>
6:24 pm - Tuesday October 19, 2021

ማርጀቱንና መበስበሱን ያለሃፍረት የነገረን ሕወሃት ሞቱን እስኪያረዳን አንጠብቅም!!!

ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ

ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያን በብረት መዳፍ ውስጥ አስገብቷት የነበረው ሕወሐት ማርጀቱንና መበስበሱን ሰሞንኑን መቀሌ ሲያደካሂደው በቆዬውና ባልቋጨው ስብሰባ ባቋራጭ በሰጠው መግለጫ አሳውቆናል፡፡ ለእርጅናዬ ምክንያት ናቸው ብሎ የገለፃቸው ነጥቦች ማለትም በሕወሃት ውስጥ የፀረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ መስፈን፣ በቡድን ተከፋፍሎ የአጥቂነትና የተከላካይነት ሽኩቻ መኖር፣ ከሌሎች እህት ድርጅቶቹ ጋር የነበረው ግንኙነት አሉታዊ የነበረ መሆኑና በዚህም ምክንያት ጠባብነትና የትምክህት አመለካከት መስፋፋታቸውን፣ ድርጅቱ ተተኪ አመራርን አለማፍራቱና ወጣትና ምሁራንን ማሰለፍ አለመቻሉ፣ በአጠቃላይም በተጠናወተው በትንሽ ነገር የመርካት አመለካከት ምክንያት ስትራቴጅካዊ አመራር መስጠት አለመቻሉንና በሐገሪቱ ያለውን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች በቂ መልስ መስጠት አለመቻል የድርጅቱ ትልልቅ ችግሮች ናቸው ብሎ ገልጧል፡፡

ይህ መግለጫው ሕወሃት አሁንም ከማርጀቱ የተነሳ አዲስ ሃሳብ ማቅረብ እንዳልቻለና ያለበትንም ደረጃ በመሰረታዊ ሃሳብ ለመረዳት የሚያስችል ቁመና እንደሌለው በግልፅ አሳይቷል፡፡ ሕወሃት ከላይ ችግሮቼ ናቸው ብሎ የዘረዘራቸው ነጥቦች የችግሩ ማሳያ ምልክቶች እንጅ በራሳቸው ችግሮች አይደሉም፡፡ በሌላ አነጋገር የበሽታ ምልክቶችን እንደ ዋና በሽታ መውሰድ ማለት ነው፡፡ የሕወሃት ችግር በስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ስንመረምረው ሕወሃት ይከተላቸው የነበሩ መንትያ የአገዛዝ ስልቶች ማርጀትና መዳከም ምክንያት ተቀባይነት በማጣታቸው የተፈጠረ የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡ ሕወሃት ደረስኩባቸው የሚላቸው ችግሮችን ብናያቸው ከተፈጥሮ ባህሪው ጋር አብረው የነበሩና እስከ ዕለተ ቀብሩም አብረው የሚኖሩ እንጅ አዲስ ግኝቶች አይደሉም፡፡ በሕወሃት ውስጥ የፀረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ሰፍኗል ሲል ቀደም ብሎ ዲሞክራት የነበረ ድርጅት ቀስ በቀስ የፀረ ዲሞከክራሲ አስተሳሰብ እያደገ እንደመጣ ለመግለፅ የተነገረ ይመስላል፡፡ በመሰረቱ ሕወሃት በአፈጣጠሩ ፀረ ዲሞክራሲ ዘረኛ ድርጅት ነው፡፡ ዲሞክራሲ ማለት በብዙሃን አመለካከት መገዛትና የአናሳዎችን መብት የማክበር የአስተዳደር መርህ ነው፡፡ ሕወሃት ግን በአናሳ ውክልና ተፈጥሮ ብዙሃንን ረግጦ የሚገዛ የአናሳ አገዛዝ ስርዓት ነው፡፡ ስለሆነም ሕወሃት ሲፈጠርም ከዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በተቃራኒ የተፈጠረ ነው፤ ወደፊትም ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ባሕሪው አይፈቅድለትም፡፡ በተጨማሪም በጎሳ አስተዳደር ዘዴ ውስጥ አናሳዎች ብዙሃኑን ረግጠው ሲገዙ በሚፈጠረው “የእኛና እነሱ” አመለካከት ጋር ተያይዞ ጠባብነትና ትምክህት መኖር የማይቀር ከጎሳ ድርጅቶች የተፈጥሮ ባህሪይ ጋር ያለና እስከ ዕለተ መቃብራቸው አብሮ የሚኖር ነው፡፡
በአጠቃላይ ሕወሃት በመቀሌው ስብሰባ ችግሩን መገንዘብ አቅቶት በአዙሪት ውስጥ ሲዳክር ተስተውሏል፡፡ የሕወሃት ችግር ሲከተላቸው የነበሩ ከሁለት የአገዛዙ አስተሳሰቦች ማርጀትና ተቀባይነት ማጣት የመነጨ ነው፡፡ እነዚህም፡- 1ኛ ሕወሃት ራሱን ነፃ አውጭ አድርጎ በአሸናፊትና በነፃ አውጭነት አመለካከት የበላይ ሆኖ ሌሎችን ከዚህ አስተሳሰብ ተጠቃሚ አድርጎ በማሳየትና በበታችነት ከስሩ አሰልፎ ሲገዛበት የነበረው ስልት በበታችነት ሲገዙ የነበሩ ካድሬዎችና አስፈፃሚዎች በአጠቃላይ ለሕወሃት ርዕዮት ከመገዛት ይልቅ የየራሳቸውን ጥቅም እያሳደዱና በሙስና እየተዘፈቁ ከመምጣታቸው በተጨማሪ ወትሮም ቢሆን ያለእውቀትና ችሎታ በዘራቸው ወይም በአድርባነታቸው ብቻ በቢሮክራሲው የተሰገሰጉ ካድሬዎች በሕዝብ ስም የተሰጣቸውን ሥራና አደራ የመወጣት አቅም ማጣት ነው፡፡ 2ኛ፡-ሕወሃት የሕዝብን አንድነትና ጠያቂነት ለማዳከም በሕገ መንግስት ስም ኢትዮጵያን በጎሳ አስተዳደር ዘልዝሎና ከፋፍሎ በኃይል ጨፍልቆ የሚገዛበት ስልት በሕገ መንግስቱ የተሰጠን ስልጣን አልተከበረም በማለት ራሳቸውን ለስልጣንና ለአቋራጭ ጥቅም ያዘጋጁ የጎሳ ፖለቲካ ኃይሎች በሚያነሷቸው የተጋፊነት ጥያቄዎች መብዛት ነው፡፡
የሕወሃትን የነፃ አውጭነትና የበላይነት አመለካከት የማይሸከም ትውልድ በመፈጠሩና በሕዌሃት የአናሳ የቁጥጥር አመለካከት ውስጥ በሕገ መንግስቱ የተፈቀደውን የሌሎችን የጎሳ ድርጅቶች መብት ተፈቀዱ የተባሉትን መብቶች ሊያከብር ስለማይችል አሁን ባለንበት ጊዜ የሕወሃት በነፃ አውጭነት የበላይነትና በጎሳ ከፋፍለህ ግዛው ስልት ስልጣንን የማራዘም ዘዴ ጊዜ ያለፈበትና ቀን የጨለመበት በመሆኑ የሕወሃት የተፈጥሮ ሞት አይቀሬ ነው፡፡
ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን የሕወሃትን ሞት በማፋጠንና በኢትዮጵያ የሃሳብ ፖለቲካ አብቦ ዜጎች በሰብዓዊና በዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ላይ ተመስርተው ሕዝባዊ አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ትግል የጋራ እርብርብ እንድናደርግ ጥሪያችንን እያቀረብን ሕወሃት ማርጀቱንና መበስበሱን እስከነገረን ድረስ “የሞተ አካል” ሞቱን በራሱ ሊያስረዳ እንደማይችል ተገንዝበን ይህንን የበሰበሰ አገዛዝ ግብዓተ መሬቱ እንዲጠናቀቅና በምትኩ ጊዚያዊ ሁሉን አቀፍ የባለ አደራ አስተዳደር እንዲሰየም ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ህዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Filed in: Amharic