>
1:40 am - Thursday October 21, 2021

ኧረ ተው ግፉን በልክ አድርጉት ይቺ ቀን ትቀየራለች (ሂሩት ሃይሉ)

※ተው ዘረኝነት ጥሩ አይደለም ስንል,, ዝም በሉ የደርግ እርዝራዦች እንባላለን!

※ተው አትከፋፍሉን አንተ ኦሮሞ፣አንተ አማራ፣አንተ ጉራጌ ፣ አንተ ምናምን እያላችሁ አታባሉን ስንል,,, ዝም በሉ የሻብያ ተላላኪ እንባላለን!

※ኧረ ተው አብሮነታችን ነው ጥሩ ፣ አንድነታችንን አትናዱት፣ ኢትዮጵያን አታፍርሷት ስንል,,, ዝም በሉ የድሮ ስርአት ናፋቂወች እንባላለን!

※አትግደሉ አትሰሩ ስንል,,, አማራ ነፍጠኛ ትምክህተኛ ገና መቶ አመት ቀጥቅጠን እንገዛችኋለን እንባላለን!

※ የኦሮሞ ተወላጆች የመብት ጥያቄ ሲጠይቁ,,,, ዝም በሉ ጠባቦች እድሜ ለኛ በሉ ከነፍጠኛ ነፃ አወጣናችሁ እንባላለን!

※ጋዜጠኞች ይፈቱ፣ የመናገር ነፃነት ይኑር ስንል,,,ምድረ ዲያስፓራ ይሄን በርገር እየበላችሁ ጠገባችሁ ዝም ብላችሁ ጩሁ ምንም አታመጡም እንባላለን!

※ኧረ ተው አሁን የምታራግቡት የዘር ፓለቲካ በኋላ አደጋ አለው ስንል,,,,, አማራ እና ኦርቶዶክስን አከርካሪውን ሰብረን ጥለነዋል እንባላለን!

※ የሙስሊሙ መሀበረሰብ የማናውቀውን ሀይማኖት አትጫኑብን፣ ኮሚቴወቻችን ይፈቱ ስንል,,,, አሸባሪወች እንባላለን!

※በአገር ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያላቸውን ወጣቶች በሰበብ አስባቡ ያስሩና የአማራ ተወላጅ ከሆነ ግ7 ነህ፣ የኦሮሞ ተወላጅ ከሆነ ኦነግ፣ ሙስሊም ከሆነ አሸባሪ ነህ የሚል ታርጋ ይለጥፍባቸውና ምንም ወንጀል ያልፈፀሙ ወገኖች መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ድረስ ቁም ስቅላቸውን አይተው እንደሙክት ተቀጥቅጠው ተኮላሽተው ተሰባብረው ይወጣሉ!

※ኧረ ተው ግፉን በልክ አድርጉት ይቺ ቀን ትቀየራለች? ስርአት ይቀየራል ይሄዳል ይመጣል ፣ ህዝብና አገር ግን ይኖራል ተው ስንል,,,,, ከነተከታዮቻቸው ጭምር ፀረ ሰላም ሀይሎች፣ ፀረ ልማት ሀይሎች፣ የደርግ እርዝራዞች፣ የሻብያ ተላላኪወች፣ ነፍጠኞች፣ ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ አሸባሪወች አድሀሪያን,,,,,,, ምን ያልተባልነው አለ?!

እኛ ወደፊት የሚመጣው አደጋ ታይቶን ጮኸናል ፣ ለፍልፈናል ካሁን በኋላ የሚጮህም የሚለፈልፍም አይኖርም! ትግላችን ግን መራር ይሆናል!! ለነፃነታችን ማድረግ ያለብንን ሁሉ እናደርጋለን! ይሉኝታችን አስጨርሶናል! አሁን ግን ይበቃል! ከኖርን አብረን በሰላም እንኖራለን፣ ከሞትንም አብረን እንሞታለን! አንዱ እየሞተ አንዱ በሰላም የሚኖርበት ምክንያት አይኖርም።።።።።

Filed in: Amharic