>
2:54 am - Tuesday October 19, 2021

የጥላቻ ወንዞችን የሚያሻግሩ ድልድዮች.... (በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ አንለይ)

በዚህ ወቅት በሀገራችን በተፈጠሩት ክስተቶች የማያዝን፣ የማይጨነቅና የማያስብ ዜጋ ይኖራል ብዬ ለማሰብ ይቸግረኛል፡፡ ሆኖም ሐዘናችንን፣ ሀሳባችንንና ጭንቀታችን የምናጋራው አካል፣ የምናጋራበት መንገድና መፍትሔ ብለን የምንወስደው ነገር ሊለያይ ይችላል፡፡ በአንዳንድ ሚዲያዎች ከማየው ደግሞ ሌላው ቀርቶ የሚያሳዝነን፣ የሚያሳስበንና
የሚያስጨንቀንም ነገር በእጅጉ ይለያያል፡፡ ይህ መሆኑ ተፈጥሮአዊ ነው ሊባል ቢችልም በእኛ ማኅበረሰብ ዘንድ ግን ከዚያ ያለፈ ነገር እንዳለው ይሰማኛል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር በዋና የዜና ማሠራጫ ሚዲያዎችም (main stream medias) ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያው ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጠውም አሁንም ለችግሩ መፍትሔ እንዲያመጣ ከሚቀርበው ነገር ይልቅ የሚያባብሰው የሚበዛ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ እውነተኛ መፍትሔ ላይ የሚያስቡና ያንንም
ለመተግበር የሚችሉትን የሚያደርጉ ሁሉ ወደ ሚዲያው በተለይም ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው ቢያንስ በፍጥነት ራሳቸው ብቅ ሊሉ እንደማይችሉ እረዳለሁ፡፡ ሆኖም መፍትሔ የሚሆነው ነገር በሚዲያው ዙሪያ ያለውንም አካል በእጅጉ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ መከራውና
ችግሩ ባለበት አካባቢ ተሳታፊ እንኳ ባይሆን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ችግሩን አባባሽነቱ በጉልህ እየጨመረ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነውና፡፡
ስለዚህ እኔም ሌሎችን ጠባቂ ብቻ ከምሆን እንደ ዜጋ ሀሳቤን ለማካፈል የወደቀብኝንን የኅሊና ግዴታ ለመወጣት ያህል በትንሹም ቢሆን ለማካፈል እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ትዝብቴን በማስቀደም ሀሳቤን እንደሚከተለው ላቅርብ፡፡

ትዝብት
ሰሞኑን በአንዳንድ ዋና የዜና ማሠራጫ ሚዲያዎችም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያው የማየው ነገር አሳሳቢ ነው፡፡ እኔ በተረዳሁት መጠን በተፈጠረው ፍግር ሀገሪቱ ወደየትኛውም አቅጣጫ ትሒድ ሳይጨነቅ እያንዳንዱ እኔ ባይ አካል ከተቻለ ብቻውን አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት
ካለበለዚያም ተሸናፊ ላለመሆን የሚጣጣር ይመስላል፡፡ በጋራ የማሸነፍና በጋራ በሰላም የመኖር ነገር ብዙም ሲነገርለት አልታየኝም፡፡ እንዲያውም በጋራ የመጥፋት፣ የመጠፋፋትና የተመተላለቅ ይመስላል፡፡ የታዘብኳቸውን አካላት በመዘርዘር ትዝብቴን በቅደም
ተከተል ለማቅረብ ልሞክር፡፡

መንግሥት
ከመንግሥት መጀመር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱን  መምራት፣ ሕዝቦቿን ለማስተዳደር ቀዳሚ ሓላፊነት ያለበት አካል ነውና፡፡ መንግሥት ምንም እንኳ ይበጃል ብሎ ያመነበትን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችን መተግበር ከጀመረ ከሩብ
ምዕተ ዐመት በላይ ቢያስቆጥርም በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ግን ከእድሜው በተቃራኒ እየቀነሰ እንደመጣ ለመረዳት ነጋሪ አያሻም፡፡ ራሱ መንግሥትም ሁኔታውን በመገንዘብ ራሱን የሚያስተካክልበትን መንገዶች በመዘርዘር ንስሐዊ ተስፋዎች ደጋግሞ
እየተናገረ ነው፡፡ ሁኔታው ግን አልተለወጠም፤ እንዲያውም እየባሰ መጥቶ ብሔራዊነት ያላቸውን ቁጣዎች አስከተለ እንጂ፡፡ ሁኔታውን እያከፋው ያለው ደግሞ አንደኛ መንግሥት የሚናገረውን አያደርግም፤ የማያደርገው ደግሞ ስለሚያቅተው ሳይሆን ጥንቱንም ንግግሩ ማታለያ ታክቲክ ስለሆነ ነው የሚል ስሜት መፈጠሩ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ
ሁሉንም ዓይነት ንግግሮቹንና ቃልኪዳኖቹን ሁሉ ማመን እየቀረ ይመስለኛል፡፡
እንደ ሁለተኛ ነጥብ ሊታይ የሚገባው ደግሞ ችግሮች ወይም ሕዝባዊ ቁጣዎች በተነሡ ቁጥር መንግሥት የሚሔድበት መንገድ ሦስት ነገሮችን ያካተተ ነው ከሚል ግንዛቤ የሚነሣው አጸፋ ይመስለኛል፡፡ መጀመሪያ በኃይል ወደ መቆጣጠር የሚወስደውን ክስተት ራሱ ይፈጥራል፤ ከዚያ በማስከተልም ችግሮቹን በሌሎች ላይ በማላከክ ሌሎችን ተጠያቂ ያደርጋል፣ በመጨረሻም ራሱን ገላጋይና ለተገፉት ደራሽ አድርጎ ማቅረብና እርሱ ራሱ በፈጠረው ክስተት ዐመፁን አስተንፍሶ በዚያ ሰበብ እንደገና ራሱ በሚጠላቸው አካላት ላይ ሕግን ሽፋን ያደረገ እርምጃ ይወስዳል የሚል ነው፡፡ በአጭሩ ከሕዝቡ ወይም ከብዙኃኑ በኩል ይህን የመንግሥት የተለመደ ሴራ አውቀንበታል ብቻ ሳይሆን በቅቶናል የሚል ድምፅም እየተሰማ ይመስላል፡፡ ሴራም እንበለው ታክቲክ፣ ቴክኒክም ይባል ስትራቴጂ፣ መንግሥት እነዚህን ነገሮች ያድርጋቸውም አያድርጋቸውም አሁን በሕዝቡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚታየው አጸፋ ግን መንግሥታዊ ታክቲኮች ተብለው እየተጠቀሱ ያሉትን እነዚህን ነገሮች ታሳቢ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ለእኔም የሚያሳዝነኝ ደግሞ (አልገባኝ ብሎ ካልሆነ በቀር) በርግጥም መንግሥት ከታክቲክ በቀር ለራሱም ሆነ ለሕዝቡ የሚጠቅም መፍትሔ ይዞ ሲመጣ አለመታየቱ ነው፡፡ እንደ አንድ ዜጋ ይህ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ መጽሐፉም እንደሚል ብዙ ከሰጡት ብዙ ይጠብቁበታልና ከመንግሥት እጅግ ብዙ ምዕራፍ ይጠበቃል፡፡ በእኔ እምነት በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ
ልሂቃኑ በደንብ የተጨነቁበት፣ ባይጸልዩበት እንኳ ያነበቡበትና  የመከሩበት ፖለቲካዊ መፍትሔ ቀርቦ ሲንጸባረቅና ከዚያም ወደ ተግባርነት ሲለወጥ የሚታይ ነገር የለም፡፡ ይህ አለመኖሩ ደግሞ የሀገርን፣ የሕዘብንና የመንግሥትን ሕልውና የሚያስጠብቁት የሀገር
ደኅንነት፣ የሀገር መከላከያና የፖሊስ አካላት ላይ ተጨማሪ ሥራ የፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ይህም በነበረው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ላይ ታክቲክና ቴክኒክ አብዝቶ መለዋወጥንና መሞከርን፡፡ ይህ ደግሞ ከሩብ ምዕተ ዐመት በላይ ለቆየ አካል እጅግ ከባድ ከመሆኑም በላይ ዘዴው ከቀደመው ጋር ስለሚመሳሰል ከሰሞኑ እንደምናየው ሩቅ የሚያስሔድ አይመስለኝም፡፡
የቀደመውን ዘዴ ባይጠቀም እንኳ ተመሳሳይ ታክቲኮችን አብዝቶ ከመጠቀሙ የተነሣ  ሕዝብ ዘንድ የተፈጠረው ግንዛቤ እንደሰሞኑ ያለ ሁኔታ ይፈጥራል፤ ፈጥሯልም፡፡
የእኛ ማኅበረሰብ ደግሞ ከተደጋጋሚነቱ የተነሣ የተረጋገጠ ሊባል የሚችለውን ነገር ቀርቶ ቴክኒክና ታክቲክ ብቻ ብዙም የሚያረካው አልሆነም፡፡ እንኳን የተለመደ የሚመስለውን ታክቲክና ስልት እውነተኛ ሆኖ ተቀራራቢ እንኳ ቢሆን ቶሎ ለመቀበል የሚቸገር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሴራና የሴራ ትንታኔ የማንነታችን አካል እስኪመስል ድረስ
ተጣብቶን ይቅርና ባይሆን እንኳ የእስካሁኑ ሂደት ራሱ መንግሥትን  ለማመንና ለመቀበል እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይህ ነገር ማኅበረሰቡ ሁሉ የሚቀባበለው ከሆነ ደግሞ ሁሉ ነገር የሴራ አካል ተደርጎ ስለሚወሰድ ምንም ነገር ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል
የግብይት እቃዎች ሁልጊዜም ቢሆን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ገበያውን መሠረት አድርገው መንቀሳቀሳቸው የተለመደ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ከሴራ ትንታኔ የተነሣ እንኳን የተሴረ ሴራ ኖሮ ማንኛውም መደበኛ የንግድ እቅስቃሴም የሴራ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የሴራውን ካርታ ሲመዝዙና ሲጫወቱ የቆዩት አካላት አጥቂ ከሚባለው ተነጥለው
ከተከላካይ መደብ ራሳቸውን ሲደምሩ ደግሞ ሁሉም ነገር ተራ ወደ መሆን ይለወጣል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታም ይህን ቅርጽ እየያዘ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ንጹሐንን ሁሉ ሰለባ ሊያደርግ እንደሚችል አለመገመት አይቻልም፡፡ እየሆነም ያለው እንደዚያ ነው፤ የኃጥዕ ዳፋ
ጻድቅ ያዳፋ እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ በሕዝቡ መካከል የሚወራው ነገር እውነትነት ካለው ደግሞ ቢያንስ  ከሚከተሉት ሦስት አስፈሪ ነገሮች ቢያንስ አንዱ መከሰቱን የሚጠቁም
ይመስለኛል፡፡ አንደኛው መንግሥት የቀደመ ፖለቲካዊ ፍልስፍናውን እንደ ሃይማኖት ዶክትሪን ሙጭጭ እንዳለ በማንኛውም መንገድ  ዝብን ማሸነፍ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ፈረንጆቹ “A politician is a man who understands government  and it takes a politician to run a government. A
statesman is a politician who has been dead ten or fifteen years” – ‘የፖለቲካ ሰው ማለት ሥነ መንግሥትን ተረድቶ ፖለቲከኛውን መንግሥታዊ ኃላፊነትን እንዲወጣ የሚያስችል ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣን ማለት ግን ዐሥር ወይም ዐስራ አምስት ዐመት በፊት የሞተ ፖለቲከኛ ማለት ነው’ እንደሚሉት ሕዝቡን ከቁጣው
የሚመልስ፣ እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ ፍትሕን የሚያሰፍን አዲስ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ማምጣትና ራሱንም ሕዝቡንም አሸናፊ
አድርጎ ለማውጣት አቅም አንሶታል ማለት ነው፡፡ ካበለዚያም ራሱን እንደ
ፖለቲካ ተቋም መምራት ተስኖት በውስጡ ባቆጠቆጡ መሳፍንታዊ
አካላት ተከፋፍሎ መደማመጥም መናበብም መምራትም መመራትም
ተስኖታል ማለት ነው፡፡ ከዚህም ውጭ አማራጭም ምክንያትም ሊኖር
ይችላል፤ ለእኔ ግን አልታየኝም፡፡ በእኔ እምነት ሦስቱም አማራጮች
የመጥፋትን እንጂ የመልማትን ተስፋ ስለማያሳዩኝ ሀሳቤ፣ ጭንቀቴና
ሐዘኔ የሚመነጨው በዋናነት ከዚህ ነው፡፡
ሌሎች ፓርቲዎች
ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ አዲስ
መፍትሔ አልሰማሁም፡፡ ምንም እንኳ ይህ ያልሆነበት ብዙ ኣሳማኝ
ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም የእኔ ዐይነቱ ሰው ግን መፍትሔ መጠበቁ
አይቀርም፡፡ በርግጥም ፖለቲካዊ ትግሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝቡ ላይ
የሰላም ተስፋ የሚያሳድር ሥራም ሊሠሩ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡
ምክንያቱም የተፈጠረውን ክስተት ተጠቅሞ የመንግሥትን መውረድ
ተስፋ አድርጎ ሊገኙ የሚችሉ ወንበሮችን ከማስላት በፊት ራሱን ለዚያ
የሚያበቃ፣ ሀገሪቱ ደግሞ እንደ ሀገር እንድትቀጥል የሚስቻል
አቅጣጫና ስልት በግልጽ ለሕዝብ ማቅረብ ሊታይ የሚገባው ጥረት
ነውና፡፡ አንደዚህ ያለ ስልትና አቅጣጫ ኖሮ እኔ አልታየኝ ብሎ ከሆነ
እሰየው፤ ግን አልመሰለኝም፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ እንደ ሀገር መቀጠል
ካልቻለች እነርሱስ በየትኛው ኃላፊነት ይቀመጣሉ? ሕዝብስ
ከራሳቸውና ከሥልጣን አልፈው ለሀገርና ለሕዝብ በሠለጠነ መንገድ
ማሰባቸውን በምን ሊያይ ይችላል? ይህም ደግሞ ሌላው እኔን ያሳሳበኝ
ነገር ነው፡፡
ነገር ቆስቋሾች (Activists)
ነገር ቆስቋሾች በአሁኑ ዘመን እጅግ ብዙ ናቸው፣ ዓይነታቸውና የሚቆሙለት የፖለቲካ ሀሳብም ሆነ ማኅበረሰብ ጥቂት እንዳልሆነም ይገባኛል፡፡ ሆኖም አብዘኛዎቹ ቆስቋሾች የሚመሳሰሉበት አንድ ዓይነተኛ መገለጫ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ከእነርሱ ውጭ የሆነን ሁሉ ስሕተት አድርጎ የመውሰድ አባዜ፡፡ ከዚህ ጽንፈኝነት አንዳቸውም የሚያተርፉ
አይመስለኝም፡፡ ለቆሙለት ፖለቲካዊ ፍልስፍና መከራከር ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅም ነው፡፡ ቆሜለታለሁ ለሚሉት ማኅበረሰብ ማቀንቀንም ጉዳቱ ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ሌላውን ሁሉ ስሕተትና ነገሩንም ሁሉ ሐሰት አድርጎ መውሰድ ግን ከባድ ችግር ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት እንዲህ ያለው ነገር የሚመነጨው ከአማኝነት
(ከሃይማኖተኝነት አላልኩም) ጠባይ ይመስለኛል፡፡ በእኛ ሀገር በሃይማኖት እና በሃይማተኞች ላይ የሚቀልዱትና የሚዘባበቱት ሁሉ ራሳቸው ጽንፈኛ አማኞች ይመስሉኛል፡፡ የሀገራችን
ኮሚኒስቶች የኮሚኒዝም ጠንካራ አማኞች እንደነበሩት፣ የዛሬ ሃይማኖት አልባዎችም “ሃይማኖት አያስፈልግም” ወይም “እግዚአብሔር የለም” የሚል አስተሳሰብ አማኞች እንደሆኑት ሁሉ ፖለቲከኞቻችንም የፖለቲካዊ ፍልስፍናቸው ጠንካራ አማኞች ይመስሉኛል፡፡ ይህን የምለውም ዝም ብዬ አደለም፡፡ በአንዳንድ ጽሑፎች ላይ ትዳራቸውን
ሳይቀር በሚከተሉት የፖለቲካ ዶክተሪን የሚመሩ ፖቲከኞች እንዳሉ ከፖለቲከኞች ግለ ማስታወሻዎች ላይ አንባቢያለሁና፡፡
ይልቁንም ደግሞ ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የማየው ተቃርኖና ተዋሥኦ ሁሉ ዐሥራስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን የአውሮፓ የሃይማኖት ጦርነት መስሎ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም በዚያ ዘመን በመጀመሪያ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተቃውሞ የወጡት እነ ሉተር፤ ዝዊንጊልና ካልቢን ከካቶሊክ ጋር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የእርስ በእርስ ልዩነት መፍጠራቸው ሳያንስ ወዲያዉኑ ከካቶሊክ አልፈው
የራሳቸው ተከታዮች ጋር ሲጣሉና ሲነታረኩ እንኳ ጊዜ አልፈጀባቸውም
ነበር፡፡ በዚያውም ላይ ደግሞ የማንኛውም ልዩነት መደምደሚያው
ጦርነት፣ መጠፋፋት እስኪመስልና አሸናፊነትም ሌላውን በማጥፋት
ብቻ ላይ የሚገኝ ተደርጎ የተወሰደ ይመስል ነበር፡፡ ይህ አሁን
የሚደነቁበት ተቻችሎ መኖር የመጣውም ቢያንስ ከሠላሳ ዐመት
ጦርነትና እልቂት በኋላ ነው፡፡ ለዛም የበቁት ምሁራን ተሰባስበው
በሃይማኖት ልዩነት ውስጥ ሆኖ በሰላም አብሮ መኖር ይቻላል ከሚል
ፍልስፍናዊ አድካሚ የሽምግልና ሂደት በኋላ እንደነበር በታሪካቸው
ተመዝግቧል፡፡ የዛሬን አያድረገውና የዛ ዘመን የእነርሱ ሽማግሌዎች
ለዚህ ማሳየነት እንደ አርአያ የሚጠቅሷትም ሀገራችንን ኢትዮጵያን ነበር፡፡
ነገሩ ሁሉ ተገላበጠና አሁን በእኛ ሀገር ያለው ሁኔታ አምስት መቶ
ዐመታትን ወደኋላ ተመልሶ የእነርሱን የዚያን ዘመን ክስተት ሊመስል
ተቃርቧል፡፡ ምክንያቱም ጥቅምና መብት ሁሉ ሌላውን ከማጥፋት
ይገኛል በሚል መርሕ ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ይመስላልና፡፡
ስድድቦቹና አተካራዎቹ፣ አንዱ ስለሌላው መረጃ ብሎ የሚያወጣቸው
ነገሮችን ለሚያይ ሁሉ የጽሑፍ ተፋላሚዎቹ ጽንፈኛ ሃይማኖት ውስጥ
ለመኖራቸው ጥርጥር አይገባውም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ
የጽሑፎቻቸውን አንድ መገለጫ ብቻ ማስተዋል ይበቃል፡፡ እኔ
እንደማየው ከሆነ አብዛኛው ነገር ቆስቋሽ ሌላውን ወገን የሚናገረው
በሚሞግተው ሰው በኩል ተሻግሮ ሌሎቹን ያላያቸውንና
የማያውቃቸውን ሁሉ አጠቃልሎና ደርቦ ነውና፡፡ መንግሥትን ወክለው
የሚጽፉት ሁሉ መንግሥት የሚለውና የሚያደርገው ብቻ ትክክል ነው
ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ በተቃራኒው ያስባሉ፡፡ የአንዱ ብሔር ጠበቃ ነኝ ብሎ
የሚጽፈው ብሔሬን እያጠቃ ነው የሚለውን ሌላውን ብሔር የጥፋት
ሁሉ ምንጭ ያደርገዋል፡፡ የሚያሳዝነውና የሚያሳስበውም የራሱ ብሔር
ውስጥ የሞተው ብቻ ነው፡፡ ሌላውም በግልባጩ እንዲሁ፡፡
እንዲያውም ይህን ሁሉ የምለው አእምሮአቸው ተበጻብጾ ወይም
የአእምሮ በሽተኞች እስኪመስሉ ድረስ የሚጽፉትን ከግምት ውስጥ
ሳላስገባ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንዱ የጭፍን ፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ
አማኝነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህንና ይህን የመሳሰሉት ሁሉ ናቸው
እንግዲህ ነገሩን ሁሉ አስፈሪና አሳሳቢ ያደረጉብን፡፡
እንደ መፍትሔ
ከትዝብቶቼ የጀመርኩት ምን እንዳሳሰበኝ ለመግለጽ ያህል ብቻ ነው
እንጂ ሁኔታዎቹ ከማንም የተሠወሩ እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ሆኖም
ነገሮች ሁሉ ሲታዩ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በ1996/7 ዓመተ ምሕረት
በቪዥን 2020 ዐውደ ጥናት ላይ ባቀረቡት አንድ ጥናታቸው ማጠቃላያ
ላይ ኢትዮጵያን ሁልጊዜም የሚያተርፋት የአምላክ እጅ (Divine
interference) ካልሆነ በቀር ሌላ ነገር የለም ሲሉ እንደ ደመደሙት
አሁንም ፈጣሪ ካልደረሰላት በቀር የምናየውና የምንሰማው ነገር ሁሉ
ደስ አይልም፡፡ በርግጥ እኔም እምነቴ እግዚአብሔር ይታደጋታል የሚል
ነው፡፡ ሰዎች ይህን ባለመቀበላቸው ሊቀር የማይችል እውነት ነውና፡፡
ሆኖም ግን አምላክ የሚታደጋት ደግሞ ቢያንስ ብዙዎቻችን አምላክን
እንዲታደጋት የሚጋብዝ እምነትና አስተሳሰብ ወይም ምግባር ሲኖረን
ስለሆነ ለሰው ሁሉ ጥሪ ማቅረብ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ የዚህ ጽሑፍ
ገፊ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ የመፍትሔ ጥቆማዎቼን በሁለት ከፍዬ
ላቅርብ፡፡
1) አዲስ ፖለቲካዊ መፍትሔ በተለይ ከመንግሥት
“The dogmas of the quiet past are inadequate to the
stormy present. The occasion is piled high with
difficulty, and we must rise with the occasion. As
our case is new, so we must think anew, and act
anew. We must disenthrall ourselves, and then we
shall save our country” – ‘የቆየው ሕግ (እምነት፣ አስተሳሰብ፣
ፍልስፍና፣ ስትራቴጂ፣ …) አሁን ላለው ማዕበል በቂ መፍትሔ
አይደለም፡፡ ወቅቱ ችግር በከፍተኛ ደረጃ የተቆለለበት ስለሆነ ከወቅቱ
ጋር የግድ መነሣት ይኖርብናል፡፡ ጉዳያችን አዲስ እንደሆነው ሁሉ
በአዲስ አስተሳሰብ አዲስ ተግባርም ይጠበቅብናል፡፡ ራሳችንን
[አሳስረን] ካቆየንበት ተመስጦ በግድ አልላቀን ሀገራችንን ማዳን
አለብን’ (Abrham Lincoln, ትርጉም የራሴ) ፡፡
አብርሃም ሊንከን በግሩም ሁኔታ እንደገለጸው አሁን ላለው የኢትዮጵያ
ችግር የቀደሙ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችም ሆኑ ታክቲኮችና ቴክኒኮች
ጠቃሚ ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ቢያንስ ክለሳ ይጠይቃሉ፡፡
ችግሩ እንደ መደራረቡና አዲስ መልክ እንደመያዙ መጠን አዲስ
አስተሳሰብና አዲስ ብልሃትም የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ይህ አዲስ
አስተሳሰብና አዲስ መንገድ ደግሞ የሚጠበቀው ከሁሉም አካላት
መሆን አለበት፡፡ አሁን ላለንበት ራስን የማጥፋት ሒደት ከመንግሥት
ብዙ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም አሁን ላለው ቀውስ ግንባር ቀደም
ተወቃሽ ብቻ ሳይሆን ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበትም አካል ነውና፡፡ ከተለያዩ
ፓርቲዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶችንና ከሆነ ዐመት በኋላ ተግባራዊ
ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅን አዲስ ምርጫ እንደመፍትሔ ወስዶ
ለመጠበቅ ትዕግስት ሊኖረው ቀርቶ አምኖ እንኳ ለመቀበል የሚችል
አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከዚያ ውጭ የሆነ ፈጣን የሚታይና የሚዳሰስ
ፖለቲካዊ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በቸልታ የሚያየው ከሆነ ግን
ሕዝብ ” Government exists to protect us from each
other. We can’t afford the government it would take
to protect us from ourselves” – ‘መንግሥት የሚኖረው
አንዳችን በአንዳችን ላይ የምናደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ነው፡፡
ስለዚህ ራሳችንን ከራሳችን እንደንከላከል የሚተወንን (እርስ በእርስ
ለመጠፋፋት አሳልፎ የሚሰጠንን) መንግሥት ልንታገሰው አንችልም ”
የሚል መንገድን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በርግጥ ይህ ጥቅስ ለሌሎች
የፖለቲካ ሃይሎች እና ነገር ቆስቋሾች ሁሉ የሚገባ ነው፡፡ ይህ ሁሉ
ከመሆኑ በፊት ግን መንግሥትም፣ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ነገር ቆስቋሾችና
ሌሎች የማኅበረሰብ አካላት ሁሉ ነገሩን በጥሞና መመርመርና
ከተለመደው መንገድ ወጣ ብለን ለመፍትሔ መረባረብ እንዳለብን
ይሰማኛል፡፡ መጠቋቆም፣ መሰዳደብና መወነጃጀሉን አቁመን
ከየፖለቲካ ፍልስፍናችንም ቢያንስ አንድ ደረጃ ሸገር ብለን፣
ከሚከፋፍለን ወደሚያገናኘን፣ ከሚያጠፋፋን ወደሚያተርፈን መንገድ
መጓዝ ጊዜ የማይሰጥ የጋራ ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡
መጪውን ጦርነት የመከላከልና በዚህ የማሸነፍ ጥበብ የሚወሰነው
ለችግሩ መሥዋዕት የሚሆን አካል በመፈለግ ሊሆንም አይችልም፡፡
በርግጥ “The search for a scapegoat is the easiest of all
hunting expeditions” እንደሚባለው ለአንዳንድ ብልጥ ነን ባይ
ፖሊከኞች ቶሎ የሚታያቸው የፈለጉትን ጥፋት ካደረሱ በኋላ እንደ ኦሪት
የመለቀቅ ፍየል በቀላሉ የሚያዝላቸው መሥዋዕት መፈለግ ሊሆን
ይችላል፡፡ ነገር ግን እንኳን እንዲህ ባለው አጣብቂኝ ወቅት ቀርቶ
በሌላም ጊዜ ሳያዋጣ የቀረበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ከላይ እንዳልነው
በሴራና በሴራ ትንታኔ ውስጥ ለሚኖር ማኅበረሰብ ደግሞ እንዲያውም
ችግሩን ያወሳስበው እንደሆን እንጂ አያቀልለውም፡፡ ስለዚህም
በርግጥም አዲስ ሀሳብ፤ አዲስ ተግባር፣ አዲስ አገላለጽና አዲስ
መንገድ ልንጀምር ያስፈልገናል፡፡ መንግሥት ዘንድ የምጠብቀውን
አዲስ ነገር ግን ከዚህ በላይ መግለጽ አሁን አልችልም፤ መጠበቄን ግን
አላቆምም፡፡ ለሁላችንም የሚበጀው አዲስ ፖለቲካዊ መፍትሔ መሆኑን
መዝለል የሚቻል አይመስልምና፡፡
2) አዲስ መንገድ ከሁላችንም
“The only way to win World War ɪɪɪ is to prevent it”
– ‘ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት በአሸናፊነት ልንወጣ የምንችልበት
ብቸኛው መንገድ ጦርነቱ እንዳይነሣ ማድረግ ነው’ /Dwight David
Eisenhower/
መንግሥትን ጨምሮ ሁላችንም ሌላም አዲስ መንገድ
እንደሚያስፈልገን ይሰማኛል፡፡ አዲስ የምለው ዋነኛው መንገድ ደግሞ
የአሁኑ ውጥረት እየጎተተው ያለውን መጪውን የእርስ በርስ ጦርነት
እንበለው ግጭት ሁሉም አካል በአሸናፊነት እንድንወጣ የሚያስችለን
ብዬ የማስበውን መንገድ የሚመለከት ነው፡፡ ዋነኛው ጥሪዬም ይህ
ነው፡፡ መንገዱም በሁለተኛው የዐለም ጦርነት ወቅት የፈረንሳይ ግዛት
የነበረችውን የነርመንዲን – Normandy ግዛት ወረራን እና የናዚን
መሸነፍ የተቆጣጠረው ጀነራል እና ሠላሳ አራተኛው የአሜሪካ
ፕሬዚዳንት አይስንሐወር እንዳለው መጪውን ጦርነት ልናሸንፍ
የምንችለው እንዳይከሰት በማድረግ ብቻ ነው የሚል ነው፡፡
የዘር፣ የብሔር እና የሃይማኖት ጦርነትና ግጭት በሰፋ መንገድ
ከተከሰተ ሁላችንም እንሸነፋለን እንጂ ማንም አያሸንፍም፡፡
የማሸነፊያው ብቸኛው መንገድም ከዚህ በኋላ እንዳይከሰት ጠንክሮ
መከላከል ብቻ መሆን አለበት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያው እንደሚታየው
ከሆነ መፍቀርያነ መንግሥት የሆኑት በመንግሥት ደኅንነት፣ መከላከያ፣
መሣሪያ፣ ጥበብና አቅም ሲመኩ ያታያል፡፡ ጸላእያነ መንግሥት የሆኑት
ደግሞ በሕዝብ ምሬትና ለሞት ሳይበገር ለተቃውሞ ባለው ቆራጥነት፣
በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ወቅታዊ የመለያየት አቋምና ዘዴ፣ … እና
በመሳሰለው ሲመኩ ይስተዋላል፡፡ እውነቱን ለመናገር በእንደዚህ ያለ
ወቅት ምንም ያህል ቢመስለን መንግሥታዊ አቅም፣ የጦር መሣሪያ፣
የሰው ብዛት፤ የቦታ አቀማመጥ፣ የረዳቶቻችን አሰላለፍ፣ … ወዘተ ሁሉ
ለምናስበው ድል ዋስትና ሊሆኑ አይችልም፡፡ ለሁላችንም አስተማማኙ
ማሸነፊያው አዲሱ መንገድ ጦርነቱ ወይም ግጭቱ እንዳይነሣ ማድረግ
ብቻ ነው፡፡ የእኔ ጽኑ እምነት ይህ ስለሆነ ይህን ለማድረግ ሊረዱን
ይችላሉ ብየ የማስባቸውን ሦስት ነገሮች በማቅረብ አሳቤን ላጠቃልል፡፡
ሀ) ጥላቻን ማስወገድ
በእኔ እምነት መጠፋፋትን ተከላክለን ልናስቀርበት የምንችለበት
ጥንካሬ ሊገኝ የሚችለው ጥላቻን ከማስወገድ ነው፡፡ ምክንያቱም
ለአንዳንድ ሞኞች እንደሚመስላቸው ጥንካሬና አሸናፊነት ማለት
በመደበኛ ጦርነት ውስጥ ጠላት የሚሉትን በመግደል በማሳደድና
በመማረክ የሚፈጸም አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ አሸነፍን ብለን
የፎከርንባቸውና አሁንም ግን እጃችን ላይ ካሉት ብዙ ችግሮች
የማንማር ከሆነ በርግጥም ከልብ ደንቁረናል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም
ቻይናዊው ፈላስፋ ሰን ትዙ እንዳለው የክህሎትና የአቅም ታላቅነት
የሚለካው መቶ ጦርነት አካሒዶ መቶ ጊዜ በማሸነፍ ሳይሆን ጠላትን
ያለጦርነት ማሸነፍ በመቻል አቅም ነውና፡፡
ስለዚህ አሁን የገጠመንን ሀገራዊና ማኅበረሰባዊ ቀውስ በድልና
በሁላችንም አሸናፊነት ልንወጣው የምንችለው ወደ እልቂት እየመራን
ያለውን አእምሮአችንን አሳጥቶ እንደ ሰካራም የሚያንገዳግደንን ትልቁን
የአእምሮ በሽታ ጥላቻን በማስወገድ መሆን አለበት፡፡
ጥላቻን ማስወገድና ማሸነፍ የሚቻለው ደግሞ የሌሎቹን ጥላቻ
ለማስወገድ ከመሞከር ሳይሆን የራስን ጥላቻ በማሰወገድ ብቻ ነው፡፡
አንተ የራስህን ጥላቻ አስወግደህ ጠላቴ የምትለው አካል ለአንተ
ያለውን ጥላቻ ባያስወግድም አንተ ልትሸነፍ አትችልም፡፡ እንዲያውም
እርሱ ይሸነፋል እንጂ፡፡ ሠላሳ ሰባተኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሪቻርድ
ሚ. ኒክሰን “አንተ እነርሱን በመጥላት ካልረዳሃቸው በቀር አንተን
የሚጠሉህ ሰዎች ሊያሸንፉህ አይችልም፤ የጠላሃቸው ጊዜ ግን ራስህን
ታጠፋለህ” ሲል እንደገለጸው አንተ ጠላቶቼ የምትላቸውን በመጥላት
ውስጥ ገብተህ ካልረዳሃቸው በቀር በጥላቻ የሰከሩ አካላት ሊያሸንፉህ
አይችሉም፡፡ ከጥላቻ ነጻ የሆነን አካል ጥላቻ ውስጥ ያለው አካል
በፍጹም ሊያሸንፈው አይችልም፡፡ በፍጹም በማለቴም እንደማልሳሳት
አውቃለሁ፡፡ ከጥላቻ የጸዳ ይሸነፋል ማለት እግዚአብሔር ይሸነፋል እንደ
ማለት ነውና፡፡ ስለዚህ ወዳጄ ሆይ በጥላቻ ውስጥ ሆነህ የተደረገውን
በማባዛት፣ ያልተደረገውን በማገናኘት ጥላቻን ከመዝራት፣ ስለሌሎቹ
ብዙ ከማውራት፣ ከመወንጀል፣ … ተቆጥበህ አንተን አስቀድሞ
ሌላውንም ተሸናፊ ከሚያደርግ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት
በአሸናፊት ለመወጣት አስተዋጽኦ አድርግ ስል እማጸንሃለሁ፡፡ ይህ
መጻኢውን ጦርነትና ግጭት ለማስቀረት የመጀመሪያውና አማራጭ
የሌለው አስፈላጊ ርምጃ ነውና፡፡
ለ) ባለፉ ክስተቶች ላይ መነታረክን ማቆም
ሁለተኛው ነገር ደግሞ ወደ ጥላቻ የሚወስዱንን ነገሮች መዝጋት ነው፡፡
በእኔ እምነት በእኛ ሀገር ከፍተኛውን ደረጃ ከሚይዙት ነገሮች አንዱ
ባለፉ የታሪክ ክስተቶቻችን ላይ የምናደርገው ያልተገባና እውቀትም
እውነትም የራቀው እሰጥ አገባ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችንና
ፕሮፖጋንዳ የሚግቱንን የካድሬ ቅስቀሳዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ
ሳናረጋግጥ በእምነት ብቻ ይዞ መጓዝ ለዚህ እንዳደረሰን ይሰማኛል፡፡
ሌላው ቀርቶ ሞቱ ስለተባሉ ሰዎች ቁጥር እንኳ እንደ “ሥላሴ ስንት
ናቸው” ጥያቄና መልስ በማይለወጥ ቁጥር ድርቅ ብሎ አንዱን አማኝ
አንዱን መናፍቅ አድርጎ መወራከብ ከተዘጋጀልን የጥላቻ መጥመድ
እንዳናመልጥ አዚም የተደረገብን ያስመስላል፡፡
ፖለቲካዊ ጥቅም ታሳቢ አድርገው ባሳለፍነው ሩብ ምዕተ ዐመት
ስለተጻፉ አዳዲስ የታሪክ መጻሕፍት ሙያዊ የሆነ የመጽሐፍ ግምገማ
ያካሔደ አንድ አውሮፓዊ ጸሐፊ (ትዝብቱን አጉልቶ ለማሳየት
ይመስለኛል) ለጥናታዊ ጽሑፉ የተጠቀመበት ርእስ “Battling the
Past” – ‘የኋልዮሽ ፍልሚያ’ የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም ጤነኛ ዜጎችን
የያዘችና በጤናማ ልሂቃን የምትመራ ሀገር ዜጎች የፊታቸውን ይዋጋሉ
እንጂ የኋላቸውን አይዋጉምና በደንብ ታዝቦናል፡፡ በርግጥም እስካሁን
ያሳለፍነው ፖለቲካዊ ተዋሥኦ ያለፈው ታሪካችን ጋር በተሳሳተ መንገድ
በመዋጋት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዶቻችን የሆነ ዘመን ሰዎች
አደረጉት የተባለውን ነገር ለራሳችን ፖለቲካዊ አቋም በሚያመቸን
መንገድ ከተረጎምን በኋላ ልክ ሰዎቹ በሕይወት ያሉ ያህል አድርገን
በምናብ ሔደን እንገጥማቸዋለን፡፡ በታሪክ እየተጠቀሱ ከሚወጉት
አካላት ራሱን ወገን ያደረገ የእኛው ዘመን ሰው ደግሞ እኛን
ይገጥመናል፡፡ እንዲህ በማድረግ ከሌሉ ሰዎች ክስተት በመነሣት
የዚያን ዘመን ጦርነት በሀሳብ አግዘፈንና በትርጉሙ አግንነን ለሁለተኛ
ጊዜ የእኛው ዘመን የሀሳብ ጦርነት አድርገነው ኖረናል፡፡ በዚያ ዘመን
ስለሞቱ ሰዎች እያወራን የአሁኖቹን ገድለናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ
በአልህና ለወገን በመቆርቆር ሰበብ የራሳችንን ኅሊና አቁስለናል፤
ገድለናል፤ ሞተናልም፡፡ ይህ ግን ሊያቆም ይገባዋል፡፡ በአብርሃም
ሊንከን ንግግር ውስጥ እንዳየነው እንኳን የሌላ ዘመን ችግር
ጨምረንለት የእኛ ዘመን ችግር ራሱ እንደ ተራራ ተቆልሎብናል፡፡
ያለፈውን ዘመን ታሪከ አንሥቶ መዋጋትና መጣላት ከመጪው ዘመን
ጋር ሁሉ መለያየት ስለሆነ በዚሁ ከቀጠልንበት እንደ እኔ ከሆነ
ሽንፈታችንን ሦስት እጥፍ ያደርገብናል፡፡ ባልነበርንበት ዘመን መዋጋት
አሁን በሕይወት ከሌሉት ጋር ራስን መደመር ስለሆነ አንድ ትልቅ ሽንፈት
ነው፡፡ ሁለተኛ በሚኖሩበት ዘመን በተገቢው መንገድ አለመኖርን
ስለሚፈጥር ይህም ሌላ ሽንፈት ነው፡፡ የወደፊቱን ጭምር ማበላሸት
ደግሞ እጅግ የከፋ የሽንፈት ሽንፈት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ማንኛውም
ማኅበረሰብ ከታሪክ መማር ተገቢ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከታሪክና
ካለፈው ዘመን፣ ከማንኛውም ካለፉ ክስተቶች ጋር መዋጋት ግን
እንደገና መሞት መሆኑን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ካልሆነ
መንገዳችን ጥቅማችን መብታችን ወደምንለው ነገር እንዴት ሊያደርሰን
ይችላል? ስለዚህ ከጥላቻ ለመውጣትና ልዩነቶቻችን ትተን በጋራ ወደ
ማሸነፍ መሔድ ካለብን ካለፈው ዘመን ጋር ያለንን ጸብ በጊዜ
እንግታው፡፡ ታሪክን በተሳሳተ መንገድ መነሻ አድርገው ለሚገለጹ
ትርጉም አልባ የአቅመ ደካሞች ትነተና እንኳን መልስ ጊዜ መስጠትም
አይገባም፡፡ እንደ እኔ ያንን ማድረግ አውቆ ከማበድም አይለይም፡፡
ሐ) ድልድዩን በጋራ እንሥራ
ጦርነቱን እንዳይከሰት በመከላከል አሸናፊነትን ሊያመጡ ከሚችሉት
አወንታዊ እርምጃዎች ውስጥ ሊቀር የማይገባው ነገር መገናኛ
ድልድዮቹን መገንባትን የሚመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ጥላቻ
የሚወስዱ ንትርኮችን ማቆምና የቆዩ ጥላቻዎችን ማስወገድ ከተቻለ
የሚቀጥለው ጉዳይ ከለያዩን ይጥላቻ ወንዞች የሚያሻግረን የድልድይ
ግንባታ ጉዳይ ይሆናል፡፡ እስካሁን በሚታየው እንደመለያያ ወንዞች
ሊጠቀሱ የሚችሉ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ላናጣ እንችላለን፡፡ ብሔሩ፣
ቋንቋው፣ ሃይማኖቱ፣ ታሪካዊ የሥልጣን ትንተናና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ
የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በቀላሉ
የሚያሸጋግሩን ድልድዮችን ለመገንባት አሁንም ጊዜው አልመሸም፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩትንና በጥላቻ ዲጅኖ ብንመታቸው ያልፈረሱትን
ጠግነንና አጠንክረን አሁንም አዳዲስ ብዙ ድልድዮችን ልንገነባ
እንችላለን፡፡
ከዚህም ሁሉ ጋር የማኅበረሰብ የእኩል አሸናፊነትና እኩል ተጠቃሚነትን
የሚያረጋግጥ ድልድይ በአንደኛው ማኅበረሰብ በኩል ብቻ ሊገነባ
የሚችል አይደለም፡፡ ኒከሰን የተባለው ሌላው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት
“ድልድዮችን በመሥራት አምናለሁ፤ ልንሠራ የሚገባን ግን በእኛ በኩል
ያለውን የድልድዩን ክፍል ብቻ ነው” እንዳለው በሌሎች በኩል ያለውን
እኛ ልንሠራው አንችልም፤ አይገባምም፡፡ ነገር ግን ስለዚያኛው አካል
መሥራት አለመሥራት ሳንጨነቅ በራሳችን በኩል ያለውን ከመሥራት
አለመቆጠብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የማኅበረሰብ መገናኛ
ድልድይ እንደ ቁሳዊ ድልድይ ስላልሆነ አንዱ የሠራው ብቻ ሊያሻግር
አይችልም የሚባል አይደለም፡፡ እንዲያውም ቀድሞ በሠራው
አማካኝነት ከሌላው በኩል መጥተው ድልድዩን አስተማማኝ አድርገው
የሚጨርሱበትን ዕድል የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም
በራሱ በኩል ያለውን ክፍል ሌላውን ሳይጠባበቅ ሲሠራ በመካከል
አላገናኝ ያለንን የልዩነት ወንዝ በቀላሉ ከሁሉም አቅጣጫ ተነሥተን
ልንሻገረው እንችላለን፡፡
በዚህ መንገድ የምንሔድ ከሆነ ለማንኛችንም የማይጠቅመውን
ጦርነትና ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ፈተናችንን ልንወጣው፤
ሁላችንም አሸናፊዎች ሆነንም ለዐለም በአዲስ ገጽታ ብቅ ልንል
እንችላለን፡፡ እንግዲያውስ የሚያለያየንን ነገር ትተን የሚያገናኘንን ፣
ከወደፊቱ ሥልጣኔና እድገትም የሚያደርሰንን ድልድይ እንሥራ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን፡

Filed in: Amharic