>
6:46 am - Friday October 22, 2021

ለቅሶዬን መልሱ! (የ5ደቂቃ ንባብ) - በፈቃዱ ዘ ሃይሉ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአደባባይ ሁለት ግዜ አልቅሻለሁ። ወይም ለቅሶ ሞክሮኛል ብል ይሻላል። ሁለቱም በአንድ ምክንያት ነው። የመጀመሪያው፣ ሕዳር 2008 ነው። ገና ዓመት ከስድስት ወር ታስሬ የተፈታሁ ሰሞን ነበር። ሰመጉ የሰብኣዊ መብቶች ቀንን እያከበረ ነበር። ድንገት እስኪ ገጠመኝህን ተናገር ተብዬ እንደጀግና መድረክ ላይ ተንደርድሬ ወጣሁ። በፈገግታ አንድ ዓረፍተ ነገር ከተናገርኩ በኋላ በሳግ ሁለተኛው ተቋረጠ። ልቀጥል ስል ሌላ ሳግ። ልቀጥል ስል ሌላ ሳግ። መድረክ መሪው “ከዚህ በላይ አስረጂ ንግግር የለም” ብሎ ብሎ ወደ ወንበሬ መለሰኝ።

ከ3 ዓመት በኋላ ሰሞኑን መንግሥት “ማዕከላዊ ሊዘጋ ነው። ሙዚዬም ሊሆን ነው” ብሎ አወራ። የቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (አፍሪካ) ጋዜጠኛ የማዕከላዊ ትዝታዬን ጠየቀችኝ። የት እንደደበቅኩት የማላቀው እምባ ባይኔ ካልወጣሁ አለ። ምላሴ ተሳሰረ። እንግሊዝኛው ጠፋ። አማርኛ አስናፈቀኝ። የማዕከላዊን ገብስ ገብሱን እየሳቅኩ ሳወራ የኖርኩ ሰው፣ በሐሳብ ተመልሼ ገባሁ። በቀላል ቋንቋ በሳግ መልስ ሰጠሁ።

ባለሥልጣኖቻችን ኮሜድያን ናቸው። ማዕከላዊ የሚዘጋው ‘ደርግ የማሰቃየት ተግባር ይፈፅምበት ስለነበር ከዚያ ትዝታ እንዲላቀቅ ለማድረግ ነው’ አሉ።  ይህም አልበቃቸውም። ኮማንደር መብራህቱ የተባሉ ሰው በጋዜጠኛ ሲጠየቁ ‘ቦታው ለቢሮ ሥራ ስለጠበበ ወደተቀያሪ ቦታ ዝውውር አድርገናል’ አሉ። የፖለቲካ ክንፉ በፕሮፓጋንዳ ሊያተርፍበት የፈለገውን ጉዳይ የፀጥታ ኃይሉ ሳያውቅ አጋልጦታል።

ኮሜድያኑ በብዛት ትራጄዲያን ናቸው። እየዋሹ በሐዘንም በደስታም ያስለቅሱናል። እኛም እንታለላን። አንዳንዴ አውቀን ነው የምንታለለው። አለበለዚያ ሕይወታችን ደረቅ እዬዬ ይሆናል። ባለፈው ሳምንት ከማዕከላዊ መዘጋት በላይ አስደሳች የሚመስለው ዜና የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ዜና ነው። እምባ የሚያመጣ ዜና ነበር። የደስታ። ከዚያ በላይ እምባ የሚያመጣው ግን ማንን ፈተው ማንን እንደሚያስቀሩ፣ መቼ ወደተግባር እንደሚፈፅሙት ባለማወቅ በተስፋ ጭንቀት የሚብሰለሰለው የእስረኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በቃል ያሉት እንዲህ ነበር፦ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው እና ጉዳያቸው በመታየት ላይ በሚገኙ የፖለቲካ አመራሮችም ሆነ ግለሰቦች […] ክሳቸው ተቋርጦ እንደዚሁም ደግሞ ምኅረት ተደርጎላቸው” ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መሠረት ይፈታሉ። ይህ በመሠረቱ ሁሉም እስረኞች (የፖለቲካዎቹን ብቻ ሳይሆን ደረቅ እስረኞችን ጨምሮ) ይፈታሉ ከማለት አይለይም። ሁሉም እንዳልሆኑ እንዳናስብ “አንዳንድ” የሚል ቃል ተጠቅመዋል። አንዳንዶቹ እነማን ናቸው የሚለውን ግልጽ ለማድረግ ደግሞ የሚፈቱበትን ምክንያት ማየት ያስፈልጋል፦ “አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ይበልጥ ለማስፋት”። የደረቅ ወንጀለኞች መፈታት ለአገራዊ መግባባትም ይሁን ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት ፋይዳ ስለሌለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፖለቲካ እስረኞች ማውራታቸው እንደሆነ ያለጥርጣሬ ማመን ይቻላል። “የፖለቲካ እስረኞች” የሚለውን ቃል ሲክዱት የኖሩትን ነገር ከማጋለጡም ባሻገር፣ ራሳቸውን ወደመወንጀል ስለሚያመራባቸው ቃሉን የጠሉበትን ምክንያት እንረዳለን። መረዳት የማንችለው የገቡትን ቃል ወደተግባር ለመቀየር ምን እንደቸገራቸው ነው።

በፌዴራል ደረጃ የፖለቲካ ክሶች መደብሮቹ – የልደታ ምድብ 4ኛ እና 19ኛ ችሎቶች ናቸው። እነዚህ ችሎቶች ይህ ብዙዎቻችንን በደስታ እምባ ያስተናነቀ ዜና ከተሰማ በኋላ ብቻ ከ30 በላይ ሰዎች ላይ ፍርድ አስተላልፈዋል። ጭራሽ በችሎት መድፈር ትልልቆቹን ፖለቲከኞች ሳይቀር የእስር ብይን አሳልፈውባቸዋል። የደስታ እምባን በሐዘን እምባ ማበስ ማለት ይሄ ነው። ቃል የተገባው ፍቺ ያለጥርጥር የሚመለከታቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ኦቦ በቀለ ገርባ ከነዚህ “የችሎት መድፈር ፍርደኞች” አንዱ ሆነዋል። በአሸባሪነት ተከሰው ከቀረበባቸው ማስረጃ አንዱ በኦሮሞ ስተዲስ አሶሲየሽን መድረክ ላይ ስለሠላማዊ ትግል አስፈላጊነት ያደረጉት ንግግር ነው። ዳኞች “ማስረጃው ለሽብር ክስ አይበቃም፤ በንግግር አመፅ የማነሳሳት ሙከራ ነው” በሚል ክሳቸው ከሽብር ወጥቷል። በወንጀል ሕጉ 257/ሀ መሠረት ክሳቸው ሲቀጥል ደግሞ በዋስ መውጣት ነበረባቸው። ተከልክለው፣ ይግባኝ ብለው፣ 30ሺሕ ብር ተፈቅዶላቸው፣ ከፍለው፣ ታግዶባቸው… በግዞት የተያዙ የፖለቲካ እስረኛ ናቸው። እኚህ ሠላማዊ ፖለቲከኛ ታዲያ አሁን የመንግሥት ቃል ሲፈፀም የትላንቱ ፍርድ ይነሳላቸዋል ወይስ እንደደረቅ ወንጀል ሊቆጠር ነው?

ወይ ሁሉንም ፍቱ፣ አልያም ለቅሷችንን መልሱ!

Filed in: Amharic