>

የህወሀት ግምገማና የከሸፈው ሌጋሲ (አርአያ ተስፋማሪያም)

ለረጅም ቀናት በመቀሌ ሲካሄድ በሰነበተው የህወሀት ግምገማ ላይ የነበረውን ሂደት በተመለከተ ከታማኝ የቅርብ ምንጮች የተገኘው መረጃ ተከታዩን ይመስላል። በስብሰባው ከተገኙ የድርጅቱ ማ/ኮሚቴ አባላት በተጨማሪ ከፓርቲው አመራር አባልነት በጡረታና በሌሎች ምክንያቶች የወጡት እነስብሃት ነጋ፣ ስዩም መስፍንና ሌሎች ተገኝተዋል። በእርግጥ ስብሃት ከፖርቲው “ወጡ” ይባል እንጂ ረጅሙ “እጅ” የእርሳቸው መሆኑን ምንጮች ይጠቁማሉ። በህወሀት ክፍፍል ወቅት በመለስ የተባረሩት እነተወልደ፣ ገብሩና አረጋሽ..የቀድሞ አመራሮች “በዚህ ስብሰባ ተገኙ” የተባለው ከእውነት የራቀና አንዳቸውም እንልዳተገኙ ምንጮች ያመለክታሉ። “ጠንካራ” የተባለው ግምገማ ሲጀመር በዋነኛነት የቀረበው አንጀዳ “የመለስ ሌጋሲ የሚባል የለም! በራሳችን ነው የምንጓዘው” የሚል ቀርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ..አዜብ መስፍን እልህና ቁጣ እየተናነቃቸው “የመለስ ሌጋሲ ነው መቀጠል ያለበት” ይሉና ስብሰባ ረግጠው ይወጣሉ። አዜብ ይህ እንደማያዋጣቸው የሚቀርቧቸው ይነግሯቸዋል። በማግስቱ ወደስብሰባው የተመለሱት አዜብ በፅሁፍ “ጉባኤው ይቅርታ ያድርግልኝ?” የሚል የይቅርታ ማመልካቻ ያስገባሉ። ስብሰባው ሲጠናቀቅ በቀዳሚነት ከተባረሩት አዜብ መስፍን ሲሆኑ፣ በሌላም በኩል በየነ ምክሩና አባይ ወልዱ ከፓርቲው ፖሊት ቢሮ እንዲነሱ ተደረገ። የትግራይ ክልል ፕ/ት አባይ ወልዱ በግምገማው የቀረበባቸው 5 ነጥብ ሲሆን እነሱም “ክልሉን መምራት አልቻለም፣ ስታራቴጂ የለውም፣ በኔትወርክ መደራጀት፣ በሀይል ማስፈራራትና የአቅም ማነስ” የሚሉ እንደነበሩ ምንጮች አስታውቀዋል። አዲስአለም ባሌማና አለም ገ/ዋህድ በከባድ ማስጠንቀቂያ ሲታለፉ ብርሀነ ኪ/ማርያም (የአዜብ የመጀመሪያ ፍቅረኛ) እንዲባረሩ ተደርጓል። የስራ አስፈፃሚው በተነሱት አባላት ቦታ ሌሎች ያልተካ ሲሆን ይህ የሚሆነው በቀጣይ ከማ/ኮሚቴ የሚባረሩ ስላሉ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ እንደሚተኩ ምንጮች አስታውቀዋል።
Filed in: Amharic