>
6:53 pm - Sunday July 3, 2022

ሁለቱ መፈንቅለ መግስቶች (ዮናስ ሃጎስ)

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስቱን የጠበቀ ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ በተካሄደ በሶስተኛው ቀን ዚምቧቤ ደግሞ ህገ መንግስት የማያውቀው ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ ተካሂዶባታል እየተባለ ነው። ሁለቱን መፈንቅለ መግስቶች በንፅፅር እንመልከታቸው እስቲ…
***
Zimbabwe
የሙጋቤ ጣጣ የጀመረው ዛሬ አይደለም። ሙጋቤ ከስልጣን እንዲወርድ በተደጋጋሚ በብዙ አካላት ተጠይቋል። ፓርላማው፣ ሕዝቡ፣ ወታደራዊው ክንፍ እና በመጨረሻም የራሱ ፓርቲ ዛኑ ጠይቆት እንቢ ብሏል። ጭራሽ በመጨረሻው ሰዓት ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን በማባረር ሚስቱን የስልጣኑ አልጋ ወራሽ ለማድረግ ሞክሯል። ባለቤቱም ሙጋቤ ቢሞት እንኳን ሬሳው ለምርጫ ውድድር እንደሚቀርብ በመናገር የነበረውን ጭላንጭል ተስፋ ድርግም ካደረጉት በኋላ ነው ነገሮች ሌላ መስክ የያዙት።
***
ማክሰኞ ዕለት በሁሉም የሙጋቤ እንቅስቃሴ ተስፋ የቆረጠው ወታደራዊ ክንፍ የሙጋቤን እንቅስቃሴ በማውገዝ ገዢው ፓርቲ አፋጣኝ እርምጃ የማይወስድ ከሆነ… የሚል ዛቻ ሲያቀርብ በግሬስ ሙጋቤ እንዲተካ ተደርጎ በፍርኃት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሸሽቶ የነበረው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሚስተር ምናጋግዋ በፓርቲው ተተኪ ፕሬዝዳንት እንዲሆን ባስቸኳይ ከተሾመ በኋላ ወታደራዊው ክንፍ እና ራሱ የሙጋቤ ፓርቲ ተባብረው በዛሬው ዕለት ሙጋቤን ‹ለክብርዎት ወደተዘጋጀ ቦታ እንውሰድዎ› በሚል በቮልስ ዋገን (ሶሪ የኃይለስላሴ መፈንቅለ መግስት ትዝ ብሎኝ ነው) ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል።
***
የዛኑ ፓርቲ ቃለ አቀባይ በዚምቧቤ ውስጥ ደም ያልፈሰሰበት መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ያመነ ሲሆን ወታደራዊው ክንፍ ግን በሙጋቤ ዘመን በሙስና የበሰበሱ ባለስልጣናት በሙሉ የሙጋቤ እጣ ፈንታ እንደሚከተላቸው ማሳወቁ ትንሽ ውጥረትን ፈጥሯል። በዚህም ምክንያት በዚህች ባሁኗ ቅፅበት የዚምቧቤ ፖሊስ እረፍት ላይ የነበሩ አባላቶቹን በሙሉ ጠርቶ ወደ ጥበቃ እያሰማራ ሲሆን የዚምቧቤ ዋና ከተማ ሮዴሽያም በታንክና ብረት ለበስ ወታደራዊ ኃይል እንድትከበብ ተደርጓል።
***
መቼም ይህን ሁሉ ካነበባችሁ በኋላ ታድያ ይህን ከኢትዮጵያ ጋር ምን አገናኘው? ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት መች ተደረገ? እኛ የምናውቀው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ታናሽ ወንድም መታወጁን ብቻ ነው… ምናምን ካላችሁሰናንተ በጣም ዓዋቂ ሰዎች ስለሆናችሁ ከዚህ በታች የተፃፈውን ማንበብ አያስፈልጋችሁም። እስካሁንም ጊዜያችሁን ስላባከንኩኝ ይቅርታ እያልኩ ልሰናበታችሁ። የተቀራችሁት ተከተሉኝ።
***
Ethiopia
ሰኞ ዕለት ጠ/ሚ/ራችን ከመከላከያ ከፍተኛ አካላት ጋር በተሰየሙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ሐገሪቷ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሲባል ‹ሰላማዊ ሰልፍ ከመከልከል› ጀምሮ ብዙ መግለጫዎችን አሰምተዋል። ይህ ሁሉ ያወሩት ቅራቅንቦ ባንድ ዓረፍተ ነገር ሲጠቃለል ‹የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሐገሪቷን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ተረክቧል›
***
ከታች በ1994 የወጣው ስለ ብሔራዊ ምክር ቤት መቋቋም የወጣ አዋጅ በግልፅ እንደሚያሳየው የዚህ ምክር ቤት አባላት የፌደራሉ ‹አንዳንድ ሚንስትሮች› እና የጦር ሐይሎች አዛዦች ብቻ ናቸው። የፌደራሊዝም ስርዓቱ ልክ የመንግስት ያህል ስልጣን ሰጥቷቸው የነበሩት የክልል ፕሬዝዳንቶች ከነ ምክር ቤቶቻቸውና አስተዳደራቸው (የክልሉን ፖሊስ ጨምሮ) እዚህ ምክር ቤት ውስጥ የሉበትም። ፓርላማው (ምንም እንኳን 100% አሻንጉሊት ቢሆን ቅሉ) በተራ አባላት እንዲወከል እንኳን አልተደረገም። ባጠቃላይ ደም ምንም ያልፈሰሰበት ከፌደራሊዝም ስርዓት ባንዴ ወደ ኢሕአዴግ እጅግ በጣም ወደሚጠላው አሃዳዊ አስተዳደር የተመለስንበት መፈንቅለ መንግስት ቢባል ምንም አያንሰውም። ምክር ቤቱ በማናቸውም ‹የሐገሪቷን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ነገሮች ላይ› ተማክሮ እርምጃ ይወስዳል ይላል የተቋቋመበት ዓዋጅ።
***
እንግዲህ የሐገራችንን መፈንቅለ መንግስት ከዚምቧቤው ለየት የሚያደርገው እና ሐገር ከስልጣናቸው እንዲነሱ የተደረጉት አሻንጉሊቱ መሪያችን ሳይሆኑ የክልል ፕሬዝደንቶች ከነሙሉ ካቢኔያቸው መሆኑ ብቻ ነው። ባለፈው ሰሞን አቶ ለማ ኢሕአዴግን ባንድ ወቅት የሞግቱ የነበሩና እስከ እስርም ደርሰው የነበሩ ግለሰቦችን ወደ አስተዳደራቸው በመቀላቀላቸው እጅግ የተከፋ አካል እንዳለ የሚያሳይ እርምጃ ብለነዋል።
Filed in: Amharic