>
2:20 am - Wednesday February 1, 2023

ሁለት መልዕክቶች ለሁለት አካላት... (ዮናስ ሃጎስ)

ይህ መንገድ አይሰራም! ይህ መንገድ ወዳልተፈለገ የእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ ነው የሚወስደን! 

1ኛ) ለትግራይ ሕዝብ

የትግራይ ህዝብ ከመረጃ እጦትም ይሁን እውነታውን በግልፅ ለማየት ካለመፈለግም ይሁን አንዳንድ የትግራይ አክቲቪስቶች የሚቀልቡትን ትምክህታዊ እሳቤን ይዞም ይሁን ብቻ ሐገሪቷ እየሄደችበት ያለውን መንገድና ወደፊት በሕልውናው ላይ እየመጣ ያለውን አደጋ በውል እንዳልተረዳው ተገንዝቤያለሁና የመጀመርያው መልዕክቴ ለትግራይ ህዝብ ነው።
***
ሕወሐት እንደ ኢህአዴግ አባል ድርጅት በድርጅቱ ላይ ያላትን የበላይነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ፍትጊያ ሳቢያ እንዲሁም ሆን ተብሎ በትግራይ ህዝብ ጠላቶችም በሚቀነባበር ፕሮፖጋንዳ ምክንያት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሐትን እና የትግራይ ህዝብን ለመለየት እየተቸገረ መሆኑን ማስተዋል ጠቢብነትን አይጠይቅም። በዚህም ስሌት በመሄድ ከትግራይ ክልል ውጪ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ሕይወታቸው፣ ቤት ንብረታቸው እንዲሁም ባጠቃላይ ሕልውናቸው አደጋ ውስጥ እየገባ ነው። ይህ ከትግራይ ክልል ተነስተው ለትምህርትና ለስራ ወደ ሌላ ክልሎች የሄዱትን ብቻ ሳይሆን ሌላ ክልል ውስጥ ከትግራይ ተወላጆች ተወልደው እዚያው ያደጉትንም ጭምር አደጋ ላይ የጣለ ክስተት እየሆነ መጥቷል። አብዛኛውን ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ ኃብታም ከሆነ ዘርፎ ኃብታም እንደሆነ ድኃ ከሆነ ደግሞ ለሕወሐት የሚሰልል አድርጎ መመልከት በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ እየሆነ እየመጣ ያለ ክስተት ሆኗል። ይህ ደግሞ አሁን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ስርዓት ለመላቀቅ ለሚያደርገው ትግል የትግራይ ተወላጆችን ዒላማ ይሆኑ ዘንድ መንገድ መክፈቱን የቅርብ ጊዜ ክስተቶች እያሳዩን ነው።
ትግራይን የሚያስተዳድረው ድርጅት ሕወሐት በዚህ ረገድ አይደለምና መፍትሄ ማበጀት ቀርቶ የኃዘን መግለጫ እንኳን ማውጣት እንደተሳነው እንደ ሊላው ክልል ባለስልጣናት እቦታው ድረስ በመሄድ ድርጊቱ የተፈፀመበትን ክልል ባለስልጣናት ለማነጋገር እንኳን ጥረት ሲያደርጉ አልታየም። በትላንትናው ዕለት ወልዲያ እንደዚያ ቀውጢ ሆና እንዲህ በምስሉ የምትመለከቱት ዓይነት አደጋ ሲደርስ በትግራይ አስተዳደር የሚመራው የትግራይ ቴሌቭዥን ‹መቀለ ከነማ ከወልዲያ ከነማ ጋር እየተጫወተ ነው› ከማለት በቀር አንዳችም ያለው የተነፈሰው ነገር የለም። እስካሁንም ስለ ጉዳዩ አልዘገበም።
ይሄ ነገር በዚህ ወቅት አንድ ሁለት እያለ እየተንጠባጠበ የሚፈፀም ጉዳይ ይሁን እንጂ ዓይናችንን ከፍተን መመልከት ካቃተንና በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለት ወደፊት ወደ ባሰ ደረጃ መድረሱ አይቀሬ ነው።
ስለዚህ ለትግራይ ህዝብ የማስተላልፈው መልዕክት በሕልውናው ላይ አደጋ እየመጣ መሆኑን ተገንዝቦ እንዲሁም የዚህ አደጋ ዋናው መንስዔ ሕወሐት መሆኑን አውቆ በሕወሐት ላይ ያለውን ዓቋም እንዲያስተካክልና ሕወሐትንም በሌላ የትግራይ ህዝብን በደንብ ሊወክል በሚችል የፖለቲካ ድርጅት ለመቀየር ትግሉን ካሁኔው ይጀምር ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁኝ።

2)  የዚህ መንግስት አስኳሉ ሕወሐት ይሁን እንጂ (መከላከያውን እና ደህንነት ተቋማትን ከመቆጣጠሩ አንፃር) ሐገሪቷ የምትተዳደረው የመንግስትነት ቅርፅ ባለው የፌደራል አስተዳደር መሆኑን መዘንጋት ብዙዎችን ወደማይፈለግ አቅጣጫ እየወሰደ ነው። በየቦታው ይህ አምባገነን መንግስት ተቃውሞዎችን ለማፈን በሚተኩሳቸው ጥይቶች ላይ የትግራይ ባለስልጣናትንና ህዝቡን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ እልም ያለ ዘረኝነት ከመሆኑ ውጪ ሌላ ትርጉም አይኖረውም። የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት በዚህ የኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ያፈሩትን ኃብትና ስልጣናቸውን ማስጠበቅ እንደሚፈልጉት ሁሉ ሌሎቹም የሌላ ብሔር ተወላጅ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት እስከ ታች የወረዳ ካድሬ በዚህ የኢሕአዴግ ዘመን ያገኙትን ኃብትና ስልጣን ማስጠበቅ ይፈልጋሉና እነርሱም ከትግራይ ተወላጆቹ ባለስልጣናት እኩል ለዚህ ስርዓት ዘብ መሆናቸውን መረዳት ካቃተን የምንታገለው ለፍትህና ዴሞክራሲ ሳይሆን በትግራይ ላይ ሂሳብ ለማወራረድ መሆኑን አምነን መቀበል አለብን።
ከዚያ በባሰ መልኩ ደግሞ አፋኝ መንግስት በሚልካቸው ወታደሮች የሚሞቱ ተቃዋሚዎችን ደም በንፁሃን የትግራይ ተወላጆች ደም ለማካካስ መሞከር እጅግ በጣም የዘቀጠ አሳፋሪ ተግባርና ምናልባትም ወዳልታሰበ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚከትተን መሆኑን ለመረዳት አለመቻል ለሁሉም አደጋ አለው። ምናልባት ራሳችንን ከኢትዮጵያ በማውጣታችን የደህንነት ስሜት የሚሰማንና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሳ እሳት አይደርስብንም በሚል ስሜት ‹በለው! በለው!› እያልን ለማጋጋል የምንሞክር ሰዎች ቢያንስ በስጋ የምንዛመዳቸው፣ በጓደኝነት ብዙ ጊዜ ያሳለፍናቸው ወዳጆቻችንን እዚያው ኢትዮጵያ ጥለን እንደወጣን እንዴት መርሳት እንችላለን? የእርስ በርስ ጦርነት ከተነሳ እኮ አንዱን ገድሎ ሌላውን የሚያተርፍ ነገር አይደለም። እሳቱ ሁሉም ቤት የሚገባ አስቀያሚ ነገር መሆኑን አምነን መቀበል መቻል አለብን።
ተወደደም ተጠላም ከ1983 በፊት ሽፍቶች በመባል ይታወቁ የነበሩት የኢሕአዴግ አባላት አሁን ዓለማቀፍ እውቅና ያላቸው መንግስት ናቸው። እንደድሮው እንደ ሽፍትነታቸው ጊዜ በጎሪላ ግጥምያ ልንገጥማቸው አንችልም። አሁን መንግስት ሆነዋልና መንግስትን የማውረድ ጥያቄ ነው ሊሆን የሚችለው እንጂ ሕወሐት ካበቃለት ሁሉም ነገር ያበቃለታል ብሎ አንዱን ብቻ የመንግስት አካል ነጥሎ ለመምታት መሞከር ፖዚቲቭ የሆነ ውጤት የሌለው እንዲሁም በተሳሳተ አተረጓጎም ሲታይ ደግሞ ኃይለኛ መከፋፈልን የሚፈጥር መሆኑን እስካሁን ከመጣንበት ጎዳና መመልከት ይቻላል።
እንደገናም ንፁህ የትግራይ ተወላጆች ላይ እንደዚህ ዓይነቱን ወንጀሎች በመፈፀም የትግራይ ህዝብን በሕወሐት ላይ እንዲያምፅ እናስገድደዋለን የሚለው አካሄድ ፍፁም ስህተት የሆነና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስድ መሆiኑን መረዳት አለብን። ይህ ዓይነቱ አካሄድ በተለይ የሚዘወተረው አንድም ከትግራይ ህዝብ ጋር ከጥንት ጀምሮ ቁርሾ በነበራቸውና አጋጣሚውን ሂሣብ ለማወራረድ እየተጠቀሙበት ባሉ አካላት አሊያም አሁን ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል ይሄ አቋራጭ መንገድ ነው የሚል ቀቢፀ ተስፋ የሚሰማቸው ምስኪን ተቃዋሚዎች ዘንድ ነው።
መልዕክቴ ግልፅ ነው። ይህ መንገድ አይሰራም። ይህ መንገድ ወዳልተፈለገ የእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ ነው የሚወስደን። ይህ መንገድ ኢሕአዴግን ሊጥል ቢችልም እንኳን በኢሕአዴግ ምትክ ደካማ የሆነችና በትንሹ ለ10 ቦታ የተከፋፈለች ሐገር ነው የሚፈጥረው እንጂ አንድ ጠንካራ መንግስት አይፈጥርም። ይህ መንገድ አቋራጭ መንገድ ሊሆን አይችልም። የትግራይ ህዝብን ራሱን በኃይል ለመጠበቅ ሲል ይበልጥ ወደ ሕወሐት ከማጣበቁ በቀር መንግስትን ጭራሹኑ አይነቀንቅም።
*******************************************************************
የሐገራችንን መጨረሻ ያሳምርልን። ሀገር ማለት ህዝብ ማለት ነውና የሕዝባችንን መጨረሻ ለማሳመር ሀገራችንን መጠበቅ ግድ ይለናል። ሐገር በእንደዚህ ዓይነት መንገድ አትገነባም!

Filed in: Amharic