>
6:50 pm - Sunday July 3, 2022

ለመለስ የተፃፈ ደብዳቤ (ፍቃዱ ጌታቸው)

እንደምን አለህ ጋሼ እንደምን ነህ መለስ
ትመጣለህ ስንል ቀረህ ሳትመለስ
እኛማ ይሔውልህ
ባንተ ሌጋሲና ባንተ ትልቅ ራዕይ
በየአደባባዩ እንላለን ዋይ ዋይ
ዛሬም ጀነራልህ ተኩስ ነው ትእዛዙ
ወገን ያጋድማል የግፍ አፈሙዙ
ለምንድን ነው ስንል ስምክን አስቀድመው
ከክርስቶስ በላይ ምስልህን አትመው
ቅዱስ መፅሐፍ ይመስል
ባንተ ራዕይና በሌጋሲህ ምለው
ቢረፈርፉንም አላለቅንምና
ደብዳቤ ላክንልህ ከሞት የተረፍነው!
~
የሆነስ ሆነና ግን አንተ ደህና ነህ
እኛማ ይኸውልህ
ደርሰህ ስትናፍቀን
አይሞትም የምትል ሙዚቃ ሞዝቀን
መቃብርህን ልንስም አበባ ልናኖር ስላሴ ብንመጣ
ፌደራል ያይሃል እስረኛ ይመስል ሾልከህ እንዳትወጣ
መቼም ስላሴ ውስጥ
ባለስም ነውና የሚቀበርበት
አንተን አየት አርገን ዞር ስንል ድንገት
እነፊታውራሪ
ግራ’ዝማች
ቀኝ’ዝማች
ፊተኛ ባለስም የሆኑት አባቶች
ያለዘብ ቆመዋል እነ አብዲሳአጋ
ጀግና መሃል ሳለህ ምነው በድንህ ሰጋ!
~
የሆነስ ሆነና
ሃየሎም ደህና ነው
እዛም ትግል ይመራል
እስር ቤት ሰባብሮ ታራሚ ያስፈታል
እዛም ከፊት ሆኖ ጭቁን ያታግላል
እዛም በጀግንነት በለኮሳት ሻማ
ነፃ ነኝ ባለባት ርዕሰ ከተማ
ትንሽ ግሮሰሪ ይገባ ይሆን ደፍሮ
እዛስ ጀማል ያሲን ፈጠረ አምባጓሮ
ሃየሎምን ሰዋው በሐሺሽ ናላው ዞሮ
እኛማ ይኸውልህ
ብዙ ሃየሎሞች ፈጥረን ስናበቃ
እልፍ ጀማል ያሲን ይሆናል ጥበቃ
ይኸው ባደባባይ
የጀግኖቻችን ደም በየቦታው ፈሶ
አለ ጀማል ያሲን ሞት ሚበይንበት ፍርድ ቤቱ ፈርሶ!!
~
ግን አንተ ደህና ነህ
አቡነ ጳውሎስስ ብፁው እንዴት ናቸው
እዚያም እንደምድሩ
አንድ አንቀፅ ያክላል መጠሪያ ስማቸው
ደረታቸው ግድም “ሽጉጥ” የሚያደርጉት አለ መስቀላቸው
እኛማ ይኸውልህ
ዳያስፖራ ጳጳስ ሾመን ባደባባይ
ከበአል ቀን ውጪ ፊታቸውን አናይ
ሰው ሲሞት
ህዝብ ሲያልቅ
እምነት ሲተራመስ አያውቁም ግሳጤ
ዝም ዝም ናቸው
ቆባቸው የጳጳስ ነብሳቸው የአጤ!!
~
እንደምን አለህ ጋሼ እንደምን ነህ መለስ
ትመጣለህ ስንል ቀረህ ሳትመለስ
ከቻልክ ፃፍልን ለደብዳቤያችን መልስ!!
Filed in: Amharic