>

የቋራው ካሳ (አጼ ቴዎድሮስ) ፩፱፱  ዓመት

ግርማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጥር 7 ቀን 1811 ዓ.ም ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ተወለዱ።

በትውልድ ስማቸው ካሳ ሃይሉሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳ ወይም አንድ ለናቱ ተብለው የሚታወቁ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፤ ወታደርና ፖለቲከኛ ነበሩ።

መይሳው ካሳ በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ታላቅ ራዕይ ይዘው የተነሱ ጀግና ስለነበሩ፤ በ1840 ዓ.ም አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ።

በጦርነት የገጠሟቸውን ባላባቶች ስላሸነፉ፣ መጀመሪያ የራስ ማዕረግን በኋላም የንጉሥ ማዕረግን በአንድ ዓመት ውስጥ ተቀዳጁ። በየጊዜው በሚያደርጉት የተሳካ ዘመቻ የዘመኑን ባላባቶች ኃይል በመሰባበር የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም ንጉሥ ካሳ ፤ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ።

የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንግሥና የዘመነ መሳፍንት መቃብር በመሆን የዘመናዊ ኢትዮጵያን ታሪክ “ሀ” በማለት ጀመረ። በዘመነ ንግሣቸው አፄ ቴዎድሮስ አገሪቱን የሚያሻሽሉ በርካታ ሥርዓቶችን አስተዋውቀዋል።

ከነዚህም ውስጥ ባርነትን የሚያግድ አዋጅ፣ የመጀመሪያው መንገድ ግንባታ፣ የሥርዓተ ንዋይና የፖለቲካ ሥርዓቱን በማዕከላዊ መንገድ ማዋቀር ለአብነት ይጠቀሳሉ። በ1852 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርስት የነበረውን መሬት ለገበሬወች በማከፋፈላቸው ከሃይማኖት መሪወች ጋር ተጣሉ።

ይህን ተከተሎ በየቦታው አመጽ በሚነሳበት መካከል አውሮፓውያን ሚሲዮኖችም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተነሳሳ አለመግባባት ምክንያት በአፄው ታሰሩ።

በመጋቢት ወር 1860 ዓ.ም ላይ የእንግሊዝ መንግሥት በሮበርት ናፒየር የሚመራ፣ በጊዜው እጅግ ግዙፍ የተባለ ኃይልን አሰናድቶ አውሮፓውያን እስረኞችን ለማስፈታት ጦር ላከ። ሚያዝያ 5 ቀን 1860 ዓ.ም ይህ ጦር በመቅደላ ምሽግ ላይ በሚገኘው፣ በአመጽ በተዳከመው የንጉሱ ጦር ላይ ጥቃት አደረሰ።
በውጊያው መሃል ንጉሠ ነገሥቱ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁ እስከመጨረሻው አሻፈረኝ በማለት በሽጉጣቸው እራሳቸውን ገድለው በጀግንነት አለፉ።

አያችሁልኝ ወይ የአንበሳውን ሞት፣
በሰው እጅ ሞሞትን ነውር አድርጎት፣
እርሳሱን እንደ ጠጅ እርሱ ሲጠጣት።

አባትና እናቱ አላንድ አልወለዱ፣
አባ ታጠቅ ካሳ ያ ወንዱ ያ ወንዱ።
የትግሬንም ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ፣
የሸዋንም ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ፣
ወንድ ያለራስዎ ገድለውም አያውቁ።

ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኙአቸው፣
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፣
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው፣
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው፡፡

በወቁቱ የእንግሊዞች ቀንደኛ ተባባሪ፣ መንገድ መሪ እና ሥንቅ አቀባይ የነበሩት የትግሬው ካሣ ምርጫ (አፄ ዮሐንስ አራተኛ) በመቅደላው ጦርነት ላይ ጀነራል ናፒር ካገሩ ሲመጣና ወደ አገሩ ሲመለስ ላደረጉለት መስተንግዶና አቀባበል 12 መድፍ፤ 900 ጠብመንጃና ብዙ ጥይት ኪርክሃም ከተባለ እንግሊዛዊ አስልጣኝ ጋር ሰጥቷቸዋል።

በዚህ ዘመናዊ የጦር መሳሪያና እንግሊዛዊ አስልጣኝ ተጠቅመው፤ በ1863 ዓ.ም አፄ ተክለ ጊዮርጊስን አሸንፈው ከእስክንድሪያ ባስመጧቸው ጳጳስ “ዮሐንስ አራተኛ” ተብለው በአክሱም ከተማ በ1864 ዓ.ም ነገሡ።

Filed in: Amharic