>
5:13 pm - Sunday April 19, 1615

ሐውዜን እና ነቀምት (ሃብታሙ አያሌው)

ያለፈውን ሰንበት እሁድ እና ቀዳሚት ሰንበት (ቅዳሜን) ያሳለፍኩት በናሽቪል ቴነሲ ስለነበረ የነቀምቱን ግፍ ለመስማት ጆሮዬ ባዳ አርጎኝ ቆየ። ምንአልባትም ጆሮዬም ልቦናዬም ሸክሙ ከብዷቸው እየሸሹ ይሆን እንደው እርግጠኛ አይደለሁም። እንደ ዘመነ አበው፣ እንደ ህገ ሙሴ የሰው ልጅ በኢትዬጵያ ምድር ላይ ኤሎሄ እያለ በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን መስማት ከጉተና የከበደ ሸክም ነው።

በዘመነ ሐዲስ በድንጋይ ተወግሮ መሞት ከህግ ውጪ በውንብድና የተፈፀመው በቀዳሜ ሰማዕት በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ ሲሆን ክርስቶስንም አይሁድ ሊወግሩት የእየሩሳሌምን የቋጥኝ ስባሬዎች አንስተው እንደ ነበረ የታወቀ ነው። እናማ ዛሬ የነቀምት ኮብልስቶን እንደምን ለጭካኔ ዋለ ካልከኝ ሃውዜንን ጠይቃት ከማለት በቀር የተሻለ መልስ የለኝም። የህወሓት ቡድን ህፃናትን በትምህርት ቤት፣ ወላጆቻቸውን በገበያ ላይ ሳሉ እንደ ወፍ እየበረረ እሳት ከሚተፋ ጀት በሚጣል ቦንብ ጭዳ እንዲሆኑ አድርጎ የፖለቲካ ትርፍ እንደቃረመ፣ ጠይቅ እንጂ ሃውዜን የምትደብቅህ ሚስጥር የለም።

በነቀምት ኮብልስቶኖች የሰውን ልጅ ራስ እንደ ቅል እያነከተ፤ እንደ እንቧይ እያፈረጠ፤ የፖለቲካ ሂሳብ ለመስራት የተነሳው ማን ነው ? ህወሓት እንዲህ ያለ ጨካኝ ነው፤ ለስልጣኑ እርከን መወጣጫ፤ ቀድሞም እየፈጀ የመጣው የትግራይን ህዝብ ነው። በህወሓት የሂሳብ ቀመርም ሆነ በህወሓት ግፍ በተቆጡ በሌሎች የግፉዓን የቁጣ በትር ትግሬ ሆኖ መገኘት ብቻውን ለሰቆቃ ሞት የሚያበቃ ምክንያት እንዳይሆን ነቅቶ በመጠበቅ፤ ንፁሃን ዜጎችን መታደግ፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም። ማንም መርጦ የተወለደ የለም፤ የጅምላ ፍረጃና ጥቃት እንዳይፈፀም መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል። የተገደሉት ከህወሓት ተልዕኮ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ለፍቶ አዳሬዎች ከሆኑ በውነቱ ሁላችን ድርጊቱን ልናወግዝ ይገባል። ህወሓት በህዝብ ትግል ትንፋሽ ሲያጥረው ነቀምትን ሐውዜን እያደረጋት እንደ ሆነ መገመቱ ለእውነት የቀረበ ይመስለኛል። ግፍ እማይታክተው የወንበዴ ስብስብ ይህ ሁሉ ጦስ ከሱ በቀር ማንን ሊመለከት ይችላል ? …
እልፍ ሃዘን አዕላፍ ቁጭት !

Filed in: Amharic