>

“ኢህአዴግ መምረጥ ያለበት ከመውደቅ እና ከመውረድ ነው”(የሽዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

በይርጋ አበበ

አለመተማመን እና መወነጃጀል “መለያው” በሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም የተቃውሞው ጎራ መተባበር እና አብሮ መሥራት የማይሞከር እስኪመስል ድረስ እንደ “ጉልት ንግድ” በየሰፈሩ ተበታትነው ይገኛሉ። ለዚህ መበታተን በርካታ ምክንያት ሊቀርብ ቢችልም በዋናነት ግን የፓርቲ አመራሮቹ እኔ ያልኩት ካልሆነ አቋም፣ የአመራር ቦታውን በመያዝ ለምትገኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ሽኩቻ፣ የገዥው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት እና የዲያስፖራው ዶላር የሚያሳድረው ተፅዕኖ የሚሉት ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል። ያም ሆኖ ግን አሁንም ትግል ላይ ነን የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ይገልፃሉ።

ኢህአዴግ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ በእድሜ አንጋፋው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በወጣቶች የተመሰረተው ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) መሪዎች ከአራት ወራት የዘለለ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ጉብኝት አድርገው ነበር። የሁለቱ ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት ወደ አሜሪካ ያቀኑት “የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)” የተባለ ድርጅት ባቀረበላቸው ግብዣ አማካኝነት ነው።

የመኢአድ ሊቀመንበር ዶ/ር በዛብህ ደምሴ እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ያደረጓቸውን ጉዞዎች አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከጋዜጠኞችም ጥያቄዎች ተነስቶላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። የጋዜጣዊ መግለጫውንና ከመገናኛ ብዙሃን ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾችን ለአንባቢ በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት

የመኢአዱ ዋና ፀሀፊ አቶ አዳነ ጥላሁን በንባብ ያሰሙት የሁለቱ ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ ይህን ይመስላል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና እየዘመነ መምጣቱ ለሁሉም የሚታይ ነው። ለዚህም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶችና ግለሰቦች አስተዋፅኦ መኖሩ ይታወቃል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ላለፉት 26 ዓመታት፤ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ ላለፉት ስድስት ዓመታት የገዥውን ጫና ተቃቁመው የየድርሻቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ። ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ከተስማሙበት መጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ውስጥ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።

የሁለቱ ድርጅቶች መሪዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ) በተደረገላቸው ግብዣ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት ድርጅቶቻቸው የሰጧቸውን ተልዕኮዎች ተወጥተው ተመልሰዋል። በዚህም መሠረት፡-

· በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የመኢአድ፣ የቀድሞ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎች በማሰባሰብ አንድ ጠንካራ የድጋፍ ሰጪ ቻፕተር በዋሽንግተን ዲሲ አጠናክረዋል።
· ሰላማዊ ትግሉን በገንዘብ የሚደግፉ ኢትዮጵያዊያንን በማፈላለግና በስብሰባዎች ላይ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማድረግ መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ችለዋል።
· የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና የሰብዓዊ መብት አያያዝ በየግዛቱ ለሚገኙ የኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲዎች፣ ለሴኔትና ለኮንግረስ ተጠሪዎች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወዳጆች አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት አድርጓል። በዚህም ስምምነት ኢትዮጵያውያን የውጭና የውስጥ ሳይባባሉ በጋራ የሚሰሩበትን እድል ፈጥረዋል” ሲል ያትታል።

የውጭ ጉዞው የመጨረሻ ግብ

ሁለቱ ሊቃነመናብርቶች በተለያዩ ግዛቶች ያደረጉት ጉዞ በገንዘብ፣ በውይይት እና አብሮ ለመስራት የተደረጉ ስምምነቶች የታዩበት እንደሆነ በመግለጫቸው አስታውቀዋል። “ኢትዮጵያዊያን የውጭ እና የውስጥ ሳይባባሉ በጋራ የሚሰሩበትን እድል ፈጥረናል” ያሉት ሁለቱ ፓርቲዎች፤ በአሜሪካ ያደረጉትን ጉዞ የመጨረሻ ግብ ሲያስቀምጡም፡-

“የዚህ ሁሉ ጥረት ዋና ዓላማም አንድ ጠንካራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሊጥልበት የሚችል አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ለመፍጠር ሲሆን ይህንንም ከመቼውም ጊዜ በላይ መኢአድና ሰማያዊ ጠንክረው እየሰሩበት ይገኛሉ። ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጰያዊ ይልቁንም አሁን ጊዜው የኢህአዴግ ቡድን የሚያደርገውን አጥቶ በሚንደፋደፍበት ወቅት በመተባበር ልንሰራው እና የህዝቡን ትግል ዳር በማድረስ የበኩላችንን እንድንወጣ አደራ እያልን በሀገር ውስጥ የሕዝብ ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ሰላማዊ ትግሉን ለድል እንደሚያበቃው የማንጠራጠር መሆኑን እየገለፅን ለዚህም በአንድነት እንድንሰራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን በማለት የትብብሩን እና የትግላቸውን የመጨረሻ ግብ በጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።”

በመግለጫው እንደተጠቀሰው በአገር ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ከባቢ አየር ለመቀየርና ለውጥ ለማምጣት የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት ወሳኝነቱ ጉልህ ድርሻ ይይዛል። ለዚህ ደግሞ መኢአድ እና ሰማያዊ ከፊት ተሰልፈው ትግሉን ለመምራት መነሳታቸውን ገልፀዋል።

የዶላር ጡንቻ በፓርቲዎቹ ፖሊሲ ላይ ያለው ጫና

ለመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል “የውጭ ገንዘብ ድጋፍ በፖሊሲያችሁ እና መርሃችሁ ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም ወይ?” የሚለው አንዱ ነው። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ “ብዙ ነገሮች የሚመጡት ከስርዓቱ አለመታመን ጋር በተያያዘ ነው። ነገር ግን ከእኛ ጋር ለመገናኘት በምንጠራው ስብሰባ የመጡ ሰዎች (በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ባደረጓቸው ስብሰባዎች) የእኛን ሃሳብ የሚደግፉ ናቸው። ይህም ማለት በመሰረታዊ የሰላማዊ ትግል መርህ የሚያምኑ እና በአገር አንድነት ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ናቸው። የሚመጡትም ያንን የሚደግፉ ናቸው። ይህን ስል ግን የብዙሃኑን አይወክሉም እንጂ ብዙ ጥያቄዎች የሚያነሱ አሉ። ከአገራቸው ርቀው እንደመኖራቸው የአገራቸውን ሁኔታ በደንብ አለመረዳትም አለ። ብዙውን ስንመለከተው በዚህ ስርዓት የሚያምን አለመሆኑን አይተናል። የቅንጅትም፣ የአንድነትም የሰማያዊም ድጋፍ ሰጭ ማህበሮች ነበሩ። ሸንጎም ይሁን፣ ድጋፍ ሰጭ ማህበሮችም ይሁኑ የሚያግዘን ያለንን ደንብ እና ፕሮግራም አይቶ ሲስማማው ነው። በኢትዮጵያ አንድነት እና በሰማዊ ትግል እናምናለን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው መተዳደር አለበት ብለን እናምናለን የሚለውን መርህ የሚደግፍ በሙሉ ይደግፈናል። ድጋፍ የሚያደርገው አካል የሸዋስን ወይም ዶ/ር በዛብህን ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ነው የሚደግፈው። እዚያ ያለ ህዝብ የሚደግፈው ራሱን፣ ወገኑንና አገሩን ነፃ እንዲያወጣ ነው” ሲሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በፓርቲዎቹ ፕሮግራም እና አካሄድ ላይ ችግር እንደማይፈጥሩባቸው ተናግረዋል።

አቶ የሽዋስ አክለውም “የአንድ አገር ነፃነት በህዝቡ እጅ ላይ ነው ያለው። ማንም አግዞት ወይም ረድቶት ነፃ የወጣ አገር የለም። ስለዚህ እኛ የህዝቡ ነፃነት በህዝቡ እጅ ላይ ነው ብለን ስለምናምን በራሱ ትግል የራሱን ሥርዓት መፍጠር ይችላል። ለዛ ብቁ መሆኑን ደግሞ በ1997 ዓ.ም አሳይቷል። ለዚህ ነው እኛ በአሜሪካ በነበረን ቆይታ እኛን ከሚመስሉት ጋር ብቻ ግንኙነት ያደረግነው” ብለዋል።

ከኮንግረስ እና ከሴኔት አባላት ጋር የተደረገ ውይይት

ሁለቱ ሊቃነ መናብርቶች በአሜሪካ ቆይታቸው በተለያዩ ግዛቶች ተዘዋውረው የፓርቲዎቹን ደጋፊዎችና አባላት ከማነጋገራቸውና የገንዘብ ድጋፍ ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ከአሜሪካ የኮንግረስ እና የሴኔት አባላት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል። ውይይታቸው ምን ይመስላል? ከውይይቱስ ምን ይጠበቃል? ለሚሉ ጥያቄዎች ሁለቱ ሊቀመንበሮች ሲመልሱ “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ የግንኙነት ታሪክ እንዳለው አገር ወዳጅነቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው መሆን ያለበት እንጂ ከአገዛዝ ጋር አይደለም። ከአገዛዝ ጋር የሚደረግ ወዳጅነት አገዛዙ ሲወድቅ ወዳጅነቱ አብሮ ያበቃል። ለምሳሌ ከመንግስቱ ጋር የነበረ ወዳጅነት መንግሥቱ ሲወድቅ ወዳጅነቱም አበቃ። ከህወሓት ጋር የሚደረግ ወዳጅነትም የመንግሥቱ ከሆነው የሚለይ አይደለም። ስለዚህ የአሜሪካ መንግሥት ወዳጅነትም ቢሆን የሚገባው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው መሆን ያለበት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቁሙ፤ የሚል ነው የእኛ ነጥብ። እነሱም ተረድተዋል በቀጠናው (ምስራቅ አፍሪካ) ያለው ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ላይ ችግር ቢፈጠር የሚሆነውን ያውቃሉ። ከእኛ ጋርም ባደረጉት ውይይት ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰናል። የዲፕሎማቲክ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ የሚሆን ውጤት እንጠብቃለን” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

የገንዘብ ድጋፍ እነማን አደረጉ?

የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት እና ግለሰቦችን ማንነት በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ መልስ የሰጡት ደግሞ የመኢአድ ም/ ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ናቸው። አቶ ሙሉጌታ ሲናገሩ “ድጋፍ አድራጊው አካል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስረታ አዋጅ 573 እንደተቀመጠውም ሆነ በፕሮግራማችን በተቀመጠው መሠረት ነው። ፓርቲዎችን በገንዘብ የሚረዱ ድጋፍ ሰጭ ማህበራት የሚረዱት በአዋጁ እና በደንቡ መሠረት ነው። የእኛ ድጋፍ ሰጭዎች የሰላማዊ ትግል አካል የሆኑ ናቸው” መኢአድን እና ሰማያዊን በገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ፖለቲካዊ ቁመና ተናግረዋል።

“ከምትወድቅ፣ ውረድ”

አቶ የሽዋስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲናገሩ “እኛ ለኢህአዴግ የምንለው “ከምትወድቅ ውረድ” የሚለውን ነው” ብለዋል። የሰላማዊ ትግል ስትራቴጂ ፊት ለፊት እንጂ የአሸዋ ገበታ መሥራት አይደለም” ያሉት አቶ የሽዋስ፤ “ኢህአዴግ አሁንም ጥያቄ መመለስም ሆነ መስተካከል አይችልም፣ አርጅቷል። መምረጥ ያለበት ከመውደቅ እና ከመውረድ ነው። እኛ የምንመርጥለት መውረድን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው የመተዳደር ብቃት እንዳለው ይታወቃል። እኛም እየገለፅን ያለነው ይህንን ነው” በማለት “የትግል ስትራቴጂያችሁ ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

አቶ የሽዋስ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም “ኢህአዴግ ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ (ከ17 ቀናት የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ የደረሰበትን አቋም) አይቸዋለሁ። ኢህአዴግ ይሻሻላል ብዬ አልጠብቅም ነበር፤ በመግለጫው ያየሁትም ያንኑ አለመሻሻሉን ነው። ወደፊትም አይሻሻልም። ስለዚህ ትግሉ የህዝብ ሆኗል። ከፓርቲዎቹ ቀድሞ ህዝቡ ትግሉን ተቀብሏል። ያ ደግሞ የሆነው በየጊዜው የሚፈጠሩ ፓርቲዎችን አገዛዙ አናት አናታቸውን እየኮረኮመ ስለሚያፈርሳቸው ነው። ፓርቲዎችን ቢሮ ይከለክላቸዋል፣ ሚዲያ ይዘጋባቸዋል፣ ምርጫ ቦርድ ሌላ አወሳሳቢ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን ተቀበለ። ይህ ደግሞ ሁልጊዜም ስናስበው የነበረ ስለሆነ ትክክል ነው ብለን እናምናለን መቀጠል አለበትም እንላለን” ብለዋል።

Filed in: Amharic