>

ኢህአዴግን የማይቃወም የደርግ ደጋፊ ነው! (ስዩም ተሾመ)

በዘንድሮ አመት የተነሳውን የተቃውሞ አንቅስቃሴ ለመግለፅ በስፋት ጥቅም ላይ ከዋሉ ቃላት ውስጥ፤ “ሰላም – ፀረ-ሰላም፥ ሽብር – ፀረ-ሽብር፥ ልማት – ፀረ-ልማት፥ ሕዝብ – ፀረ-ሕዝብ፥ ሕጋዊ – ሕገ-ወጥ፣..” የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ ደግሞ በመንግስት ሚዲያዎች፤ “የፀረ-ሰላም ኃይሎች፥ የነውጥና ብጥብጥ ቀስቃሾች፥ የሽብር ኃይሎች፥…” የሚሉ ለዛ-ቢስ አባባሎች (Cliches)፣ “ሣይቃጠል በቅጠል፥ ፀጉረ-ልውጥ፥…” የመሳሰሉ አሰልቺ ዘይቤዎች (tired metaphors)፣ እንዲሁም “ጥቂት፥ የተወሰኑ፥ አንዳንድ፥…” የሚሉ የግብር-ይውጣ አገላለፆች (lazy writing) በስፋት ይደመጣሉ። እንግሊዛዊው ፀኃፊ “George Orwell” ይሄን “የፖለቲካ ቋንቋ” (Political language) በማለት ይገልፃል። የሀገራችን ምሁራን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ያደረጋቸው ፍርሃት ዋና ምንጩ ደግሞ የፖለቲካ ቋንቋ ነው።

የፖለቲካ ቋንቋ በስፋት በሚዘወተርበት ሁኔታ አብዛኞቹ ምሁራን “ደጋፊ” ወይም “ተቃዋሚ” ተብለው በጅምላ እንዳይፈረጁ በመስጋት አስተያየት ከመስጠት ይቆጠባሉ። እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ከትችትና ነቀፌታ አልፎ ለእስራትና ሞት ሊዳርግ ይችላል። ስለዚህ ምሁራን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አሰተያየት በነፃነት መግለፅ ይፈራሉ። ነገር ግን፣ George Orwell”፣ የመንግስትን አቋምና እርምጃ በይፋ ለመቃወም የሚፈሩ ምሁራንን “un-political’ imaginative writers” በማለት ይገልፃቸዋል። እነዚህ ምሁራን ለዛ-ቢስ፥ አሰልቺና የግብር-ይውጣ የሆኑ የፖለቲካ ቃላትና አባባሎችን ከሚፅፉትና ከሚያነቡት የመንግስት ጋዜጠኞች ብዙም የተለዩ እንዳልሆኑ እንደሚከተለው ይገልፃል፡- 

“And so far as freedom of expression is concerned, there is not much difference between a mere journalist and the most ‘un-political’ imaginative writer. The journalist is unfree, and is conscious of un-freedom, when he is forced to write lies or suppress what seems to him important news: the imaginative writer is un-free when he has to falsify his subjective feelings, which from his point of view are facts. …If he is forced to do so, the only result is that his creative faculties dry up. Nor can he solve the problem by keeping away from controversial topics. There is no such thing as genuinely non-political literature.” (George Orwell, Politics And The English Language, 1946)

በፍርሃት ምክንያት ሃሳብና ተቃውሞን በይፋ አለመግለፅ መንግስት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ላለው ጭቆናና በደል ድጋፍና ትብብር እንደማድረግ ነው። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ምሁር ለበደልና ጭቆና ድጋፉን ከመስጠት ይልቅ ፍርሃቱን መጋፈጥ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ የፍርሃቱ ምንጭ የሆነው የፖለቲካ ቋንቋ መሰረታዊ ዓላማ ምን እንደሆነ ከመረዳት ይጀምራል። እንደ “George Orwell” አገላለፅ፣ የፖለቲካ ቋንቋ ውሸትን እውነት፣ ግድያን ክብር በማድረግና ከነጭ-ውሸት ጋር ህብረት እንዳለን ለማስመሰል የተቀረፀ ነው “Political language is designed to make lies sound truthful and murder respectable, and to give an appearance of solidity to pure wind”.

በዚህ ላይ “Edward Said” የተባለው ምሁር ደግሞ ምሁራን ከእንዲህ ያለ ቋንቋና ተግባር ጋር ምንም ዓይነት ሕብረት ሊኖራቸው እንደማይገባ ይጠቅሳል። እ.አ.አ በ1993 ዓ.ም “Representations of an Intellectual – Holding Nations and Traditions at Bay” በሚል ርዕስ በሰጠው ትንታኔ፣ ምሁራን ከተጨቆኑ ውገኖች ጎን በመቆም ትችትና ተቃውሟቸውን የማሰማት ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“Never solidarity before criticism” is the short answer. …This does not mean opposition for opposition’s sake. But it does mean asking questions, making distinctions, restoring to memory all those things that tend to be overlooked or walked past in the rush to collective judgment and action.”

እንደ “Edward Said” አገላለፅ፣ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት መንግስትን በግልፅ መተቸት ነው። ከምሁራን የሚጠበቀው፣ ሁሉንም ነገር በጭፍን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መለየትና መፍትሄ የሚሹ ነገሮችን መጠቆም፣ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ችግሮችን በማስታወስ ዳግም እንዳይከሰቱ ማሳሰብ እና የመሳሰሉትን በማድረግ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ነገር ግን፣ እንደ ኢትዮጲያ ባሉ የተለያዩ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች ባላቸው ሀገራት ነገሮች ቀላልና ቀጥተኛ አይደሉም። አሁን በኢትዮጲያ እንደሚታየው ዓይነት፣ ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲኖር ምሁራን በተዓማኒነታቸው ላይ ምህረት-የለሽ አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ። 

እንደ ማንኛውም ሰው ምሁራን የራሳቸው ሀገር፥ ብሔር፣ ማህብረሰብና ቤተሰብ አላቸው። ምንም ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ቢኖራቸው፣ ምሁራኑን ከቤተሰቦቻቸው፥ ማህብረሰባቸው፣ ብሔርና ሀገራቸው ጋር ከሚያስተሳስረው ተፈጥሯዊ ገመድ በላይ ጠንካራ ሊሆን አይችልም። በዚህ ምክንያት፣ ለምሳሌ በራሳቸው ብሔር ተወላጆች ወይም በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭቆና ሲደርስ ከሌሎች ብሔር ተወላጆች በላይ ሊሰማቸው፣ ከወትሮው በተለየ ትችትና ተቃውሞ ሊያሰሙ ይችላሉ፡፡

በኢትዮጲያ ታሪክ መንግስታት ከአንዱ ወይም ከሌላው ብሔር የቋንቋ፣ ባህልና ሥልጣን የበላይነት ጋር ተያያዥነት አለው። ስለዚህ፣ የመንግስት አስተዳደራዊ ችግሮች በብሔሮች ላይ የተፈፀሙ በደሎችና ጭቆናዎች ተደርገው የመወሰድ እድላቸው የሰፋ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ምሁራን በሕዝቦች መካከል ያለው ልዩነት ሰው-ሰራሽ እንጂ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ማሳመን ይጠበቅባቸዋል። በአንድ ሕዝብ ላይ የተለየ ጥቃትና ጭቆና ሲደርስ ግን ሕዝቡን በመወከል መተቸትና መቃወም፣ በሕዝባቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ወይም ከዚህ በፊት የደረሰውን በደል፣ ጭቆና እና ግድያ በይፋ በመቃወም ለህዝባቸው ያላቸው ድጋፍና አጋርነት መግለፅ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን፣ እንደ “Edward Said” አገላለፅ፣ ምሁራን በራሳቸው ሀገር፥ ብሔር፣ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ ስለደረሰው ግፍና በደል ከመናገርና ከመዘከር ባለፈ ተጨማሪ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው ይገልፃል፡-

“…It is inadequate only to affirm that a people was dispossessed, was oppressed or slaughtered, was denied its rights and its political existence without affiliating those horrors with the similar afflictions of other people. This does not at all mean a loss in historical specificity, but rather it guards against the possibility that a lesson learned about oppression in one place will be forgotten or violated in another place or time. And just because you represent the sufferings that your people lived through, which you yourself might have lived through also, you are not relieved of the duty of revealing that your own people now may be visiting related crimes on their victims…..” (Representations of an Intellectual – Holding Nations and Traditions at Bay)

ከላይ እንደተገለፀው፣ የምሁራን ኃላፊነት በሀገራቸው፥ ብሔር፥ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ የደረሰውን በደልና ጭቆና ከመናገር ባለፈ ተመሣሣይ በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደርስ መናገር፣ ማሳወቅ፣ መተቸትና መቃወም ነው። በቀድሞ ስርዓት በእኛ ብሔር፥ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ ስለደረሰው ድብደባ፥ እስርና ግድያ መናገርና ማስታወስ እንዳለ ሆኖ፣ የምሁራን መለያ ባህሪ በእነሱ ብሔር፥ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ የደረሰው በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደገም፣ በእነሱ ላይ ሲደርስ የተቃወሙትን ነገር በሌሎች ላይ እንዳይደርስ መቃወም ነው። 

ምሁራን በራሳቸው ብሔር ላይ ስለደረሰው በደልና ግፍ ብቻ የሚናገሩ ከሆነ ግን ሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦችም ተመሣሣይ በደልና ጭቆና ሊደርስባቸው ይገባል እንደማለት ነው። ከዚህ በፊት በእነሱ ብሔር፥ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ የደረሰው በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደርስ የሚከላከሉ፣ በማንኛውም መልኩ ከደረሰ ደግሞ የሚቃወሙ ምሁራን በሌሉበት የቀድሞው በደልና ጭቆና ተመልሶ ይመጣል። በሌሎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭቆና በዝምታና በቸልታ ማለፍ በራስና እና በሌሎች ላይ ተመሣሣይ በደልና ጭቆና እንዲመጣ ጥሪ እንደማቅረብ ነው። ለዚህ ደግሞ “Edward Said” የደቡብ አፍርካውን አፓርቲይድ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።

በደቡብ አፍሪካ ቀድመው የሰፈሩት “Boers” የሚባሉት ነጮች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ “Orange Free State” እና “South African Republic” የሚባሉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ነፃ መንግስታት ነበሩ። ነገር ግን፣ እ.አ.አ. በ1866 የአልማዝ፣ በ1886 ደግሞ የወርቅ ማዕድን በአከባቢው መገኘቱን ተከትሎ ብዙ እንግሊዚያዊያን (utilanders) ወደ ሁለቱ ቦታዎች በብዛት መጉረፍ ስለጀመሩ በ1890ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቁጥራቸው ከ”Boers” በሁለት እጥፍ በለጠ። በዚህ ምክንያት፣ የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች በውጪ ሀገር ዜጎች ከደረሰባቸው የመዋጥ አደጋ ለመከላከል ያደረጉት ሙከራ ከእንግሊዝ ጋር “Second Boers War” ወደ ተባለው ጦርነት አስገባቸው። ጦርነቱ በእንግሊዝ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፣ “Boers” ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ ወደ ማጎሪያ ጣቢያዎች ተጋዙ፣ ብዙ ሺህዎች በበሽታና በጦርነቱ ሞቱ። 

በመጨረሻም፣ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ደቡብ አፍሪካ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ነፃ ስትወጣ “Boers” “ብሔራዊ ፓርቲ” (National Party) የሚል ፓርቲ አቋቋሙ። ይህ ፓርቲ ነው እንግዲህ የአፓርታይድን መንግስት የመሰረተው። እንግሊዞች በ”Boers” ላይ የፈፀሙት በደልና ጭቆና አፓርታይድ በጥቁሮች ላይ ፈፀመ። በመሠረቱ፣ አፓርታይድ በጥቁሮች ላይ የፈፀመው ግፍና በደል በእንግሊዞች የደረሰባቸው ግፍና በደል ተመልሶ እንዳይደርስባቸው ከመስጋት የመነጨ ነው።   

“Edward Said” ትውልደ ፍልስጤማዊ-አሜሪካዊ በመሆኑና ትንታኔውን የሰጠበት መድረክ እንግሊዝ በመሆኑ  ምክንያት እንጂ፣ ዛሬ ላይ የእስራኤል መንግስት በፍልስጤሞች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍና በደል እንደ ማሳያ መጥቀስ ይችል ነበር። ከዚህ አንፃር ናጄሪያዊው ሎሬት “Wale Soyinka” በዓረአያነት የሚጠቀስ “ምሁር” ነው። በአንድ ወቅት የእስራኤል መንግስት በፍልስጤሞች እየፈጸመ ያለውን ግፍና ጭቆና በአካል ሄዶ ከታዘበ በኋላ በቀጥታ ወደ እስራኤሉ ፕረዜዳንት ሺሞን ፔሬዝ በመሄድ “ናዚ ጀርመን በአይሁዶች ላይ የፈፀመውን ግፍና በደል እናንተ በፍልስጤሞች ላይ እየፈፀማችሁ ነው!” በማለት ተቃውሟል።

ትላንትም፥ ዛሬም ሆነ ወደፊት፣ “በእኛ ላይ የደረሰው ግፍና በደል በሌሎች ላይ ሊደርስ አይገባም!” ብሎ ድርጊቱን ማውገዝና መቃወም ለሌሎች ውለታ ለአንድ ምሁር ግን ግዴታ ነው። በዘንድሮው አመት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሲደበደቡና ለእስር ሲዳረጉ ዳር ቆሞ ሲመለከት የከረመ፣ የራሱ ብሔር፥ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ሲጎዳ ግን ከሁሉም ቀድሞ ትችትና ተቃውሞ የሚያሰማ ሰው “ምሁር” ለመባል የሚያበቃ ስብዕና የለውም። ከዚህ በፊት በእሱ ብሔር ላይ ስለደረሰው ግፍ አበክሮ የሚናገር፣ ነገር ግን በሌሎች ላይ እየደረሰ ያለውን ለማውገዝ የሚፈራ ሰው የቀድሞውን ግፍ በራሱ ላይ መልሶ ለማምጣት እየሰራ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል። ኢህአዴግን የማይቃወም ምሁር፤ በደርግ ዘመን የተፈፀመው ግፍ በሌሎች ላይ እንዲፈፀም ፈቅዷል ወይም ደርግ ተመልሶ እንዲመጣ አበክሮ እየሰራ ነው። ከዚህ አንፃር፣ “ኢህአዴግን ያልተቃወመ ምሁር የደርግ ደጋፊ ነው” ማለት ይቻላል።

Filed in: Amharic