>

ኢህአዴግ ሳይፈቅድ የህወሀትን ተጽእኖ ማስወገድ ይቻላል? (ስዩም ተሾመ)

መንደርደሪያ – አሁን ያለው ሁኔታ (the status quo) (በአኖኒመስ)
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ሀገሪቱ በፌደራላዊ ስርአት እንድትደዳደር ከመደንገጉ በተጨማሪ በውስጡ በርካታ ጥሩ ነገሮችን አዝሏል። በአለም አቀፍ ደረጃ (universally) የታወቁ ሰብአዊ መብቶች መጠበቅ እንዳለባቸው፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው፣ የመንግስት ስልጣን ገደብ እንዳለው፣ የፍትህ አካላቱ ገለልተኛና ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ መሆን እንዳለባቸው፣ ወዘተ ደንግጓል። ሕገ መንግስቱ በነዚህና በውስጡ በያዛቸው ሌሎች ተራማጅ (progressive) ድንጋጌዎች ምክንያት በተለይ መጀመሪያ አካባቢ በብዙ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትና ተስፋ ፈጥሮ ነበር። ነገር ግን የመንግስት የተለያዩ አካላት ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ሕገ መንግስቱን በሰፊው ይጥሱታል፤ በዚህም ምክንያት በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልትና ጉዳት ደርሷል።

ላለፉት 26 አመታት ኢህአዴግ የፌደራል መንግስቱንና አራት ክልሎችን (ማለትም አማራ፣ ኦርሚያ፣ ደቡብና ትግራይ)  እንዲሁም አዲስ አበባን ብቻውን ሲገዛ ኖሯል። ኢህአዴግ የሚባለው ግንባር በውስጡ አራት ድርጅቶችን፤ ማለትም ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደህዴንና ህወሀትን ያቀፈ ይሁን እንጂ ዋናውና አዛዡ ህወሀት እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው። የተቀሩት ሶስቱ “እህት” ድርጅቶች፣ በፌደራሊዝሙ አወቃቀር መሰረት በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች እንኳ ሳይቀር፣ ያለህወሀት ፈቃድ ያሻቸውን ማድረግ ሳይችሉ እንደኖሩ ይታወቃል።

ህወሀት በፌደራል ፓርላማ ውስጥ ያለው ወንበር/ድምጽ 37 (6.7%) ብቻ ነው ። ስለዚህ የሚፈልገውን ፖሊሲ ፓርላማው በህግ መልክ እንዲያወጣለት ለማድረግ የሚያስፈልገው ወይም እርሱ የማይፈልገውን ህግ ፓርላማው እንዳያወጣ ለማደረግ የሚያስችለው አብላጫ ድምጽ ፓርላማ ውስጥ የለውም። ከሌላ አንድ ፓርቲ ጋር ቢቀናጅ እንኳ አብላጫ ድምጽ ማግኘት አይችልም። በአንጻሩ ኦህዴድ 178 (32.5%)፣ ብአዴን 134 (24.5%)፣ ደህዴን 108 (19.7%) ወንበር/ድምጽ አላቸው። ስለዚሀ ኦህዴድና ብአዴን ብቻ እንኳ ተቀናጅተው 57% ድምጽ ይኖራቸዋል። ኦህዴድና ደህዴንም ቢሆኑ በጋራ 52% ድምጽ ይኖራቸዋል። ነገር ግን የፓርላማው አባላት ያለ ህወሀት ፈቃድ ወይም የህወሀትና ደጋፊዎቹን ጥቅም የሚጻረር አንድም ህግ ማውጣት ሳይሳናቸው ኖረዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

አንዱ ይህ እንዲሆን ያስቻለው ምክንያት ህወሀት የፊደራል መንግስቱን የማስገድጃ ተቋማት አመራር ቦታዎች (ማለትም መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስና የደህንነት መ/ቤትን) ሙሉ ለሙሉ ለማለት ትንሽ እስኪቀረው ድረስ በቀድሞ ታጋዮቹና የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የህወሀት ደጋፊዎች ወይም አባላት ስላስያዘና ተቀናቃኞቹን ለማጥፊያ ወይም ለማዳከሚያ ሲጠቀምባቸው ስለሚታይ የሶስቱ “እህት” ድርጅቶች መሪዎችና አባላት በእጅጉ ይፈሩታል።

ሁለተኛውና ከዚህ ጋር የሚያያዘው ምክንያት አራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ያስመረጧቸው የፓርላማው አባላት ፓርቲዎቻቸው ያልፈቀዱትን ህግ (በተለይ የህወሀትና ደጋፊዎቹን ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ) ፓርላማው እንዳያሳልፍ/ እንዳያወጣ ማድረጋቸው ነው። ፓርቲዎቻቸው ደግሞ ኢህአዴግ (በጋራ) ያላጸደቀው (በሌላ አነጋገር ህወሀት ያልፈለገው) ህግ ከሆነ ተመራጮቻቸው ፓርላማ ውስጥ እንዲጥሉት/ እንዳያሳልፉት መመሪያ ይሰጣሉ። የሚያፈነግጥ የፓርላማ አባል ቢገኝ እንኳ ወንጀል ተፈልጎለትና ያለመከሰስ መብቱ እንዲነሳ ተደርጎ ወደ እስር ቤት ይወረወራል። ይህ አሰራር በግልጽ የህገ መንግስቱን አንቅጽ 54(4) የሚጻረር ነው።

ከጥቂት አመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በተለይ ደግሞ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል። ተቃውሞው በአብዛኛው ያተኮረው የህወህት የበላይነትንና ለትግራይ ተወላጆች የሚደረገውን አድሎ በማስቀረት ላይ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የራሱ የኢህአዴግ አባል የሆኑት ሁለት ድርጅቶች (ማለትም ብአዴንና ኦህዴድ) ከፍተኛ መሪዎች የድርጅቶቻቸውንና የህዝባቸውን ድጋፍ መከታ በማድረግ የህወሃትን ተጽእኖና አዛዥነት ለማስቀረት ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ይታያሉ። እንዲያውም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ውስጥ የህወሃት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተጽእኖ በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ ችለዋል ማለት ይቻላል።

ሁለቱ ድርጅቶች በክልሎቻቸው ውስጥ የጀመሩትን የህወሀትን ተጽእኖ የማስወገድ ወይም የመቀነስ ትግል አሁን ደግሞ ወደ ፌደራል ደረጃ እያሳደጉት እንደሆነ ይታያል። ለምሳሌ እየተካሄድ ባለው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሁለቱ ድርጅቶች ተነስቶ ከፍተኛ ክርክር የተደረገበት አንዱና ዋነኛ ጉዳይ የህወሀት የበላይነት ማብቃት አለበት የሚለው ነው። የህወሀት መሪዎች እንዲህ አይነት ነገር የለም፤ ይህ የጠባቦችና የትምክህተኞች አመለካከት ነው፤ ወዘተ እያሉ ክደው ተከራክረዋል። ሆኖም የኦህዴድና የብአዴን መሪዎች በበኩላቸው የፌደራል መንግስቱ የማስገደጃ ተቋማት የአመራር ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ ለማለት ትንሽ እስኪቀረው ድረስ የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የህወሀት ደጋፊዎች ወይም አባላት መያዛቸው፤ እነዚህን ተቋማትም በአዛዠነትና መሪነት ባስቀመጣቸው ሰዎች አማካይነት ህወሀት ላሰኘው ተግባራት ሲጠቀምባቸው እንደኖረ ጠቅሰው ይህ ከዚህ በኋላ መቀጠል እንደሌለበት፣ እነዚህ የመንግስት የማስገደጃ ተቋማት ህገመንግስቱ አንቀጽ 87(1) ላይ ባስቀመጠው መሰረት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ስብጥር ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ያካተቱ መሆን እንዳለባቸው አስምረው ተከራክረዋል።

እስካሁን የተመጣበት መንገድ ሀገሪቱንም፣ ህዝቧንም፣ ኢህአዴግንም፤ ህወሀትንም ጭምር አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደጣለ ለማንም ግልጽ ነው። በዚህ መቀጠል አይቻልም፤ ከዚህ ችግር መውጫ ሌላ መንገድ መገኘት አለበት።

የዚህች አጭር ጽሁፍ አላማ ኢህአዴግ/ህወሀት ሳይፈቅድ ወይም ኢህአዴግ/ህወሀትን ወደጎን በመተው ፓርላማው ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን ለውጥ (የህውሀትን የበላይነት ማስቀረትን ጨምሮ) ማምጣት እንደሚችል ለማመላከት ነው።

የዚህ አመለካከቴ ምርኩዝ (premise) ኢህአዴግ ተፈጥሮአዊ ድክመት (inherent weakness) ያለው ሲሆን በተጻራሪው ደግሞ ፓርላማው ተፈጥሮአዊ ጥንካሬ (inherent strength) አለው የሚል ነው። ከዚህ ተነስቼም መደምደሚያዬ ላይ ፓርላማው እንዴት ተፈጥሮአዊ ጥንካሬውን በአግባቡ ተጠቅሞ ህዝቡ እየጠየቀ ያለውንና፣ ሀገሪቱም በእጅጉ የሚያስፈልጓትን ለውጦች ያለኢህአዴግ/ህወሀት ፈቃድ ማምጣት እንደሚችል እጠቁማለሁ።

የኢህአዴግ ተፈጥሮአዊ ድክመት (inherent weakness) 

ከላይ እንደተጠቀሰው ኢህአዴግ አራት ድርጅቶች አባል የሆኑበት ግንባር ነው። ግለሰብ በኢህአዴግ ውስጥ አባል መሆን አይችልም። በየደረጃው የተዋቀሩት የግንባሩ የተለያዩ የስልጣን አካላትም ቢሆኑ (ማለትም ኮንግረስ፣ ምክር ቤት፣ ስራ አስ ይፈጻሚ) የተሞሉት በአራቱ ድርጅቶች ተወካዮች ነው። እያንዳንዱ ድርጅት እኩል ተወካይ ያዋጣል።

ከፍተኛው የስልጣን አካል ኮንግረሱ ሲሆን በተዋረድ ሁለተኛው የስልጣን አካል ምክር ቤቱ፣ ሶስተኛው ደግሞ ስራ አስፈጻሚው ናቸው። የኢህአዴግ አደረጃጀት ከላይ እንደተጠቀሰው ይሁን እንጂ እስካሁን ባሉት አመታት ኢህአዴግ በተግባር የተለያዩ ድርጅቶች/ፓርቲዎች እንዳሉበት ግንባር ሳይሆን እንደ አንድ ወጥ ፓርቲ ሲንቀሳቀስና ሲታይ ቆይቷል። ይህም ሊሆን ከቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙብታል፤

 1. የግንባሩ የተለያዩ አካላት ህወሀት የደገፈውን/የፈለገውን ውሳኔና አቋም ብቻ እንጂ እነሱ ቢፈልጉትም እንኳ ሌላ ውሳኔ ማስተላልፍ አይችሉም።
 2. በዚህ አይነት ግንባሩ (በህወሀት ፍቃድ) የሚያስተላልፈውን ማንኛውንም ውሳኔ አባል ድርጅቶቹ በዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት መርህ መሰረት በአባሎቻቸውና በሚመሩት ክልል ውስጥ ተፈጻሚ የማደረግ ግዴታ አለቸው። የፓርላማ ተመራጮቻቸውንም ይህንኑ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያዙዋቸዋል።

በዚህ ምክንያት እንግዲህ ኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅት መስሎና ሆኖ ቆይቷል። ይህ የሆነው ግን ግንባሩ ተፍጥሯዊ ጥንካሬ (inherent strength) ኖሮት ሳይሆን የህወሀትን ትእዛዝ አስፈጻሚ፣ አራቱም አባሎቹ እኩል ይሁንታ (say) የሌላቸው ስለነበረና ይህም በተግባር (effectively) እንደ አንድ ፓርቲ እንዲንቀሳቀስ ስላደረገው ነው። እንዲህ አይነቱ የግንባሩ ጥንካሬ ሊቀጥል የሚችለው የህወሀት ጥንካሬና በመንግስት የሀይል ማስፈጸሚያ መ/ቤቶች ውስጥ ያለው የበላይነት እስከቀጠለ ድረስ ብቻ ነው። ይህ ሲቀየርና አራቱም ድርጅቶች ያለተጽእኖ ወይም ያለፍራቻ መንቀሳቀስ ሲችሉ የኢህአዴግ ተፈጥሯዊ ድክመት ጎልቶ የሚወጣ፣ ጊዜያዊ ጥንካሬውም በኖ የሚጠፋ ይሆናል። በምትኩ ተፈጥሯዊ ድክመቱ ጎልቶ ይወጣል።

ለኢህአዴግ ተፈጥሯዊ ድክመት ምክንያት ከሚሆኑት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፤

 • የአራቱ ድርጅቶች ተውካዮች ሆነው በኢህአዴግ የተለያዩ የስልጣን አካላት ላይ የሚሳተፉት ሰዎች የላካቸውን ድርጅት አቋም ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጭ የግላቸውን አቋም ቢከተሉ የላካቸው ድርጅት ውክልናቸውን ሰርዞ በምትካቸው ሌላ ሰው ሊልክ ይችላል። ይህ አሰራር በአባል ድርጅቶቹ መሀል አለመግባባት/ሽኩቻ በሚኖርበት ጊዜ (ለምሳሌ አሁን ከህወሀት ጋር እንደተፈጠረው) የኢህአዴግ አቋም ተብሎ የሚወሰድ ውሳኔ ማስተላለፍ ብዙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፣ ወይ ደግሞ ከነአካቴውም ውሳኔ ማስተላለፍ አይቻላቸውም። በዚህ ምክንያት ግንባሩ ውስጥ ሽባነት (paralysis) ይፈጠራል። ባለፉት ሳምንታት ውስጥ እየተካሄድ ባለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ ይህ እየታየ ነው።
 • በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረ አለመግባባትና ሽባነት (paralysis) ወደ መንግስት አካላትም ሊዛመት ይችላል። ለምሳሌ ፓርላማው ለሀገሪቱ አስፈላጊ የሆኑ ህጎችን ለማውጣት የኢህአዴግን ውሳሌ የሚጠብቅ ከሆነ (እስከዛሬ ሲደረግ እንደነበረው) እንደዚህ አይነት ህጎች ሳይወጡ ረጅም ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፤ ወይም ከናካቴውም ላይወጡ ይችላሉ። የህጉን መውጣት የተወሰኑ ድርጅቶች የሚፈልጉት ከሆነ ደግሞ (የግንባሩ አባል ሆኑም አልሆኑ) በፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ህጉ እንዲወጣ ማድረግ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ኢህአዴግን የበለጠ እንዲዳከም ወይም ተሰሚነቱ እንዲቀንስ ያደርገዋል።
 • ኢህአዴግ ተሳክቶለት የፖሊሲ ውሳኔዎች በሚፈለገው ፍጥነት ቢያሳልፍ እንኳ፣ የፓርላማው አባላት ለኢህአዴግ ውሳኔ ተገዢ በመሆን ያንን የፖሊሲ ውሳኔ ወደ ህግ የመቀየር ግዴታ የለባቸውም። እንዲያውም ለኢህአዴግ ተገዢ ሆነው ህግ ቢያወጡ ድርጊታቸው ከህገመንገስቱ ጋር የሚጋጭ ይሆናል፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 54(4) ላይ እንዲህ ይላልና፤ 

የምክር ቤቱ አባላት የመላው ህዝብ ተወካዮች ናቸው። ተገዥነታቸውም፤

 • ሀ) ለሕገ መንግስቱ፤
 • ለ) ለሕዝቡ፤ እና
 • ሐ) ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናል።

የፓርላማው ተፈጥሮአዊ ጥንካሬ (inherent strength) 

ፓርላማው የተቋቋመው በህግ፣ በተለይ ደግሞ የሀገሪቱ ህጎች ሁሉ ቁንጮ በሆነው በህገ መንግስቱ ነው። ተፈጥሮአዊ ጥንካሬውም የሚመነጨው ከዚህ አፈጣጠሩ ነው። በአንጻሩ ኢህአዴግ የተቋቋመው በአባሎቹ “መልካም ፍላጎት”  እንጂ በህግ አይደለም።

ፓርላማው (በተለይ ደግሞ የተውካዮች ምክር ቤት) ከፍተኛው የሀገሪቱ ህግ አውጪ አካል ሲሆን ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 55 ስር ለፓርላማው እጅግ ብዙ ስልጣን (sweeping powers) ይሰጣል። አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፤

 • የጠቅላይ ሚኒስትሩን፤ የሚኒስትሮችን፤ የዳኞችንና የሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ሹመት ያጸድቃል፤ ወይም ውድቅ ያደርጋል።
 • የፌደራል መንግስት፤ የሀገርና የህዝብ መከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ሀይል አደረጃጀትን ይወስናል። በስራ አፈጻጸማቸው ረገድ የሚታዩ መሰረታዊ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶችና የሀገር ደህንነት የሚነኩ ጎዳዮች ሲከሰቱ ያጣራል፤ አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ያደርጋል።
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ሌሎት የፌደራል መንግስት ባልስልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የህግ አስፈጻሚውን አካል አሰራር የመመርመር ስልጣን አለው።
 • ያስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያወጣል። የተለያዩ ህጎችን ያወጣል። የጦርነት አዋጅ ያውጃል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ መሰመር ያለበት ጉዳይ፤ ማንኛውም የፓርላማው አባል በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተዘረዘረውን ስልጣኑን ተግባራዊ ሲያደርግ፤

 • ተገዢነቱ ለህዝቡ፣ ለሕገ መንግስቱና ለህሊናው ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። ለፓርቲው አይደለም። ከፓርቲው ጋር ሳይግባባ ቀርቶ ፓርቲው ባይፈልገው እንኳ የፓርላማ ዘመኑ (term) ከማለቁ በፊት ከፓርላማ ሊያወጣው አይችልም።
 • በፓርላማው ውስጥ በሚሰጠው ድምጽ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም። አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም።
 • ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ፓርላማው ፍቃድ አይታሰርም፤ በወንጀል አይከሰስም።

ፓርላማውና የፓርላማ አባላት እነዚህና ሌሎችም በርካታ ስልጣኖች በህግ ተሰጥተዋቸዋል። እነዚህ በህግ የተደነገጉ ስልጣኖቻቸውና ጥበቃዎች ናቸው እንግዲህ ፓርላማውና አባላቱ ተፈጥሮአዊ ጥንካሬ (inherent strength) አላቸው የሚያስብለን።

ፓርላማው ምን ማድረግ አለበት? 

ላለፉት 26 አመታት የታየው ፓርላማው የኢህአዴግ ታዛዥ (rubber stamp) ሆኖ ሲያገለግል እንጂ ተፈጥሮአዊ ጥንካሬውን በአግባቡ ሲጠቀምበት አይደለም። እንዲያውም በሕገ መንግስቱ የተጣለበትን ሀላፊነትና የተሰጠውን ስልጣን ችላ ብሎ ወይም ዘንግቶ የህዝብን በደልና የሀገርን ጉዳት ማስቆም ሳይችል ቀርቷል። ለምሳሌ፤

 • የመከላከያ ሰራዊት፤ የደህንነት መ/ቤትና የፌደራል ፖሊስ አመራር የተያዘው በአብዛኛው በትግራይ ተወላጆች ነው። በተለይ በመከላከያ ውስጥ ከ90% በላይ የሚሆኑት ጄነራሎች የትግራይ ተውላጆች ናቸው። ይህ አሰራር የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 87(1) የሚጻረር ሆኖ ሳለ ፓርላማው በአንቀጽ 55(7) የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ ለማስተካከል የሞከረው ነገር የለም።
 • በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች፤ በተለይ ደግሞ በኦሮምያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በኮንሶ፣ ወዘተ እጅግ ብዙ ንጹሀን ዜጎች በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ መብቶቻቸው እንዲከበሩ በሰላማዊ መንገድ ስለጠየቁ ብቻ ተገድለዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። ግድያዎቹና የመብት ጥሰቶቹ የተፈጸሙት በአብዛኛው በመከላከያ ሰራዊት፣ በደህንነትና ፌደራል ፖሊስ አባላት ነው። ፓርላማው በእነዚህ ተቋማት ስራ አፈጻጸም ረገድ የሚታዩ መሰረታዊ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶችና የሀገር ደህንነት የሚነኩ ጎዳዮች ሲከሰቱ እንዲጣሩና አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ስልጣንና ሀላፊነት ቢኖረውም እስካሁን በዚህ ረገድ ምንም ሚዛን የሚያነሳ ስራ ሲስራ አልታየም።
 • መንግስትን አጥብቀው የተቃወሙ መሪዎችና ግለሰቦች ሽብርተኛ ተብለው መታሰራቸውና መከሰሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ አሰራር ነው። ሰዎቹ በርግጥ ሽብርተኛ ሆነው ቢሆን ኖር መታሰራቸው ተገቢ በሆነ ነበር፤ የሆነው ግን ይህ አይደለም። መንግስት የሽብር ህጉን እየተጠቀመበት ያለው የኢህአዴግ/ህወሀትን ጠንካራ ተቀናቃኞች ለማጥፊያና ለማስፈራሪያ ነው። መንግስት ይህን ህግ ዜጎችን ለመጨቆኛና መብታቸውን ለመጣሻ ሲጠቀምበት ህጉን ያወጣው ፓርላማ በቸልተኝነት ሲመለከት ኖሯል።

ፓርላማው ሀላፊነቱን በአግባቡ ስላልተወጣና ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ ስላልተጠቀመበት፤ እንዲሁም አስፍጻሚው አካል ለፓርላማው ያለው ተጠያቂነት (accountability) ስለተመናመነ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት አደግኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቃለች። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ አሁን ያለው ሁኔታ (the status quo) መቀጠል የለበትም፤ የህወሀት የበላይነት ያብቃ፤ ለውጥ እንፈልጋለን፤ ሕገ መንግስቱ ይከበር እያለ ይጮሀል። ግድያውም ሆነ እስራቱ እንደዚሁ ቀጥሏል።

ኢህአዴግ ሀገር መምራት እንዳቃተው ራሱ እየተናገረ ነው። አባላቱም እየተጣሉ ነው። በቅርብ ጊዜ ሪፖርተር ጋዜጣ በርእስ አንቀጹ እንዳለው ሀገሪቱን ያቆማት የህዝብ ጨዋነት እንጂ የኢህአዴግ የአመራር ብቃት አይደለም። ፓርላማው በዚህ የደከመ ሁኔታ ላይ ላለ ግንባር እራሱን ተገዢ አድርጎ የሚቀጥል ከሆነ ህገመንግስቱን መጣስ ብቻ ሳይሆን ሀገር እንድትጠፋና ህዝብ እንዲጎዳ ተባባሪ ሆነ ማለት ነው። የፓርላማው አባላት ተገዢነታቸው ለህዝቡ፣ ለሕገ መንግስቱና ለህሊናቸው ብቻ እንጂ ለኢህአዴግ እንዳልሆን በሕግ መንግስቱ ውስጥ ተደንግጓል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርላማ ውስጥ (በተለይ ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ) ተስፋ የሚሰጡ አካሄዶች እየታዩ ነው። ለምሳሌ የብአዴንና ኦህዴድ ተመራጮች ተቀናጅተው መስራት ጀምረዋል። የሁለቱ ድርጅቶች ተመራጮች ብቻቸውን 57% ድምጽ ያላቸው በመሆኑ የኢህአዴግ/ህወሀትን ትእዛዝ ሳይጠብቁ ወይም ወደ ጎን ብለው አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ማምጣት ይችላሉ። እንዲሁም የሁለቱን ድርጅቶች ህብረት በማስፋት ሌሎች የህወሀት ተጽእኖ ያንገሸገሻቸውን ክልሎች/ድርጅቶች ተወካዮችም ተሳታፊ/ተባባሪ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል/ይገባል።

ፓርላማው በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ በርካታ ለውጦችን ማምጣት ቢችልም ቅድሚያ መስጠት ያለበት የሰብአዊ መብቶችን መከበር ማረጋገጥና የመከላከያ/ደህንነት/ፖሊስ መስሪያ ቤቶች ላይ የአሰራር ለውጥ (reform) ማምጣት ላይ ቢሆን የተሻለ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድ፤

 • የመከላከያ ሰራዊት፤ የደህንነት መ/ቤትና የፌደራል ፖሊስ አመራር በአብዛኛው በትግራይ ተወላጆች የተሞላ መሆኑ ቀርቶ ሕገ መንግስቱ በሚደነግገው መሰረት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ስብጥር ሚዛናዊ በሆነ ሁኒታ ያንጸባረቀ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል።
 • በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩት መሰረታዊ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች የሚጥሱና የሀገር ደህንነት የሚጎዱ ድርጊቶች እንዲቆሙና ባጥፊዎቹ ላይ አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግ አለበት። በተለይ ደግሞ የመብት ጥሰቶቹ የሚከናወኑት በየከተሞቹና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሕገ መንግስቱን በጣሰ መንገድ የፖሊስን ስራ እንዲሰሩ በተላኩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በመሆኑ፣ እነዚህ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአስቸኳይ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ መደረግ አለበት።

ፓርላማውና አባላቱ እነዚህ ለውጦች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመጡ ለማድረግ የሚያስችላቸው ስልጣንና ብቃት አላቸው። ፍላጎቱ አላቸው? ቆይተን የምናየው ይሆናል።

የፓርላማው አባላት ህዝቡ እያለ ያለውን አድምጡ። የሕገ መንግስቱን መከበር አረጋግጡ። የህዝብ መበደል፤ የሕገ መንግስቱ መጣስ፤ የኢትዮጵያ አደጋ ላይ መውደቅ ህሊናችሁን ይቆጥቁጠው።

Filed in: Amharic