>
8:34 pm - Wednesday February 8, 2023

ሼኹን በምን መልኩ እናስባቸው? (አሰፋ ሃይሉ)               

– አ ል ረ ካ ኹ ም !

ስለዚህ ሰው ብዙም ሃተታ አላበዛም፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በሃገራቸው በሣዑዲ መንግሥት በሙስና ተጠርጥረው ታሥረዋል፡፡ በእርግጥ ከዚህም ቀደም በክሊንተን አድሚኒስትሬሽን ዘመን –  እኚሁ ሰው – በ‹‹መኒ ላውንድሪንግ›› ተጠርጥረው በአሜሪካኖቹ ተከስሰው – በጠበቃ ተከራክረው ነፃ መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ አሁንም መጨረሻቸው በነፃ መለቀቅ ይሁን ወይስ ሌላ በትክክል አይታወቅም፡፡

እና አሁን ስለዚህ ሰው ምን አነሳሳኝ? የተለያዩ ሰዎች የሚሰነዝሩት ሃሳብ ነው ያነሳሳኝ፡፡ አንዳንዱ ከሰዉ በላይ – እዝጌሩ በታች – አክብዶ ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡ ከሌላው ደግሞ – ከንቧ በታች – ከቆንጆይቱ አርቲስት ጎን – ከሸራተን በስተጀርባ – ከሚቆፍሩት ወርቅ በታች – እጅጉን ወደታች አርቆ – መቀመቃዊ ህልውናን ይቸራቸዋል፡፡

እና እኚህ ሰው በእርግጥም አወዛጋቢ ማንነትን የተላበሱ ናቸው፡፡ በሃገራችንም ‹‹ዌልዚ ማን›› ምን የመሠለ እንደሆነ ብቸኛ ማጣቀሻ የሆኑ የለየላቸው የዲታ ሪፈረንስ ናቸው፡፡ እና ይህን ሰው ታዲያ በምን ዓይነት እንሳለው? በትክክል ምን ዓይነት ሰው ነው? እኛስ እንዴት ብለን፣ የትኛውን ኢሜጅ እንቀበል? የቸገረ ነገር ሆነብንኮ!!

ቆይ እስቲ ለጊዜው የሼኹን ነገር እዚህ ላይ ልግታው፡፡ እመለስበታለሁ በኋላ፡፡ አሁን – በመጀመሪያ በቀጥታ – ካነበብኩት ልጀምር – እንደ አካደሚክ ባግራውንድ ዓይነት፡፡ የምጀምረው – ከጥቂት ዓመታት በፊት – አንድ ሠሎሞን ማሞ (?)– በተባለ ኢትዮጵያዊ እጩ የዶክትሬት ተመራማሪ ዋነኛ አጥኚነት – በሆላንድ ሃገር – ማስትሪሽት ዩኒቨርሲቲ የተሰራ – የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለበትን ትክክለኛ ደረጃ የሚዳስስ – እና ከጎረቤት የአፍሪካ ሃገራት ጋር – የዚህችን ሃገር እውነተኛ እያነፃፀረ እውነተኛውን ሃቅ የሚያስቀምጥ– የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ማሟያ ቴሲስ ነው፡፡

ያ ቴሲስ – በርካታ የውጭ ሃገር ምሁራን በአማካሪነትና በተጓዳኝ ከላሽነት የተሳተፉበት – ደረጃውን የጠበቀ ጥናት ነው፡፡ እዚያ ላይ – የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ (ግዝፈቱንና አጠቃላይ የእድገት ደረጃውን) – በታወቁ ዓለማቀፍ መስፈርቶች አንፃር በዝርዝር እየለካ – ከጎረቤቶቻችን ከእነ ግብጽና ኬንያ ጋር እያወዳደረ ያሳየናል፡፡ የመንገድን፣ ስልክን፣ ጤናን፣ ት/ትን፣ ኑሮን፣ አመጋገብን፣ ምርትን፣ ንግድን፣ ኢንተርኔትን፣ መኪናን፣ ፋብሪካን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢን፣ የኤሌክትሪክ ኃይልን – እና ሌሎችንም ነገሮች ሁሉ እያወዳደረ፡፡ እናም – በሁለት ዲጂት አደገ እየተባለ የሚነገርለትን የሃገራችንን ኢኮኖሚ – ከጎረቤቶቻችን ሃገራት – በምን በምን ነገሮች እጅጉን አሽቆልቁሎ እንደምናገኘው – በምንስ በኩል ተመስገን ብንል እንደማንኮነን – በእውነተኛ አሃዞች እያስተነተነ ያስረዳል፡፡

ችግሮቹን ማስረዳት ብቻም ሳይሆን – መፍትሄዎቹንም ያመላክታል፡፡ ችግሮቹ ኢትዮጵያ ለኢንቬስትመንት አመቺ ያለመሆኗን ያመጡ ናቸው፡፡ በርካታ ናቸው፡ ከመፍትሄዎቹ ውስጥ ደግሞ፡- የሃገሪቱ ሠላም እርግጠኛ መሆን ማስፈለግ፣ የባከነው ዲሞክራሲ መቃናት አስፈላጊነት፣ የሙስናው ሃይቅ መድረቅ አስፈላጊነት፣ የመሠረታዊ ኢንፍራስትራክቸር መዘርጋት ቀዳሚነት፣ የፖለቲካው ከባቢ አየር መረጋጋትና ክፍት መሆን ግድ ባይነት፣ የመነጠቅ፣ የመፈናቀልና፣ የረብሻ ስጋት – ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው – ቀጥታ የውጭ ኢንቬስትመንት ከሚያደርጉ ባለሃብቶች አዕምሮ – ጨርሶ መፋቅ እንዳለበት፣ እና ወዘተ ወዘተ ወዘተ ሌሎችንም በርካታ ነገሮች በሃቅ እና ለሃቅ ግልጽ አድርጎ ያስረዳል፡፡

ታዲያ የሚገርመው ያ ጥናት – ገና በ2003 – ስለግብጽና ኬንያ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ውጥንቅጥ የተነበየውና የዳሰሰው እውነታና ትንበያዎች ሁሉ – ጊዜያቸውን ጠብቀው እውን መሆናቸውን ጭምር ስናይ ነው፡፡ እና አሁን ታዲያ ይህ ጥናት ከሼህ ሞሃመድ አልአሙዲ ጋር ምን አገናኘው?? ብሎ ለሚጠይቅ መልሱ እነሆ፡፡

ያ የምሁራን ጥናት – ምን ይላል? ኢትዮጵያ ከብዙ ከተዘረዘሩ ለውጭ ባለሃብቶች አመቺነት አስፈላጊ ከሆኑ ነጥቦች አንፃር ስትመዘን – እነዚያን ችግሮቿን ለመሻገር – የተወሰነ መውተርተርና ፍላጎት ብታሳይም እንኳ – ነገር ግን – አሁን ባለው የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መረጋጋት ቁመናዋ – ፈጽሞ – ፈጽሞ – ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቬስተሮች – አመቺ አይደለችም – ብሎ ነው የሚደመድመው፡፡ እና በዚህ ድምዳሜው (የጥናት ውጤቱ) በሃገራችን ኢንቬስት የሚያደርጉ የውጭ ሃገራትን ሲጠቅስ ትልቁ ድርሻ የሳዑዲ መንግሥት ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት መሆኑን ይናገራል፡፡ ከሃገሪቱ የውጭ ኢንቬስትመንት 70 በመቶው – የሣዑዲ ነው፡፡

እንዴት? እንዴትማ ጥሩ ነው፡፡ እንዴታው እኚሁ ሼኹ ናቸው፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት በኢትዮጵያ ምን ያህል እንደሆነ ያ ጥናት ሲያስቀምጥ – 70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የውጭ ኢንቬስትመንት – በእኚሁ በአንዱ ሰው እጅ ባሉ ኢንቬስትመንቶች ብቻ እንደሚከወን – እኚያም ኢንቬስተር – ሳዑዲያዊ ዜግነት ያላቸው – ሼኽ ሙሃመድ አል አሙዲ ብቻ እንደሆኑ – ያም ቢሆን – ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቬስተሮች አመቺ በመሆኗ የተገኘ የውጭ ኢንቬስትመንት ሣይሆን – ሰውየው –  ኢትዮጵያዊ ትውልድ ስላላቸው – በዘር ሃረግና በሃገር ስሜት ተስበው ያፈሰሱት ኢንቬስትመንት እንደሆነ – እንጂ – እንዲያ ባይሆን – ኢትዮጵያ ያን ሁሉ መዋዕለ ነዋያቸውን ይዘው እንኳን ኢንቬስት ሊያደርጉ – ባጠገቧ ዝር እንደማይሉ – ጭምር – ይናገራል – ያ ጥናት፡፡

ያኔ ጥናቱን ሳነበው ብዙ ያላወቅኩትን ነገሮች ነበር የፈነጠቀልኝ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ከምንደሰኮረው በተሻለ – ከጎረቤቶቻችን ጋር አነፃጽሮ እውነታውን ለመረዳትም ለፈለገም እጅግ የሚደንቅ ጥናት ነበር፡፡ ግን ግን – በሼኹ ላይ የያዘው አቋም – ‹‹ለምን ኢንቬስት አደረጉ?›› የሚል ወቀሳዊም፣ ንዴታዊም ቃና ያለበትም መስሎኛል ደሞ፡፡

እንዴ? ደግሞስ ነጋዴ መሆናቸው ይረሳል እንዴ! ለጽድቅ እኮ አይደለም ኢንቬስት የሚያደርጉት፡፡ ለጽድቅ ነበር እንዴ – አልታድን አፍርሰው – የግላቸው ለማድረግ –  እንዲያ ከእነ ታደለ ይድነቃቸው ጋር – ስንት መንገድ የተዳረሱት? ጽድቅ ቢሆን ነው እንዴ በኢንቬስትመንት ውስጥ የሚቆዩት? ለጽድቅ ቢሰሩ ነው እንዴ – ሃብታቸው ከቀን ቀን እየጨመረ የመጣው? እና ብዙው ነገር ግራ አጋብቶኝ ነበረ፡፡

ግን ግን የሆነስ ሆነና – የቻሉትን ይጠቀሙም፣ አይጠቀሙም – ይለፍላቸውም፣ አይለፍላቸውም – ይህች ሃገር እርሳቸውን ጠቅማቸውም ይሁን – አሊያም እርሳቸው ይህችን ሃገር ጠቅመዋት – አሊያም ተጠቃቅመውም ይሁን አይሁን –  አሁን ግን ከሰሞኑ – ከብዙ ሰው አንደበት – ስለእርሳቸው እጅግ የተራራቁ ነገሮችን መስማቱ ያስገርማል፡፡ ቶታል ኤክስትሪምስ –  እጅግ የተራራቁ ተቃራኒ ዋልታዎች ያሏቸው አስተያየቶች ናቸው – ስለእርሳቸው የሚሰሙት፡፡ እና የቱን እንመን? ቸገረን እኮ!

– አንዴ ለብሰውት በአደባባይ ‹‹አገሌን ምረጡ!›› እያሉ በቀሰቀሱበት በዚያ የንብ ቲሸርት ማሊያቸው እንደሣልናቸው እንቅር? ወይስ. . .

– በሃገራችን ያሉ የተለያዩ ታዋቂ አርቲስቶችን በመደገፋቸው፣ ሲታመሙ በማሳከማቸው፣ የተቸገሩትን በመርዳታቸው፣ ቆሼ ለተደረመሰባቸውም፣ አሲድ ለተደፋባት አሚናትም፣ ለእግር ኳስ ተጫዋቾችም፣ ለበረኞችም፣ ለሌሎችም በሚሰጡት ዘካዎች እንመዝናቸው? ወይስ . . .

– የተለያዩ ከመንግሥት ጋር ተሻርከው (ማለቴ እርቀ-ሰላም አውርደው) የሚመጡ ታዋቂ አርቲስቶችን ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ፣ ውድ የመኪና ስጦታዎችን እና በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ሽልማቶችን በመስጠታቸው እናስባቸው? ወይስ . . .

– እንደሚወራው ሃሜታ . . . በከተማችን አለች የተባለችን ቆነጃጅት ሁሉ . . . እንዲያው በቸርነታቸው . . . አሉ የተባሉ ዘመናዊ መኪኖችን በማደላቸው . . . ወይም እንዲያ እየተባለ በሚወራባቸው . . . አንዳንዴም በፎቶዎች ሁሉ ሳይቀር እየተደገፈ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጭባቸው አሉባልታ እንሳላቸው እርሳቸውን? ወይስ . . .

– እንደሻኪሾሶ ወርቃቸው ካማረው፣ እንደሸራተናቸው ከሚያስጎመጀው፣ እንደሚድሮክ ከሚያማልለው፣ ወይስ እንደኩሪፍቱ ከሚያንቀባርረው የጣና መከዳቸው፣ ወይስ በዓመት በሚሊዮን ዶላሮች ከሚያፈሱትም፣ ከሚያፍሱትም እንደ አማላይ አይነኬ እህትማማች ድርጅቶቻቸው፣ ወይስ እንደግዙፉ አማላዩ ባንካቸው፣ ወይስ እንደአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ሰፋፊ ሁዳዶቻቸው፣ ወይስ እንደገነቡት የጎንደሬው ፎቃቸው፣ ወይስ አጥረው እንዳስቀመጡት የፒያሳ ሜዳቸው፣ ወይስ እንደግችሌ ሜዳቸው፣ ወይስ እንደስጋ ማሸጊያቸው፣ ወይስ እንደ ኤልፎራ ዶሮና እንቁላል እርባታቸው፣ ወይስ እንደመርቲያቸው፣ ወይስ እንደሩዝ እርሻቸው፣ ወይስ እንደእንስሳ መኖ ለሳዑዲ እንደሚያርብ ሰፊ ሁዳዳቸው፣ ወይስ እንደተለያዩ የግልና የጋራ የተንቀባረሩ ኢንቬስትመንቶቻቸው –  በየትኛው መነጽራችን እንመልከታቸው እኚህን – የደላቸው እና አሁን ያልደላቸው – ትልቅ ሰው???? ወይስ . . .

– አንዴ (በሃሜት ሲወራ) የናጠጠው ሃብታም – የዲ ኤች ገዳ ባለቤት – ነፍሱን ይማርና – አለ እንደተባለው – ‹‹እኛ እሳቸው ሳላሉ ድሆቹ እሺ የት ሄደን ሰርተን እንብላ?›› አለ እንደተባለው – እንደ እርሱ – እና አከሰሯት፣ ምናምን እየተባለ እንደተወራው – እንደሣራ አምፖል – እንደዚያ አድርገን እንመልከታቸው – ወይስ እንደምንወዳት – እና እያየናት አጣናት እንዳልናት – እንዳለፈላት ተዋናይት – ማን ነበር ስሟ ?? – ኤጭ ሲፈልጉት ደሞ ስም አፍ ላይ አይመጣም እኮ – አፍ ሲያመልጥ፣ ፀጉር ሲመለጥ አይታወቅም እኮ – አይይይይ…! ኤኤጭጭጭጭ . . .! ምነው ሸዋ! እንዴት እንዴት ነው ነገሩ? አልበዛም ከዚህ በላይ?! በዛ እንጂ! በቃ! ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም . . . ባይሆን ሃብት ቢበዛ ግን ይጫናል –  መሠለኝ –  በምናባቴ አውቄው –  እኔ ለራሴ መናጢ ደሃ!! አ ል ረ ካ ኹ ም !  አ ል ረ ካ ኹ ም !  አ ል ረ ካ ኹ ም !  አ ል ረ ካ ኹ ም !

ለሼኹም፣ ለዚህችም ሃገር፣ ለእኛም፣ ለሁላችንም፣ ለጠላቱም ለወዳጁም፣ መልካሙን ሁሉ ተመኘሁ፡፡ ቻው

Filed in: Amharic