>
6:04 pm - Tuesday October 19, 2021

በቤንሻንጉል ልዩ ኃይል ፖሊስ እገዛ ከ50 በላይ ዐማሮች ሲገደሉ ወደ 400 የሚሆኑ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ (ስዩም ተሾመ)

በቤንሻንጉል ልዩ ኃይል ፖሊስ እገዛ ከ50 በላይ ዐማሮች ሲገደሉ ወደ 400 የሚሆኑ ቤቶች ተቃጥለዋል፤

ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ- ከማሽ ዞን፣ በሎጅጋንፎይ ወረዳ፣ በሎደዴሳ ቀበሌ ቀን፤ ከጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ መነሻ ምክንያት፤ የክልሉ ልዩ ኃይልና በወረዳው አመራሮች አስተባባሪነት የዐማሮችን ንብረት መዝረፍ እየተለመደ እንደመጣና በዚህም ምክንያት አልፎ አልፎ ግጭት ይፈጠር ነበር፡፡ በሎንደዴሳ ቀበሌ የዐማራ ንብረት ለማውደም የሄደ የጉምዝ ተወላጅና ባለንብረቱ ሰው መካከል ጠብ ተነሳ፡፡ በዚህ መካከል ሊዘርፍ የሄደው ሰው ይሞታል፡፡ ይህን ጊዜ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ኖኖ እና ወ/ሮ ጥሩነሽ እንዴት ዐማራ የእኛን ሰው ይገድላል! በሚል ቁጭት የልዩ ኃይል ፖሊሱን በማስተባበር በዐማሮች ላይ ጀምላ ጥቃት መድረስ ጀመረ፡፡

ውጤቱ- በቀበሌው ከ2000 በላይ አባውራዎች ሲኖሩ አብዛኛዎቹ ከሳር የተሠሩ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲቃጠሉ የቆርቆሮ ጣራ ያላቸው ብቻ ናቸው የተረፉት፡፡ በዚህም ከ400 በላይ የሚሆኑ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የሰው ሕይወት፤ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ቁጥር ቢናገሩም እስካሁን ከ50 በላይ ሰው እንዳለቀ ያነጋገርናቸው ገልጸውልናል፡፡ አስከሬን በየቦታው ወዳድቆ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን አልተነሳም፡፡ አስከሬን ለማንሳት የሄዱ ሰዎች ተከልክለዋል፡፡ በጅምላ በጉድጓድ የተከማቸ አስከሬንም እንዳለ ተናግረዋል፡፡ መትረፍ የሚችሉ ሰዎች ከአስከሬን ጋር አብረው በአንድ ጉድጓድ በመጠራቀማቸው ሕይወታቸው እንዳለፈም ተናግረዋል፡፡

አቶ አልማው የተባለ የቀበሌው ነዋሪ በሕይወት ከአስከሬን ጋር ወደ ጉድጓድ በመጣሉ አብሮ ሊሞት እንደቻለ ምስክሮች ገልጸዋል፡፡

ከ300 የሚበልጡ ሕጻናትና ሴቶች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም፡፡ የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ወደ አካባቢው የደረሰ ቢሆንም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ኖኖ ከእኛ አቅም በላይ አልሆነም እያለ እየመለሰ እንደሆነም ነግረውናል፡፡ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አስከሬኖች አልተነሱም፡፡ የሞቱት ሰዎች ቁጥርም ሊያሻቅብ እንደሚችል ነግረውናል፡፡

Filed in: Amharic