>

ስለ ሰሎሞን ዴሬሣ በጥቂቱ

” ደራሲ ይደርሳል ፤ አንባቢ ያነባል ፤ ሃያሲ ይተቻል። ምንም ቢወታተብ የስነጽሑፍ ጣጣ ከእንዚህ ድንክዬ ዐረፍተ ነገሮች አያልፍም” ያለው ሰሎሞን ዴሬሣ በወለጋ ጩታt በተባለች መንደር በ1929 ወይም በ1930 ዓ.ም. ተወለደ። ራሱ እንደገለጸው የተወለደበትን ዓመትና ዕለት እቅጩን አያውቀውም። በጣሊያን ወረራ ጊዜ አራት አመት ሲሞላው ዘመዶቹ ወደ አዲስ አበባ አመጡት።

“ልጅነት”! ትምህርት አልገባ ብሎታል ተብሎ ያልገባበት ትምህርት እንዳልነበር የገለጸው ሰሎሞን ደሬሣ በ16 ዓመቱ በቀድሞው ቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ገባ። በዚሁ የ”ውምበርሲቲ” ቆይታው ከትምህርቱ ይልቅ የ” ልጅነት ጨዋታ” ያመዝንበት ስለነበር – መደበኛ ትምህርቱን አላጠናቀቀም። ይልቅ በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ አብረውት ከነበሩት ልጆች ቤተመጻሕፍቱን እንደሰሎሞን ዴሬሣ  የተጠቀመበት ተማሪ እንዳልነበር ይነገርለታል።
ሰሎሞን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ለ3 ወራት ያህል በኢትዮዽያ ሬዲዮ በእንግሊዝኛ ዜና አንባቢነት ተቀጠረ። “በ”ልጅነቱ” የተነሣ ሥራ ላይ ከአለቃው መጋጨት የጀመረው ሰሎሞን እንዳጋጣሚ ፈረንሳይ ሀገር ነፃ ትምህርት ዕድል አገኘ።
ሰሎሞን ፓሪስ ሲደርስ 20 ዓመቱ ነበር። በቱሉዝ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ቀጠለ። ትምህርቱ በፈረንሳይኛ ቢሆንም እንዳልተቸገረ ይናገር የነበረው ሰሎሞን ከጥናቱ ይልቅ ቀልቡን የሳበው የሀገር ጉብኝት ነበር። አውሮፓን ሲዞር ከርሞ ለፈተና ይቀመጣል፤ ያልፋል።
ፓሪ! የአውሮፓ ታላላቅ ደራሲያን የሙዚቀኞችና የሠዓሊያን መናሃሪያ ነበረች። ሰሎሞን – ትዝታውን ነግሮን ነበር። “– ፓሪስ ነፃ ክፍት ከተማ ስለነበርና ልጅ ስለነበርኩ ቁልፉን የከተማው ከንቲባ እንደሰጠኝ ነው ያየሁት። በኋላ ትልልቅ የሆኑ ፀሐፊዎች የሙዚቃ ሰዎች ሰዓሊዎች ነበሩ። እንዲያውም ለአንድ አቫንጋርድ የፈረንሳይ ጋለሪ ማንም ሳይሾመኝ ስእል አውቃለሁ ብዬ ገብቼ እንደ አማካሪ ሆኜ ያኔ የመረጥኳቸው ሠዓሊዎች አሁን በአለም የታወቁ አሉ። ..
” ከትቁር አሜሪካውያን ጋር በጣም በጣም ቅርብ ነበርኩኝ፤ በተለይ ከጃዝ ሙዚቀኞች ጋር። በብዛት የምሰማው ሙዚቃ የኢትዮፕያ ጃዝና ክላሲክ ሙዚቃ ነው። ከፈረንሣይ ፀሓፊዎች ጋርም ያለእድሜዬና ያለእውቀቴ እኩል ገብቼ ዋልኩኝ። በማንበብ ሳይሆን አብሮ በመዋል እንዳባቶች ሆነው አሳድገውኛል። ከፈረንሳይ፤ ከእንግሊዝ፤ ከአሜሪካን ፀሃፊዎች ወስጥ ሪቻርድ ራይት ለትንሽ አመለጠኝ ግን የእሱ ጓደኞች ከሚውሉበት ነበር የምውለው። እሱ እንደሞተ ነው ፓሪስ የደረስኩት። እንስተር ሃይምስ፥ ጀምስ ቦልድዊንና ስማቸውን ከማላስታውሳቸው ፀሐፊዎች ጋር አብሮ መዋል እኔጋም ፀሐፊ ያደረገኝ መስሎኝ ነበር። ያሳደጉኝ እነሱ እነጂ የፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲ አይደለም። በተጨማሪም ፓሪስ ከተማ አለች ከኢትዮዽያውያን ጓደኞቼ ጋር እየዋልኩኝ ወደ ሙዚየም፥ ቤተመጻሕፍት ፥ ቴአትር ቤት፥ ኮንሰርት እሄድ ነበር። ገንዘብ ብዙ አልነበረኝም። ከትሬንታ ላይ ሌሊት አትክልት እያወረድኩ ነበር የምኖረው። ግን አንድ ሳንቲም ኪሴ ሳይኖር እንደሚሊኒየር ልጅ ነው ፓሪስን የኖርኩባት። ከአዲስ አበባ ቀጥላ የትውልድ ከተማዬ የምትመስለኝ ፓሪስ ነች።”
ሰሎሞን ደሬሣ – ያኔ ነበር ከእውቁ ኢትዮዽያዊ ሠዓሊ እስክንድር በጎሲያን ጋር ፓሪስ የተገናኘው፤ ወዳጅነት የመሰረተው። እስክንድር አንዲት ጥቁር አሜሪካዊት አጭቶ ለሠርጉ ወደ አሜሪካ አላባማ ሲሄድ ሰሎሞን ሚዜው ነበር። የፈረንሣይ ትምህርቱን አቁዋርጦ አሜሪካ ገባ። ምናልባትም ከዚያን ጊዜ ወዲህ አውሮፓን ዳግመኛ አልረገጠም። ቢሆንም ፓሪስ ላይ በፈረንሣይኛ ግጥሞች ጽፏል፤ ጥቂቱም ታትመውለታል።
” ኪነጥበብ ለኪነጥበብነቱ ” Art for Arts sake የሚለውን የጥበባት መርኄ ይከተላል የተባለው ሶሎሞን – በ1991 ዓ.ም ” ዘበት እልፊቱ – ወለሎታት ” የተሰኘች ሁለተኛ የግጥም መድበሉን በማበርከትም ለአማርኛ ዘመናዊ ሥነግጥም በተለይ የ” ነፃ ስንኝ “ወለሎ ስንኝ ወይንም የእንግሊዘኛውን Free Verse ዘዬ የመሰረተ በኩር ልጅ መሆኑን በተሰጥኦውና በብርታቱ አስመስክሯል። ነባሩን የኪነጥበብ አመለካከት ማኔላ ብቻ ሳይሆን አዲሱን የሥነግጥም አስተሳሰቡንም ገልጿል። ” የወለሎ ውበቱ – የስሜቱ ግላዊነት፥ የስሜቱ ፍላት፥ የአገላለጹ ትባትና ብርቅዬነት፥ የአመጣጡ ድንገቴነትና የአጠፋፉ ቅፅበታዊነት ናቸው።” የጋሽ ስብሐት አምቻ፣ የነይልማ ደሬሳ ባለስጋ ብኩኑ ፈላስፋ ስደተኛው ገጣሚ ሰሎሞን ደ’ሬሳ ምድርን ተሠናበተ፡፡ በሰላም እረፍ ጋሽ ሰለሞን!
*****
ምንጭ: ብርሀነመስቀል ደጀኔ 2000ዓ.ም ብራና.ማ.ቤ ካሌንደር።
Filed in: Amharic