የተመሩ እንደነበሩ በማሰብ ባሁኑ ዘመን በትጥቅ ትግል ከሚደረጉ ትግሎች ጋር በተለዬ ሁኔታ መታየት አለባቸው እላለሁ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በቅርብ ጊዜ የትጥቅ ትግል የጀመሩት ይቅርና ዓለም በሁለት ጎራ በተከፈለችበት ወቅት ጀምረው የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነቡሩት ለአብነት ያህል የኮሎምቢያው ፋርክ፤ የኩርዶቹ ፒኬኬ፣ የስፔኑ ኤታ፤ የዩጋንዳው ሎርድ ሬስታንስ እና ሌሎችም የትጥቅ ትግል አራማጆች እየተዳከሙ እንደመጡና አሁን ለውጥን በድርድና በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ጥረት ላይ እንዳሉ ስናይ አሁን ባለንበት ዘመን በትጥቅ ትግል ለውጥ ለማምጣት እየከበደ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም በትጥቅ ትግል ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ኃይሎች ዓለም ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሰለባ በመሆናቸው እስካሁን ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት አልቻሉም፡፡ ወደፊም ቢሆን ለምዕራባውያንም ሆነ ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ጥቅም መከበር ተቃዋሚዎች ከገዥው ቡድን የበለጠ ምቹ ሆነው ስለማይገኙ ድጋፍና እርዳታ አግኝተው ገዥውን ቡድን በትጥቅ ትግል የማውረዳቸው እድል እጅግ የመነመነ ይመስለኛል፡፡

3ኛ. በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ለውጥ ማምጣት
በሐገሮች መካከል የሚደረጉ ዲፕሎማሲዊም ይሁን ሌላ ዓይነት ግንኙነት መሰረታዊ መነሻው ሁሉም የየራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በመሆኑ እያንዳንዷ የሚያደርጓት እንቅስቃሴ ከጥቅማቸው መከበር ወይም ማጣት ጋር ያለውን ተፅዕኖ በማስላት ነው፡፡ እንደ መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ዛሬ በመላው ዓለም በስልጣን ላይ የተቀመጡ አምባገነኖች ዜጎቻቸውን ቀጥቅጠው እየገዙ ቢሆንም በመሸጦነታቸው የውጭ ኃይሎችን ጥቅም በማስከበር ለለውጥ ከሚታገሉ የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች በላይ እጅግ የተመቹ በመሆኑ አገልጋይነታቸውን በማሳየት ከውጭ ኃይሎች የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ እያሳነሱ መጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የውጭ ኃይሎች የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም እስካስከበሩ ድረስ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀመው በደልና ግፍ ብዙም ግድ ስለማይሰጣቸው በበደል ሰለባዎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት ያሳስበናል እያሉ ሲቀልዱ ከመኖር አልፈው የእነሱን ጥቅም ያልነካን አምባገነል እንዲያውም በተቃራኒ በስውርና በግልፅ ድጋፍ ከማድረግ አልፈው ተፅዕኖ በመፍጠር ለለውጥ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ወትሮም ለዲሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር ደንታ የሌላቸው ራሳቸውም በአምባገነኖች ስር ያሉና የወደቀው የኮሚንስት ርዕዮተ ዓለም ትራፊ የሆኑ የምስራቁ ዓለም ሐገሮች ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚታገሉ ኃይሎችን ትግል ደግፈው ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብሎም አይታሰብም፡፡ እንግዲህ የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች መሸጦነታቸው በስልጣን ላይ ካሉት አምባገነኖች በላይ ሆኖ የውጭ ኃይሎች ብሔራዊ ጥቅማቸውን የበለጠ የሚያስጠብቁበትን መንገድ ካላሳዩ በስተቀር የውጭ ኃይሎች በአምባገነኖች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት ያላቸው ሚና በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ የማይታሰብ ነው፡፡

4ኛ. በህወሃት/ኢህአዴግ በሚወሰዱ የየማሻሸያ እርምጃዎች ለውጥ ማምጣት
ከዲምክራሲያዊ ስርዓት በተቃርኖ የተቀመጠው የሕወሀት/ኢህአዴግ ገዥ ቡድን ህዝባዊ አመፅ ባናወጠው ሰሞን አክራሪ ጠባብ ኃይሎችና የትምክህት ኃይሎች ለስልጣኑ አደጋ እንደሆኑበት በመግለፅ እነዚህን ጠባብና የትምክህት ኃይሎች በጥልቅ ተሃድሶ አጥፍቶ ለውጥ አመጣለሁ በማለት ሲንደፋደፍ ታይቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር እጦትና አንዳንድ መሰረታዊ የሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎችን ከተቃዋሚዎች ጋር በመነጋገር አንዳንድ ህጎችንና የህገ መንግስት ማሻሻያ በማድረግ ኢህአዴግ ራሱን ለውጦና አሻሽሎ በገዥነቱ ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት ለማሳከት የሄደበትን የምኞት መንገድ ታዝበናል፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደተጠቀሰው ኢህአዲግን በህዝባዊ አመፅ ጭንቅ ውስጥ አስገብቶት ዛሬ ሐገራችንን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንድትወድቅ ያደረጋት ጠባብነትና ትምክህት ነው የሚለው የሕወሀት/ኢህአዴግ የግምገማ ግንዛቤ እወነት ነው እንኳ ብንል ጠባብነትና ትምክህትን ገዥው ቡድን ላለፉት 26 ዓመታት ውሃ እያጠጣና እየኮተኮተ በየደረጃው እያሳደጋቸው የመጡ ችግሮች እንጅ በድንገት የተፈጠሩ ስላልሆኑ የተፈጥሮ እድገታቸውን ጨርሰው የሚያደርሱትን ጥፋት አድርሰው ይከስማሉ እንጅ በሕወሀት/ኢህአዴግ የድርጅት ግምገማ ሊጠፉ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ህወሀት በባህሪውና የተመሰረተበትን የማነነት ፖለቲካ እስካልቀየረ ድረስ የራሱ የችግር መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህትን መዋጋት አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ለማታለልም ቢሆን በማንነት ላይ ተመርኩዞ ራስን ለማስተዳደር በህገ መንግስት የተፈቀደው መብት በክልሎች ዘንድ እያደገ ስለሚሄድና ከህወሃት ተፈጥሯዊ የጠቅላይነት ባህሪ ጋር በፅኑ ስለሚቃረን የውስጥ ሽኩቻውን ከጊዜ ጋር እያጠናከረው ይሄዳል፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ህወሃት አሁን በያዘወ የችግር አፈታት ዘዴ ከጊዜ ጋር በተቃራኒው መንገድ ስለሚሄድ ጊዜ በጨመረ ቁጥር የማንነት ጥያቄዎችና ሽኩቻዎች እያደጉ ድርጅቱ እራሱን በራሱ እየበላ ወደማይቀረው ሞት አፋፍ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም በህወሃት/ኢህአዴግ በሚወሰዱ የየማሻሸያ እርምጃዎች ለውጥ ማምጣት አይቻላቸውም፡፡

5ኛ. በመፈንቅለ መንግስት ለውጥ ማምጣት
በመሰረቱ መፈንቅለ መንግስት ሊደረግ የሚችለው የፖለቲካውና የወታደራዊ ኃይል አንደኛው ከሌላው ገለልተኛ ሆኖ የተዋቀረ ሲሆንና አምባገነኖች ባሉበት ሐገር ወታደራዊ ኃይሉ የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ከሆነ ወይም ወታደራዊ ኃይሉ ከሲቪል አስተዳደሩ የተለየ አመለካከት ሲኖረው ነው፡፡ በግልፅ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋማትና የደህንነት ኃይሎች እና ገዥው የሕወሀት/ኢህአዴግ በዘርም ሆነ በአመለካከት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች በመሆናቸው እንደ ሁለት የተለያዩ አካላት ሊታዩ አይችሉም፡፡ አመራሩ መቶ በመቶ በአንድ ሰፈር ልጆች የተያዘው የኢትዮጵያ የወታደራዊ ኃይል የሰፈሩ ልጆችና የጥቅም ተጋሪው የሆኑ የሲቪል አስተዳደሩን መሪዎች አውርዶ በጠላትነትና እንደ ባዕድ በሚቆጥራቸው የዲሞክራሲ ኃይሎች እንዲተካ የራሱን ሚና ይጫወታል ብሎ መጠበቅ ሲበዛ የዋህነት ይሆናል፡፡ ስለዚህም በሕወሀት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ለውጥ በመፈንቅለ መንግስት ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡

6ኛ. በህዝባዊ እምቢተኝነት ለውጥ ማምጣት
የሕወሀት/ኢህአዴግ የማስመሰያ የሲቪል አስተዳደር ኢትዮጵያን የማስተዳደር አቅሙ ተዳክሞ ዛሬ ሐገራችንን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡ ለውጥ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት ለውጥን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ብዙ ዋጋ የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖትና የሞራል ሰዎች፣ የኪነጥበብና የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ያደረጉአቸው አስተዋፅዖዎች ስርዓቱ ዛሬ ለወደቀበት የጭንቅ መንገድ የራሰቸውን ሚና አበርክተዋል፡፡ በሕወሀት/ኢህአዴግ አስተሳሰብም ዛሬ ላጋጠመኝ ፈተና መነሻው ጠባብነትና ትምክህት ነው የሚለው አስተሳሰብም ለማታለያነት ታስቦ በሰነድና በሕግ የተቀመጠ የመብትና የአስተሳሰብ መሰረትም እያደገ መጥቶ ጥቂቶች ብዙሃኑን እየገዙ የሚኖሩበት ስርዓት በህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ለውጥ እየተገፋ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ ደረሸበታለሁ በሚለው ግምገማም ሆነ አማካሪዎቹ በአደባባይ የሚሰጡት ምክር ለውጥ ማድረግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አከራካሪነቱ አክትሟል፡፡ ነገር ግን የሕወሀት/ኢህአዲግ የችግር ግምገማና የመፍትሔ መንገድ ችግሮችን የመፍታት አቅም ስለሌላቸው የትንሽ ጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሕዝባዊ ተቃውሞውን አያቆመውም፡፡ ሕወሀት/ኢህአዴግ በጥገናዊ ለውጥ ሊያቆመው የፈለገው ስርዓትም መፈራረሱ አይቀሬ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ የታገሉ ዜጎች በፈጠሩት የፖለቱካ ጫና ያስከተለው ህዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ በሕወሀት/ኢህአዴግ የግምገማ ድምዳሜ ጠባብና የትምክህት ኃሎች የፈፀሙት ሕዝባዊ አመፅ ስርዓቱን ወደ ከፍተኛ ጭንቅ በመክተት ባለፉት 25 አመታት ካጋጠሙት ፈተናዎች በላይ ወደ መፍረስ ጫፍ ስላመጣው የሲቪል አስተዳደሩን አፍርሶ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ሐገራችንን በወታደራዊ አገዛዝ ስር እንድትወድቅ በማድረግ የሲቪል አስተዳደሩን ለመመለስ ፍርሃትና ጥርጣሬ ውስጥ ከቶት ይገኛል፡፡ ከላይ ከተነተንናቸው የትግልና የለውጥ አማራጮች መካከል ሕዝባዊ እምቢተኝነት በስርዓቱ ላይ ተጨበጭ ጫና በመፍጠር ከሌሎች ስልቶች የተሻለ ለውጥ የማምጣትም አቅም ያለው ስልት መሆኑን አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና አሁን ባለው የዓለም የኃይል ሚዛን አሰላለፍ አንፃር ሲታይ በገዥው ቡድን ላይ የመጨረሻውን ለውጥ ለማምጣት የተሻለ እድል ያለው የትግል አማራጭ ስልት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

7ኛ. የእርስ በእርስ ፍጅት እና የሐገር መፍረስ አደጋ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንደምንገነዘበው ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር መልካም አጋጣሚ የነበሩ በርካታ የለውጥ ሙከራዎች በእርስ በእርስ ሽኩቻና በአመራር ድክመት ምክንያት በትክክል ሳንጠቀምባቸው በማለፋችን አሁን ሐገራችን ላለችበት ምስቅቅል አድረሰናታል፡፡ አሁንም ሊመጣ ያለውን ለውጥ በተጠናና በምክንያታዊ አስተሳሰብ ካልገራነው በስተቀር አሁን እያቆጠቆጡ የመጡት የአመለካከት ጫፎች በኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ፍጅትና የሐገር መፍረስ አደጋ ያንዣበበ መሆኑ ብዞዎቻችን ባንወደውም አፍጥጦ እየመጣ ያለ ሐቅ ነው፡፡ ሐገር መፍረስ በዜጎች ላይ የሚያመጣውን ስቃይ፣ በአጎራባች አካባቢዎች የሚፈጥረውን ትርመስ ግምት ውስጥ በማስገባት በሌሎች ሐገሮች የደረሰው መከራ በእኛም ላይ ከመድረሱ በፊት ሁላችንም ለመፍትሔው የበኩላችንን መልካም አስተዋፅዖ ማድረግ ይኖርብናል እላለሁ፡፡

3. የሚመጣውን ለውጥ እንዴት ወደ ተሻለ ሁኔታ መምራት እንቻላለን
በሁለቱ ዋና ርዕሶች ለማሳየት እንደሞከርኩት ሕወሀት/ኢህአዴግ ችግሮችን የሚገመግመው በተሳሰተ መንገድ መሆኑና የሚያቀርባቸው የምፍትሔ ሐሳቦችም ችግሮች አሁን ያሉበትን ደረጃ የማይመጥኑ በእውነትም መፍትሔ የማያመጡ በሙሆኑ በእኔ አስተያዬት በኢትዮጵያ የለውጥ ማዕበል አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያና አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሕዝባዊ እምቢተኝነት በተግባር ውጤት ያመጣና የወደፊቱንም የሐገራችንን የለውጥ ሂደት በመወሰን ከሌሎች አማራጮች የተሻለ እድል እንዳለው ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን በህዝባዊ እምቢተኝነት የሚመጣ ለውጥ በአግባቡ ካልያዝነው የእርስ በእርስ ፍጅትና የሐገር መፍረስ አደጋም ሊያመጣ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን አደጋ በመገንዘብና ካለፈ ታሪካችን ትምህርት በመውሰድ ለዉጡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአወንታዊነት የሚቀበሉትና ለውጤታመነቱም የሚሰሩለት የጋራ አጀንዳ መፍጠር ይኖርብናል፡፡
እዚህ ላይ የታሪካችን አካል የሆነውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የመሬት ላራሹ አጀንዳን መጥቀስ አሁን ላለንበት ሁኔታ ትምህርት ሰጭ ይመስለኛል፡፡ የመሬት ላራሹ ጥያቄ በአፈፃፀሙና በውጤታማነቱ ላይ አከራካሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በወቅቱ ግን በኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎችን ለማሰባሰብና ለማስተባበር በብዙዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትልቅ የጋራ አጀንዳ ነበር፡፡ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን ያለመተማመን የሚቀንስ የኢትዮጵያን የሽግግር ወቅት የሚመጥን ሁሉን አቀፍ የሆነና በጊዜ የተገደበ “የባለ አደራ መንግስት መቋቋም አለበት” የሚል አጀንዳ ከፍ ብሎ መውጣትና መሰባሰቢያ የለውጥ ግብ ሆኖ መቀረፅ አለበት፡፡ የባለ አደራ መንግስቱ ይዘት፣ ስልጣንና ኃላፊነት ውክልናና አሳታፊነት በሂደት በዝርዝር በድርድርና በውይይት ቅርፅ ሊይዝ የሚችል ጉዳይ ይሆናል የሚል እምነትም አለኝ፡፡

ከትውልድ ተጠያቂነት ለማምለጥ የተሻለውን ነገር ለመስራት ከአሁን የተሸለ ጊዜ የለንም!!!!
አመሰግናለሁ!!!

Filed in: Amharic