>

ዜግነት እውነት ነው፤ ብሄረሰብነት እምነት ነው (በእውቀቱ ስዩም)

ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ፤ ጥንታዊ ወታደር በባላገር ላይ ሲያደርስ የኖረውን በደል ፅፎ አይጠግብም፤ ባንድ ቦታ ስለ አንድ ገበሬ የሚከተለውን ይተርካል፤
•….“ከነዚህ መከረኞች አንዱ(ገበሬ) መልከ ቅን ምሽት ነበረችው፤ አንድ ቀን በቴዎድሮስ ጊዜ አንድ ቅማጫም ነፍጠኛ ተቤቱ ተመርቶ ገባና ባለቤቲቱ መልከ ቅን ሆና ባያት ጊዜ ነፍጡን ተጉልበቱ  ላይ አድርጎ ‘አንተ ይቺ እህትህ ስንት አመቱዋ ነው ?ቁጭ አንተን ትመስላለች፤ አለው፡
ያ ባላገር ግን ምሽቴ ናት ማለቱን ፈራ፤ ያም ርጉም ነፍጠኛ በጥፊ እያጣፈረ ያችን ምሽቱን ይዞበት አደረ፤ ከዚህ በሁዋላ ያ መከረኛ ድሃ አዘነና ንዴት ያዘውና_፤
ታገር እኖር ብየ
ከብት እነዳ ብዬ
ልጅ አሳድግ ብየ
ለባሻ ዳርኩለት ምሽቴን እቴ ብየ
 
ብሎ አንጎራጎረ፤…’’
ያፈወርቅን ትረካ በተለያየ መንገድ  ልንተረጉመው እንችላለን፤ ታሪኩ፤ አንድም፤ ‘ገደብ የለሽ ስልጣን ገደብ የለሽ ብልግና ይወልዳል ‘ ለሚለው አሳብ ማስረጃ  ሊሆን ይችላል፤ የጠመንጃ አስማት ቀላል አይደለም፤ ሚስትህን ወደ እህትህ ለውጦ የማሳየት ችሎታ አለው፤
ታሪኩን ቆይቼ ስገርበው ሌላ ነገር አወጣሁበት፤ ስለ ብሄር ማንነት ያለንን አመለካከት የሚፈታተን ፍሬ ነገር አገኘሁበት፤
አፈወርቅ ያለ ስም የተወውን መከረኛውን ገበሬ : አያ ጌድዮን የሚል ስም እንስጠው፤ አያ ጌድዮን ከሚኖርበት ከዘጌ ፤ ማሚት የምትባል አንዲት ቆንጆ መርጦ አገባ፤ ባልና ሚስቱ ሲተጫጩ የማን ልጅ ነው የማን ልጅ ናት ተባብለው ተጠናንተው ወገን ለወገን ተዋውቀው ነው፤ የሚወልዱዋችው ልጆች ያብራካቸው ክፋይ እንደሆኑ ርግጠኛ ናቸው፤
ሲኖሩ ፤ሲኖሩ ፤አንድ ቀን አንድ ወታደር ቤታቸው ውስጥ ተመርቶ ገባ፤ አፈወርቅ በገለጠው መልኩ፤ ማሚት ተደፈረች፤ በዘጠኝ ወሩ ልጅ ተወለደ፤ በጊዜው ልጁ የወታደሩ ዲቃላ ይሁን የባላገሩ ልጅ የሚጣራበት መንገድ አልነበረም፤  የወታደሩ ነው ብለን እናሰብ፤  የልጁ ዘር ምንድነው? በጥንት ጊዜ ለገስታት ከተለያዩ ነገዶች ወታደር የመመልመል ልማድ ነበራቸው፤አጤ ቴዎድሮስ ሰራዊት ከቅማንት አማራ ትግራይ ሳሆ የየጁ ኦሮሞ የተዋቀረ ነበር፤ማሚቴን የደፈራት ወታደር ብሄሩ ምንድነው? ኬትኛውም ብሄርና ሃይማኖት ይወለድ ያልተገደበ ስልጣን ካሸከምከው የማይባልግ ሰው የለም፤ በዚህ ሂሳብ: ወቴው ከላይ ከተዘረዘሩት ነገዶች የአንዱ ተወላጅ ሊሆን ይችላል፤ደፋሪው ወታደር በማግስቱ ሰፈሩን ለቅቆ ስለሚሄድ ዘሩን ማጠያየቅ እንኩዋ አይቻልም፤
ይህ ባንድ ዘመነ መንግስት ብቻ የሚደረግ አይደለም፤ የተቀቡም ሆነ ያልተቀቡ ጉልበተኞች ርሃብ ሲያባርራቸው ፤ወረርሽሽኝ ሲያባርራቸው ወይም  የርስት ፍላጎት ሲነዳቸው ካንዱ ስፍራ ወደሌላ ስፍራ ሲዛወሩ ኖረዋል፤ ተከትሉዋቸው ሲተም የኖረው ወታደር የባላገሩን ትዳር ሲደፍር ኖሩዋል፤  አለቃ ለማ ባጤ ዮሀንስ ዘመን ብዙ ያገራቸው(የላስታ) ሴቶች ካጤው ወታደሮች ማርገዛቸውን  ለልጃቸው ለመንግስቱ ለማ አጫውተውታል፤
ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው በሚለው የቸከ አባባል ላይ አንድ ነገር ጨክኜ ልጨምር፤” ኢትዮጵያ ባሸናፊው ዱላና ባሸናፊው ቁላ የተፈጠረች አገር ናት “ ይላል ጉዋደኛየ ምዑዝ እዚህ ላይቭሰሎሞን ደሬሳ አለዝቦ የትናገረውን ላክርረውና የወንድ አያቶቻችንን ሚስት ቀምቶ ያስረገዘውን ወታደር ብሄር አናውቀውም፤ጉልበተኛ ሁሉን አድራጊ በሆንነበት አገር ውስጥ የሚስትን ጭን መጠበቅ ማሽላን በወንጭፍ አንደመጠበቅ የሚቀል ነገር እንዳልነበረ “ካገር እኖር ብየ ብሎ” ያንጎራጎረው ገበሬ ምስክር ነው፤
እንደ አገሮች ሁሉ እያንዳንዱ ቤተሰብ ያደባባይና የማጀት ታሪክ አለው፤ አባቶቻችን ጮክ በለን እንድናገረው የሚያስጠኑን የዘር ሀረግ  ለኑሮ የሚያዋጣውን ሊሆን ይችላል፤ለመኖር ሲባል ወይም ለስልጣን ሲባል የዘር ሀረግን መከለስ  የተለመደ እንደነበር ለማወቅ የነገስታቱን ታሪክ ማየት ነው፤
ከዲኤንኤ ግኝት በፊት ‘እናትነት እውነት ነው አባትነት እምነት ነው”የምትል ማለፍያ ፍልስፍና ነበረች፤የሰዎች ማንነት በማጥመቅና በጉዲፈቻ ሲቀየር   በኖረበት አገር ፤የብሄረሰብ ማንነትም እምነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ላለፉት ሃያ ማናምን አመታት በብሄር ስም ፓርቲ የሚያቆሙ፤ ምጥዋት የሚሰበስቡ ፤አላፊ ጠፊ ዝና የሚሰበስቡ ፤ አፅም የሚሰበስቡ ዜጎች፤ ወክለነዋል ሰለሚሉት ብሄር ጥራት ሲናገሩ ይህንን እውነታ ከግምት አያስገቡም፤ ስለ አንዱ ወገን ሲናገሩ ከሌላ ፕላኔት ስለመጣ ፍጡር እንጂ ምኝታንና መከራን ሲካፈል ስለኖረ ህዝብ የሚናገሩ አይመስሉም፤
ምናልባት በእምነታችን ላይ ጢኖ ጥርጣሬ፤ ትንሽ ኑፋቄ ብንጨምርበት፤ ከያዘን በሽታ እናገግም ይሆን?
Filed in: Amharic