>

የኢትዮጵያና የእንግሊዝ የድንበር ስምምነት (በላይነው ኣሻግሬ)

እንዲያው የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ሲነሳ ሁል ጊዜ ይገርመኛል፡፡ እኔ እንኳ እንደማስታውሰው በ2000፣ 2002፣ 2007፣ እና ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ደግሞ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ ሁለቱ ሀገራት ድንበር ሳይኖራቸው ቀርቶ ነው ይህ ሁሉ ነገር መፈጠሩ? አይደለም፡፡ የድንበር ስምምነት ሳይኖር ቀርቶ ነውን? አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በዓለም አቀፍ የታወቀ ድንበር ነው ያላት — በቀድሞው ኢጣሊያ-ሶማሊላንድ በኩል ካለው ድንበር በስተቀር፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ለመለየት የተደረገ ስምምነት መኖሩን ስለማውቅ፣ ብዙ ጊዜ ብቅ እልም እያለ የሚያተክረውን የሁለቱን ሀገራት ድንበር ለመለየት የተደረገውን ስምምነት ለመፈለግ ተነሳሁ፡፡ በጎግል በአራቱም አቅጣጫ ሳስስ ሰነበትኩ፡፡ ተሳክቶልኝ አጤ ምኒልክ ከእንግሊዝ እና ከኢጣሊያ ጋር ያደረጓቸውን ሁለት የድንበር ስምምነቶች (treaties) በእጅ የተጻፈና ማኅተም ያለበትን ዋናውን ቅጅዎች አገኘሁ፡፡ ለዛሬ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ በኩል የተደረገውን የድንበር ስምምነት ላካፍላችሁ፡፡

• ስምምነቱ የተደረገበት ዘመን፡ ግንቦት 7፣ 1894 ዓ.ም (ሜይ 15፣ 1902 እ.ኤ.አ)
• ስምምነቱ የተደረገበት ቦታ፡ አዲስ አበባ
• ስምምነቱ የተደረገበት ቋንቋ፡ አማርኛና እንግሊዝኛ
• ስምምነቱን የፈረሙት፡ ዳግማዊ ምኒልክ በኢትዮጵያ በኩል እና ሌ/ኮሎኔል ጆን ሌን ሀሪንቶን (1) የእንግሊዝ መንግሥት ወኪል
ስምምነቱ 5 አንቀጾች አሉት፡፡ የስምምነቱ ቃል ባጭሩ እንደሚከተለው ነው፡፡

አንቀጽ 1፡ ስለ ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር:: የስምምነቱ አካል የሆነ ሁለት ካርታ አባሪ ተደርጓል፡፡ (ካርታውን ተመልከት፡፡) ካርታው ላይ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር በቀይ ቀለም ተሰምሯል፡፡ በስምምነቱ እንደተቀመጠው የኢትዮጵያ ድምበር ከኮር እምሀገር አንስቶ እስከ ገላባት ድረስ፤ ከገላባት እስከ ጥቁር ዓባይ፣ ባሮ ወንዝ፣ ፒቦር ወንዝ፣ አኮቦ ወንዝ፣ እስከ መሊሌ ድረስ፤ ከመሊሌ አንስቶ እስከ 6ኛው ማዕርግ (latitude) እና 35ኛው ማዕርግ (longitude) መገናኛ ድረስ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሱዳን አይደለም መተማ ልታልፍ ይቅርና እኛ እስከ ገላባት ድረስ መጠየቅ እንችላለን፡፡

አንቀጽ 2፡ ከካርታው ላይ የተሰመረውን ድንበር መሬት ላይ ስለመወሰን (ስለማካለል)፡፡ ሁለቱም ወገኖች ተስማምተው ሰው ልከው ድንበሩን መሬት ላይ ያስቀምጣሉ፡፡ ወሰኑ መሬት ላይ ከተበጀ በኋላ ሁለቱም መንግሥታት በአዋጅ ለሕዝባቸው ያሳውቃሉ፡፡ (2)

አንቀጽ 3፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝና በጣና ሐይቅ ላይ ከእንግሊዝ ጋር ሳትስማማ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳትሠራ የሚከለክል (አሁን ድረስ ግብጾች መከራከሪያ የሚያደርጉት)

አንቀጽ 4፡ በባሮ ወንዝ አጠገብ ኤታንግ እንግሊዞች የንግድ ከተማ እንዲሠሩበት 4 ሺ ሄክታር መሬት በሊዝ እንዲከራዩ ኢትዮጵያ እንደፈቀደች፤ ሰዎቹም በእንግሊዝ ስር እንዲተዳደሩ፤ እንግሊዞች ለቀው ሲወጡ ለኢትዮጵያ እንዲመልሱ (3)

አንቀጽ 5፡ እንግሊዝ ሱዳንና ኡጋንዳን በባቡር ለማገናኘት መስመሩን በኢትዮጵያ ግዛት ላይ እንድትዘረጋ እንደተፈቀደላት፤ የሚደነግጉ አንቀጾች ይዟል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ድንበር ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት ድንበር እንዲሆን የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት)  መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ ስለዚህ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውሳኔ መሠረት በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ያለው ድንበር አጤ ምኒልክና የሱዳን ቅኝ ገዥ የነበረችው እንግሊዝ በ1894 ዓ.ም ያደረጉት ስምምነት ገዥ ወይም ተፈጻሚ መሆኑን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ ስምምነት እስካሁን ድረስ የጸና ነውና፡፡
ተጨማሪ ማስረጃዎችና ክርክሮች በማቅረብ ከዚህ የበለጠ የዳበረ ጽሑፍ ማቅረብ ይቻላል፡፡

—————————————————————-
(1) ሌ/ኮሎኔል ጆን ሌን ሀሪንቶን ማለት ንግሥት ቪክቶሪያ ለዳግማዊ ምኒልክ በፎኖግራፍ የተቀረጽ መልክት ስትልክላቸው በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ዋና መልክተኛ የነበረና የድምጽ መልክቱን በ1891 ዓ.ም ለጃን ሆይ ያስረከበ ነው፤ እንዲሁም የዐፄ ምኒልክን እና የእቴጌ ጣይቱን የድምጽ መልክት በ1891 ዓ.ም ለንግሥት ቪክቶሪያ እንዲደርስ ያደረገ ነው፡፡

(2) የድንበር መካለሉ በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል የተደረገ አይመስልም፡፡ ለዚህም ይመስላል የሱዳን ወታደሮች ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እየዘለቁ የሚያስቸግሩት፡፡ በተለይ በዘመነ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ድንበር እንደፈለጉ ጥሰው ይገባሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ በቤንሻንጉል በኩል ባለው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር እስከ ኩርሙክ ድረስ ሄጄ ነበር፡፡ ከድንበር ወዲህ ማዶ የኛ ኩርሙክ አለች፤ ከድንበር ወዲያ ማዶ ደግሞ የሱዳን ኩርሙክ ከተማ አለች፡፡ በአካባቢው የሚገኝ አንድ የኛ ፖሊስ ስጠይቀው የኢትዮጵያ ድንበር አሁን ካለችው የኩምሩክ ከተማ ባሻገር እስካለው ጋራ (የሱዳንን ኩርሙክ ጨምሮ) ድረስ ነበር፡፡ ታዲያ የኦነግ ሠራዊት እዚህ ላይ ሰፍሮ ስለነበር፣ ደርግ፣ ኦነግን ለማጥቃት ሲል ኦነግ ሰፍሮበት የነበረውን መሬት ለሱዳን ሰጠ፤ ብሎ አጫውቶኛል፡፡

(3) እንግሊዝ በ1956 ዓ.ም ሱዳንን ለቃ ስትወጣ ጋምቤላን ለኢትዮጵያ ላለመመለስ አንገራግራ ነበር፤ ነገር ግን የወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አክሊሉ ሃብተ ወልድ እንግሊዞችን አንቆ ይዞ በሦስት ቀናት ውስጥ ጋምቤላን አስመልሶታል፡፡  “የአክሊሉ ማስታወሻ” 2003 ዓ.ም፣ አ.አ.ዩ ፕሬስ፣ ገጽ 75 – 77 ተመልከት፡፡

 

Filed in: Amharic