>
2:46 am - Tuesday January 31, 2023

ማንም ኢትዮጵያን ሊነሳህም ሊመፀውትህም አይችልም!! (ሳምሶን ጌታቸው)

ከኢትዮጵያዊነት በተቃራኒው ለመጓዝ መሞከር ኢተፈጥሮአዊ ነውና ከተራራ ላይ ለመዝለል እንደመሞከር፣ በባሕር ላይ ለመራመድ እንደመጣር ሕይወትን ከመገበር ሌላ አይሳካም፡፡ ጥላቻ እና ጎሰኝነት የአቅመ ቢሶች ፖለቲካ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጠነከረች፣ ሠላም ከሆነች፣ ሕዝቧ የአንድነት ስሜቱ ስለሚበረታ፤ ገዢዎች የዕውቀት ልምሻ አለባቸውና ተሸክመዋት ሊቆሙ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ነው ኢትዮጵያን ከጥንካሬያቸውና ከብርታታቸው በላይ እንዳትሆንባቸው፤ በእነሱ ልፍስፍስ አቅም ልክ በጎሣ ከፋፍለው የሚያውኳት፡፡ ለዚህ ነው ከእነሱ ልፍስፍስ ዕውቀት በላይ ያወቀ ትውልድ እንዳይፈጠር የትምህርት ሥርዓቱን የሚያሽመደምዱት፡፡ ለዚህ ነው በየአስተዳደር መዋቅሩ የበታቾቻው በሙሉ እንዳይገዳደሯቸው፣ ደረጃውን ያልጠበቀ ትምህርት በተማሩ ሰዎች የሚሞሉት፡፡ በዕውቀት መወዳደር ስለማይችሉ ነው የመሃይም መሣሪያቸው በሆነው ጎሰኝነት በጭካኔ ሴራቸው በሀገር ላይ የሚቀልዱት፡፡ ግን ይሄ ሁሉ እየሆነም ለኢትዮጵያ እና ሕዝቧ መዳኛው አንድ ነው፡፡ በወጀቡ የምትንገላታዋን ሀገር ለመታደግና ለማሸነፍ አብሮ በሕብረት መሰለፍ፡፡ 

ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሮአዊ ነው

ከተፈጥሮአዊ አካኼድ በተቃራኒ የሚደረግ እንቅስቃሴ በሙሉ መጨረሻው ውድመትና ጥፋት ብቻ ነው፡፡ ከስበት ሕግ ውጭ ለመዝለል እንደመሞከር መሰባበርና መድቀቅ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግሎባላይዜሽን ዓለም እየተጓዘችበት የምትገኝበት “ተፈጥሮአዊ” አቅጣጫ ነው፡፡ ክልላዊ ብሔርተኝነት (ጎሰኝነት) ደግሞ በላንቁሶ አቅሙ ከግዙፏ ዓለም በተቃራኒ አቅጣጫ ለመጓዝ እምቡር እምቡር የሚል የመንደር ወጠጤ ነው፡፡ ዓለም እንደ ቀልድ ነው ደፍጣጣ የምታልፈው፡፡ ለዚህ ነው ከተፈጥሮ ጋር ሳይላተሙ ፊትን አዙሮ በትክክለኛው አቅጣጫ መገስገስ መጀመር የሚያስፈልገው፡፡ እናም እውነታው ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ውዴታ ብቻ አይደለችም፡፡ ግዴታችንም ጭምር ነች፡፡ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ ተጓደለ ብለህ በኢትዮጵያዊነትህ ላይ ጥያቄ አታንሳ፣ አትደራደር፡፡ ይሄ መልፈስፈስ፣ መሸነፍ ነው፡፡ የአያት አባቶችህን ወንድነት አታራክስ፡፡ የተጓደለብህን በውድም በግድም ለማስከበር ተፋለም፡፡ ማንም ኢትዮጵያን ሊነሳህም ሊመፀውትህም አይችልም!!

የሰው ዘር በአባቱ አይወሰንም

ኦኬ… በትምህርታችን መሠረት ጥያቄ  =D
ማነው አማራ? ማንስ ነው ኦሮሞ?…

•በአባቱ ኦሮሞ በእናቱ አማራ?
•በእናቱ አማራ በአባቱ ኦሮሞ?
•ከኦሮሞ ቤተሰቦች አማራ “ክልል” ተወልዶ ኦሮምኛ ሳይችል ያደገ?
•ከአማራ ወላጆች የተገኘ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል ተወልዶ ኦሮምኛ አቀላጥፎ የሚናገር?

በእናቱም ብቻ አይደነገግም፡፡ የሰው ዘር በአባት ይወሰናል የተባለው እንደስም መጠሪያ ለአሰራር እንዲያመች ተብሎ እንጂ ተፈጥሮአዊ እውነታ የለውም፡፡ ምሳሌ፦ በቅሎ በአባቷ አህያ፣ በእናቷ ፈረስ ናት፡፡ በቅሎ፣ በቅሎ ናት እንጂ አህያ ወይም ፈረስ አይደለችም፡፡ ወይም ደግሞ በአንዴ ሁለቱንም ናት ማለት ይቻል ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic