>
7:06 pm - Tuesday October 26, 2021

ኢህአዴግ- ከግንባር ወደ ውህድ ፓርቲ? ''(ተስፋለም ወልደየስ  - ሸዋዬ ለገሠ)

 

በኢትዮጵያ በገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ  ውስጥ “አለ” የሚባለው ሽኩቻ ስር መስደዱ ይነገራል፡፡ በግንባሩ ስር የተሰባሰቡት አባል ድርጅቶች በየፊናቸው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ፓርቲውን እንዳይሰነጥቀው ይፈራል፡፡ ኢህአዴግ ላለበት ቀውስ እንደአንድ መፍትሄ እየቀረበ የሚገኘው “ከግንባርነት ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ መቀየር” የሚል እንደሆነ ይሰማል፡፡

 የኢህአዴግ አደረጃጀት ለውጥ መፍትሔ አይሆንም- አቶ ገብሩ አስራት

የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ገዢው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግን) ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመቀየሩ ውጥን መነሳት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ወቅት በየጊዜው ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በ2001ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ሊቀመንበርነት የተካሄደው ሰባተኛው የድርጅቱ ጉባኤ ጉዳዩ ከተነሳባቸው ስብሰባዎች አንዱ ነው፡፡ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በ2005 ዓ.ም በባህር ዳር በተካሄደው ዘጠነኛው የድርጅቱ ጉባኤም ኢህአዴግን ወደ ወጥ ፓርቲ ማሸጋገር በሀሳብ ደረጃ ቀርቦ ነበር፡፡

አሁን በአረና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትን እና ቀድሞ የህወሓት አባል እንደዚሁም የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳው በባህር ዳር ተካሄዶ በነበረው የድርጅቱ ጉባኤ ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

“እንግዲህ እኔ እስከማውቀው ድረስ ኢህአዴግ ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የማሳደጉ ጉዳይ በውል የተነሳው በባህርዳር ጉባኤ ላይ ነበር፡፡ ያኔ በደንብ የተመከረበት ጉዳይም አልነበረም፡፡ ከክፍፍሉ በኋላም፣ ከ93 ዓ.ም በኋላም እንዲሁ በተወሰነ ደረጃ ግንባሩ ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ እንደሚሸጋገር ተነግሮ ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን የፓርቲው መሪ፤ በዚያን ጊዜ አቶ መለስ ነበሩ፤ የተቀበሉት አይመስለኝም፡፡ ሌሎችም ዋናዎቹ የፓርቲው አባላት ይህን ስላልተቀበሉ እንዳለ በግንባር ተሰባስቦ ነው የቆየው፡፡ ከዚያ በፊት ግን እኔ እስከማውቀው በማሊሌት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በግንባርነት እንዲቀጥል እንጂ በአንድ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲደራጅ የተወሰነበት ሁኔታ አልነበረም” ይላሉ አቶ ገብሩ፡፡

ኢህአዴግ ወደ ወጥ ፓርቲነት እንዲቀየር የማይፈልግበት ምክንያት በድርጅቱ ውስጥ “አለ የሚባለውን የህወሓትን የበላይነት ለማስጠበቅ” እንደሆነ የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፡፡ አቶ ገብሩ ዋናው ምክንያት “ይህ አይመስለኝም” ይላሉ፡፡ ግንባሩ ወደ አገራዊ ፓርቲነት እንዲቀየር ሀሳብ የቀረበውም እንደውም የህወሓት አባል በነበሩት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡

“እንግዲህ እንደሚታወቀው ኢህአዴግ የሚከተለው የፌደራሊዝም ስርዓት አለ፡፡ የፌደራሊዝም ስርዓቱ በዋነኛነት ብሔርን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ እና እነዚህ ብሔሮች የየራሳቸው አካባቢዎችን ለመምራት፣ ፓርቲዎቻቸውም እነዚያ አካባቢያቸውን ግንባር ቀደም መሪ ሆነው ለመምራት ስለሚፈልጉ ዋናው ትኩረታቸውም ወደ የግንባሩ፣ ወደየአካባቢያቸው ስለሆነ ሀገራዊውን ጉዳይን እንደ ሁለተኛ ነገር ስለሚያዩት ነው፡፡ እንደሚባለው ወሳኙ ነገር ይሄ ክልሉ ያለው የፌደራል ጉዳይ ነው ተብሎ ስለሚነገር ካልሆነ በስተቀር የአንድ ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ነው ብዬ አላየውም፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ እኮ አልገፉበትም፡፡ እንዲያውም በኦህዴድም፣ በብአዴንም በኩል የነበረው የገፋበት አልነበረም፡፡ ጉዳዩም የተነሳው የሚመስለኝ ከህወሓት በኩል ነው፡፡ አቶ ስዩም [መስፍን] እና ሌሎች ናቸው ያነሱት፡፡ ሌሎችም ያነሱ ሊኖሩ ይችላሉ ግን በውል የታወቀውና በጉባኤ ያነሳው አቶ ስዩም ነበር” ሲሉ ትውስታቸውን ያጋራሉ፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላለው የፓለቲካ ቀውስ እና በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ተካርሯል ለሚባለው ሽኩቻ እንደ አንድ መፍትሄ ከሚቀርቡት ውስጥ የገዢው ፓርቲ አደረጃጀትን መለወጥ ነው፡፡ የተወሰኑ የፖለቲካ ታዛቢዎች የኢህአዴግ አጋር ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) ከአራቱ አባል ድርጅቱ በተጨማሪነት ሊካተት ይገባል ሲሉ ገሚሶቹ ደግሞ ግንባሩ ወደ ውህድ ፓርቲነት መቀየር እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ አቶ ገብሩ የኢህአዴግ የአደረጃጀት ቅርጽ መለወጥ “የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ እና ችግር አይፈታም” ባይ ናቸው፡፡

“ሀገራዊ ፓርቲ ወይም ክልላዊ ፓርቲ መሆኑ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በእርግጥ ሀገራዊ ፓርቲ መሆኑ በግንባር የሚታየውን የድርጅቶች ሽኩቻ ሊያረግበው ይችል ይሆናል፡፡ ይሄ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ዋናው ነገር ግን ሀገራዊ ፓርቲ ብቻ መሆን ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ ሀገራዊ ፓርቲ መሆን አለበት፡፡ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የተለየ አስተሳሰብ ምጥቀት ሊያመጣ የሚችል፣ በሀገሪቱ ብዙሃን ፓርቲዎች ስርዓት እንዲኖር የሚያምን፣ በሀገሪቱ የህዝቦች ነጻነትና የስልጣን ወሳኝነት የሚያምን፣ በሀገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ የሚቋቋም ፓርቲ በአጠቃላይ ሀገራችን ያለችበትን ችግር ተገንዝቦ ወደፊት ሊገፋ የሚችል መሆን አለበት፡፡ በተለይ በዲሞክራሲ፣ በምርጫ ረገድ፣ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ሊያካሄድ የመረጠ ፓርቲ እና በአጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ የሆነ መሆን አለበት፡፡

አሁን አምባገነን ፓርቲ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ነው ያለው፡፡ ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ አስተሳሰቡ የሚወጣ ፓርቲ ነው ኢትዮጵያን ሊታደግ የሚችል እንጂ እንዲሁ ተበታትኖ የነበረ በግንባር የተሰባሰበ አምባገነን ፓርቲ በአንድ ሀገራዊ አምባገነን ፓርቲ ቢጠቃለልም ለኢትዮጵያ የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ እየፈለገች ያለችው የኢትዮጵያ የተለያዩ ፓርቲዎች፣ አስተሳሰቦች የሚወከሉበት፣ በኢትዮጵያ ያለው ብዝሃነትን የሚያስተናግድ፣ ህዝቡ እንዲወስን የሚያደርግ፣ የህዝቡ ነጻነት የሚፈቅድ ፓርቲ ነው፡፡ እንጂ እንዲሁ ከግንባር አምባገነንነት ወደ ሀገራዊ አምባገነንነት የሚሻገር ፓርቲ በኢትዮጵያ የሚያመጣ ለውጥ የለም፡፡ ለዚህም የአስተሳሰብ፣ መሰረታዊ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ እና እነዚህን በሙሉ፣ በተሟላ መልኩ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ፓርቲ ነው ኢትዮጵያን ሊታደግ የሚችል እንጂ እንዲሁ ቅርጹ፣ አደረጃጀቱ ብቻ ለውጥ አያመጣም፡፡ አደረጃጀት እና አስተሳሰቡን አንድ ላይ አጣምሮ ለውጥ ሲመጣ ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው” ሲሉ መፍትሔ የሚሉትን ይጠቁማሉ፡፡

Filed in: Amharic