>
4:34 pm - Wednesday October 17, 0621

እንከን የበዛባቸው የኢትዮጵያ የፖሊስ ተቋማት አወቃቀር እና መዘዛቸው፤ (በውብሸት ሙላት)

 

የፖሊስ ሥልጣንና አወቃቀር፣የፌደራልና የክልሎችና የፌደራል የፖሊስ ኃይል የማቋቋም ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን፣ የፖሊስ ኃይሎቹ ሥያሜና የመሳሰሉት ጉዳዮች ለሚዲያች መሆን ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የፖሊስ ተቋማቱ ካሉባቸው መዋቅራዊ ችግሮች በመነሳት የሰብኣዊ አያያዝና ሕገ መንግሥቱ ላይ ያላቸውን አንድምታ በአጭሩ እንቃኛለን፡፡

ወንጀል መከላከል የሌላ ወንጀል ምርመራ የሌላ፤

የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ወንጀልን ከመከላከል ሊጀምር እንደሚችል መከራከር ይችል ይሆናል፡፡ ይሁንና የፍትሕ ሥርዓቱ ሞተር መሽከርከር የሚጀምረው ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ስለሆነ መከላከል የሥርዓቱ አካል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም፣ስለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሲነሳ ትርጉም የሚሰጠው አንድ የወንጀል ድርጊት እንደተፈጸመ መረጃ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ሒደት ነው፡፡

አገራት ወንጀል መከላከልን በተመለከተ ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስጠት የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ወንጀል ምርመራን ደግሞ ለፍትሕ ሚኒስቴር፡፡ ለአብነት የአሜሪካን ብንወስድ ወንጀል መከላከል ኃለፊነቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ (Department of Homeland Security) ነው፡፡ ወንጀልን ለመከላከል የሚቀጠሩ ፖሊሶች ተጠሪነታቸው ለዚሁ መሥሪያ ቤት ነው፡፡
ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ምርመራ የማከናውን ደግሞ ኃላፊነቱ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ነው፡፡ የዚህ ቢሮ ተጠሪነት ደግሞ ለፍትሕ ሚኒስቴር ነው፡፡

ለወንጀል መከላከልና ምርመራ የሚያስፈልገው ዕውቀትም ሥልጠናም የተለያየ ነው፡፡ ትምህርቱም ሆነ ቴክኖሊጂው እንዲሁ ይለያያል፡፡ በተለይ ለወንጀል ምርመራ የሚሠለጥኑ ሰዎች የወንጀል አደራረጉንና ረቂቅነቱን ከፈጻሚዎቹ በበለጠ ሊረዱ ይገባል፡፡ የኮምፒውተር ወንጀል ቢፈጸም መርማሪ ፖሊሱ ጥልቅ የኮምፒተር ዕውቀት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ የቴሌኮም ወንጀል ቢፈጸምም መርማሪው እንዲሁ ጥልቅ የቴሌኮም ዕውቅት ከሌለው ምርመራውን በአግባቡ ማከናውን የመቻሉ ጉዳይ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ከዚህ አንጻር ለመርማሪ ፖሊስነት የሚመለመሉ ዕጩዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡

በፌደራል ኢትዮጵያ ክልሎቹም ይሁኑ ማእከላዊው መንግሥታት የወንጀል መከላከልም ሆነ ምርመራ ተቋማት የሚመሩት በአንድ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ የክልሎቹም በክልል ፖሊስ ኮሚሽን የፌደራሉም እንዲሁ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፡፡ መርማሪ የሚሆኑት ፖሊሶችን በተለያዩ ጊዜያት የምርመራ ሳይንስና ጥበብ ቢማሩም፣የሚመረመረውን ጉዳይ (ለምሳሌ፡- ፋይናንስ፣ኮምፒውተር፣ቴሌኮም፣ሕክምና…ወዘተ) ዕውቀት ሳይኖራቸው ብቁና የተዋጣላቸው መርማሪዎች የመሆናቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡

የወንጀል መከላከልና ምርመራውነ በአንድ መሥሪያ ቤት ሥር ማዋቀር ከዚህም የከፋ ችግር አለው፡፡ በወንጀል መከላከል ጊዜም ሆነ ተጠርጣሪን ለመያዝ በሚደረግ ጥረት ፖሊስ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሊፈጽም ይችላል፡፡ አንድ ወረዳ ላይ ፖሊስ ለሚፈጽመው የወንጀል መተላለፍ ምርራውን እንዲያከናውን የሚጠበቀው እዚያው ወረዳ ላይ ያለው ፖሊስ ነው፡፡ አንድ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችን አንዱን አንዱ እንዲመረምር የሚደርግ ተቋማዊ አወቃቀር ውጤታማቱም ፍትሐዋነቱም ጥያቄ ውስጥ የገባ ነው፡፡

በተለይ በክልሎች የተቋቋሙትን በተለምዶ አድማ በታኝ ወይም ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉት የፖሊስ አካላትን ሌላው መደበኛ ፖሊስ የመመርመር ብዙም ድፈረት ሲኖራቸው አይስተዋልም፡፡ የወንጀል ምርማራውና መከላከሉ በተለያዩ ተቋማት ቢመሩ አንዱ አንዱ የማሳጣት፣የማጋለጥ፣የመመርመር ድፍረትም ሥልጣንም ይኖራቸው ነበር፡፡ እናም፣በአገሪቱ ያለው የፖሊስ አወቃቀር ከዚህም አንጻር አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ምልመላ ነገር፤

የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ ነው፡፡ አደረጃጀቱን፣ አሰራሩን፣ ሥልጣናን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን የስታንዳርዳይዜሽኖችን አቅጣጫዎችን የሚወሰነው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡

የከተማው መስተዳድር በጀትና ዕቅድ ማጽደቅ፣የዕለት ተግባር ስምሪትን ይከታተላል፡፡ የከተማ መስተዳድሩን ተቋማትና እና ባለሥልጣን ይጠብቃል፡፡ የከተማውን ጥቅም ያስጠብቃል፡፡ ኮሚሽነሩን ከንቲባው አይሾምም፡፡ ከኮሚሽኑ በታች የሚሾሙት ላይ ከኮሚሽነሩ ጋር ይመካከራል፡፡ በጀቱ በከተማ መስተዳድሩ ይሸፈናል፡፡ ሕግ የሚያወጣለትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ኮሚሽነሩ እና ምክትሉም በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር በኩል ይሾማል፡፡

እነዚህ ከላይ የተገለጹት ሕገመንግሥታዊ መሆን አለመሆናቸው እንደተጠበቁ ለአዲስ አበባ የፖሊስ ቅጥር ማስታወቂያ የሚወጣውና ምልመላውም የሚከናወነው ከየክልሎቹ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ለመቅጠር የመዝገባ ቦታው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአራት ክልሎችም ይከናወናል፡፡ ኦሮሚያ፣አማራ፣ትራይና ደቡብ ክልሎች፡፡ እዚህ ላይ የሚከተሉትን ጥያቄዎች (ሕገ መንግሥታዊ) ያስነሳል፡፡

የከተማው ኗሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን እያለው፣በጀቱንም ከተማ መስተዳድሩ የመሸፈን ግዴታ እንዳለበት እየታወቀ፣ ራሱን ለሚጠብቀው ፖሊስ ስለምን ከሌላ ክልል ይቀጠራል? ሕገ መንግሥታዊውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጥስ አይደለም ወይ? የከተማውን ወጣት የሥራ ዕድልስ ማጣበብ አይደለም ወይ?

ከአዲስ አበባ ኗሪ ለፖሊስነት የሚመለመል ሰው ሳይጠፋ እንዲሁም በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከአራት ክልሎች ብቻ ለምን ምልመላ ይደረጋል? ሌሎቹን ክልሎች ከምዝገባ ውጭ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ነውን? ራስን በራስ ማስተዳደር በፖሊስም ጭምር መጠበቅን ይመለከታል፡፡

የፌደራልም በፌደራል የክልልም በክልል፤

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስሩ ወጥ የሆነ የፖሊስ አሠራር ለማስፈን በፌደራል ደረጃ ሕግ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ይሄንን ንግግር መነሻ የሆነው በየክልሎቹ የተቋቋሙት የተለያዩ ስያሜ ያላቸው የፖሊስ አደራጃጀቶች ይመስላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ እሳቸው የተናገሩትን የሚደግፍ አይመስልም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት፣ የፌደራሉን እና የክልሎችን ሥልጣን በሚዘረዝሩት አንቀጾች 51(6) እና 52(2)(ሰ) ላይ እንደተገለጸው ሁለቱም መንግሥታት የየራሳቸውን የፖሊስ ተቋሟት እንደሚያቋቁሙ ይገልጻል፡፡ ሁሉም የክልል ሕግጋተ-መንግሥታትም ይሄንኑ ሥልጣናቸውን በድጋሜ አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም በክልሎች ውስጥ ስላሉ የሕግ እና ሥርዓት ማስከበር፣ የሕዝብ ደህንነት እና ሠላምን ማስጠበቅ የየራሳቸው ተግባር ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ሥራ ለማስጠበቅ የተለያዩ ስያሜ ያላቸውን የፖሊስ ኃይል ቢያቋቁሙ ከልካይ የለባቸውም፡፡

ዘጠኙ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በግዛታቸው ውስጥ የሚገኙ ፖሊሳዊ ተግባራት የሚያከናውኑ የፖሊስ ኃይል ካለቸው፣ የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልል ለመግባት አይችልምም፡፡

ፖሊስ፣ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት መከላከል እና ከተፈጸመ ደግሞ ምርመራ የማከናወን ሁለት ዐቢይ ተልእኮዎች አሉት፡፡ የፌደራል ፖሊስ፣ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የወንጀል ድርጊቶችን የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡ እነዚህ ወንጀሎች የተፈጸሙበት ቦታ በክልሎች ውስጥ ቢሆን እንኳን ለክልል ፖሊስ በውክልና እስካልሰጠ ድረስ የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡

የመከላከል ሥራ ግን በቀዳሚነት የክልሎች ድርሻ ቢሆንም የተወሰኑ የወንጀልን፣ ለአብነት እንደ ሳይበር ጥቃት፣ፋይናንስ ነክ ወንጀሎችን ደግሞ የመከላከልም ሸክም የፌደራል ፖሊስ ነው፡፡ ቀድሞ በነበሩትም ይሁን አሁን በሥራ ላይ ባለው የፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ክልሎች ውስጥ በራሱ ማለትም ውክልና ሳይሰጥ ለሚያካናውናቸው የወንጀል ምርመራ ሥራ የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ግንኙነት በመፍጠር አሳውቆ መሆን መቻል አለበት፡፡

በመሆኑም፣ የፌደራል መንግሥት ወጥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት ቢያስብ እንኳን በሕግ ለፌደራል መንግሥት የተሰጡትን ወንጀል የመመርመርና እንዲሁም ፌደራል መንግሥቱን የሚመለከቱ የወንጀል መከላከል ጉዳዮችን ብቻ እንጂ የክልሎችን ሊሆን አይችልም፡፡ የክልል ሕግጋተ መንግሥታትም ክልሎች የራሳቸውን ፖሊስ እንዲያቋቁሙ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡

ወጥነት የጎደለው የፖሊስ አወቃቀር፤

ፌደራላዊም ይሁኑ አሃዳዊ አወቃቀር የሚከተሉ አገራት በአንድ እዝ ሥር ያለ ፖሊስ ወይንም ደግሞ በተለያዩ እዞች ሥር የሚገኙ የተለያዩ የፖሊስ ተቋማት አሏቸው፡፡ በርካታ የፖሊስ ተቋማት ያሏቸው፣ በጥምረት እና በቅንጅት የሚሠሩበት መጠን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የእያንዳንዱ ፖሊስ ተቋማትም ተግባር እና ኃላፊነት ግልጽ ድንበር ከመኖር አንጻር የተለያዩ አሠራሮች አሏቸው፡፡የፖሊስ ተቋማት ብዛት እና የዳበረ ቅንጅታዊ አሠራር መኖር ወይንም አለመኖር፣ ከግለሰብ መብት መከበር፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከተጠያቂነት ጋር ግንኙነት አለው፡፡

የኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ የክልሎች እና የፌደራል ፖሊስ አሉ፡፡ የክልሎች ደግሞ መደበኛ እና ልዩ ኃይል አላቸው፡፡ የአካባቢ ፖሊስም (ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) አለ፡፡ በፌደራልም፣ ከልዩ ኃይሉ በተጨማሪ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ፖሊስ አለ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የገቢዎችና ጉምሩ፣የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር እና ሌሎችም የፖሊስ አደረጃጀቶች ነበሩ፡፡ ሌላው ደግሞ የክልሎች እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ፖሊሶች አሉ፡፡

ይህ ሁሉ የፖሊስ ዓይነት የየራሱ ተጽእኖ አለው፡፡ ከተጽእኖቹ ውስጥ አንዱ ሰብኣዊ መብት አከባበርን የሚመለከት ነው፡፡ ለአብነት የሚከተለውን እንውሰድ፡፡ በተለይ ሕዝብ ሰልፍ በሚያደርግበት እና ተቃፌደራላዊም የአገር አስተዳደር አወቃቀር የሚከተሉ ሆነው በአንድ እዝ ሥር ያለ የፖሊስ ተቋማት ያላቸው አሉ፡፡ በርካታ የፖሊስ ተቋማት ያሏቸው፣ በጥምረት እና በቅንጅት የሚሠሩበት መጠን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የእያንዳንዱ ፖሊስ ተቋማትም ተግባር እና ኃላፊነት ግልጽ ድንበር ከመኖር አንጻር የተለያዩ አሠራሮች አሏቸው፡፡ የፖሊስ ተቋማት ብዛት እና የዳበረ ቅንጅታዊ አሠራር መኖር ወይንም አለመኖር፣ ከግለሰብ መብት መከበር፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከተጠያቂነት ጋር ግንኙነት አለው፡፡

ከእዚህ በተቃራኒው ደግሞ የፖሊስ ተቋማት መበራከት ለራሱ ለመንግሥትም ቢሆን አቀናጅቶ ከመምራት አንጻር ፈተና ሊሆንበት ይችላል፡፡ ለእዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በተከሠቱት ግጭቶች ውስጥ የተለያዩ ክልሎች ልዮ የፖሊስ ኃይሎች የነበራቸውን ተሳትፎ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ሁኔታ በመገንዘብ ይመስላል ወጥ የሆነ የፖሊስ አሠራር መኖር እንዳለበት በቅርቡ የተናገሩት፡፡

የፖሊስ አወቃቀር በፌደራል ሥርዓት፤

ቀድመው አሃዳዊ የአስተዳደር ዘይቤ ይከተሉ የነበሩ አገራት የፀጥታና የፖሊስ ተቋማት አወቃቀራቸው ወጥ ነው፡፡ ለየክልሎቹ የራሳቸውን የፖሊስና የሚሊሻ ኃይል ማቋቋምን ይከለክላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራርን አይፈቅዱም፡፡ ለነገሩ ክልሎችም የራሳቸው ሕገ መንግሥትም የላቸውም፡፡ ቀድመው ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊ አገራት የነበሩ እና ኋላ ላይ በፌዴሽን የተዋሃዱ ከሆኑ ግን የራሳቸውም ሕገ መንግሥትም የፀጥታ አካላት ስለሚኖራቸው የያዙትን ይዘው መቀጠል የተለመደ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግን ከላይ ከተገለጸው የአገራት ልምድ እና አካሄድ አኳያ በተቃራኒው የተጓዘ ነው፡፡ የክልሎች እና የፌደራል ፖሊስ አሉ፡፡ የክልሎች ደግሞ መደበኛ እና ልዩ ኃይል አላቸው፡፡ የአካባቢ ፖሊስም አለ፡፡ በፌደራልም፣ ከልዩ ኃይሉ በተጨማሪ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ፖሊስ አለ፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር እና ሌሎችም የፖሊስ አደረጃጀቶች ነበሩ፡፡ ሌላው ደግሞ የክልሎች እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ፖሊሶች አሉ፡፡

በመሆኑም፣ ቅንጅት የጎደለው የእዝ ሰንሰለቱ የተዘበራረቀ እና የተለያዩ ትዕዛዝ ሰጪዎች መብዛት ፖሊስ የሚጠቀመውን ኃይል መመዘን ይቅር እና ተጎጂዎች አቤቱታም ሆነ ክስ የሚያቀርቡበትን እና ምርመራው የሚከናወንበትን ፖሊስ ማንነቱንም ይሁን ተጠሪነቱን ስለማያውቁት ደመ ከልብ ይሆናሉ፡፡ ፖሊስ አገልግሎት መሥጠት ያለበት ተወልዶ ባደገበት ወይንም በመኖሪያ አድራሻው አካባቢ መሆን አለበት፡፡ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ጭካኔ የተሞለበት ኃይል እንዳይጠቀምም ይረዳል፡፡
ይህንን እንደ ማሳያ የተነሳው ምንም ዓይነት ሌላ ንድፈ ሐሳብ ዋቢ ማድረግ ሳያስፈልግ የታሪካችን አካልም እንደ ነበር ነው፡፡ በተለይ የጭካኔ ተግባርን ለመቀነስ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲህ ዓይነቱን አሠራርን ማስፈን ተገቢ መሆኑን ጥናቶችም ያስረዳሉ፡፡

እናም…..

ፖሊሳዊ አሠራርን የሚያጎለብት፣ ባሕርይን የሚገራ ዝርዝር የሥነ ምግባር ደንብ እንዲኖር እና በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የፖሊስ ሕገ ወጥ ተግባር የሰብአዊ መብትን ከመጣሱም በተጨማሪ የመልካም አስተዳዳር እጦትንም ያስከትላል፡፡ ስለሆነም እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ሕግ እንዲኖር እና የሚቆጣጠሩ ተቋማት ማስፈን ተገቢ ነው፡፡

በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ ከተጣሉበት ኃለፊነቶች አንዱ ፖሊስና እና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት የሰብኣዊ መብት ሲጥሱ፣ ሕግን በጣሰ ሁኔታ የፌደራል ፖሊስ ክልሎች ውስጥ ሲገባ እና የመከላከያ ሠራዊቱ በአገር ውሥጥ የጸጥታ ጉዳይ ሲሰማራ ተገቢውን ማጣራት እና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

ከአወቃቀር አንጻርም ሲታይ የወንጀል መከላከልና ምርመራን በአንድ ተቋም ሥር ማድረግ እንዲሁ የሰብኣዊ መብትን ጥሰትን ለመቆጣጠርም ብቻ ሳይሆን ውጤታማ የምርመራ አገልግሎት አሰጣጡን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ምልመላን በተመለከተም እንዲሁ የሕገ መንግሥታዊነትም ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ለከተማው አዲስ የሆኑ ሰዎችን ለፖሊስነት መመልመልም ወንጀልን ከመከላከል አኳያ ቢታይም ውጤታማነቱ አጠያያቂ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡

Filed in: Amharic