>
5:13 pm - Friday April 18, 4842

“ብሔሮክራሲ” እና ጣጣው፤! (በውብሸት ሙላት)

በአሁኑ ሕገ መንግሥት መሠረት በኢትዮጵያ የሉዓላዊነት መንበር የተሰጠው ለብሔሮች፣ ለብሔረሰቦችና ለሕዝቦች ነው፡፡ የትኛውም ሥልጣን መነሻውና መድረሻው ከሰማንያ በላይ የሆኑት ቡድኖች እንጂ መቶ ሚሊዮን ገደማ የሆነውን ኢትዮጵያውያንን በቀጥታ አይመለክትም፡፡ በመሆኑም፣ የአገዛዝ/የአስተዳደር መሠረቱ ጅምላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን አስቀድሞ ወደ ብሔር፣ብሔረሰብ እና ሕዝብ ከተከፋፈለ በኋላ የሚገኙት ቡድኖች ናቸው፡፡

ከዚህ አንጻር ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሚሆነው “ዴሞ” የሚለው ቃል ሳይሆን በእሱ ምትክ የግሪኩ “ኢትኖ/ethno” የሚለው ነው፡፡ በአማርኛ “ብሔሮ” ብንለውና ‘ክራሲያን’ ብንጨምርበት፣ በአንድ ላይ “ብሔሮክራሲ” ይሆናል፡፡ በመሆኑም ሉዓላዊነቱም እንደሌሎቹ ሕዝባዊ ሉዓላዊነት ከመባል ይልቅ የብሔር ሉዓላዊነት ነው መባል ያለበት፡፡ በውክልናም በተሣትፎም በዋናነት መረጋገጥ ያለበት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦች ስለሆነ ነው፡፡

‘ታዲያ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚሰጠው ሁሉም ብሔሮች ተደምረው አይደል ወይ? ምን ለውጥ አለው?’ እንል ይሆናል፡፡ የሁሉም ብሔሮች አባላት በአንድነት ሆነው ሙሉ ኢትዮጵያውያንን መስጠታቸው እሙን ነው፡፡ ቢሆንም ለሥልጣን፣ ለውክልና፣ ለተሳትፎና ለመሳሰሉት ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያንን በእኩል ወይንም በተቀራራቢ ቁጥር ተከፋፍለን ሳይሆን የምንወከለውና በሥልጣን የምንሳተፈው በየብሔራችን መሠረት ነው፡፡

ለአብነት በፌደሬሽን ምክር ቤት ያለውን አወካከል ብናይ መነሻው የክልል ሕዝብ ሳይሆን ብሔሮች ናቸው፡፡ በሕዝብ ብዛት ቢሆን ኖሮ በፌደሬሽን ምክር ቤት ብዙ መቀመጫ ሊኖረው የሚችለው የኦሮሚያ ክልል ነበር፡፡ የደቡብ ክልል ተወካዮች ግን ኦሮሚያና አማራ በአንድነት ካለቸው ተወካዮች ይበልጣል፡፡ በመሆኑም የአብርሃም ሊንከንን “ከሕዝብ፣ለሕዝብ የሕዝብ” የሚለውን የዴሞክራሲ አተረጓጎም ትንሽ ለወጥ በማድረግ ብሔሮክራሲ ማለት ‘ከብሔር፣ለብሔር የሆነ የብሔር መንግሥት ነው’ ማለት እንችላለን፡፡ በአገራችን ያለው ሥርዓት ከዴሞክራሲ ይልቅ ብሔሮክራሲ ነው፡፡

የብሔሮክራሲያዊ አስተዳደር ስልት ጥቅም እንዳለው ሁሉ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ መዘዝ ቁጥር አንድ ማእከላዊ መንግሥትን ለመጋራት ሲባል የሚመነጭ ነው፡፡ ማእከላዊው (የፌደራል) መንግሥቱን ለመምራት በአንድ በኩል ብቃት ይፈለጋል፡፡ በሌላ በኩል የብሔረሰቦች ውክልና ያስፈልጋል፡፡ ውክልናው ደግሞ እንደ ብሔረሰቡ አባላት ቁጥር መመጣጠን ይጠይቃል፡፡

ምጥጥኑ ደግሞ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በሚያዙት የሥልጣን ዓይነቶችም ጭምር መሆንን ይጠይቃል፡፡ እዚህ ላይ ብቻ የሚነሳውን ችግር ብንመለከት ብቃት ያለውን ሰው ሲፈለግ ውክልናው ይዛነፋል፡፡ ውክልናው ሲሟላ ብቃት ይጎድላል፡፡ ውክልናው ሲሟላ የሥልጣን ዓይነቶቹ (ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣የደኅንነት ኃላፊነት ወዘተ…ከግብርና፣ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትርነት ጋር ስለማይመጣጠኑ) አልመጣጠን ይላሉ፡፡ ከእዚያ ቅሬታ ይነሳል፡፡

የዚህ የመጀመሪያው መዘዝ ሌላ ተከታይ መዘዝ አለው፡፡ ቁልፍ የፖለቲካ ሥልጣን ቦታዎችን ለማግኘት በሚደረግ ሽኩቻ የሚፈጠረው መቃቃር ነው፡፡ መቃቃሩ፣በልሂቃኑ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሕዝብ በቀላሉ መተላለፉ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ሽኩቻው ውስጥ በተግባርም ባይሆን እንኳን በሐሳብና በመንፈስ መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡ የሰው ልጅ ባሕርይ ስለሆነ፡፡ ቁልፍ የፖለቲካ ሥልጣንን ለረጅም ጊዜ በአንድ ብሔር አባላት እጅ ብቻ ከወደቁ በልሂቃን ብቻ ሳይወሰን በሌሎች ብሔሮች ላይ ቅያሜው መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡

መዘዝ ቁጥር ሦስት፡- ከላይኞቹ መዘዞች የሚወለድ ነው፡፡ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችን የሚቆጣጠር ቡድን ኢኮኖሚያዊ አውታሩንም መቆጣጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ “የነፍጠኛው ሥርዓት የፖለቲካ ሥልጣኑን በመቆጣጠር ኢኮኖሚውንም ተቆጣጥሮታል” የሚል ግምገማ ኢሕአዴግ እንዳለው የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ፣የነፍጠኛውን ሥርዓት አከርካሪ በመሥበር በሌላ ኃይል መተካትን መፍትሔ አድርጓል፡፡ እናም፣ ቁልፍ የፖለቲካ ሥልጣን ያለው ብሔር ኢኮኖሚያዊ የበላይነት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

መዘዝ ቁጥር አራት፡- ብቃት ያለው ተቋም ግንባታ እንዳይኖር ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ብቃት ያለቸው የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ተቋማት ከተገነቡ የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ ብልግናን በቀላሉ መቅረፍና ማስተካከል ስለሚቻል እንዲህ ዓይነት ተቋማት ለብሔሮክራሲያዊ አስተዳደር ምቹ አይደሉም፡፡ በመሆኑም፣ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት ዳተኝነትን ስለሚያስከትል በብሔሮች መካከል የሚነሳን አለመግባባት እንኳን በቀላሉ እልባት መስጠት አዳጋች ይሆናል፡፡

መዘዝ ቁጥር አምስት፡- ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር ይያያዛል፡፡ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሲባል መቶ ፐርሰንት ሁሉን ነገር በራሳቸው የብሔር አባላት ብቻ ለመሙላት ጥረት ይደረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ባይኖርም ከማን አንሼ ይመጣል፡፡ ከተለያዩ ክልሎች ከሚመነጭ ገቢ ጭምር ሳይቀር እተቀነሰ በድጎማ መልክ ለሁሉም ይሰጣል፡፡ የድጎማ በጀቱን ሳይቀር በአግባቡ ካለማስተዳደራቸው የተነሳ (ብዙውን ለግላቸው ሊያውሉት ስለሚችሉም) ሌሎቹ ቅሬታ ውስጥ ይገባሉ፡፡

መዘዝ ቁጥር ስድስት፡- ከአምስተኛው የሚመነጭ ነው፡፡ ራስን በራስ በማስተዳደር ሰበብ የሌሎች ብሔር ተወላጆችን ከሥራ ማባረር፣ ከአካባቢው ማፈናቀል ይከሰታል፡፡ ተከስቷልም፡፡ ለነገሩ በግዲያ የታጀበም ጭምር! ራስን ማስተዳደር ሲባል የየክልሉን፣ዞኑን ወዘተ መሬት ጭምር የብሔር የግል ሃብት አድርጎ መቁጠር ልማድ ሆኗል፡፡

መዘዝ ቁጥር ሰባት፡- የተለያዩ ውሳኔዎች በሚኖሩበት ጊዜ በውሳኔው የሚሳተፉት ሁሉ ከብሔራቸው አንጻር መመልከታቸው ስለማይቀር፣ እያንዳንዱ ብሔርም እንዲሁ ስለሚጠብቅ፣ከአብሮነት ይልቅ ወደ ነጠላ ብሔርተኝነት ማድላት ያይላል፡፡ በሁሉም ዘርፍ የብሔሮች ፉክክር ይጧጧፋል፡፡ እየበዛ ሲሄድ ጥልንም ይወልዳል፡፡

መዘዝ ቁጥር ስምንት፡- በአገሪቱ የሚፈጠሩትን ችግሮች ከብሔር አንጻር ብቻ መመልከትን ማምጣቱ ነው፡፡ የግለሰቦችም ግጭት ሳይቀር የብሔር ቅርጽ መያዝ የተለመደ ይሆናል፡፡ በሚኖሩት የፍትሕ ተቋማት እንኳን የሚሰጥን ውሳኔ መቀበል ይቀራል፡፡

መዘዝ ቁጥር ዘጠኝ፡- በርካታ ችግሮች የብሔር ቅርጽ መያዛቸው ስለማይቀር ወይንም እንዳይዙ ፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ በአገሪቱ ውስጥ መግነን ማስከተሉ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ውሳኔዎች የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት በማድረግ እንጂ ቀድሞ በተዘጋጀ ሕግ፣በታወቀ መርሕ ስለማይመሩ ቀድሞ የሚገመት አሠራር እና ውሳኔ ባህል አይሆንም፡፡

ከላይ የተገለጹትን መዘዞች የሚያባብሱ በርካታ አሠራሮች በአገራችን ዳብረዋል፡፡ ከብሔሮክራሲያዊ አስተዳደር ውጭም መሆን አለመቻል ደግሞ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ሌሎች አገራት ሲጀመር ብሔሮክራሲያዊ አስተዳደር አልመሠረቱም፡፡ ይሁንና ከኢትዮጵያ ጋር የተቀራረበ የፌደራል ሥርዓት የሚከተሉ አገራት የብሔሮችን የውክልና፣ የተሳትፎ፣ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት፣ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሥርጭትን፣ ባህላዊ መብቶችን ለማረጋገጥ እና ለማስከበር የሚስችሏቸውን ተቋማት ገንብተዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን አስፍነዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊነትን ባህላቸው አድርገዋል፡፡

ምስኪን ኢትዮጵያ ከሕዝቦቿ አንድነት በስተቀር ምንም ለሌላት!

Filed in: Amharic