>

የዘረኝነትና ብሔርተኝነት አዙሪት?! ሟቹም ገዳዩም እኛው ነን! (በአለማየሁ አንበሴ)

የዘረኝነትና ብሔርተኝነት አዙሪት?!

(ውጥረት–ስጋት—ፍርሃት—አለመተማመን)

• ዝም ብለን “ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ሀገር ነች” ማለቱ አያዋጣም
          • የፖለቲካ አስተዳደር ምልክቶች፣ግንብ ሆነው ሊያራርቁን አይገባም
          • አሁን እየታየ ያለው የብሄር ግጭት አዝማሚያ እጅግ አሳሳቢ ነው
          • ብሔርተኝነቱ በሁሉም አቅጣጫ ፈሩን እየለቀቀ ነው

ከሰሞኑ በአገሪቱ የተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ ብሄር ተኮር ግጭቶች፣ የአራት ተማሪዎች ህይወት መጥፋቱን መንግስት አረጋግጧል፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀልና በመቶዎች ለሚቆጠሩቱ ህልፈት ምክንያት የሆነው፣ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የድንበር ግጭት ዳግም አገርሽቶ 90 ያህል ሰዎች ለሞት  መዳረጋቸውም ታውቋል፡፡ መንግስት እንደ ወትሮው፤አጥፊዎችን ለህግ እንደሚያቀርብ ያስታወቀ ሲሆን በግጭቱ ለሞቱት ዜጎች ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማውና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንደሚመኝ ገልጿል፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤የመንግስት ሃላፊነት የሀዘን መግለጫ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ሞትም ሆነ ጉዳት በዜጎች ላይ እንዳይደርስ መከላከል ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
ግጭቶችን ተከትሎ በየክልሎቹ ተቋርጦ የሰነበተው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሰሞኑን መቀጠሉን ት/ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን ከየዩኒቨርሲቲዎቹ ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሄደው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ተደርጓል፡፡ ይሄ ማለት ግን ዘርና ብሄር ተኮር ግጭቶች ከዚህ በኋላ አይከሰቱም ማለት አይደለም፡፡ ብዙዎች ጉዳዩ ስጋት ላይ እንደጣላቸውና ፈጣን መፍትሄ ማበጀት ካልተጀመረ፣አገሪቱ ወደ ጥፋት መንገድ ማምራታችን አይቀሬ ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡
ለመሆኑ በአዲሱ ትውልድ አዕምሮ ውስጥ የተዘራውን ክፉ የጎሰኝነትና ዘረኝነት መርዝ እንዴት ማርከስ ይቻላል?  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የሃይማኖት አባቶችንና ምሁራንን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንዲህ አጠናቅሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄዎች!!

“ብሔርን ማንም መርጦ አልተወለደም”
ፓስተር ፃድቁ አብዶ የኢ/ወ/አ/ፕሬዚዳንት

ሁሉም ወገን ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲይዘውና እንዲመለከተው ስንመክር ቆይተናል፡፡ ብሄርተኝነቱ በሁሉም አቅጣጫ ፈሩን እየለቀቀ ነው፡፡ የራስን ማንነት ማወቅ መልካም ቢሆንም ያለፈን ታሪክ ለዛሬ የቁርሾ መነሻ ማድረግ ግን አይጠቅምም። እኔ እንደሚመስለኝ፣ ልዩነታችንን ከሚገባው በላይ አስፍተን ወስደናል፡፡ ይሄ ነው አሁን እየጎዳን ያለው። ሰው በአርአያ ሥላሴ ሲፈጠር ራሱን እንዲገዛ ነው። ግን ራስን መግዛት ካልተቻለ ደግሞ ሰላምን ማደፍረስ በጣም ቀላል ነው፡፡
አሁን የተፈጠረው ችግር በአንዳንድ ቦታዎች የብሄር መልክ ያለው ይምሰል እንጂ ቀውሱ ሁለንተናዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ እምነቶች ውስጥም ችግር አለ፡፡ መንግስትም ጋ ችግር አለ። ሌላውም ጋ ችግር አለ፡፡ ውሉ የጠፋው እነዚህን ችግሮች እንዴት እንፍታ ሲባል ነው፡፡ ለችግሮች ሁነኛ የአመራር መፍትሄ መስጠት ሲቻል ነው ሰላም የሚሰፍነው፡፡  አንድ ሰው መጀመሪያ ሰው መሆኑን መቀበል አለበት፡፡ ብሄርን ማንም መርጦ አልተወለደም፡፡ የሰው ዘር ከአንድ መሰረት የመጣ ነው፡፡ በብሔር መለያየት ከሰው ደረጃ ሊያወርደን አይገባም፡፡ በዚህ ደግሞ ሰላም ማጣት የለብንም፡፡
አንዳንዴ ወጣቶቻችን ትዕግስተኛ መሆን አለባቸው፡፡ ጎረቤቶቻችንን ብንመለከት ብዙ እንማራለን፡፡ ጋዳፊ አምባገነን ቢሆኑም ሃገሪቱ በሳቸው ጊዜ ሰላማዊ ነበረች፡፡ አሁንስ? ብለን ብንጠይቅ፣ ለዜጎቿ የማትሆን ሀገር ሆናለች። ስለዚህ ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡ ሰው ከራሱ ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ያኔ ነው እርስ በእርስ መተሳሰብ መፍጠር የምንችለው፡፡ ፖለቲከኞች ከአፋቸው የሚወጣውን ቃል መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ እውነተኛ የሀገር ሽማግሌዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እኛ የሃይማኖት አባቶችም አምላክን እንወክላለን እስካልን ድረስ ለእውነት መቆም አለብን፤ ለእርቅ መቆም አለብን። በስለናል የምንል ሁሉ ትንሽ ረጋ ብለን ስለዚህች ሀገር ቀጣይ እጣ ፈንታ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ቤተ እምነቶች መፀለይ አለብን፡፡
አንዳንዴ ዝም ብለን ችግሮችን እያየን፣ “ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ሀገር ነች” ማለቱ አያዋጣም። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእስራኤል በላይ በቃል ኪዳን ሀገርነት የተጠቀሰ የለም፡፡ ችግር ሲጀምር በትንሹ ነው፡፡ እሱ እየሰፋ ሄዶ ነው የማንወጣው አዙሪት ውስጥ የሚከተን፡፡ ከኛ ቀድመው መጥፎ ሁኔታ ውስጥ የገቡ ሀገራትን መመልከት አለብን። ትዕግስት ያስፈልገናል፡፡ መታገስ ደስ ላይል ይችላል፤ ግን ፍሬው ጥሩ ነው፡፡

“መንግስት ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ሥራ መስራት የለበትም”
አቡነ ቀውስጦስ

የሠላም ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህም በሃገራችን ሠላም እንዲሠፍን ፈጣሪን በምህላ ፀሎት እየለመንን ነው፡፡ የኛ ትልቁ መሣሪያችን ይሄ ነው፡፡ አደራ ተሠጥቶታል የተባለው መንግስት ደግሞ ሃገሪቱን በእኩልነት መምራትና ማስተዳደር አለበት፡፡ አጥፊዎችን ለህግ እያቀረበ ስርአት ማስያዝ አለበት፡፡ ተጎጂዎቹን ደግሞ ቦታ ቦታ ማስያዝ ይገባዋል፡፡ ዝም ብሎ ከዳር ሆኖ እንደ ማንኛውም ሰው አዝኛለሁ ቢል አይሆንም፡፡ ሃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ እንደ ሌላ ሃገር መንግስታት፣ እሱም አብሮ የሃዘን መግለጫ ማስተላለፍ አይጠበቅበትም። ሃዘኑ እንዳይደርስ የመከላከል ስራ መስራት ግዴታው ነው፡፡ አንድነትን ማፅናት ስራው ነው፡፡ ድሮም የተፈራው ይህ አይነቱ ግጭት እንዳይመጣ ነበር፡፡ በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል፡፡ የፈራነው ነው እየደረሰ ያለው። አሁንም ሳይስፋፋ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ሃላፊነት ያለበት ደግሞ መንግስት ነው፡፡
አዝማሚያው ከተስፋፋ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው፡፡ እኔ በ1999 ስለዚህ ጉዳይ የፃፍኩት መፅሐፍ አለ፡፡ በወቅቱ አስጊ መሆኑን ተናግረናል፡፡ መንግስት ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ሥራ መስራት የለበትም፡፡  አንዳንዶቹ ቤተክርስቲያናችንን እያፈረሱ ነው፡፡ ይሄ  ከፈጣሪ ጋር ያጣላናል፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው እየሆነ ያለው፤ እያለቀስን ነው። መንግስት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡
ይሄን ስንል የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናቸው እንባላለን፡፡ ይሄ ደግሞ አያዋጣም፡፡ ሃገሪቱ አንድነቷ ፀንቶ፣ ልማት ሰፍኖ፣ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ማየት ነው ምኞታችን፡፡ ስልጣን የያዘ አካል ደግሞ በሥነ ስርአት መምራት አለበት፡፡
አጥፊዎችን ችላ እያለ፣ ህዝብን እርስ በእርስ ማፋጀት የለበትም፡፡

“መንግስት ለዜጎች ህይወት ጥበቃ ማድረግ አልቻለም”
አቶ አመሃ መኮንን
(የህግ ባለሙያና የሰመጉ አመራር)
በዚህ ሃገር ንፁሃን ዜጎች በየምክንያቱ የሚሞቱበትን ሁኔታ መስማት ከጀመርን ቆይቷል። በ2008 ዓ.ም በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ህዝባዊ አመፆች እየተቀሰቀሱ፣ አመፆቹን በኃይል ለማስታገስ በሚደረግ ሙከራ ብዙ ወጣቶችና ህፃናት፣ ተማሪዎች፣ ገበሬዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች የሚሞቱበትን ሁኔታ ስንሰማ ነበር፡፡ ይሄ እንደ ሀገር ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግድያዎችና ውድመቶች ደግሞ በተለይ ድርጊቱን ፈፅመዋል፣ አስፈፅመዋል በሚባሉ አካላት ላይ የህግ እርምጃ ሲወሰድ አናይም፡፡ አሁን ደግሞ መልኩ ተለውጦ ብሄር ተኮር ግጭቶች፣ ግድያዎች ሲፈፀሙ እያየን ነው፡፡
አሁንም ንፁሃን ዜጎች በብዛት ህይወታቸውን እያጡ ነው፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ዋጋ ህይወት ነው፡፡ መንግስትም ከሁሉም በላይ ጥበቃ ማድረግ ያለበት ለህይወት ነው፡፡ ግን መንግስት ይሄን ማድረግ አልቻለም፡፡
በአጠቃላይ መንግስት የዜጎችን የመኖር መብት በዓለማቀፍ ደረጃ ማስጠበቅ አልቻለም፡፡ እስካሁን ድረስ በመንግስት በኩል እያየን ያለነው፣ “ሃዘናችንን እንገልፃለን” የሚሉ መግለጫዎችን ነው፡፡ ይሄ ግን ባለስልጣናት በህዝቡ ቅቡልነት ያስገኝልናል ብለው የሚያደርጉት ካልሆነ በስተቀር ችግሩን በመቅረፍ ረገድ የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ከተፈለገ፣ አንደኛ፣ የችግሩን መንስኤዎች፣ በቅንነት በጥናት መለየት ያስፈልጋል፡፡  ምናልባትም ገለልተኛ ወገኖች የተሳተፉበት ምርመራ  ማድረግ፣ ህዝቡ ራሱ የሚያምንበትን የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ። ከመፍትሄዎቹ አንዱ ደግሞ በእንዲህ አይነት ግድያዎች እጃቸው ያለበት የመንግስት አካላትን ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ በሶማሌና በኦሮሚያ ግጭት፣ የፌደራል መንግስት ሊቆጣጠረው ያልቻለው ኃይል፣ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እውነትስ ከመንግስት አቅም በላይ ነው ወይ? ይሄን መንግስት ማብራራት አለበት፡፡ አሁን እየሰማን ያለነው ግድያውን ወይም የሁነቱን ውጤት ብቻ ነው፤ ሌላውን ህዝብ እያወቀ አይደለም፡፡ ህዝብ ማወቅ አለበት። በህዝብ ላይ ጉዳት እየደረሰ ያለው መንግስት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ባለመሆኑ ነው፡፡
ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችም ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል አለበት፡፡ የችግሩ መፍትሄ የሚጀምረው ግን በቅንነት ጉዳዩን ማጥናትና ማጣራት ሲቻል ነው። ከሚደርሰው ጉዳት አንፃር በመንግስት በኩል ተመጣጣኝ ምላሽ  እየተሰጠ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ግራ መጋባትና ስጋት ውስጥ ነው ያለው፡፡

 “ሟቹም ገዳዩም እኛው ነን፤ ሌላ የውጭ አካል የለም”
ፕ/ር አህመድ ዘካሪያ
(በአ.አ.ዩ የታሪክ ምሁርና የሀገር ሽማግሌዎች ህብረት አባል)

አሁን እየታየ ያለው የብሄር ግጭት አዝማሚያ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ከአቅም በላይ እንዳይሆን በጊዜ መታረም አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ የፖለቲካ አዝማሚያው መስተካከል አለበት፡፡ የአመራር ሁኔታው እንደገና የሚጠናከርበትና ስርአት የሚይዝበት መንገድ  መታሰብ አለበት፡፡ እሱ ካልተስተካከለ መውጫው ከባድ ነው፡፡ ጉዳዩ ከግለሰብ ወደ ማህበረሰብ እየሄደ ነው፡፡ ነገ መሳሪያ የሚያቀብል ከተገኘ ደግሞ እየባሰ ነው የሚሄደው። ከዚህ አዙሪት የመውጫ ቀዳዳውን የሃገር ሽማግሌዎች ማመላከት አለባቸው፡፡ ህዝቡ ሁሉም ወንድማማች ነው፡፡ በቋንቋ በቀላሉ የሚለያይ አይደለም፤ ህዝባችን፡፡ የፖለቲካ አስተዳደር ምልክቶች ግንብ ሆነው ሊያራርቁን አይገባም። ብዙ ሃገሮች በእንዲህ መሰሉ ችግር ጠፍተዋል፤ የቀውስ ቀጠና ሆነዋል፡፡ ስለዚህ መፍትሄውን ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡ በስርአት መምራት ከቻልን፣ የዚህች ሀገር ፀጋ ለሁላችንም ይበቃል፡፡
በህገ መንግስቱ ያሉ ድንጋጌዎችን በሥርአት መተግበር ያስፈልጋል፡፡ የምናወጣቸው ህጎች ወደ ታች መውረድ አለባቸው፡፡ ልጆቻችን በት/ቤት የስነ ምግባር ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አሁን ባለው የሲቪክስ ትምህርት ተማሪዎች መብታቸውን ተምረው፣ የህይወት ፍልስፍናና ግዴታቸውን አልተማሩም፡፡ ይሄ የህይወት ፍልስፍና የሚመጣው በሃይማኖት ትምህርትም ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄን ትምህርት በስርአተ ትምህርት ውስጥ አስገብተን፣ ልጆቻችን መግራት አለብን፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችንን መጀመሪያ ሰው መሆናቸውን እንዲቀበሉ ማስተማር ያስፈልጋል፤ ብሄር እያልን ፅንፍ መውሰድ የለብንም፡፡ እኔ በሃገራችን የማየው የባህል ልዩነት ነው፤ የብሄር ጉዳይ ብዙም አይታየኝም፡፡ አብዛኛውም ኢትዮጵያዊ የተዋሃደ ነው፡፡ ጠበኞችን በባህላችን ማስታረቅ እንችላለን፡፡ ሟቹም ገዳዩም እኛው ነን፤ ሌላ የውጭ አካል አይደለም፡፡ ስለዚህ መፍትሄውም በእጃችን ነው ያለው፡፡ በሽምግልና ተገፍቶ “ገዳዩም ሟቹም እኔ ነኝ” ብሎ ማስታረቁ ይቀላል፡፡ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በዚህ በኩል ድርሻቸው የላቀ ነው፡፡

አዲስ አድማስ

Filed in: Amharic