>
5:39 pm - Sunday December 5, 2021

ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ጦማሪያኖችና ዜጎች "አሸባሪ" የማይባሉበት ዘመን ናፈቀኝ? (ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ)

የዕንቁ መጽሔት ዋና ኣዘጋጅ ኤሊያስ ገብሩ በሃገሪቱ ውስጥ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን የህግና የመብት ጥሰት እንዲሁም የማዕከላዊ እስር ቤት ገጠመኙን በማስመልከት የጻፈውን ጽሁፍ ያቆመው በ”ይቀጥላል” ነበር። ቀጣዩን ኣግኝተናል።እነሆ:-
———-
ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ጦማሪያኖችና ዜጎች “አሸባሪ” የማይባሉበት ዘመን ናፈቀኝ?

…..መታስር ሳይገባኝ የዚያኑ ዕለት ወደእስር ቤት እንዳመራ ተደረገ፡፡ ወደእስር ቤት ለመግባት በተቋሙ የሚደረገውን የአሰራር ሒደት ጨርሼ ለመጀመሪያ ጊዜ የእስር ቤትን በር አየሁት፡፡ በተለምዶ ‹‹ሻራተን›› ወደሚባለው ክፍል ተቃለቀልኩ፡፡ በ10 ክፍሎች ከ80 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵውያን፣ ኤርትራውያን፣ ደቡብ ሱዳናውያን፣ ሱማሌያዊውያንና ኖርዌጂያዊ ዜግነት ያላቸው የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ከሆኑት አቶ ኦኬሎና ከሌሎች እስረኞ ጋር ተቃለቀልኩ፡፡ 8 ቁጥር ክፍል ውስጥ እንድገባ ተደረገ፡፡ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ሁላችንም ወደክፍላችን ተቆጥረን ገብተን በሩ ተቀረቀረብን፡፡ የምርመራው ሂደት እና ዋስትና የተከለከልኩበት ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን አናድዶኝ ስለነበረ እና ድካም ስለተሰማኝ ፍራሼ ላይ ጋደም አልኩ፡፡ ጓደኞቼ ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣ አልባሳትና ራት አመጡልኝ፡፡ የሌሎች እስረኞችን የእስር ጉዳይ ጠይቄ ሳዳምጥ በጣምአዘንኩ፡፡ መኝታውም ሳይመቸኝ በመቅረቱ የረባ እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር ነጋ፡፡ ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ረፋድ 5፡00 ሰዓት ላይ ለምርመራ ተጠራሁ፡፡ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እጆቼ በብረት ካቴና ታሰሩ፡፡ ጓደኞቼ እና የሙያ አጋሮቼ የሆኑ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን አራዳ ፍርድ ቤት እጆቻቸው በዚሁ ካቴና ታስሮ በተመለከትኩኝ ጊዜ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ በዚህን ቅጽፈት በአዕምሮዬ መጡ፣ በራሴም ደረሶ አየሁት፡፡ …ለመርማሪዬ ቃሌን ሰጥቼ ጨረስኩ፡፡ ከሰዓት በኋላ አራዳ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ተጠራሁ፡፡ ‹‹እስላማዊ መንግሥት ለመመስረት ተንቀሳቅሰሃል›› በሚል ጉዳይ ተጠርጥሮ ከድሬደዋ ከተያዘው አንድ ወገኔ ጋር አንድ አንድ እጆቻችን በካቴና ታሰረው ወደፍ/ቤት አመራን፡፡
ጓደኞቼ መሳይ ከበደ፣ ሰባ፣ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ እና ዳዊት ሰለሞን እንዲሁም የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ካማራ ማን እና ግራፊክ ዲዛይነር አብነት ረጋሳ ከእኔ ጋር በችሎት ታደሙ፡፡
ዳኛው ስሜን፣ ሙያዬንና አድራሻዬን ጠይቆ ከመዘገበ በኋላ የተከሰስኩበትን ጉዳይ አነበበልኝ፡፡ ስለቀረበብኝ ክስ እንድናገር ጠየቀኝ፡፡ ለፖሊስ የሰጡት ቃል እንዲያያዝልኝ ሀሳብ አቀረብኩ፡፡ ‹‹ለፖሊስ ቃልህን ሰጥተሃል፡፡ አሁን ለፍ/ቤት ነው መስጠት ያለብህ›› ብሎ ደጋግሞ ነገረኝ፡፡ በሂደቱ የመጀመሪያ ልምዴ ነበረ፡፡ የዋስትና መብቴ እንዲከበር እና ጉዳዩንም ውጪ ሆኜ መከታተል እንድችል ፍ/ቤቱን ጠየኩ፡፡ ለፖሊስ ከሰጡት ቃል ጋር በሚመሳሰል መልኩ የተከሳሽነት ቃሌንም አሳጥሬ ተናገርኩ፡፡ የፖሊስ መርማሪዋም ‹‹በጉዳዩ ላይ ምርመራ ስላልጨረስን እና ከጽሑፉ ጀርባ ያለውን ጉዳይ ለማጣራት እንድንችል ዋስትና ሳይሰጠው የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ይፈቀድልን›› ስትል ለፍ/ቤቱ አመለከተች፡፡ እኔም በተራዬ በፕሬስ አዋጁ መሰረት የዋስትና መብቴን የምጠይቀው ሕገ-መንግሥታዊ መብቴን መሰረት በማድረግመሆኑ በመጥቀስ፣ ዋስትናዬን ብከለከል የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በጻፈው ጽሑፍ ወይም በተጻፈ ጽሑፍ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም›› በማለት በተደጋጋሚ ከሚገልጹት ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመናገር የዋስትና መብቴ እንዲከበር በድጋሚ ለችሎቱ ዳኛ አመለከትኩ፡፡ ዳኛውም የግራ ቀኙን አስተያየት ከተመለከተ በኋላ ‹‹ምንም እንኳን ጉዳዩ ዋስትና የማያስከለክል ቢሆንም የዋስትና ጥያቄ ላይ ገደብ አይጣልም ማለት አይደለም፡፡ ፖሊስ ለጠየቀው ተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ሳይሆን ሰባት ቀናት ተፈቅዶለታል፡፡ አሁን ቀጠሮ እንይዛለን፡፡ ግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም በስምንት ሰዓት ቅረብ›› ብሎ መዝገቡን ዘጋው፡፡
እኔም ሆንኩ ጋደኞቼ በወቅቱ ተናድደን ነበር፡፡
በነጋታው ረቡዕ ግንቦት 20 2006 ዓ.ም፣ 23ኛው የግንቦት 20 ቀን የሚከበርበት ዕለት ነበር፡፡ ንጋት ላይ መድፍ ሲተኮስ ሰማሁ፡፡ ኢቴቪ ከጠዋት ጀምሮ ያው በተለመደ መልኩ የቀጥታ ሥርጭት ፕሮግራም ሲያስተላለፍ ነበር፡፡ የተወሰኑ እስረኞች በኮሪደሩ ጥግ ላይ ወደተሰቀለው ቴሌቭዥን አይናቸውን ተክለው ይመለከታሉ፣ ገሚሱ በቀኑ ይቀልዳል፡፡ [ይህች ቴሌብዥን የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ በዚሁ በማዕከላዊ ታስረው በነበረበት ወቅት በግላቸው ያስመጧት መሆኑን ከእስር ከተፈታው በኋላ አንድ ወዳጄ ነግሮኛል፣ ወዳጄም በአንድ ወቅት ለ42 ቀናት በማዕከላዊ ‹‹ጭለማ ቤት›› እና ‹‹በሸራተን›› ታስሮ የተፈታ ነው፣ ጋዜጠኛ ግን አይደለም] እነ ጠ/ሚ/ ኃይለማሪያም ዳሳለኝን ጨምሮ የሥርዓቱ የበላይ አመራሮች‹‹የግንቦት 20 ፍሬዎች…›› እያሉ ደጋግው የሚናገሩትን ንግግር መኝታ ክፍሌ ሆኜ ሳዳምጥ አንዴም ሳቄ እየመጣ፣ አንዴም እየገረመኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ውስጤ ቆጣ እያለ ነበር፡፡ ሹመኞቹ ‹‹የግንቦት 20 ፍሬዎች …›› እንዳሉት ሁሉ ሚዛናዊ በመሆን ‹‹የግንቦት 20 ኪሳራዎች፣ ውድቀቶች፣ ጥፋቶች …›› ማለት መናገር ይጠበቅባቸው ነበር – እንደማይሉት ባውቅም፡፡
በቀጣይ የፍርድ ቤት ቀጠሮዬ የዋስትና መብቴን ለማግኘት ከሕግ ባለሙያ ጋር ለመገናኘት ከጋዜጠኛ ጓደኞቼ እና ከባልደረባዬ ፍቃዱ ጋር ሊጠይቁኝ በመጡ ጊዜ ጠበቃበመምረጥተማም አባቡልጉ እንዲሆን ተስማምተናል፡፡ ሆኖም በነጋታው ሐሙስ ዕለት ረፋድ ላይ በአንድ ፖሊስ ተጠራሁ፡፡ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ወይም ጓደኞቼ ያስጠሩም መስሎኝ ነበር፡፡ እጆቼ ላይ ካቴና ሲጠልቅ ምርመራ መሆኑ ገባኝ፡፡ አንድ ወንድ መርማሪ ክፍል አስገቡኝ፡፡ ቢሮውን እና መርማሪውን ስመለከተው ከፍ ያለ ኃላፊነት ያለው መርማሪ ፖሊስ መሰለኝ፡፡ ቢሮው ውስጥ ሶስት ቦታ የአቶ መለስ ፎቶ ግራፍ ተሰቅሏል፡፡ አንደኛም በትልቁ እጋራቸውን አነባብረው ወንበር ላይ ተቀምጠው የተነሱት ፎቶ ግራፍ ነው – ፊት ለፊቴ፡፡ ከጎኔ ያለው የምርመራ ኃላፊ ብቻውን አይደለም፡፡ በመንፈስም ቢሆን አቶ መለስ አሉ ብዬ በውስጤ አሰብኩ፡፡ በመንግሥት ተቋማት ቢሮ ውስጥ የእኚህን የቀድሞ መሪ ፎቶግራፍ የማላይበት ቦታ የት ይሆን? ሁሉም ቦታ አሉ፡፡
በተረጋጋ እና በጣም በጨዋ ቋንቋ ያናግረኝ ጀመር፡፡ እኔም የማምንበትን እመልስለታለሁ፡፡ ‹‹ዘርን ከዘር ሳይሆን ሀገርን አንድ ስለሚደርጉ ነገሮች ጻፉ›› አለኝ፡፡ እኛም ስናደርገው የነበረው ይህንኑ መሆንኑ አስረዳሁት፡፡ የዘረኝነት ጉዳይ ኢትዮጵያን ዋጋ እንዳስከፈላት፣ ዛሬም እድገታችንን ወደኋላ እንደጎተተውና ከዚህ አዙሪት ውስጥ ካልወጣን የዕድገታችን አንዱ ጸር እንደሆነም የልቤን ነበርኩት፡፡ (ኢትዮጵኖች በዘር እንድንከፋፈል እና በጎሪጥ እንድንተያይ የጊዜው የሀገራችን የኢሕአዴግ መንግሥት ክፉ ሴራ እንዳለበት በግሌ በደንብ አምናለሁ)፡፡ ሥርዓቱየዘረጋውን ጎጂ የዘረኝነት ዘር፣ ዛሬ ፍሬውን በሚጎዳን መልኩ እያጨድነው እንገኛለን ብዬ በግሌ አስባለሁ፡፡
ለየት ባለ መልኩ፣ ባነሳቸው በተወሰኑ ሀሳቦች ላይ ከማርማሪው ጋር ተስማምቻለሁ፡፡ መንግሥት በነጻ ፕሬሶች መተቸት እንደሚኖርበት አምኖልኛል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ከግሌ ፕሬስ ጠቃሚ ጽሑፎችን አንብቦ በመጠቀም ችግሮችን ማስተካከል እንደሚችልም ካካፈለኝ ሀሳብ ውስጥ አንዱ ነበር፡፡
…በፍርድ ቤት የዘገባ ተሞክሮዬ በተለያዩ ጉዳዮች፣ በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥተው የሚገቡ በርካታ ዜጎች በምርመራ ወቅት ድብደባ …(ቶርቸር) እንደሚፈጸምባቸው ለፍ/ቤት አቤቱታ ሲያቀርቡ ማድመጤን፣ መደብደባቸውንም በአካል የነገሩኝ ሰዎች መኖራቸውንና በድብደባ የሚገኝ ማስረጃም ቢሆን በሕግ ፊት ተቀባይነት እንደማይኖረው በኢትዮጵያ ሕግ ላይ መደንገጉን ገልጬ ይህ ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን እንዲያረጋግጥልኝ ነጻ ሆኜ ጥያቄ አቅርቤለት ነበር – ለምርማሪ ኃላፊው፡፡
‹‹ለምንድን እንደበድባለን?፣ ደብድበን መረጃ አንቀበልም፡፡ ውሸት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ያንተን መነጽር አውልቄ በጥፊ ብመታህ ብልግናው የእኔ ነው፡፡ እኔ እንደዚያ ስላደረኩ የተቋሙ ስም መነሳት የለበትም፡፡…›› እንግዲህ እጆቼ ታስረው፣ ምርመራ ላይ ሆኜም ቢሆን እንኳን ሙያውን ከልብ እንደሚወድ አንድ ጋዜጠኛ የተለያዩ ጥያቄዎችን መርማሪውን መጠየቅ በመቻሌ ግን ደስ ብሎኛል – ከኃላፊው ያላመንኳቸው ምላሾች ቢበዙም፡፡
በመጨረሻም ምርማሪው ‹‹ዋስ አምጥተህ መውጣት ትችላለህ›› ሲለኝ በፍ/ቤት የቀጠሮዬ ዕለት መስሎኝ ነበር፡፡ ግን ‹‹ዛሬውኑ ከሰዓት በኋላ›› ስባል መገረሜ አልቀረም፡፡ ሕጋችን እና የፍትህ ሥርዓታችን ጉራማሌ ሆኑበኝ፡፡ መታሰር ሳይገባኝ ታሰርኩ፡፡ የዋስ መብቴ መከበር ሲኖርበት በላዬ ላይ ተናደ፡፡ ለሶስት ቀናት በማዕከላዊ እስር ቤት የነበሩ ወገኖቼ ላይ የደረሰባቸውን ድብደባ ከአንደበታቸው ስሰማ እና የተደበደበ አካላቸውን ስመለከት የራሴን ጉዳይ ዘንግቼ የእነሱ ሕመም ውስጤን አመመኝ፡፡ ‹‹በሀገሬ የእስረኞች ቁጥር የሚቀንሰው እና የእስር ቤቶች ወይም የማረሚያ ቤቶች ቁጥር የሚመናመኑት መቼ ይሆን?›› ብዬ ውስጤን ጠየኩት፡፡ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ጦማሪዎችና ዜጎች “አሸባሪ” የማይባሉበት ዘመን ናፈቀኝ?
….በጣም ረጋ ብሎ ለሚያናግረኝ መርማሪ የመጨረሻ ጥያቄን አቀረብኩለት፡፡ ‹‹እውነት፣ በሽብር ጉዳይ እየተባሉ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተጠርጥር የሚመጡ ዜጎችና በፍርድ ሂደት የተፈረደባቸው ወገኖች በሙሉ አሸባሪ ሆነው ነውን?፣ አሁን አሁን እኮ፣ “ሽብር” የሚባለው ቃል በራሱ ለአፍ እየቀለለን መጣ! …›› ከወንበሩ ብድግ ብሎ፣ በመጠኑ ፈገግ እያለ ‹‹በል ውጣልኝ›› አለኝ፡፡ እኔም ክፍሉን ለቅቄ ወጣሁ፡፡
በዕለቱ ከምሳ ሰዓት በኋላ በድጋሚ ተጠራሁ፡፡ ዋስ የሚሆነኝን ሰው እንድጠራም ነገሩኝ፡፡ ለባልደረባዬ ፍቃዱ እንዲደውሉልኝ አስደረኩ፡፡ እሱም ብዙም ሳይቀይ መጣ፡፡ ወዲያው ‹‹የመጽሔቱ ጉዳይ እሱንም ስለሚመለከተው እሱ ዋስ መሆን አይችልም፡፡ ሌላ ሰው አስብ›› ተባልኩ፡፡ ይህንን በተባልኩበት ወቅት እቃዎቼን ለመውጣት አሰናድቼ እና ለሶስት ቀናት አብሬያቸው የነበሩ ወገኖቼን በፍቅር ተናብቼ ነበር፡፡
ድጋሚ በመጀመሪያ ቃሌን የሰጠሁበት ክፍል ተጠራሁ፡፡ ፍቃዱ ቆጭ ብሎ ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ነበር፤ እሱ እንደነገረኝ ከሆነ ‹‹አንተም ቃልህን መስጠት አለብህ›› ተብሎ ነበር፡፡ …የ30 ሺህ ብር ዋስ ተብሎ በተሰናዳው ፎርም ላይ ሁለታችንም ፈረምን፡፡ ‹‹ስንፈልግህ እንጠራሃለን፡፡›› ተባልኩ፡፡ በመጨረሻም በድጋሚ ወደ እስር ቤቱ ግቢ አምርቼ እቃዎቼን ካወጣሁ በኋላ ተፈትሼ እና አስፈትሼ ማዕከላዊን ተሰናበትኩት፡፡
ነገም ሆነ ከነገወዲያ፣ በእኔም ሆነ በሌሎች ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች ላይ ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር በተያያዘ የምንሰራቸው ሙያዊ ሥራዎችን ተከትሎ ምን ሊደርስ እንደሚችል በግሌ እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ተንዶ እና ተሸራርፎ በገሃድ አይቻለሁ፡፡ አሁን ላይ ፕሬሱ ላይ እየተደረጉ ያሉ አካሄዶች በሀገራችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታችን ትልቅ አደጋ ላይ እንደሚገኝም ይበልጥ እንድረዳ አድርጎኛል፡፡ ይህንን መብት በደንብ ለማስከበር ግን ሁላችንም በድፍረት መሥራት እና መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ እየፈሩ ጋዜጠኝነት የለም! ይህ የልቤ ቃል ነው፡፡
በቅርቡ እንኳን የቅርብ ጓደኞቻችን እና የሙያ አጋሮቻችን የሆኑ ሶስት ጋዜጠኞች እና ስድስት ጦማሪያን በሽብር ጉዳይ ተጠርጥረው በዚህ በነበርኩበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ‹‹ጨለማ ቤት›› በሚባለው ክፍል ውስጥ አሁንም ድረስ በአሳዛኝ መልኩ ታስረው ይገኛል፡፡ በሶስት ቀናት የእስር ጊዜያቶቼ ወቅት ከታሩት ውስጥ አንዳቸውን እንኳን ባገኛቸው፣ በዓይኔ ባያቸው ብዬ ባልምም ሳይሆን ተመልሻለሁ፡፡ ከእሱ ጋር በጨለማ ክፍል ታስረው የነበሩ ሰዎች ግን አግኝቼ የማነጋገሩን ዕድል ግን አግኝቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር ብርታት እና ጥንካሬን ይስጣቸው!
በዚህ አጋጣሚ፣ እስሬን ተከትሎ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የሙያ አጋርነታችሁን፣ ፍቅራችሁን፣ ተቆረቋሪነታችሁን፣ ጓደኝነታችሁን፣ ወንድም እና እህትነታችሁን፣ ቤተሰባዊነታችሁን፣ ወዳጅነታችሁን …በተለያዩ መንገዶች ላሳያችሁኝ በሙሉ ከልቤ አመሰግናችኋለሁ፡፡ስለእኔ የሚሰማችሁን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የገለጻችሁት ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን፣ አናንያ ሶሪ፣ ነብዩ ሐይሉ፣ አቤል ዓለማየሁ፣ መልካም ሞላ፣ ብስራት ወ/ሚካኤል …አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው)፣ እስከዳር አለሙ፣ መስከረም አበራ፣ ይድነቃቸው ከበደ፣ ጆ ማን መርጉ…ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ (በትዊተር) በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡ እንዲሁም የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ እናካሳሁን ይልማ (የአሁኑ ኢሳት ጋዜጠኛ) ስለመልካም ምክራችሁ አመሰግናለሁ፡፡ በተጨማሪምጋዜጠኛ ስለሺ ሐጎስ በታሰርኩ ምሽት የላክልኝ ኮንፎርት ብርድ ልብስ ሙቀቱ ተመችቶኛል፡፡ Cheers! ሌሎች በዚህ ጽሑፍ ላይ ስማችሁን ያልጠቀስኳችሁ በሙሉ 10Q!
ማዕከላዊ ድረስም ተመላልሳችሁ የጠየቃችሁኝ እና ‹‹አይዞህ!›› በማለት ያበታታችሁኝን ጓደኞቼን፣ ወዳጆቼንና ቤተሰቦቼን በሙሉ በድጋሚ ላመሰግናችሁ ወደድኩ፡፡ ዳዊት ሰለሞን አምስት ጊዜ ተመላልሶ በመጠየቅ ሪከርድ ይዟል፡፡ lol ልትጠይቄኝ መጥተችሁ ምርመራ ላይ በመሆኔ ሳቢያ እና ከተፈታሁ በኃላ (መፈታቴን ሳታውቁ) ልትጠይቁኝ ለመጣችሁና ለመምጣት አቅዳችሁ ለነበራችሁት ወዳጆቼ ምስጋና አቀረብኩላችሁ፡፡ ‹‹ኤልያስ፣ መታሰሩም አግባብ ነበረ›› ያላችሁ ወገኖቼም በሙሉ በሀሳብ ነጻነት ልቤ ስለሚያምን ሀሳባችሁን እንዳከበርኩላችሁ ብታውቁት ደስ ይለኛል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና፣ እስከመጨረሻው ድረስ እንወያይ፣ እንከራከር፣ እንሟገት …ጠንክረን እንቁም!
ከዚህ በኋላ በማዕከላዊ ሸራተን እስር ቤት ውስጥ ስለገጠሙኝ ሁነቶች አንድ ወይም ሁለት መጣጥፍ አስብነባችኋለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Filed in: Amharic