>
11:17 pm - Monday October 25, 2021

አነጋጋሪው የሳዑዲ እስር (ዶይቼ ቬሌ)

ተስፋለም ወልደየስ እና ኂሩት መለሰ

ሳዑዲ አረቢያ ከትላንት በስቲያ ምሽት ልዑላንን፣ በስራ ላይ ያሉ እና የቀድሞ ሚኒስትሮችን፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ባለወረቶችን በድንገት አስራለች፡፡ ከታሰሩት ውስጥ በኢትዮጵያ በርካታ የንግድ ተቋማትን የሚያንቀሳቀሱት ሼህ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡

እርምጃው ለአልጋ ወራሹ «ስልጣን ማደላደያ ነው» ተብሏል

የባህረሰላጤዋ ቁልፍ ሀገር ሳዑዲ አረቢያ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በተከታታይ በተከሰቱ ፖለቲካዊ ሁነቶች እየተናጠች ትገኛለች፡፡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የተደራረቡት ክስተቶች የአካባቢውን ፖለቲካ በቅጡ ለሚከታተሉ ተንታኞች እንኳ ያልተጠበቁ እና እንግዳ ሆነውባቸዋል፡፡ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር በሪያድ ሆነው ስራ መልቀቃቸውን ማወጃቸው፤ ሳዑዲ በሪያድ ላይ የተቃጣ የሚሳኤል ጥቃትን አከሸፍኩ ማለቷ፣ የሀገሪቱ የብሔራዊ ዘብ የበላይ የሆኑ ልዑል ከኃላፊነት መነሳት፣ በሳዑዲ አልጋ ወራሽ የሚመራ የጸረ-ሙስና ኮሚቴ መቋቋም የበርካታ ልዑላን፣ ባለስልጣናት እና ባለወረቶች እስር እንደዚሁም በሂሊኮፕተር መከስከስ የአንድ ልዑል መሞት በ48 ሰዓታት ውስጥ የተሰሙ ዜናዎች ናቸው፡፡

  ከሁሉም በላይ ትኩረትን ስቦ እስካሁን እያነጋገረ ያለው ግን የእስሩ ጉዳይ ነው፡፡ ቅዳሜ ምሽቱን ይፋ በወጣው የእስራት እርምጃ 11 ልዑላን፣ አራት በስራ ያሉ እና 11 የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ “በሙስና ላይ የተከፈተ ዘመቻ” በተባለለት የእስራት እርምጃ ቢሊየኖሮች ጭምር ያሉበት የናጠጡ ባለሀብቶች ስብስብም ተካተውበታል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ መገናኛ ብዙሃን ስማቸው ከተዘረዘረ ባለሀብቶች መካከል በኢትዮጵያ በርካታ የንግድ ተቋማት ባለቤት የሆኑት ሼህ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ አንዱ ናቸው፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ ያወጧቸው መረጃዎች ባለሀብቱን ፎቶ ጭምር የያዙ ቢሆንም ከእርሳቸው ወገን የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ባለመሰጠቱ ነገሩን ድፍንፍን አድርጎታል፡፡ ጉዳዩን እየተከታተለ የሚገኘው የሪያዱ ዘጋቢያችን ስለሺ ሽብሩ ግን የአላሙዲን መታሰር ከምንጮቼ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አላሙዲ የተወሰኑት ታሳሪዎች እንዲቆዩ ተደርገውበታል በተባለው የሪያዱ ሪትዝ ካርልቶን ባለአምስት ኮኮብ ሆቴል ውስጥ እንደሚገኙ ምንጮቹ እንደነገሩት ገልጿል፡፡

“እዚህ ነገሩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ለእኔ በስልክ እንዳረጋገጡልኝ፣ ዛሬም አጣርቼያለሁ እንደነገሩኝ እዚሁ አለ የተባለው ትልቁ ሆቴል ውስጥ ካሉት ሰዎች መካከል አንደኛው እርሳቸው እንደሆኑም ዛሬም አረጋግጠውልኛል፡፡ ሞሮኮ ሀገር ትልቅ ንብረት አላቸው፡፡ የዘይት ማጣሪያ ተቋም አላቸው፡፡ የሞሮኮ መገናኛ ብዙሃን ጥቅማቸው ስለሆነ የእርሳቸውን መታሰር በሰፊው ዘግበውታል” ይላል ስለሺ፡፡

በእርግጥም “አላሙዲን በቁጥጥር ስር ውለዋል?” የሚለውን ለማጣራት በአዲስ አበባ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ የሚሰጠን ማግኘት አልቻልንም፡፡ የሼህ መሐመድ አላሙዲን እስር በኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋገሪያ እንደሆነው ከዓለም ቁንጮ ቱጃሮች አንዱ የሆኑት የልዑል አልዋሊድ ቢጥላል በቁጥጥር ስር መዋል የብዙዎችን ቀልብን ስቧል፡፡ ልዑል አልዋሊድ እንደ ትዊተር፣ አፕል፣ ሲቲግሩፕ ባንክ እና ፎር ሲዝን ሆቴሎች ባሉ ዓለም አቀፍ ስመ ጥር የንግድ ተቋማት የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ናቸው፡፡

ከሳዑዲ አረቢያ መስራች አባት ከንጉስ አብዱል አዚዝ አልሳዑድ የልጅ ልጆች አንዱ የሆኑት የ62 ዓመቱ ልዑል አልወሊድ ከሳዑዲ ከንጉሳውያን ቤተሰቦች መካከል ”በግልፅ ነገሮችን የሚናገሩ ነበሩ” ይሏቸዋል፡፡ የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለመሪነት በዕጩነት በቀረቡ ጊዜ የወረፏቸው ሁሌም በምሳሌነት ይነሳል፡፡ ልዑሉ ትራምፕን “ለመላው አሜሪካ ማፈሪያ” ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ከዕጩነትም ራሳቸውን እንዲያገልሉ ሁሉ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ በረዥም ጊዜ የሴቶች መብት ተሟጋችነትም የሚታወቁ ናቸው፡፡ የሪያዱ ስለሺ የልዑል አልወሊድ መታሰር “ከባድ እርምጃ ነው” ይላል፡፡

የልዑል አልወሊድ መታሰር ለሀገሬው ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ባለወረቶች ጭምር ድንጋጤን እንደፈጠረ ኮንትሮል ሪስክስ በተሰኘ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ግርሃም ግሪፍትስ ይገልጻሉ፡፡“እርሳቸው ማለት እኮ ታማኝ ሸሪካቸው እና በንጉሳውያን ቤተሰብ ውስጥ የሚታመን አይነት ሰብዕና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃም የንጉሳውያን ቤተሰቡን የንግድ ጥቅሞች የሚከታተሉ የነበሩ ናቸው፡፡  ለበርካታ የንግድ ሰዎች እርሳቸው ተያዙ ማለት ባጣሙኑ የሚያደናግር ነው” ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ፡፡

ከታሰሩት 11 ልዑላን መካከል ሌላው ከፍተኛውን ትኩረት የሳቡት አሁን በስልጣን ላይ ካሉት ንጉስ ሰልማን በፊት ሀገሪቷን የመሩት የንጉስ አብደላህ ልጅ ልዑል ሙጢብ ቢን አብደላህ ናቸው፡፡ እስከ ቅዳሜ ምሽት ድረስ የሀገሪቱ ብሔራዊ ዘብ ኃላፊ የነበሩት ልዑል ሚጠብ ስልጣናቸውን ተነጥቀው እምብዛም ሳይቆይ ነው ለእስር የተዳረጉት፡፡ ልዑል ሙጢብ በአንድ ወቅት አሁን 81ኛ ዓመታቸውን የያዙትን የንጉስ ሰልማንን ዙፋን የመረከብ ተስፋ የነበራቸው ነበሩ፡፡

ሆኖም ባለፈው ዓመት የ32 ዓመቱ ንጉስ ሰልማን ልጅ መሐመድ ቢን ሰልማን አልጋ ወራሽ ተብለው ሲሰየሙ ከዙፋን ተረካቢነት ገሸሽ መደረጋቸው በግልጽ ታይቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ በሳዑዲ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን እና የአልሳውድን ስርወ መንግስት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሸከመው የብሔራዊ ዘብ ኃላፊነት ይዘው ቆይተዋል፡፡ የሪያዱ ስለሺ የልዑል ሙጢብ ከስልጣናቸው መነሳት አንደምታን  ያስረዳል፡፡

የልዑል ሙጢብ መታሰር የአልጋ ወራሹን የሞሐመድ ቢን ሰልማንን ስልጣን ለማደላደል የተወሰደ እርምጃ አድርገው ከሚያስቡት መካከል የፖለቲካ ተንታኙ ግርሃም ግሪፍትዝ ይገኙበታል፡፡ “ሞሃመድ ቢን ሰልማን በጦር ኃይሎች እና በደህንነት አገልግሎቱ ውስጥ የወሰዱትን የማጠናከር ስራን ተመልከቶ እርሳቸው ከስልጣናቸው የመነሳታቸው ጉዳይ አይቀሬ እንደሆነ ተገምቶ ነበሩ፡፡ ሞሃመድ ቢን ሰልማን መጀመሪያ የመከላከያ ሚኒስትሩን ቀጥሎ የጸረ ሽብር  እና የሀገር ውስጥ ደህንነት አገልግሎትን በእርሳቸው የበላይ ጠባቂነት ስር እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ ከዚህ ውጭ የነበረው አንድ ኃይል የብሔራዊ ዘቡ ነበር፡፡ የብሔራዊ ዘቡን አመራርን ለመለወጥ የነበሩ ሌሎች ዕቅዶች ቢኖሩም ነገር ግን ቀጥተኛ መነሻ ምክንያቱ ያ ነው” ይላሉ ግሪፍትዝ፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ ከልዑሉ እስር ጀርባ ያለውን ፖለቲካዊ ምክንያት እንዲህ ቢገልጹም አንድ የሳዑዲ መንግስት ባለስልጣን ግን በልዑል ሙጢብ ላይ የተወሰደው እርምጃ ከገንዘብ ምዝበራ ጋር የተያያዘ ነው ሲል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡ ልዑል ሙጢብ “10 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የስራ ውል ለራሳቸው ድርጅቶች መስጠታቸው፣ በእውን የሌሉ ሰራተኞች እንዳሉ አስመስለው ቅጥር መፈጸማቸው ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል ይገኙባቸዋል” ሲሉ ባለስልጣኑ ገልጸዋል፡፡

ልዑል አልዋሊድም ተመሳሳይ የሙስና ክስ እንደቀረበባቸው ባለስልጣኑ አመልክተዋል፡፡ ልዑሉ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ ማድረግ፣ ጉቦ መስጠት እና ባለስልጣናት ላይ ጫና በማሳደር መጠርጠራቸውን ለሮይተርስ መረጃውን የሰጡ ባለስልጣን ዘርዝረዋል፡፡ ይህ የገንዘብ ምዘበራ ጉዳይ በመንግስት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን በቅርበት በሚከታተሉ በተወሰኑ ተንታኞችም ዘንድ የሚቀነቀን እንደሆነ ስለሺ ይናገራል፡፡

የሳዑዲ ፖለቲካ ተንታኝ እና ጋዜጠኛ ማንሱር አል አሚር የእስር እርምጃው ከፖለቲካዊ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አለው ብለው ከሚያምኑት አንዱ ነው፡፡ “በሙስና የተያዙት ሰዎች በከፍተኛ ስልጣን ደረጃ ላይ ያሉና በርካታ ገንዘብም ያላቸው ናቸው፡፡ በዓለም በበርካታ አህጉራትም የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይህ መሪዎቻችን የኢኮኖሚውን ዘርፍ እንደ ጠቃሚ ጉዳይ መውሰዳቸውን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢላማ ያደረገው በዓለም ደማቅ ስም ያላቸው ሰዎችን ቢሆንም አሁን የሙስና ትግሉ የሚካሄድበት የኢኮኖሚው ምህዳር ተዓማኒነት እንዲኖረው ለማድረግም ነው” ይላሉ ማንሱር አል አሚር፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ ግርሃም ግሪፍዝ ግን ጉዳዩ የሙስና ዘመቻ መሆኑ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ይመስላል፡፡  “እኔ እንደሚመስለኝ ነገሩ በትከክልም የጸረ-ሙስና ጉዳይ ቢሆንም  መንግስት የሚጠራጠረውን የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ለማሳመን አስቸጋሪ ጊዜ የሚገጥመው ይመስለኛል፡፡ ሁሌም ቢሆን ይህ ከፖለቲካ ስሌት እና አጀንዳ ጋር የተያያዘ መሆኑ ላይ ጥርጣሬ ይኖራል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ማንም ሰው በሙስና ጉዳይ ሊመረመር እንደሚችል ለብዙዎች በግልጽ መልዕከት ያስቀመጠ ነው” ሲሉ የሳዑዲ እስር አንደምታው ያስረዳሉ፡፡

 

Filed in: Amharic