>
4:34 pm - Saturday October 17, 0240

ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ያስተላለፈው መልዕክት

አሠላሙ አለይኩም ወራህመቱሏሂ ወበረካትሁ!…
ውድና የተከበራችሁ ወገኖቼ መታመሜ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ህክምና አገኝ ዘንድ ድምፃችሁን ላሰማችሁ፣በዱአ (በፀሎት) በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ለምትገኙ ወገኖቼ በሙሉ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው።
መታመሜን ተከትሎ ከጎኔ በመቆሙ ሒደት ላይ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ውድ ወገኖቼ የኃይማኖት አጥር ሳይገድባችሁ በሰብአዊ ርህራሄ ድምፃችሁን በማሰማቱ ረገድ ያሳያችሁትን አጋርነት ሰምቼ እጅግ በጣም ተደስቻለሁ። ለተደረገው ነገር ሁሉ በአላህ ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ።
በአሁኑ ወቅት ያለው የጤናዬ ሁኔታም በኩላሊቴ ቱቦ የገባው ብረት ከሰውነቴ ጋር እየተላመደ በመምጣቱ መጠነኛ ለውጥ ስላለው ጥቂትም ቢሆን እፎይታ ሰጥቶኛል። ነገር ግን በቀጣይ ከፍተኛ የህክምና ክትትል እንደሚያስፈልገው ተነግሮኛል። በአላህ ፈቃድ የጤናዬ ሁኔታ እንዲስተካከል ሁላችሁም ዱዐ (ፀሎታችሁ) እንዳይለኝ ስል እጠይቃለሁ።
በጤናዬ ጉዳይ ይህንን ካልኩ፣ ይኸው የእኔ መታመምና ቀጣይ ጤናዬ ሁኔታ አሳስቧቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ለህክምና የሚውል ገንዘብ የሰበሰቡ ወገኖች እንዳሉ ተረድቻለሁ። በዚህም በናንተ በወገኖቼ አርቆ አሳቢነትና ተቆርቋሪነት ልቤ ተነክቷል። በድጋሚ አመሰግናለሁ።

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ለእኔ ህክምና ምንም ገንዘብ የሚያስፈልግ ባለመሆኑ እስካሁን የተሰበሰበውና ወደፊትም የሚሰበሰበው ገንዘብ በሙስሊም ትግል ታስረው በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣ በሸዋሮቢትና በዝዋይ ማረሚያ ቤቶች ላሉ ታሳሪዎች እንዲከፋፈልልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

ሁሉም ማህበረሰብ ከነዚህ ታሳሪዎች ጎን በመቆም ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም እላለሁ። ይህንን እንዲያደርጉ ለተወሰኑ ወንድሞች በቤተሰቤ በኩል መልዕክቴ እንዲደርሳቸው ሃላፊነት አስተላልፌያለሁ።
በድጋሚ ከጎኔ በመቆም አጋርነት ላሳያችሁኝ ውድ ወገኖቼ ላደረጋችሁት ሁሉ አመሰግናለሁ።

አህመዲን ጀበል ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት

ምንጭ:- Selman Ahmed

Filed in: Amharic