>

ምህረት ምንድን ነው? ምህረት አድራጊውስ?ምህረት ሌላ ይቅርታ ሌላ! (ውብሸት ሙላት)

 

በቅርቡ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር፣አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑና የተወሰኑ ሌሎች እስረኞችን፣የተፈረደባቸውም ይሁን ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉ፣ እንደሚፈቱ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ፣የሚፈቱት እስረኞች ማንነትም ይሁን የሚፈቱበት ሥርዓት እስካሁን ግልጽ አልሆነም፡፡ እንደውም፣አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከተናገሩት በተለዬ ሁኔታ፣ የሚፈቱ እስረኞችን ዝርዝር ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ከማረሚያ ቤት አስተዳደር እንዲቀርበላቸው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በይፋ የገለጹት በምህረት (amnesty) እንደሚፈቱ ሲሆን፤ ፕሪዚዳንቱ እንደቀርብላቸው የጠየቁት ደግሞ በይቅርታ (pardon) ለሚፈቱ እስረኞች የሚደረግን ሥርዓትና ሂደት ነው፡፡ በመሆኑም በዚች አጭር ጽሑፍ የምህረትን ምንነት ከኢትዮጵያ ሕግ አንጻር ማሳየት እና ምህረት አድራጊውስ ማን እንደሆነ ማመልከት ነው፡፡

በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 ለምህረት ግልጽና ቀጥተኛ የሆነ ትርጓሜ አላስቀመጠም፡፡ ነገር ግን ከድንጋጌው ምንነቱን መረዳት ይቻላል፡፡ ከይቀርታ የተለዬ ስለመሆኑም በተከታታይነት ከተቀመጡት ከአንቀጽ 229 እና 230 መረዳት አይከብድም፡፡

ምህረት፣ለአንድ ዓይነት ወንጀል ወይም በአንድ ዓይነት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወንጀለኞች ሊሰጥ ይችላል፡፡ ምህረትን የሚያስከለክሉ ወንጀሎች መኖራቸው በሕግ ከተገለጸ ግን ጭራሹንም አይሰጥም፡፡ ለምሳሌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ላይ ለተዘረዘሩት ድርጊቶች ማለትም ዘር ማጥፋት (genocide)፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ (summary executions)፣ አስገድዶ ሰውን መሰወር (forced disappearance)፣ ኢሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶች መፈጸምን (torture) በሚመለት ምህረት አይሰጥም፡፡ በመሆኑም በሕግ በእዚህ አኳኋን ገደብ ካልተደረገ በስተቀር ለማንኛውም ዓይነት የወንጀል ድርጊቶች ምህረት ሊሰጥ ይችላል፡፡

ምህረት የሚሰጠው አገሪቱ ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ሲታይ ምህረት ማድረጉ ለአገሪቱ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሊሆን እንደሚችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 ይገልጻል፡፡ በመሆኑም፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያን እንዳጋጠማት ዓይነት ችግር ሲፈጠር ምህረት ሊሰጥ ይችላል፡፡ የሚሰጠውም ለአንድ ዓይነት ወንጀሎች (ለምሳሌ በሽብር ለተከሰሱ፣ከኦነግና ግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አድርጋችኋል ለተባሉ ወዘተ) ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም፣በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወንጀለኞች (የግንቦት ሰባት፣ የኦነግ አባል የተባሉ፣ የሸፈቱ ወዘተ) ምህረት ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ምህረት ለተወስኑ ሰዎች ተነጥሎ አይሰጥም፡፡ በአንድ ወንጀል የተከሰሱ፣ ጥፋተኛ የተባሉ ሁሉንም የሚያካተት ነው፡፡

ምህረት በሚሰጥበት ጊዜ ገደብ ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል፡፡ ምህረት የተደረገላቸው ሰዎች ላይ በወደፊት ሕይወታቸው ሊያደርጓቸው የማይችሏቸው፣ የሚታቀቡባቸው ድርጊቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ምንም ገደብ የሌለበት ምህረትም የማድረግ ሁኔታም እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ገደብ የሌለበት ምህረት፣ገደብ ያለበት፣ግዴታ የሚያስከትሉ የምህረት ዓይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ስለምህረት ምንነት ይሄን ያህል ካልን ቀጣዩ ጉዳይ ምህረት የሚያደርገው አካል ማን ነው የሚለውን ደግሞ እንመልከት፡፡ ይቀርታ የሚያደርገው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት እንደሆነ ሕገ መንግሥቱም የይቅርታ አዋጁም ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ምህረትን በተመለከተ ግን በግልጽ ይህ ተቋም ነው ባይልም የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ውክልና የተሰጠው (ለምሳሌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት) ሊሆን እንደሚችል መረዳት ቀላል ነው፡፡

አንቀጹ ምህረት በሚደረግበት ጊዜ ለማን እንደሚደረግ፣ ዓላማው ምን እንደሆነ፣ የተፈጻሚነቱ ወሰን ምን እንደሆነ በሕግ መገለጽ አለበት፡፡ ይህ ሕግ ቀድሞ የሚወጣ ሳይሆን ምህረት ማድረግ በሚያስፈልግበት ጊዜ የሚወጣ ነው፡፡ እያንዳንዱ ምህረት የሚደረግበት ወንጀል ለይቅርታ አሰጣጥ አስቀድሞ ሥነሥርዓቱና ሂደቱ ምን መምሰል እንዳለበት ሕግ ያስፈልጋል፡፡

ምህረት የሚደረገው ግን በጅምላ አንድ ዓይነት ወንጀል ፈጽመዋል ለተባሉ ወይም ደግሞ በወንጀል አፈጻጸሙ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ምህረት ለማድረግ የሚያስገድዱ አልበለዚያም ምህረት ማድረጉ የሚያስገኘው ጥቅም አሳማኝ እስከሆነ ድረስ ሕግ አውጭው (ፓርላማው) ምህረት ማድረጉ ያስፈለገበትን ምክንያት (ዓላማ)፣ የተጠቃሚዎቹን ማንነት በመወሰን ምህረት ያደርጋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምህረት የማድረጉን ሥልጣን በውክልና፣ ምህረት ማድረግ የሚያስፈልግበትን ሁኔታዎች በመግለጽ ሥልጣኑን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በዚህ መልኩም ቢሆንም ምህረት የሚደረገው ሕግ በማውጣት ነው ማለት ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣ ምህረት ማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን ነው፡፡ ምህረት በሚደረግበት ጊዜ ሁሉ ለእያንዳንዱ ምህረት ራሱን ያቻለ ሕግ በማውጣት በአዋጅ ይፈጸማል፡፡ አሁን ምህረት የምንለው በቀድው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ “የአዋጅ ምህረት” ይባል እንደነበርም ያስታውሷል፡፡

ከአንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ከሰሞኑ በየሚዲያው እንደሚሰማው፣ አስቀድሞ በምን መልኩ ምህረት መደረግ እንዳለበት የምህረት አደራረግ አዋጅ አያስፈልግም፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቃል የገቡት ምህረት ማድረግ እንጂ ይቅርታ አይደለም፡፡ ምህረት የሚደረገውም በተመሳሳይ ወንጀል ለተከሰሱ ወይም ጥፋተኛ ለተባሉ ወይም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወንጀለኞች ነው፡፡ ስለሆነም፣አቶ ኃይለማርያም የሕዝብ ተወካዮች አባላት ጋር ተመካክረው፣ቃል የገቡትን ፓርላማው በአዋጅ ምህረት በማድረግ እንዲፈቱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምህረት ያሉትን ወደ ይቅርታ ዝቅ ካላደረጉት ማለት ነው፡፡

Filed in: Amharic