>

ና በወሎ፤ ...ገና-የክርስቲያንም የሙስሊምም የጋራ በዓል፤ (ውብሸት ሙላት)

ይህ ጽሑፍ የገናን ታሪክ የመተረክ ዓላማ የለውም፡፡ ይህ ጽሑፍ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ነገርም አይናገርም፡፡ ይህ ጽሑፍ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሕሳስ 29 ወይንም 28 ቀን የሚከበረውን ሃይማኖታዊ ሥርዓትም አይገልጽም፡፡ ይልቁንም በዚሁ ዕለት ስለሚደረገው የገና ጨዋታ ሁኔታ በተለይም በወሎ አካበቢ ስለሚደረገው  በአጭሩ ቃል ከእነ አንድምታው መግለጽ ነው፡፡

ዛሬ፣ታሕሳስ 29 ቀን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም የገና ጨዋታ በደቡብ ወሎ ዞን አካባቢ እንዴት እንደሚከበር አስተላልፏል፡፡

የገና ጨዋታ፣ በተለይም በወሎ የክርስቲያንም የሙስሊምም የጋራ በዓል ነው፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ገና ከመድረሱ በፊት ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል ማታ ማታም ጨዋታው ይደረጋል፡፡ ጨረቃ በምትኖርበት ጊዜ በየአካባቢው የሚኖሩ ጎረምሶች በየሰፈራቸው በሚገኙ ሜዳዎች ይጫወታሉ፡፡

የገና ዕለት ሲሆን ደግሞ ከምሳ ሰዓት በኋላ ሰፊ ሜዳ ባለባቸው አካባቢዎች ጀንበር እስክትጠልቅ ድረስ ጨዋታው ይቀጥላል፡፡

ጨዋታው ላይ የሚሳፉት ወንዶች ናቸው፡፡ ለጨዋታው የሚያገለግል የተሸለመ እና ቆልመም ያለ በትር (ዱላ) እና አነስተኛ፣ ነገር ግን ጠንካራ ኳስ ያስፈልጋል፡፡ ኳሷ፣ ከጠፍርም አልበለዚያም ከቃጫም ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነት ኳስ “ጥንግ” ይባላል፡፡ ከእንጨትም ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ የእንጨቱ “ቋሊ” ይባላል፡፡

ተጫዋቾቹም የክት (አዲስ) ልብስ በመልበስ ከየሰፈራቸው በገና ዕለት በሚዜሙ በሆታና በጭፈራ ወደሜዳው ይመጣሉ፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት:-
“ አሲና በል አሲና ገናዬ’’
‘’ እዮሃ’’
‘’አሲና በል’’
‘’እዮሃ’’
‘’አሲና ገናዬ”
ከ’አሲና በል’ ውጭም፡-
“ሆይ ማሬ ሆይ ማሬ በለው”
እየተባለ ሆታው ይቀጥላል፡፡

ከዚያም ለጨዋታው የመጣው ወጣት በሙሉ የገና ዱላቸውን አንድ ላይ ያስቀምጡታል፡፡ አንድ ተጨዋች ዐይኑን ተሸፍኖ ዱላዎቹን ለሁለት ቡድን ይከፍላቸዋል፡፡ ሁሉም ወጣት በጨዋታው ይሳተፋል፡፡ የቁጥር ወሰን የለውም፡፡ የዕድሜም ወሰን የለም፡፡

ለሁለት ከተከፈለው  ቡድን አንድ አንድ ሰው (አምበል ዓይነት) ይመረጥና ከሜዳው አጋማሽ ላይ ኳሷን በማስቀመጥ ‘ሙግ’ ይተከላል፡፡ “ሙግ” መትከል ማለት ሁለት ወጣቶች በዱላቸው ኳሷ ሳይመቱ ነገር ከጎኗ መሬቱን በዱላቸው በመምታት “አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት” በማለት ቁጥር በመጥራት ጨዋታውን መጀመር ነው፡፡

ለጨዋታው እንደ ጎል በመሆን የሚያገለግለው የሜዳው ሁለት ተቃራኒ ጫፎች/ጎኖች ናቸው፡፡ ጨዋታው፣ ከሜዳው ውጭ ኳሷ እንዳትወጣ ጠንክሮ መጫወት ነው፡፡ ኳሷ፣ ከሜዳው ከወጣች ግብ ተቆጠረ ማለት ነው፡፡
ግብ በሚቆጠርበት ጊዜ፣ እስከ ሜዳው አጋማሽ ድረስ በሆታ መመለስ የጨዋታው ደንብ ነው፡፡ በሆታው ውስጥ ግብ የተቆጠረበትን ማብሸቅ ልማድ ነው፡፡
“አሲና በል አሲና ገናዬ”
“እዮሃ”
“አሲና በል፣ አምና የገና ዕለት”
“እዮሃ”
“አሲና በል፣ የበላው በርበሬ፤”
“እዮሃ”
“አሲና በል፣ ከቂ*  ላይ በቅሎ”
“እዮሃ”
“አሲና በል፣ይለቀማል ዛሬ፡፡”
ጨዋታው በዚህ መልኩ ከተካሄደ በኋላ ሲጠናቀቅ አንዳንድ ቦታ ምርቃት  አለ፡፡ ምርቃቱ የሚፈጽሙት ሙስሊም አባቶች (አዛውንቶች) ናቸው፡፡ ከምርቃት በኋላም ሴቶችም ወንዶችም በአንድነት ተሳባስበው ዘፈንና ጭፈራ ሊኖር ይችላል፡፡

የገና ጨዋታን  የሙስሊም የክርስቲያንም ነው፡፡ በጨዋታው ዕለት በኳስም ይሁን በድንገት በገና ዱላ የተመታ ሰው ቢኖር ቂም አይያዝም፤በቀልም የለም፡፡ የሃብታም ወይም የድሃ ልጅ የሚባል ልዩነት የለም፡፡ በባለሥልጣን ወይም በሎሌ ልጅ  መካከል ልዩነት የለም፡፡ የተመታው ልጅ የባለሥልጣን ልጅ ቢሆን እንኳን በገና ዕለት ሁሉም ዕኩል ነው፡፡  “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” አይደል የሚበለውስ?

የገና ጨዋታ በወሎ፣ የሁላችንም እንጂ የእንቶኔ የእንቶኔ አይባልም፡፡ ሃይማኖት አይለይም፡፡ የመጣው ሁሉም ይጫወትበታል፡፡ ማንም አይገለልም፡፡

ገና የአንድነት፣ የእኩልነት፣ የአብሮነት፣ የሁሉን አካታችነት፣ የይቅርባይነት ተምሳሌት የሆነ ጨዋታ ነው!

ወሎም የአንድነት የአብሮነት አቻ የሌላት ተምሳሌነት መሆኗም ለእዚህ ነው፡፡ ኢድ፣አረፋና መውሊድን አብሮ የሚያከብር፤የጊዮርጊስንም የሸህ አሊ ጅሩንም ጸበል በአንድነት የሚጸበል፤ገናንም ጥምቀትንም አብሮ የራሱ አድርጎ የሚኖር ሕዝብ በሚኖርባት! ዛሬ፣በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲታዩ የነበሩት ፈረሰኞችን ጥር አስራ ስምንት ቀን የሰባር አጽሙ ቀን ማየቱ ተጨማሪ ምስክርነት ነው፡፡ አብዝኃኛዎቹ ፈረሰኞች ሙስሊሞች ቢሆኑም ከደሴ ቢለን ጊዮርጊስ አጅበው ሆጤ ስቴድዬም ከዚያም በሚቀጥለው ቀን አጅበው የሚያስገቡት በመቻቻል መንፈስ አይደለም፡፡ እንደራሳቸው በመውሰድ እንጂ!

“አልሃምዱድላሂ ታቦታችን ገባ” ይላል የወሎ ሰው ሲባል ለሚገርመው ሰው መልሱ ሲያጅበው የነበረው   ታቦት በሰላም ሲገባ ታዲያ ምን እንዲል ተፈልጎ ነበር ቀድሞውንስ? ለነገሩ ወዳጃ የሚያደርጉ፣ በየወዳጃው የሚሳተፉ ክርስቲያኖችም “አላህ መሶሌ አለሟሃመዴ ሰይድና አሰለምአለይኩም” ሲሉ መስማት ብርቅ አይደለም፡፡ ዱኣ በሚደረግበት ወቅት “ዘይኔው ነብዬ ወይሰለምአላ ሰላምአለይኩም” የሚል ነሽዳን/መንዙማን ወሎ ውስጥ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም እኩል  እንደሚሉት ወሎዬ የሆነ ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡

በነገራችን ላይ የፌደራሊዝም ዋና ግብ እንደ ወሎ ዓይነት፣ወሎን የሚመስል አገር መገንባት ነው፡፡ ፌደራሊዝም በየትም አገር ልዩነትን አይሰብክም-አንድነትን እንጂ! መንግሥት ስለፌደራሊዝም ግብ ከወሎ መማር ይጠበቅበታል፡፡

መልካም የገና በዓል!

Filed in: Amharic