>
5:16 pm - Thursday May 23, 4672

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከሸገር ታይምስ መፂሄት ጋር ያደረገው ሙሉ ቃለ ምልልስ

‹‹የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ› ተመስርቶ ሳይውል ሳያድር ሥልጣን መረከብ አለበት!››

‹‹በጉሽ ጠላ እየተገፉ ሥልጣን ለቅቄያለሁ ማለት አይሠራም!››
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ሸገር ታይምስ፡- ዛሬ ከወህኒ ከወጣህ ስንተኛ ቀንህ ነው?
ተመስገን፡- ይህ መጽሄት በሚወጣበት ቀን ወደ ሶስተኛ ሳምንቴ እጠጋለሁ፤
ሸገር ታይምስ፡-እነዚህ ቀናት እንዴት አለፉ?
ተመስገን፡- እጅግ በርካታ ሰዎች ወደ እናቴ ቤት እየመጡ ደስታቸውን እየገለጹልኝ ፣ እኔም እነሱን እያስተናገድኩ ነው ያለፈው፡፡ በነገራችን ላይ ከጠያቂዎቼ 95 የሚሆኑት በመቶ በሚዲያው ላይ በነበረኝ አስተዋፅኦ የሚያውቁኝ ናቸው፡፡
ሸገር ታይምስ፡- የጤናህስ ጉዳይ አሁን እየተረጋጋህ ነው?
ተመስገን፡- የጆሮዬ ህመም ተስፋ አለው፡፡ የጀርባዬ ትንሽ ከበድ ያለ እንደሆነ ተነግሮኛል፡፡ በሰርጀሪ ነው የሚድነው ወይስ በሌላ ህክምና የሚለውን ለማወቅ ኤም አር አይ ከተነሳው በኋላ የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡
ሸገር ታይምስ፡- የጀርባ ህመሙ መነሻ ምንድ ነው?
ተመስገን፡- ወህኒ ከመግባቴ ከ4 አመት በፊት የመጣ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ እንክብካቤ አደርግ ስለነበር እፎይታ ነበረው፡፡እስር ቤት ከገባሁ በኋላ ግን የእስር ቤት አያያዝ ለበሽተኛ ቀርቷ ለጤነኛም አይሆንም እና እየተባባሰብኝ ሄዷል፡፡
ሸገር ታይምስ፡- ወቅታዊ የህክምና ክትትል ባለማግኘትህ ነው የተባባሰው?
ተመስገን፡- አዎ ህክምና ያለማግኘቴ ነው ህመሙን ያባባሰው፡፡ ህክምና ባገኝማ ኖሮ እንዲህ አስጊ ደረጃ ላይ ባልደረሰ፡፡ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነጥብ የሀይማኖት አባቶች ገሀነምን ምድር ላይ የሌለ አድርገው የሚሰብኩት ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ገሀነም ያለው እዚህ ኢትዮጵያ፣ በተለይ ደግሞ እስር ቤቶች ውስጥ ነውና፡፡
ሸገር ታይምስ፡- የታሰርኩት በፃፍኩት ነገር ነው ብለህ ታምናለህ?
ተመስገን፡- እኔ ብቻ ሳልሆን አብዮታዊ ግንባሩም አልካደውም፡፡ በግላጭ አምኗል፡፡ በክሱ ሂደት ላይም በምስክርና በማስረጃነት ተቆጥረው የቀረቡብኝ ፍትሕ ጋዜጣ ላይ የታተሙ ጽሑፎች ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አንድ ጋዜጠኛ ብቻ ነው በፅሁፍ ያሰርነው›› እያሉ ሲናገሩ የነበረው፡፡
ሸገር ታይምስ፡- ፅሁፎቹ የትኞቹ ናቸው? ያስከስሱስ ነበር?
ተመስገን፡- በተለያዩ ጊዜ የታተሙ አምስት ፅሁፎች ተጨምቀው ነው ሦስት ክስ የወጣባቸው፡፡ የክሶቹም ጭብጥ የመጀመሪያው ‹‹ወጣቶች ህገመንግስቱን በሀይል እንዲጥሱ ግፊት ማድረግ››፤ ሁለተኛው ‹‹የመንግስትን ስም ማጥፋት››፤ ሦስተኛው ‹‹የህዝብን አስተሳሰብ ማናወጥ›› የሚሉ ናቸው፡፡
የሆነ ሆኖ በአራቱም ሚዲያዎች እኔም ሆንኩ ጓዶቼ በሀገራችን የቀለም አብዮት ተነስቶ ስርአቱ እንዲቀየር የተቻለንን ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ይሄ ዓይነቱ ህዝባዊ እምቢተኝነት የዜጎች ተፈጥሯዊ መብት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በግልባጩ ይህንን መሠሉን ንቅናቄ ‹ዋጋ-ቢስ ነው፤ የሚያዋጣው ጠብመንጃ ብቻ ነው› ያሉ የሀገሬ ልጆች ጫካ ገብተዋል፡፡ ግና ምንም ዓይነት ተቃውሞ መስማት ያልፈቀደው ወያኔ ሁለቱንም በእኩል ዓይን አይቶ የሀገሪቱን መከላከያ ሠራዊት በማዝመት በዜጎች ላይ ሞት መርጨቱ ዛሬም ተግ ሊል አልቻለም፡፡ ለዚህም ነው ጠብመናጃ ነካሹንም ሆነ በባዶ እጁ መብቱን እየጠየቀ ያለውን ዜጋ በተመሳሳይ የፀረ-ሽብሩ አንቀጽ ‹‹አሸባሪ›› እያለ የሚከሰው፡፡ በነገራችን ላይ መንግስት ከጎረቤት ሀገር ጋር ወደ ጦርነት ቢገባ እንኳ ሰሞኑን በኦሮሞ ህዝብ ላይ ካዘመተው የተለየ የሰራዊት አሰላለፍም ሆነ የውጊያ ስትራቴጂ ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ምክንያቱም የገዛ ህዝቡን እየጨፈጨፈ ያለው ልክ ከጠላት ሀገር ጋር በሚዋጋበት አቅም ነውና፡፡
በተቀረ እነዚህ እየታዩ ያሉ ኩነቶች ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ አንዱ አካልና ህጋዊነት ያለው ነው፡፡ ስለዴሞክራሲ እና መብቶች በሚያወሩ ሀገራት ህዝባዊ እምቢተኝነት በጠብመንጃ አይጨፈለቅም፡፡ ህዝቡ ከፈቀደልህ ስልጣን ላይ ትወጣለህ፤ እምቢ ካለህ ደግሞ ስልጣን ማስረከብ እንጂ ጦር ሠራዊት ማዝመት ወንጀል ነው፡፡ ወያኔ ግን የስርዓቱን የማፍያነትና የጨፍላቂነት ባህሪይ በሚያጎላ መልኩ በጭፍጨፋው ቀጥሏል፡፡
ዞሮ ዞሮ እኔ የተከሰስኩት ህዝባዊ እንቢተኛነት ጠርተሃል ተብዬ ነው፡፡ ይሄ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በጭፍን ጥላቻ ያደረግኩት አይደለም፡፡ ባለፉት 20 አመታት የተከሰቱ ትላልቅ ሥርዓት-ወለድ ችግሮችና ብሔራዊ ውድቀቶችን በመገምገምና በመፈተሸ እንዲሁም አገዛዙ ራሱን ሊያሻሽል አይችልም ከሚል አሳማኝ ድምዳሜ ነው፡፡ አራት ምርጫዎችንኮ በጠራራ ፀሐይ አጭበርብሯል፡፡ እናም በምርጫ መቀየር ቢቻል ኖሮ ወደ ህዝባዊ እንቢተኛነት አንሄድም ነበር፡፡ ህገመንግስቱ ላይ ‹‹መንግስት የሚቀየረው በምርጫ ነው››የሚለውን በድን አንቀጽ ዘንግቼው አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ሰማይ ሥር የምርጫ ፖለቲካ ፉርሽ ስለሆነ እንጂ፡፡ በምርጫ ለውጥ ማምጣት ካልቻልክ ደግሞ ያለህ አማራጭ አብዮት አሊያም ጠብመንጃ ይሆናል፡፡ እኔ ግን አብዮቱን መረጥኩ፤ አብዮት (ህዝባዊ እምቢተኝነት) ደግሞ የትኛውም ሀገር የሰላማዊ ተቃውሞ አንድ አካል ነው፡፡ እኔና ጓዶቼ የታመንለት አብዮት እንደ ብሉይ አብዮት ጠብመንጃ ያነገበ አይደለም፡፡ በቀዘቃዛው ጦርነት ዘመን እንደነበረው አይደለም፡፡ የእኛ መንገድ በፊሊፒንስ ከተካሄደው የ1986ቱ (እ.ኤ.አ) የቀለም አብዮት ጋር የሚጋመድ ነው፡፡ የቀለም አብዮት ላይ ጠመንጃ የለም፤ መንግስት እንደሚለውም ጭራቅ አይደለም፡፡ በታሪክ ፀሀፊዎች የመጀመሪያው የቀለም አብዮት የተባለው የቢጫ አብዮት የሚል ስም የተሰጠው ፊሊፕንስ ውስጥ የተካሄደው ነው፡፡ ፈርዲናንድ ማርቆስ የተሰኘው አምባገነን መሪ በስልጣን ተሸንፎም ስልጣን አለቅም አለ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን አሰረ፡፡ ያኔ ወጣቶቹ መዲናዋን ማኒላን አጥለቀለቋት፡፡ መሪው ታንክ ቢያዘምትባቸውም ቢጫ አበባ ይዘው ለታንከኞቹና ለወታደሮቹ አጠለቁላቸው፡፡ ባለታንከኞቹ ከወጣቱ ጋር ተቀላቀለው ስርዓቱን ቀየሩ፡፡ ታሪክ ፀሀፊዎች የወጣቶቹን ቢጫ አበባ አይተው ‹‹ቢጫ አብዮት›› ብለው ጠሩት፤ የብርቱካን፣ የቡልዶዘር፣ የቬልቬት….. አብዮት እየተባለ ቀጠለ፡፡ ሆንግኮንግ ላይ ወደ አደባባይ የወጡ ሰዎች ዝናብ በመዝነቡ ጃንጥላ ይዘው ወጡ፤ ክስተቱን የተከታተሉ ፀሀፊዎችም ‹‹የጃንጥላ አብዮት›› ሲሉ ሰየሙት፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ ‹‹የስካርፕ አብዮት›› ሊባል ይችል ይሆናል፤ ማን ያውቃል?
ሁለተኛው ክሴ ‹‹የመንግስትን ስም ማጥፋት›› የሚለው ነው፡፡ ይሄ ቧልት ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ዓይነቱ ቀማኛ መንግሥት ቀርቶ የምዕራባውያኖቹም የሚጠፋ ስም የላቸውም፡፡
ሦስተኛው ክስ ‹‹የሰዎችን አስተሳሰብ አናወጠ›› የሚለው ነው፤ ይሄ የተለመደው ህዝብን አያውቅም ብሎ የመናቅ የመዘባበት አባዜ ውጤት ነው፡፡ የኔ ፅሁፍ የሚያሳምን ከሆነ አንባቢ ይቀበለዋል፤ ካላሳመነ ደግሞ ቀዳድዶ ይጣለዋል፡፡ በተረፈ በግለሰብ አስተሳሰብ የሚናወጥ ኢትዮጵያዊ የለም፤ ቂል አይደለማ፡፡ ማህበረሰቡኮ ነቅቷል፡፡ በአጠቃላይ ሦስቱም ክስ ዋጋ ቢስና ፍሬ ቢስ ነበሩ፡፡
ሸገር ታይምስ፡- የአንተ ፅሁፎች ለእውነታዎች መነሻ ሆነዋል? የወጣቱን አስተሳሰብ ቀይሯል?
ተመስገን፡- በእርግጥ ቀየረ አልቀየረም የሚለውን ለመመለስ ጥናት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የእኔን ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ ፍትህ፣ ፋክት፣ ልዕልና እና አዲስ ታይምስ ካነበብክ በተለያየ አካባቢዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመረዳት አትቸገርም፡፡ በአናቱም በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች የህይወት መስዋዕትነት ያስከፈሉት ህዝባዊ እንቢተኝነቶች ገፊ ምክንያት ስንቀሰቅሳቸው የነበሩ፣ ስንወድቅ፣ ስንነሳ፣ በየፍርድ ቤቱ ስንመላለስ ሚዲያዎቻችን ሲዘግቡት የነበሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እናም እነዚያ ዛሬ በመካነ-መቃብር ያሉ ሚዲያዎቻችን በሕያውያን መካከል ፍሬ አፍርተዋል ብሎ ለመናገር የሚያስደፍሩ ምልክቶች አሉ፡፡
ሸገር ታይምስ፡-ተመስገን እንዲታሰር ያደረጉት ፅሁፎቹ ብቻ ናቸው ብለህ ታምናለህ?
ተመስግንን፡- እንደሚታወቀው በተቻለ አቅም የሚዲያ ኃላፊነት መረጃ መስጠት፣ ማስተማር፣ ማዝናናት፣ ንቃተ ህሊና መፍጠር… የሚለው ላይ ለማተኮር ሞክረናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የግብፅና የቱኒዚያን አመፅ እንደጥሩ ተሞክሮ ወስደነዋል፡፡ መንግስት እዚህ ጋር የሚቀላቀላቸው የሊቢያና የሶሪያ አመፅ ባህሪ እኛ በሀገራችን እንዲቀሰቀስ ከዋተትንለት ንቅናቄ ይለያል፡፡ ከሞላ ጎደል ቡድንተኝነት ተንፀባርቆባቸዋል፡፡ የግብፅና የቱኒዚያ አመፅ ግን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ እንቢታዎች ናቸው፡፡ እኔ ስቀሰቅስበት በርካታ ፅሀፊዎች ሲወተውቱ የነበረው የግብፅና የቱኒዚያን ተሞክሮ ነው፡፡ ቤን አሊን የመሰለ ከነሚስቱ ዘራፊ የነበረን፤ እንደ ሆስኒ ሙባረክ ያለ የወታደር አምባገነንን ያለብዙ መሰዋትነት የገረሰሰ ህዝባዊ አመፅ ነው፡፡ እናም ወያኔ ስራውን ስለሚያውቅ እና ህዝብም የተማረረበት ስለሆነ ነው ወደ እስር ቤት የከተተኝ፡፡ ከዚያ ሌላ የምርጫ ወራቱ መቅረቡ ነው፡፡ ስታሰር ምርጫው 6 ወር ነበር የቀረው፡፡ አራት ምርጫ አጭበርብሮ፣ አምስተኛ ምርጫ መግባት እርሱን መተባበርነው የሚል አመለካከት አራምድ ነበር፡፡ ከአምስተኛው ምርጫ ይልቅ የአምስት ቀናት ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስትን ያፈራርስው ነበር፡፡
ሸገር ታይምስ፡-ሰዎች እንዳይጎበኙህ ይደረግ ነበር? አንት ላይ ለምን ነገሩ ከረረ? አንተንስ ያውቁሃል?
ተመስገን፡- ቂሊንጦና ቃሊቲ ያሉት ከሞላ ጎደል ስለ ጋዜጠኞች መረጃ አላቸው፤ የዝዋዮቹ እኔን የሚያውቁኝ እነሱ ጋር የደረስኩ ዕለት ነው፤ ሆኖም የዛኑ ቀን (ጥቅምት 3/2007) ሃላፊዎቹ ባያውቁኝም የተላለፈላቸውን መረጃ ብቻ ተቀብለው ጨለማ ቤት ከተቱኝ፡፡ ሰዎቹ ካላነበቡኝ ሊያውቁኝ አይችሉም፡፡ ካላወቁኝ ደግሞ ለምን ጨለማ ቤት ከተቱኝ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆነ በነበርኩባቸው ሦስት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ያሉ ሃላፊዎች የህወሀት ታጋይ የነበሩ ስለሆነ በቀላሉ የተነገራቸውን ተቀብለው የአንድ ብሄር ጠላት አድርገው ለመቁጠር አልተቸገሩም፡፡ ሌላው ደግሞ ይሄ መንግስት ከበቀለኛና ቂመኛነቱ አንፃር ነው በቤተሰቦቼ ሆነ በወዳጅ ዘመዶቼ እንዳልጎበኝ ሲያደርግ የነበረው፡፡ በረሀ ላይ ያውም ጨለማ ቤት ውስጥ ታስሬ ምንም አልፈጥርም፣ ጠመንጃ የለኝ፣ የምመራው ሰራዊት የለኝ፣ የምመራው ሚዲያ ነው፣ ሚዲያውን ደግሞ ዘግቶታል፡፡ ለምን እንዲህ እንደሚሸበሩ ይገርመኛል፡፡ ከቤተሰቤ የሚላከውን ምግብ ግማሹን ደፍተው ግማሹ እንዲገባ እየፈቀዱ ህክምና የሚባል ነገር እንዳላገኝ እያገዱ ማሰቃየት እውነተኛ የወያኔ ባህሪይ ነው፡፡
ሸገር ታይምስ፡- ታምክ ወደ አዲስ አበባ ሪፈር ተብለህ ነበር፤ ነገር ግን ተግባራዊ አልተደረገም……. ለምን?
ተመስገን፡- የሚያሳዝነው ይሄ ነው፡፡ በተለያዩ ግፊቶች አቅሜ እየደከመ ሲሄድ ባቱ ሆስፒታል ተላክሁኝ፡፡ እዚያ ያሉ ሀኪሞች ደግሞ ጉዳቴ ከበድ ያለ ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ‹ሪፈር› ፃፉልኝ፡፡ ይሁንና ከሳምንት በላይ ወደ አዲስ አበባ ሳያመጡኝ ሲቀሩ የእስር ቤቱን ሥራ አስኪያጅ እና የጥበቃና ደህንነት ኃላፊው አስጠርቼ ለምን እንደማይልኩኝ ስጠይቃቸው ቃል በቃል የሰጡኝ ምላሽ፣ ‹‹ምንም ልናደርግ አንችልም፤ አንተን እንኳን ወደ አዲስ አበባ ቀርቶ እዚያው ግቢ ውስጥ ከክፍል ክፍል ስናዘዋወር ለበላይ አሳውቀን ነው፤ ስለዚህ ምንም ማድረግ አንችልም›› አሉኝ፡፡ ስለዚህም እዚያው ይሰቃይና ይሙት ብሎ የወሰነብኝ የፖለቲካው አመራር ነው፡፡
ሸገር ታይምስ፡- በቃ በዚሁ ህክምናው ተሰርዞ ቀረ?
ተመስገን፡- ከሁለት ወር በኋላ ቀይ መስቀሎች መጡና ራጁን አሳየኋቸው፡፡ የተለያዩ ሚዲያዎችም ህክምና መከልከሌን ሲዘግቡ ስለነበረ እንደባለፉት 26 አመቶች ሁሉ ማስቀየሻ መንገድ አዘጋጁ፡፡ እናም የማረሚያ ቤቶች የሜዲካል ዳይሬክተር የሆነው ዶ/ር ለማን ላኩት፡፡ ማታ ወደ 11፡00 ሠዓት አካባቢ አስጠራኝና በሚገርም መልኩ እጅህን ዘርጋ እጠፍ ብሎ ካየኝ በኋላ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለኸው፣ ህክምና አያስፈልግህም አለኝ፡፡ ይኸው የራጅ ውጤቱን ለምን አታየውም ዕብጠትና መላላጥ አለው ስለው ወይ ተመስገን በዚህ ዘመን ራጅኮ ጥቅም የለውም ብሎኝ አረፈው፡፡ እግዜር ያሳያችሁ! ይሄ ዶ/ር ነው፤ ከቴክኖሎጂ ውጤት ይልቅ ቁጭ ብድግ አሰርቶኝ ጤነኛ ነህ ያለኝ፡፡ ይሄ ያማል፡፡ በእርግጥ የሰውየውን መታወቂያ ስላላየሁኝ ዶ/ር ይሁን ታጋይ ለይቼ አላወቅሁም፡፡ ራጅ በዚህ ዘመን ዋጋ የለውም የሚልን ሰው ሃኪም ነው ማለት ግን ይቸግረኛል፡፡
ሸገር ታምስ፡- የፓርላማና የደህንነት ሰዎች መጥተው እንደጎበኙህ ሰምቻለሁ፡፡ አትግባባም አሉ…… እዚያም ሆነህ ተናጋሪ ነህ እንዴ?
ተመስገን፡- ተናጋሪ አይደለሁም ከፓርላማ ሰዎች ያልተግባባሁት ም/ቤቱን በህዝብ የተመረጠ ማድረጋቸውና መንግስትንም ችግር ፍቺ አድርገው ማቅረባቸው ነው፡፡ ከችግር ይልቅ ለመንግስት ጥቅም አደሉና ዞር በሉልኝ አልኳቸው፡፡
ሸገር ታይምስ፡- ልዩነቱን እስቲ አብራራው?
ተመስገን፡- ከዚያ ይልቅ ሌላ ገጠመኝን ላውራህ፡፡ ሦስት አመት ተፈርዶብኝ በ2007 እስር ቤት ገባሁ፡፡ 8 ወር አካባቢ እንዳለፈ ከጨለማ ቤት አውጥተው 2000 እስረኛ ካለበት ግቢ ውስጥ ቀላቀሉኝ፡፡ እናም የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ከዚያ ቤት ያወጣንህ ምርጫው ስላለፈና ጥቅምት 3 ቀን 2008 ስለምትፈታ ነው ብለው ከመናገራቸውም በላይ ‹‹ኦራንቴ›› ላይ በተጠቀሰው ቀን እንደምፈታ ፅፈው ሰጡኝ፡፡ ለጠበቃዬም በመልእክት ነገርኩት፡፡ ሁለታችንም አልገባንም፡፡ ሆኖም ምናልባት አብዮታዊው ግንባር እኔን ወደ እስር ቤት የከተተው ምርጫው አስፈርቷት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ደግሞ ምርጫውን አሸነፍኩ ብሎ አውጆአል፡፡ ስለዚህ እስር ቤት ማቆየት አልፈለገም ይሆናል ብዬ ተቀበልኩት፡፡ ዞሮ ዞሮ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ደረሰ፡፡ እንደተጠበቀውም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ በግቢው ያለውን ወደ 2000 የሚጠጋ እስረኛ ወደ ቤት እንዲገባ በሚኒ ሚዲያ ተናገሩና አስገብተው ቆለፉባቸው፡፡ ይሄ የሆነው እኔን ሲፈቱ እስረኛው ደስታውን በፉጨትና በጩኸት መግለፁ ስለማይቀር ረብሻ ሊነሳ ይችላል ብለው ሰግተው ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ሃላፊዎቹ መጡና ተፈትሃል፤ እቃህን ይዘህ ውጣ አሉኝ፡፡ እኔ ባለሁበት ክፍል ያሉ እስረኞቹን ተሰነባብቼ ያለኝን ቁሳቁስ ሰጥቼ ሁለቱንም የእስረኞች ግቢ ለቅቄ ወጣሁ፡፡ እና ቢሮ አስገቡኝ፡፡ ኋላም የማላውቃቸው ሰዎች ‹‹ቀጣይ አላማህ ምንድነው›› ብለው ጠይቀውኝ ሳንግባባ ቀረን መሰለኝ በስህተት ነው የተፈታኸው አሉና መልሰው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ላይ ወደ ክፍሌ አስገቡኝ፡፡ (ጥቅምት 3 ቀን 2008 ተፈትቼ እንደነበር ሰው አያውቅምና ይህን አዲስ መረጃ ለመናገር ነው፡፡) ወደ ክፍሌ ስመለስ ከደቡብ ክልል ማረሚያ ቤት ለሥራ ከመጡ እስረኞች ጋር አሰሩኝ፡፡ የከተማ ልጆች አይደሉም፤ እነሱን ማሳመፅ አይችልም ብለው አስበው ነበር፡፡ ያን ምሽት እስረኞቹ እንደ ሀዘንተኛ እያፅናኑኝ አይዞህ ሲሉኝ አደርን፡፡ ያከፋፈልኳቸውን ቁሳቁሶቼንም መለሱልኝ፡፡ ይሄ የሆነው ሞራሌን ለመንካት አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ እኔም የስርዓቱ ባህሪ የት ድረስ መሄድ እንደሚችል አውቅ ስለነበር ብዙም አልተገረምኩም፡፡
ሸገር ታይምስ፡-ከህመም አንፃር ብዙ ውሃ ትጠቀም እንደነበር፣ ግን ከውሃ አንፃር እንኳን እንዳይገባልህ ትከለከልም እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
ተመስገን፡-ኩላሊቴን ያመኝ ነበር፡፡ በርግጥ የሚረባ አይደለም እንጂ የእስር ቤቱ ጤና ጣቢያ ነበር፡፡ ድሮም ቢሆን የታሸገ ውሃ እጠጣ ስለነበር ውሃ ከውጪ እየተገዛ እጠቀማለሁ በብዛት የውሃ ተጠቃሚ መሆኔን ሲያውቁ ውሃ አይገባም ብለው አገዱ፡፡ ይሄ አንዱ የማሰቃያ መንገድ መሆኑ ገብቶኛል፡፡
ሸገር ታምስ፡-እስቲ ወደ አመክሮ እንመለስ……መፈታት ካለብህ ሦስት ቀናት ዘግይተህ ነው የተፈታኸው… ለምንስ አመክሮ ተከለከልክ?
ተመስገን፡- የአመክሮ ክልከላ የነሱ ውሳኔ እንዳልሆነ አስቀድሜ መረጃው ስለነበረኝ ያኔ እንደተከለከልኩ አልተሰማኝም.. የህወሓት አመራር ነው የከለከለኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ነገር ግን እኔ ፋይል ላይ የፃፉት አመፅ ቀሰቀሰ ብለው ነው፡፡ አመፅ ግን አልተቀሰቀሰም፤ ከደቡብ ክልል ማረሚያ ቤት የመጣ አንድ እስረኛ ሞቶ ተገኘ፡፡ አሟሟቱ አሰቃቂ ነበር፡፡ ጓደኞቹ የሱ አሟሟት ካልተጣራ እኛም ልንሞት እንችላለን ብለው ፈሩ፤ ስለዚህም ስራችሁን ለመቀጠል አስከሬኑ ቤተሰቡ ጋር መላክ አለበት፤ ለዘላቂ ዋስትናም አሟሟቱ መመርመር ሲችል ብቻ ነው ብዬ ምክር ለገስኳቸው፡፡ ይሄ አመፅ አይደለም፡፡ ወደ 300 እስረኛ በሙሉ ስራ አቆሙ፡፡ የእስር ቤቱ ዋና ገቢ ደግሞ የግቢ ልማት የሚባለው ሰፊ የእርሻ መሬቱ ነው፡፡ ቲማቲም፣ አቮካዶ፣ ወይን፣ ሽንኩርት…… ያመርታል፡፡ በእርግጥ በእስረኛ ርካሽ አንዳንዴም የነፃ ግዴታ ጉልበት የሚመረተው ምርት ተመልሶ ለእስረኛው ውጪ ከሚሸጥበት ዋጋ ጨምሮ እጅግ በውድ ዋጋ ይሸጥለታል፡፡ ገቢው ለማን እንደሆነ ግን አልገባኝም፡፡ ኦዲት ይደረግ እንደሁ እንኳ አላውቅም፡፡ ለማንኛውም ልጆቹ ሦስት ቀን ስራ ካቆሙ በኋላ መፍትሄ አገኙ፡፡ እናም ይሄ አመፅ አይደለም፡፡
ሸገር ታይምስ፡- ከመረጃ በመራቅህ ምን አይነት ኢትዮጵያን ታስብ ነበር?
ተመስገን፡- ከመረጃ ርቄያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ያለፉት አመታት የወያኔ ባህሪን ስለማውቀው የተለየ ነገር ይመጣል ብዬ አላሰብኩም፡፡ ከርሱ ይልቅ የግፍ፣ የበደሉን ሁኔታ ያለቅጥ እንደጨመረ መገመት እችል ነበር፡፡ አንዳንድ ከቤቶቼ በኩል ተገዝተው የሚመጡ ነገሮችን ዋጋ ሳስተውል ያለውን የኑሮ ውድነት እረዳ ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ይሄ መንግስት የሚሻሻል አይደለም ምንም ለውጥ መጠበቅ አይቻልም፤ በበደልና በክፋት የተሞላ ነውና ከነበርኩበት ጊዜ የከፋች፣ አደጋ ያንዣበባት አስጊ ኢትዮጵያ እየመጣች እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፡፡ በቃ ስሜቴ እንዲህ ነበር፡፡
ሸገር ታይምስ፡- ከተፈታህ በኋላ ሞጆ ከተማ በሠላማዊ ሠልፍ ላይ የኦነግን ባንዲራ አይተህ………ተገርመሃል?
ተመስገን፡- መደነቄን ያመጣው የኦነግን ባንዲራ ያውለበለቡና ቲሸርቱን ያደረጉ ወጣቶች በሁሉም የኦሮሚያና የፌዴራሉ እስር ቤቶች ዛሬም ድረስ እየማቀቁ መገኘታቸውን ነው፡፡ በሠላማዊው ሠልፍ ላይ ሌላው ያስገረመኝ የኦነግን ባንዲራ ያውለበልቡ የነበሩት ሰልፈኞች በክልሉ ፌዴራሎች ታጅበው ሲፎክሩ እና ሲዘምሩ ማየቴ ነው፡፡ የወያኔ የፀረ ሽብር ህግ አርማና ባንዲራ ቀርቶ ስለድርጅቶቹ ማውራት ሽብር እና አሸባሪነት ነው በሚባልባት ሀገር ሞጆ ላይ ይህን ማየቴ አስገርሞኛል፡፡
ሸገር ታምስ፡-ምናልባት ይሄ ነፃነቱ ይሆን?
ተመስገን፡-እንግዲህ ነፃነት ነው አይደለም ለማለት ጊዜ የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የሚመስለኝ መንግስት አሁን ያለበት እንደ ደርግና ኢሰፓ የ83ቱ ጊዜ አይነት ነው፡፡ በመቃብሩ ጠርዝ ላይ የቆመ ይመስለኛል፡፡
ገር ታይምስ፡ እስቲ አብራራው
ተመስገን፡- አገዛዙ ተፈጥሮአዊ ዕለተ ሞቱ፣ የማይቀረው ግበአተ መሬቱ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ምንም አያከራክርም፡፡ ነገር ግን አሟሟቱን ለማሳመር ሁለት ዕድል አለው፡፡ የመጀመሪያው ቢዘገይም በቀራቸው የሰአታት ዕድሜ አገራችንን ወደእኛ ልጆቿ መመለስ አለባቸው፡፡ ከዚህ ወዲያ ኢትዮጵያውያን ይህን መንግስት የሚታገሱበት ሁኔታ የለም፤ በዛኮ፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ ታራግፈዋለህ አትችልምና እንቢ ነው የምትለው፡፡ ሌላው ቀርቶ አላምደህ ያሳደግህው ውሻና ድመት በር ዘግተህ መግረፍ አትችልም፤ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ዘለው ሊከመሩብህና ከባድ ጉዳት ሊያደርሱብህ ይችላሉ፡፡ ህዝባችን በርሃብ መሞት ወይም አሸንፎ ረሃብን በጥጋብ መቀየር የሚለው ሁለት ምርጫ ብቻ እንዳለው በሚገባ ተረድቷል፡፡ የእነሱም ምርጫ ማስረከብ ወይም መሞት ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ትንቢት ሳይሆን የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ እናም መሪዎቻችን በዚሁ የዕብሪት መንገድ ከቀጠሉ ከዘግናኝ ሞታቸው ውጪ የሚጠብቃቸው ተስፋ የለም፡፡ ይሄን በጥቂት ጊዜ ውስጥ እናያለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ገር ታይምስ፡- ከዚህ አደጋ የመውጫው በር ምን ይመስልሀል
ተመስገን፡- አሁን በሀገሪቱ ላይ የሥልጣን ክፍተት አለ፤ ሕዝቡ ከተለመደው ውጪ ክፉኛ ተቆጥቶአል፤ አገዛዙ ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስበት ቁመና ላይ አይደለም፤ ሌላው ቀርቶ የመጨፍለቂያ አቅሙም ፍርሃትን በሰበሩ ጀግኖች ዝሎአል፡፡ ሆኖም ይህ አይነቱ በድን፤ ግን ጨርሶ ያልሞተ ሥርአት ሀገር የማፍረስ አቅሙ ግዙፍ ነውና በጣም ያሳስበኛል፡፡ ስለሆነም ሃላፊነት የሚሰማቸው እና የሕዝብ አመኔታ ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፣ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶችን… ያሰባሰበ ‹‹የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› ተመስርቶ ሳይውል ሳያድር ሥልጣኑን መረከብ አለበት፡፡ ይሄ ሃሳብ በ1983 ወያኔ ወደ አዲስ አበባ ሲንደረደር አዛውንቱ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም አቅርበውት ከነበረው ‹‹የሽማግሌ መንግሥት›› ጋር ይመሳሰላል፡፡ ፕሮፍ ለነፃነት ታግለናል ብላችሁ እንደተንደረደራችሁ ስልጣን መያዝ አግባብ አይደለም፡፡ የሽማግሌ መንግስት ይቋቋም ሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ፓርቲ ተወዳድሮ ተአማኝና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ስልጣን ለሚይዝ አካል ይስጥ ብለው ነበር፡፡ መለስ ዜናዊና ጠመንጃ ነካሽ ጓደኞቹ ግን የታገሉት ለግል ስልጣን ስለነበር መንግስታዊ ኃላፊነቱን ይዘው ባለፉት 26 አመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ አደቀቁ፤ ህዝባችንን በሀይማኖትና በብሔር ከፋፍለው እነሆ እንዳንተማመን አደረጉ፡፡
የሆኖ ሆኖ የፕሮፌሰር ሀሳብ ዛሬ ከመቼም ጊዜ በላይ ወሳኝነት አለው፡፡ ለወያኔ መሪዎች ማምለጫ በር የሚሰጣቸው ይሄ ሀሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ተስማምተው ያላንዳች አሻጥር ሥልጣኑን ጠቅልለው ማስረከብ ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ ኮሚቴውም ሥልጣኑን በተረከበ በስድስት ወር ውስጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሳትፍ ምርጫ ሊያካሂድ ይችላል፡፡ ይሄ ጉዳይ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግን ጨምሮ ለሁሉም ፓርቲዎች ምቹ መወዳደሪያ መድረክ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይሄ ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛ ሀገር እንዳይፈርስ ያደርጋል፤ ሁለተኛው ለራሳቸው ለወያኔ መሪዎች ይጠቅማል፡፡ ከዚህ ባለፈ እንዲያው በጉሽ ጠላ እየተገፉ ስልጣን ለቅቄያለሁ የሚሉት ቀልድ ቦታ የለውም፡፡ ምክንያቱም በዚህ የስቃይ ምድር ብዙ ሰው ተገድሏል፤ ተሰዷል፤ የሀብት ዘረፋ ተካሂዷል፤ ሀገር ፈርሷል፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ ተጠያቂ ናቸው፡፡ እናም እጅ ወደ ላይ ከመባላቸው በፊት በዚህ መንገድ ሀገሪቱን ቢያድኑ ምንም እንኳ ምህረት የማድረጉ ውሳኔው የህዝብ ቢሆንም በተወሰነ መንገድ የሚድኑበት ዕድል አይጠፋም ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህች ሀገር ችግር ዙሪያ ሥልጣን የለቀቁትም አሁንም በስልጣን ላይ ያሉትም እኩል ተጠያቂ ናቸው፡፡ በተለይ እነ በረከት ስምኦንና አባይ ፀሀዬ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው፡፡ እንዲያው እንደዋዛ ሽንት ቤት ደርሶ እንደመመለስ ቀላል አድርገው ስልጣን ለቅቄያለሁ ማለታቸው ከሠይፍ አያድንም፡፡
ሸገር ታይምስ፡- የአቶ በረከትና የአቶ አባዱላ ገመዳን መውጣት እንዴት አየኸው?
ተመስገን፡- እርሱ ላይ ለመናገር ሁለት አይነት ጠርዞች አሉ፡፡ እነ አቶ በረከት ከ1983 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈፀሙ ቅጥ ያጡ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ ጥፋቶች…… እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ለተንሰራፋው ሙስና ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ሞተዋልኮ! ያን ሁሉ ጥፋት ሲፈፅሙ ቆይተው ድንገት ተነስተው ስልጣን ለቅቄያለሁ ብለው ከህዝብ ጋር ተቀላቅለው ማኪያቶ መጠጣት የሚችሉበት ቦታ አለ ማለት ይቸግረኛል፡፡ ይሄ የብዙ ሰዎች ሀሳብ ነው፤ የገደሉትን ገድለዋል የዘረፉትን ዘርፈዋል በዚህ መንገድ ሌሎች ይከተሉና ይቅር እንበላቸው የሚሉ ወገኖች እየተነሱ ነው፡፡ በኔ እምነት ሁለቱም ሊታይ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት በአጭር ጊዜ ውስጥ የመፍትሔ አፈላላጊ የሚባል መዋቅር ተፈጥሮ በሞግዚትነት ስልጣን መያዝ አለበት፡፡ የእነሱም ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኘው በቡድን ተደራጅተው ያለማንገራገር ሲያስረከረቡን ብቻ ነው፡፡
ሸገር ታይምስ፡- የሀገሪቱ ዕጣ ፋንታ ምን ይመስላል?
ተመስገን፡- ተናገርኩኮ፤ አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡ መተማመን ጠፍቷል፤ በዘር ተከፋፍለናል፤ ከብዙ ጥፋቶች ለመዳን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በሀገር ወዳድ፣ ፈቃደኝነቱም ድፍረቱም ባላቸው ኢትዮጵያውያን ተነሳሽነት በፍጥነት ሊቋቋም ይገባል፡፡ በኮሚቴም ውስጥ መንግስት እንደሚቀልድበት የሽማግሌ ቡድን (እነ ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ) ቀልድ ሳይሆን፣ እንደ ሲቪክ ማህበራት፣ ተለጣፊ ድርጅቶች ሳይሆን ሁሉም የሚያምናቸው፤ ሊመሩን ይችላሉ የሚባሉ ታማኝ ሰዎች ከሁሉም ብሔር ብሄረሰቦች የተወጣጡ አባላት ኖረው ሀገሪቱን ከወያኔ መዳፍ ካልተቀበሉ በቀር ከባድ አደጋ ላይ ነን፡፡ ውጤቱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን 26 አመት ሲረግጡን ለነበሩ ሰዎችም ዘግናኝ ሞት ነው፡፡
ሸገር ታይምስ፡-ከእስር ቤት ከወጣህ በኋላ በፖለቲካ ጉዳዮች ለሸገር ታይምስ የሰጠኸው ቃል ምልልስ ለመጀመሪያ ጊዜ ነውና ነፃነቱን እንዴት አገኘኸው?
ተመስገን፡-ነፃነት አለው ማለት ይቸግራል፤ ምክንያቱም በተፈታሁ በሳምንቱ ማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ከሶስት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ ስልኬ ሲከፍት ከሁሉ ቀድመው የደወሉት የመንግሥት ሰዎች ናቸው፡፡ ስለቀድሞ ፋክት መፅሄት ግብር ልናናግርዎ ነው የደወልነው አሉኝ፡፡ ይሄ የመጀመሪያው የማስፈራሪያ መልዕክት ይመስለኛል፡፡ እናም በነፃነት እየተንቀሳቀስኩ ነኝ ማለት አልችልም፡፡ አንተም ሃገሪቱም ነፃ አይደላችሁም፤ እንኳን እኔ ጨካኝ አምባገነኖች ስልጣን ለመልቀቅ ነፃ አይደሉም፡፡ ልዩነቱ ምንድነው? እኔ ነፃነቴን ከማንም አልፈልግም፤ ለነፃነቴ የሚያስፈልገውን ዋጋ እከፍላለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ተመልሼ መታሰር ካለብኝም እታሰራለሁ፤ መሰቀል ካለብኝ እሰቀላለሁ፡፡ ነፃነቴን ለማንም አልሰጥም! ይቺ መከረኛ ሀገር የእኔም ነች፡፡ ነፃነቱ ከዚህ አኳያ ነው መታየት ያለበት፡፡
ሸገር ታየምስ፡- አመሰግናለሁ፡፡
ተመስገን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምንጭ:- ታሪኩ ደሳለኝ Tariku Desalegn

 

Filed in: Amharic