>

“ ዘረኝነት” 

መ/ር ንዋይ ካሳሁን
ዘረኝነት(racism) ለአፍሪካውያን ብሎም ለአለም አዲስ አስተሳሰብ አይደለም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ፤ በጀርመን እና በአይሁዳውያን መካከል  የነበረውን ዘረኝነት ስናስተውል ችግሩን በብዙ አሰቃቂ ክስተቶች የተሞላ እንደ ነበር ብዙ ማሳያዎች አሉን። ዘረኝነት የተለያየ የአፈታት ዘዴ እንደሚኖረው ታሳቢ አድርገን የበላይነት እና የበታችነት ታናችና ታላቅ ጥቁር እና ነጭ በማለት በሰዎች መካከል ልዩነት የሚፈጥር ሰው ወለድ ሥርዓት ነው።አንዱ ከሌላው እንደሚበልጥ  እንደሆነ የሚናገር የሚንቅና የሚጨቁን ሲመቸው ባርያ አድርጎ የሚገዛ ሥርዓት ነው። ዘረኝነት ቀለምን ቋንቋን ባህልን መሰረት ሊያደርግም ይችላል። በአጭሩ ዘረኝነት የእኔ ዘር ከሌላው የተለየ የተሻለ ነው ብሎ ማሰብ  እና በሌላው ላይ የበላይ ሆኖ መታየት ነው። ብሔርተኝነት  (tribalism) በዚሁ የተዛመደ ሲሆን አንድ ዘር በሆኑት መካከል ደግሞ በብሔር፤በነገድ  ደረጃ ማሰብ ሲሆን  የእኔ ብሔር  ከሌላው ይሻላል  የሚል እሳቤ ሲሆን ጎሰኝነትም እንዲሁ ጎሳን ማእከል አድርጎ የሚፈጥር መደባዊነት ነው።
ብዙ ሰዎች ዘረኛ አለመሆናቸውን ይናገራሉ ዘረኞች የሚያደርጉትን እነርሱ ይደግሞታል። ሌላውን የተቃወምነውን በሌላ መልኩ እኝ የምናደርግው ከሆነ አቅም እና ጊዜ አልፈቀደልንም እንጂ ቀድሞም ያው ዘረኞች ነበርን ማለት ነው። በብዙ መልኩ በሃገራችን ያለው የፖለቲካም ይሁን የሃይማኖት መሪዎች እሳቤ በዚሁ የብሔርተኝነት ዘውግ ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል። በማሕበራዊ ሚዲይ ስማቸው አስተሳሰባቸው ከሰብዓዊነት ወይንም ሰው ከመሆን ጋር ሳይሆን ከብሔር ማንነት ጋር ከኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በጎጥ ጋር የተያያዘ መሆኑ በራሱ አስተሳሰቡ ምን ያክል እንደሰረጸ ያሳያል።
ብሔርተኝነት ጠብን የሚዘራ በሰዎች መካከል እኩል አስተሳሰብ እንዳይኖር የሚያደርግ ርካሽ ተግባር ነው። በኢትዮጵያም የተሰራው ይህው ነው። አንዱን ብሔር ከሌላው ለማጋደል ለማጫረስ ለማቃቃር ብዙ እንደተሰራ የአደባባይ ሚስጢር ነው። እሳትና ጭድ ለማድረግ ብዙ ተሰርቷል። የኢትዮጵያን ሕዝብን የሚከብደው ማጋጨት ነው እንጂ አንድ አድርጎ ማኖር አይደለም። አብሮ መኖርን ለሺህ ዘመናት የኖረበት እንጂ አዲስ የሚለምደው አይደለም። አብሮ ተከባብሮ ለመኖር ፖለቲከኞች አያስፈልጉትም። መደባዊ ወገንተኝነትነትን አስወግዶ ሕዝብ በሚበጅ አስተዳደር ሕዝብን አንድ አድርጎ ልዩነታቸውን ለአንድነታቸው ግብዓት አድርጎ ማስተዳድር ካልተቻለ ጠላትነት ሁሌም ሊቀጥል ይችላል። እንደ ኢትዮያ ባሉ ሐገራት ችግሩ በአግባብ ካልተያዘ መዘዙ ዘመናትን ሊሻገር ይችላል።
ክርስትና ከዘረኝነትም ይሁን ከብሔርተኝነት ጋር ምንም ዝምድና የለውም ። ይልቁንም አጥብቆ ይጠየፈዋል። ” ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?አንዱ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም፦ እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? ፩ቆሮ.፫፡፫”
መድሃኒታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያድን የመጣው ዘርን ብሔርን አይደለም ሰውን ስብዕናን እንጂ። ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው በሕዝብ እና በአሕዛብ አንድነት ነው። ሰዎች ሰርተውት የነበረውን ገደብ አፍርሶ ተወለደ። ሲሞት የሰው ኃጢአት ሞተ፤ ሲነሳ የሰው ትንሳኤ ሆነ። የብሔረኝነትን ግንብ ለመናድ የተዘጋጀ ልብ ያስፈልጋል። ይህ ማለት ብሔር ይጠፋል ማለት እንዳልሆነ ግን ልብ እንበል። የብሔረተኝነት ትልቁ ችግሩ መከፋፈል እና መገነጣጠል ነው። አብረው በጋራ መኖር ካልቻሉ መደማመጥ ማደግ አይችሉም።
ዘረኝነትም ይሁን ብሔርተኝነት ምንጩ ብዙ ሲሆን መሰረቱ ግን ትዕቢት ነው። በኃላፊነት ሊጠየቅ የማይችል ያልተገለጠ ትዕቢት። ከሌላው እሻላለሁ የሚል ትዕቢት። ሌላው ፍርሃት የብሒርተኝነት አስተሳሰብን ሊያመጣ ይችላል። አንዱ ሊያጠቃኝ ይችላል ባይነት። እንዲሁም ቂም የብሔርተኝነትን አስተሳሰብ ያመጣል። ይህውም አንዱን ለመበደያ መሳሪያነት ለመጠቀም ብሔርተኝነትን ሊያራምድ ይችላል።
ብሔረተኝነት ለማንም እንዳልጠቀመ ከዓለምም ከአፍሪካም ሐገራት አይቶ መማር ያስፈልጋል። በሐገራችን ለትምሕርት የወጡ ወጣት ተማሪዎች በብሔር መገደል ሲጀምሩ በየክልሉ የተለያዩ ችግሮች ማጠንጠኛቸው ብሔር ነው። መገዳደል ደግሞ ብሔረተኝነት ትልቁ መታያው ነው። በሰው መሆን ማሰብ ካልተቻለ በሰላም መኖር አዳጋች ይሆናል።
Filed in: Amharic