>
4:31 pm - Wednesday July 6, 2022

የክልሎቹ ሕገ-መንግሥት ወዴት አሉ? ምንስ እየፈየዱ ነው? (ውብሸት ሙላት)

ፌዴራላዊ ሥርዓት፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የራስ ገዝነታቸውን በማስጠበቅ  በማእከላዊው መንግሥት በጋራ መሳተፍ በሚያስችላቸው መልኩ አገርን የማቋቋምና የማስተዳደር ጥበብን የሚከተል የአስተዳደር ዘዴ ነው፡፡ የፌደራል መንግሥት እና የፌደሬሽኑ አባላት(ክልሎች) በተጻፈ ሕገ-መንግሥት ሥልጣናቸው በየድርሻቸው ተለይቶ ይሰጣቸዋል፡፡ የፌዴራል እና የክልሎቹ መንግሥታት የተናጠል ሥልጣን እንዲሁም ሁለቱም በጋራ የሚያከናውኗቸው ሥልጣን ሊኖራቸው ይችላል፡፡

የፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ የተወሰኑ አገራት ግዛቶቻቸው ወይንም ክልሎቻቸው ሕግጋተ መንግሥታት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለአብነት አሜሪካ፣አውስትራሊያ፣ጀርመን እና ኢትዮጵያን መጥቀስ ይቻላል፡፡በአንጻሩ የክልሎችን ሥልጣን፣ተግባር፣ሓላፊነት እና ሌሎች ጉዳዮችንም በፌደራሉ ሕገ መንግሥት ውሥጥ ያስቀመጡ አሉ፡፡ ህንድ እና ስፔንን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ፣ ምንም እንኳን ክልሎቹ (Provinces) የራሳቸው ሕገ መንግሥት ሊኖራቸው እንደሚችል ቢፈቀድም የአገሪቱ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት በዝርዝር ተመልክቶ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር ምንም ነገር ተቃርኖ እንደሌለው ተረጋግጦ የምስክር ወረቀት ሲያገኝ ብቻ ይጽድቃል፡፡ በመሆኑም እስከ አሁን አንዱ ክልል ብቻ ሕገ መንግሥት አለው፡፡

የክልል ሕገ መንግሥታትን ሁኔታ ስናጤን በሚጸድቁበት እና በሚሻሻሉበት መንገድ፣ በይዘታቸው፣ በሚያቋቁሟቸው መንግሥታት እና የአስተዳደር እርከኖችን፣ ለሰብአዊ እና ለአናሳ ቡድኖች መብቶች በሚያደርጉት ጥበቃ መጠን ልዩነቶች ይስተዋሉባቸዋል፡፡

የፌደራሉ ሕገ መንግሥት እንዳለ ሆኖ፣የክልሎች ዋና ሕጋቸው የክልላቸው ሕገ-መንግሥቶች ናቸው፡፡ የክልሎቹን የፖለቲካ ሕይወት ይወስናሉ፡፡ በክልሉ ውስጥ ስለሚኖሩ ዜጎችም ይሁን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከፌደራሉ ባልተናነሰ ሁኔታ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ አላቸው፡፡

የክልል መንግሥታት የሚቋቋሙት በክልል ሕገ-መንግሥታት መሠረት ነው፡፡ ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እንዴት እንደሚዋቀሩ፣ ሥልጣናቸው ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚመረጡ ወይንም እንደሚሾሙ፣ እና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች በተመለከተ መስመር ያስይዛሉ፡፡ ሥልጣን ያከፋፍላሉ፤ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ አስተዳደራዊ እርከኖችን ይፈጥራሉ፡፡ መንግሥታዊ ሥራ እንዴት መከናወን እንዳለበትም ይደነግጋል፡፡ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን መብቶችንና ግዴታዎችንም ያሳውቃል፡፡

በኢትዮጵያ ሲሆን ደግሞ፣ በመርሕ ደረጃ፣ የክልል ሕገ-መንግሥት የላቀ ትርጉም አላቸው፡፡ ሉዓላዊ የሥልጣን ባልተቤቶች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስለሆኑ ኢትዮጵያን ወደውና ፈቅደው የመሠረቷት አገር እንደሆነች በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ላይ ተገልጿል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ እና አንቀጽ ስምንት መረዳት እንደሚቻለው፣ ብሔሮች ሉዓላዊ በመሆናቸው፣ እነሱ የሚኖሩባቸው ክልሎች ተደማምረው ኢትዮጵያን መሠረቷት እንጂ ኢትዮጵያ እንደ አገር በራሷ መሬትም ድንበርም የላትም፡፡ የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ሁለትም ይሄንኑ ያጠናክራል፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ፣ በዐጼ ኃይለሥላሴና በደርግ ጊዜ እንደወጡት ሕገ-መንግሥቶች አዋሳኞቿና ድንበሯ አልተገለጸም፡፡ የአገሪቱ ዳር ድንበር የክልሎቹ ወሰን ነው፡፡

ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ ይሄም አንቀጽ በዚህ መልኩ መደንገግ እንደሌለበት፣ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሉዓላዊ አገራት ሁሉ፣ የራሷ የሆነ ዳር ድንበርና አዋሳኞች ሊኖሯት እንደሚገባ ክርክር እንደነበር ከተለያዩ ሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ሳይቀር የሚወሰነው በክልሎች ሕግጋተ መንግሥት ስለሆነ እንዚህ ሰነዶች ከራሳቸው ከክልሎቹ ባለፈ ፌደራል ሥርዓቱ ላይም ቀጥተኛ ፋይዳ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ክልሎች አዋሳኞቻቸውን ብሎም ድንበራቸውን የደነገጉ ቢሆንም የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሕገ መንግሥት ግን የክልሉ ወሰን የዞኖቹ እና የወረዳዎቹ ነው በማለት ደንግጓል፡፡ ደቡብን በተመለከተ የኢትዮጵያን ወሰን እና ድንበር ለማወቅ የእያንዳንዱን ወረዳ ድንበር ማወቅ ከማስፈለጉም ባሻገር የእነሱን ስምምነት አስቀድሞ ማወቅ ይጠይቃል፡፡

ይሁን እንጂ እንኳንስ ወረዳ እና ዞን ይቅርና ከልሎችም ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር ዓለማቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ስለማይችሉ ይህ ዓይነቱ በክልል፣በዞን እና በወረዳ የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን በተለይም ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር የምትዋሰንባቸውን ድንበሮች መለየት ለአፈጻጸምም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለሰሚም ግራ ነው፡፡

የክልል ሕገ መንግሥት ፋይዳዎች

ፌዴራሊዝም አንዱ ጥቅሙ ልዩነቱን በማቻቻል በአንድነት መኖርን ማጠናከር ነው፡፡ሁሉም ክልልች (ብሔሮች) በፍትሐዊነት የኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ በረከቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ወደውጭ ከማሠብ ወደ ውስጥ ማየትን ያበረታታል፣ ዳሩን ማሀል የማድረግ ፋይዳም አለው፡፡

የፌደሬሽን አባላት የራሳቸው የሆነ የተለየ ባህል፣አስተዳደር፣ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕሴቶች ስላላቸው ይሄንኑ ልዩነት ለማስጠብቅ የሚረዳቸው ሕግ ያወጣሉ፡፡ አንጻራዊ ነጻነት ወይም ሉዐላዊነት ስላላቸው የፈለጉትን የአስተዳደር ዘዴም ይቀይሳሉ፡፡

የክልል ሕግጋጸ መንግሥታት ሲቀረጹም፣ ሲተረጎሙም፣ ሲተነተኑም የክልሎቹን ልማድ እና ወግ፣ አስተዳደራዊ ዘይቤያቸውን፣ ሃይማኖታዊ እና ኪነጥበባዊ ዕሴቶችን መጠበቅ እና ከግምት ማስገባት የተለመደ ነው፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች በራሳቸው የዳበሯቸውን ማንነቶች ማበልጸግም አንዱ ግባቸው ነው፡፡ ለአብነት የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ገዳ ላይ የተመሠረተ የዳበረ ባሕል ስላለው ይሄንኑ ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃና እና ዕውቅና ሊያርግለት ይችላል፡፡ከፌደራሉ በተሻለ ሁኔታ የአካባቢያዊ መንግሥትን ሥልጣን ይደነግጋሉ፤ይገድባሉ፤ተጠያቂነትን ያረጋግጣሉ፤ በመሆኑም ዝርዝርነታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ከፌደራሉ በተሻለ ለሕዝብ ፍላጎት ምላሽ ይሰጣሉ፣በቀላሉ ይሻሻላሉ፡፡በተሻለ መንገድም የሰብአዊ መብትን ለማስጠበቅ ይችላሉ፡፡የፌደራሉ ሕገ መንግሥት ላይ የተገለጹትን መብቶች እስካልጣሱ ድረስ ጥበቃ ማድረግ የተፈቀደ ነው፡፡ ለምሳሌ በክልሉ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥት የሕክምና ተቋማት ነጻ ሕክምና የማግኘት መብት አለው በማለት ሊደነግጉ ይችላሉ፡፡

ብሔሮች እና የክልል ሕገ መንግሥት

ብሔሮች ሉዓላዊ ሥልጣናቸው በዋናነት ሥራ ላይ የሚውለው በክልልና ከዚያ በታች ባሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ነው፡፡ ብሔሮች ለብቻቸው ባዋቀሯቸውና በሚያስተዳድሩት ልዩ ዞን፣ ወረዳ ወይም ልዩ ወረዳ ማለት ነው፡፡ የፌደራል መንግሥቱ የሁሉም የጋራ ሲሆን እነዚህኞቹ አስተዳደራዊ እርከኖች ግን የአንድ ብሔር ወይንም የተወሰነ ቁጥር ያላች ብሔሮች ብቻ ናቸው፡፡ በጋራ አብረው ሲኖሩ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የተስማሙበትን ሕግ እስካልጣሱ ድረስ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚጨርሱት በእነዚህ አስተዳደሮች ውስጥ ነው፡፡ስለሆነም የክልል ሕገ-መንግሥታት ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በውስጡ ለሚኖሩት ዜጎች ብዙ ነገር ማለት ናቸው፡፡

የክልል ሕገ-መንግሥታት ከላይ ከተገለጸው በእጅጉ የበዛ ዋጋና ፋይዳ ይኑራቸው እንጂ፤ አይደለም እንዴት እንደወጡ፣ እንደተሻሻሉ፣ ይዘታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ቀርቶ፤ መኖራቸውም በአግባቡ አይታወቅም፡፡ የክልል መንግሥታትም ቢሆኑ ከአፋቸው የማይለየው የፌደራሉ እንጂ የራሳቸው ሕገ-መንግሥት ባለመሆኑ፣ ዳኞችም፣ጠበቆችም፣ ዐቃቤያነ-ሕጎችም ቢሆኑ የክልሎችና የፌደራሉ ሕገ-መንግሥቶች ልዩነት ያላቸው ስለማይመስላቸው ትኩረት ተነፍጓቸዋል፡፡ ምንአልባትም በአሃዳዊ መንግሥት መተዳደር ስለለመድን አሁንም አስተሳሰባችን ከተዋረዳዊውና አሃዳዊው ሥርዓት በተግባር የተለየ አይመስልም፡፡

በመሆኑም እንደነዚህ ዓይነት ሕጎች ያላቸውን ፋይዳ በቅጡ አልተረዳንም፤ መንግሥቶቻችንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አላስተዋወቋቸውም፡፡ እንደ ሌላ ተራ መጽሐፍ እንኳን በገበያም ላይ ሲሰራጩ አይታይም፡፡ ማወቅ ለሚፈልግም ተደራሽ አይደሉም፡፡

የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት መጽደቅና የክልል ምክር ቤት ምርጫን ተከትሎ በ1987 እና በ1988 ዓ.ም. ጸደቁ፡፡ ከዚያ በፊት እንደማእከላዊው መንግሥት የራሳቸውን የክልል የሽግግር ቻርተር በማውጣት ይተዳደሩ ነበር፡፡ እነዚህ ሕግጋተ መንግሥታት ሲረቀቁም ይሁን ሲጸድቁ ከአርቃቂው ክፍልና ከአጽዳቂዎቹ የክልል ምክር ቤቶች ውጭ ሳይታወቁ በ1994 እና በ1995 ዓ.ም. ደግሞ ሁሉም ተለወጡ፡፡ የተለወጡትን ረቂቅ ከፌደራል መንግሥት ወደ ክልሎች የተላኩ እንጂ ክልሎች አርቃቂ ወይንም የሚለውጥ ኮሚሽን አቋቁመው፣በጥልቀት መክረውባቸውና እና ዘክረውባቸው የወጡ እንዳልሆኑ ማስረጃዎች አሉ፡፡

የቀድሞዎቹ፣የክልል ሕገ-መንግሥታት በሕግ አውጭውና በሕግ ተርጓሚው መካከል ልዩነት አልነበራቸውም፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት (በወቅቱ አጠራር) አፈ-ጉባኤም ጭምር ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ በደርግ እና በሽግግር ዘመኑም እንዲሁ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቶቻችን አፈጉባኤም ጭምር ነበሩ፡፡ የወረዳዎችና ሌሎች አስተዳደረዊ እርከኖችም በሕገ-መንግሥቱ የተገለጸ ዋስትናም ይሁን ሥልጣን አልነበራቸውም፡፡ ሌላም ሌላም ችግር ስለነበረባቸው ተለወጡ፡፡በተለይ ለመለወጣቸው አንዱ ምክንያት በወቅቱ የወጡት ፖሊሲዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ቀድሞም ስለመኖራቸው በአግባቡ ሳይታወቅ ተለወጡ፡፡ ከዚያም በኋላ የተወሰነ ማስተካከያ (ማሻሻያ) የተደረገባቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ፣የአማራ እና የትግራይ፡፡

የክልል ሕገ መንግሥትን የማጽደቅ ሥልጣን የማን ነው?

የክልል ሕገ-መንግሥትን የማውጣት፣ የማሻሻልና የመለወጥ ሥልጣኑ በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 50(5) መሠረት የየክልሎቹ ምክር ቤቶች ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ድምፅ ሳያሰሙ አጸደቁ፡፡ ኋላም ለወጧቸው፡፡ ነግር ግን በዚህ መሠረት መሆን ነበረበት ወይ? በክልሉ የሚኖረው ሕዝብና ብሔሮች ሊመክሩባቸውና ሊሳተፉባቸው አይገባምን? ሕገ-መንግሥትን ያህል ነገር ምክር ቤቶች “ኮሽታ” ሳያሰሙ ማውጣት፣ መቀየርና መለወጥ ይገባቸዋልን?

የክልል ምክር ቤቶች ሕገ-መንግሥቶቹን የማውጣትና የማሻሻል ሥልጣን ቢኖራቸውም ሌሎች አካላት እንዳይሳተፉ አይከለክልም፡፡ ለዚያም ነው በሁሉም ክልሎች ሕገ-መንግሥቶቻቸው ሲሻሻሉ ቢያንስ የወረዳና ሌሎች አስተዳደራዊ መዋቅሮች ተሳትፎ የተካተተው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ሕዝቡ ስለሚሻሻሉት የሕገ-መንግሥት አንቀጾች የሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ቢኖር ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ የባልተቤትነት ስሜትንና ቅቡልነትንም ይጨምራል፡፡ በእርግጥ የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ሲሻሻል  በይፋ አልተነገረም፤ ማሻሻያዎቹም በሕግ አልወጡም፡፡

የክልል ሕገ መንግሥት እንዴ ዴሞክራሲ ቤተሙከራ

የፌደሬሽኑ አባላት በሕገ-መንግሥቱ ተለይቶና ድንበር ተደክቶ የተቀመጠውን ሥልጣናቸውን በተመለከተ ሕግ የማውጣት፣ ያንን የማስፈጽምና ለሚያወጧቸው ሕጎች ትርጉም በመስጠት ግጭትን የሚፈታ የዳኝነት አካላት ማቋቋም ዋነኛ መለያ ባሕርያት ናቸው፡፡ ከክልል ባለፈም በሌሎች ዝቅተኛ እርከኖችም ላይ ይሄው ሁኔታ ሊደገም ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ልዩ ዞን፣ ልዩ ወረዳ፣ ወረዳና ቀበሌዎች ይህ ዓይነት አወቃቀር አላቸው፡፡ የክልል ሕገ-መንግሥት በተራቸው የክልሉንና የነዚህን ሥልጣን ለይተው ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ይበጀናል ያሉትንም ፖሊሲ ማውጣት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እንደ ዴሞክራሲ ቤተሙከራም ይቆጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ክልሎች በተመለከተ የፌደራሉ ሕገ መንግሥትን በመመርኮዝ ምሁራን ሦስት የተለያዩ አመለካከተችን በማንሳት ሲሟገቱ ይታያል፡፡

ክልሎች ለዴሞክራሲያዊ ቤተ-ሙከራነት እንዲያገለግሉ የሚረዳ ሕገ-መንግሥታዊ ሜዳ የላቸውም በማለት በተለያዩ ማሳያዎችን የተደገፈ ሙግት አለ፡፡ በተለይ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 51(2) ላይ የተገለጸው የፌደራል መንግሥቱ “የአገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና እቅድ ያወጣል፣ያስፈጽማል፡፡” ካለ ለክልሎች የተረፋቸው የለም፤ ከሕጋዊ ማዕቀፉ በተጨማሪ ኢሕአዴግ እንደፓርቲ ያለው የማእከላዊ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ለክርክሩ እንደአስረጂ በማድረግ ይቀርባል፡፡

አንዱን ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ አሸንፎ ቢያስተዳድረው የፌደራል መንግሥቱ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጅዎችና እቅዶች ብቻ የሚያስፈጽም ከሆነ ማሸነፉስ ምን ይፈይዳል ይላሉ? ከዚህ አንጻር የፕሮፌሰር አንድርያስ እሼቴ ሰፊ ሙግት ተጠቃሽ ነው፡፡ ሕግ አውጪ እንዲኖር ያስፈለገው እኮ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ከፌደራሉም የተለዬ ቢሆን ፖሊሲዎችንና ሕጎችን እንዲያወጣም ጭምር ነው የሚል ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ክልሎች በቂ ሥልጣን አላቸው በሚል የሚቀርብ መከራከሪያም አለ፡፡“የክልሉን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና እቅድ ያወጣል፣ያስፈጽማል፡፡” ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 52(2)(ሐ) ይህንን ይል የለም ወይ? በተለይ በዚህ አንቀጽ መሠረት ብዙ ሥልጣን አላቸው፤የፌደራሉ እንደ ቢጋር ወይንም ጥቅል አቅጣጫ እንጂ ለክልል የሚሆን፣ የእያንዳንዱን ክልል ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ፖሊሲና ሕግ፣የፌደራል መንግሥቱ ስለማያወጣ፣ ከተጠቀሙበት በቂ ነው የሚል ዓይነት መከራከሪያ አለ፤ ችግሩ በዋናነት አተገባበሩ ላይ እንጂ ማለትም ከፓርቲ ሥርዓታችንና ከመሳሰሉት የሚመነጭ እንጂ ከሕገ-መንግሥቱ የመጣ እንከን አይደለም ይላሉ፡፡  ይህ በዋናነት የዶ/ር አሰፋ ፍሥሐ ሙግት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሦስተኛው አመለካከት ደግሞ ሥልጣን ተሟጣ ለክልሎች ስለተሰጠች ኢትዮጵያ እንደአገር ወይንም ፌደሬሽን እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣን የላትም የሚል አመለካከትም አለ፡፡መከራከሪያው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ መሆናቸው፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመገንጠል መብት ያላቸው መሆኑ፣ ሕገ-መንግሥቱን የሚተረጉመው፣ የድንበር ግጭት ላይ እልባት የሚሰጠው፣ ስለራስን ዕድል በራስ መወሰን ውሳኔ የሚያሳልፋቸው የክልሎች (ዞሮ ዞሮ ክልል የብሔሮች ስለሆኑ) ተወካዮች ከሆኑ የጋራዋ ኢትዮጵያ ምንም አልተረፋትም፡፡ ስለሆነም ክልሎች በሕግ ዋስትና የተሰጣቸው ሞልቶ የተትረፈረፈ ሥልጣን አላቸው ይላሉ፡፡ የዚህ ሐሳብ ዋና አራማጅ ፕሮፌሰር ምናሴ ኃይሌ  ናቸው፡፡

ተግባር ወዲህ ሕግ ወዲያ ከሆነ ሕጉ ምንም አልፈየደም ማለት ነው፡፡ ጭራሹኑ ክልሎች እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣን በሕግ አልተሰጣቸውም ወይንም ፌደራል መንግሥቱ ምንም ሥልጣን የሌለው ከሆነ መሠረታዊ የሆነ መዋቅራዊ ችግር አለ ማለት እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ-መንግሥቱ ሳይሆን አተገባበሩ ከፌደራላዊ ሥርዓት ይልቅ ወደ አሃዳዊነት ይቀርባል ማለት ይቻላል፡፡

የአውራ ፓርቲና ማእከላዊ ዴሞክራሲ የክልል ሕገ መንግሥት ሸክሞች

ከላይ የቀረበው ክርክር እንዳለ ሆኖ ክልሎች የራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የአፋር እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስለ አርብቶ አደር፣ የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ሕገ-መንግሥት ደግሞ የክልሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በነጻ ገበያ መርሕ እንደሚመራ መደንገጉ በኢትዮጵያም ክልሎች የዴሞክራሲ ቤተ-ሙከራ ናቸው ሊያሰኝ የሚችል ጭላንጭል አለ ማለት ቢቻልም፤ በአንድ አውራ ፓርቲ መመራት ልማድ ባደረገች አገር ውስጥ የባህል ልዩነትና ብዝሃነት እንጂ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነትም ይሁን ብዝሃነት ስለማይኖር ቤተ-ሙከራ ሆነው ማገልገላቸው አጠያያቂ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት መሠረት ክልሉ በነጻ የገበያ መርሕ መመራት ሲገባው፣ ያው የሚመራው በልማታዊ መንግሥት እንጂ በነጻ ገበያ አይደለም፡፡

ከዚህ የበለጠ የሚከፋው ግን በየክልሉ የሚገኙ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የሚገኙ ባለሥልጣናት ከክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይልቅ የፌደራሎቹን እንደዋና አለቆቻቸው መቁጠርና እነሱን እንደማጣቀሻ አድርጎ የመወሰድ አባዜም፣ አዝማሚያም፣ ጥንውትም ሥር መውደቅ ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት አሃዳዊ አስተዳደርን የለመደ አስተሳሰብ በተግባር በፌደራሊዝም በረከቶች ላይ ሥልጣንና ተጠሪነትን በትክክል መገንዘብ ላይ ጥርጥርና ማመንታት ያለ ይመስላል፡፡

በሕግ የተሰጠን ሥልጣን በመተው በራስ ገደብ በመጣል፣ በራስ ለሌላ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አካሔድ ዋናው ምክንያት የአንድ ፓርቲ ለዚያውም አውራ ሆኖ በመንገሥና ፓርቲውም የሚመራበት መርሕ ማዕካላዊ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ነው፡፡

የፌደራሉን ሕገ መንግሥት ግብን ለማሳካት የክልል ሕግጋተ መንግሥታት ሚና

በኢትዮጵያ  ሠላምና ዴሞክራሲን ከማስፈን ባሻገር አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው ግቡ፡፡ የሕገ- መንግሥቱ ዋናው ግብ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ከሆነ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት ተቋማትና የሚወጡት ሕጎችም ይሁኑ ፖሊሲዎች ይህንን ለማሳካት መሆን አለባቸው፡ መነሻው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰብችና ሕዝቦች የፖለቲካ አንድነት አልነበራቸውም፣ አልፈጠሩምም ነው፡፡

በባህልና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና በመደብም እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ልዩነት ስለነበረ እራሳቸውን እያስተዳደሩ፣ ራሳቸው እየወሰኑ፣ በጋራ እየመከሩ፣ በጋራ ሀገሪቱን እየመሩና በሌሎችም አኳኋን አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሕዝብ መፍጠር ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያ የሆነ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ሲፈጠር ተናጠላዊ ማንነቱን ማጣት የለባትም፡፡

ተናጠላዊው የብሔር ማንነቱ እንደተጠበቀ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር የሁልጊዜም ጉዞ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሚቋጭ ሳይሆን ሁሌም የሚቀጥል ግብ፡፡ ይሁን እንጂ የክልሎች በቆዳ ስፋት፣በሕዝብ ብዛት፣ በተፈጥሮ ሃብት አለመጣጣም ላይ የዴሞካራሲ እጦት ሲጨመርበት ግቡን ማሳካት አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡ የተወሰኑ ምሳሌዎችን በማንሳት እንብራራው፡፡

በክልሎች መካከል፣ በተፈጥሮ ሀብት የሠፋ ልዩነት ካለ ያንን ሀብት ለብቻ ለመጠቀም ሲባል ሀብቱ ያለበት ብሔር/ ክልል መገንጠልን ሊመርጥ ይችላል፡፡ በሀብት የተሻለው በሀብት የደኸየውን ላለመርዳትና ላለመደገፍ ሲል ሊገነጠል እንደሚችል ቀድሞም ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ፣ ወደፊት እንደአንድ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ተነስቶ ነበር፡፡

ያልተመጣጠነ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛትም መኖር መገንጠልን ሊያበረታታ ይችላል፡፡ ሰፊ የቆዳ ስፋት ካለው፣ የሕዝብ ብዛቱ ከፍተኛ ከሆነ በአንድነት መኖር ላያጓጓው ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶችም ጭማር ነው ናይጀሪያ 3 የነበሩት ክልሎቿን ቀስ በቀስ እየከፋፈለች ወደ 36 ያደረሰቻቸው፣ የነ ቢያፍራ የመገንጠል ስሜት እየቀዘቀዘ የሔደው፡፡ ልዩነቱ ሳይጠፋ በመከፋፈል፣ አንድም አስተዳደራዊ መዋቅርን ተደራሽ በማድረግ ሕዝባዊ አገልግሎትን በቅርብ መስጠት አስችሏታል፡፡

የግዛት አንድነቷንም ለማስጠበቅ ረድቷታል፡፡ በተጨማሪም አንድ ብሔር አንድ ሰፊ ክልል በመያዝ ለመገንጠል የሚያበረታታውን ሐሳብ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ይህ አካሄድ ለክልሎች በጣም የተለጠጠ ሥልጣን መሥጠትን የሚቃወም ነው፡፡

የክልሎቹ ሕግጋተ መንግሥታት ከመግቢያቸው ጀምሮ ዝርዝር ይዘታቸው እና ሊያሳኩት የሚፈልጓቸውን ግቦች ምንያህል ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር የተሰናሰለ እንደሆነ በቀጣይ ማየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገ መንግሥታዊነት የሚሰፍነው፤ የሕግ የበላይነት ሥር የሚሰደው የክልል ሕገ መንግሥትንም ትኩረት በመሥጠት ተግባራዊ በማድረግ ነው እና ስውርነታቸው ተገልጦ ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡

Filed in: Amharic