>

የእስረኞች አለመፈታት፣ የብሔር የበላይነትና የቄሮ ምርመራ (ተስፋለም ወልደየስ -አርያም ተክሌ)

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ያነሷቸው ጉዳዮች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መወያያ መሆናቸው ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን “ቄሮ” ተብሎ በሚጠራው የወጣቶች ስብስብ ላይ ምርመራ እንደጀመረ መገለጹም አነጋግሯል፡፡ለአስራ ሰባት ቀናት በር ዘግተው ሲመክሩ የሰነበቱት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እና የተወሰኑ የቀድሞ ታጋዮች ስብሰባቸውን አገባድደው የጸሁፍ መግለጫ ሲያወጡ በርካታ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ግራ መጋባታቸውን በተለያየ መልክ ገልጸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካዊ ቀውስ ላይ ቁልፍ ውሳኔዎች ያስተላልፋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው ስብሰባ ምንም የተለየ ነገር ይዞ አልመጣም? ሲሉም ተችተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት ስለ ስብሰባው ውጤት በጋራ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ግን ጉዳዩ ሌላ መልክ ይዟል፡፡ 

በመንግስታዊው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሶስት ክፍሎች በተከታታይ የቀረበው የሊቀመናብርቱ መግለጫ በፈርጅ በፈርጅ እየተመዘዘ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች መወያያ ሆኗል፡፡ በብዙዎች ዘንድ ተደጋግሞ የተነሳው በመግለጫው ወቅት ቃል የተገባው የእስረኞች ፍቺ ጉዳይ ነው፡፡ “የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት” በማሰብ ከእስር ይለቀቃሉ የተባሉ እስረኞች እስካሁን አለመፈታታቸው ጥያቄ ወልዷል፡፡

Venezuela Symbolbild Gefängnis (Getty Images/AFP/J. Barreto)

ዲ. በቃና በሚል የትዊተር አድራሻ የሚጠቀሙ ግለሰብ ረቡዕ ዕለት በጻፉት አስተያየት ሁኔታውን በኢትዮጵያ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ካለውን እቀባ ጋር አያይዘውታል፡፡ “የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ከሰማን ሳምንት ሆነን፡፡ የሚያሳዝነው የጭቁን ህዝብ መብት ተሟጋቾችም፣ የጭቁን ህዝብ መተንፈሻ የሆነው ኢንተርኔትም ታፍኗል(አልተፈታም)” ብለዋል፡፡ ገልጋሉ አባ ዋቆ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ “መንግስት አለ ወይ?” ብለው እስከመጠየቅ ተጉዘዋል፡፡

“ኢህአዴግ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ካለ በኋላ ምንም ሳናይ ይሄዉ ሁለተኛ ሳምንት ልንይዝ [ነው]፡፡ ይህን ለማድረግ የተገደድነው ያለዉን የፖለቲካ ዉጥረት ለማርገብና ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄድን ለማበረታታት ነው በማለት ቃል ገብተዉ ነበር። ከምር ይህን ካሰቡ የታሰሩትን ለመልቀቅ እንዴት ይህን ያህል ይከብዳል? ወይስ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ቃል የሚተገብር ጠፋ? አረ መንግስት ካለ ቃሉን ወደ ተግባር ይቀይር” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። 

ገዢው ፓርቲ “ይፈታሉ የተባሉት የፖለቲካ እስረኞች ሳይሆን የተወሰኑ የፖለቲካ አመራሮች እና ግለሰቦችን ነው” ቢልም አሁንም ድረስ በርካታ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች “የፖለቲከኛ እስረኞች” የሚለውን አገላለጽ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል፡፡ የእስረኞቹ ፍቺ መዘግየት ያሳሰባቸው ዘላለም አባተ ከእነዚህ ውስጥ ይመደባሉ፡፡ “የፖለቲካ እስረኞችን እና የተወሰኑ ግለሰቦችን ለመፍታት ቃል ገቡ፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ዜናውን በስፋት ዘገቡ፡፡ ከሳምንት በኋላ ግን የገቡትን ቃል ቀነሱ፡፡ በሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት መካከል አለመስማማት ተፈጠረ፡፡ አንድም እስረኛ ሳይለቀቅ ቀረ፡፡ በሚያዝሳን ሁኔታ ማንም ስለዚህ የጠየቀ የለም” ሲሉ ባለፈው ረቡዕ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡  

በማህበራዊ ድረገጾች “የፖለቲከኛ እስረኞች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?” ከሚሉ ትንታኔዎች አንስቶ “እነማን ይፈታሉ?” እስከሚሉ መላምቶች ድረስ ያሉ ጽሁፎች መነበባቸው ቀጥሏል፡፡ የፍቺው ወሬ ከተሰማ ወዲህ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ ሁነቶችን በውሳኔው መነጽር መመልከትም ሌላው በማህበራዊ መገናኛዎች የተስተዋለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በተለይ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ባለ የፖለቲካ አመራሮች እና ሌሎች ግለሰቦች የችሎት ውሎዎች ጎልቶ ታይቷል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና አብረዋቸው የተከሰሱ የፓርቲው አባላትን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የትላንት ውሎ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ሄኖክ ጂ. ገቢሳ በትዊተር “ጠቅላይ ሚኒስትር [ኃይለማርያም] ደሳለኝ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ካሳወቁ ከሳምንት በኋላ የፈደራል ፍርድ ቤት [በቀለ] ገርባን እና ሌሎች ሶስት ሰዎችን ፍርድ ቤት በመዳፈር ስድስት ወር ፈርዶባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በፖለቲካ አስረኞች ላይ የሚሰራው የዳኝነት ትያትር ቀጥሏል” ሲል ጽፏል፡፡ ሚክያስ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው “ጥፋተኛ ብለው በይቅርታ ለመልቀቅ እና ክሬዲት ለመውሰድ በማሰብ ይሆን የዛሬውን  የአነ በቀለ ገርባ ትያትር ያሳዩን?” በ“ተስፋ” ጥቄያቸውን አስነብበዋል፡፡  

እንደ እስረኞች ፍቺ ሁሉ በሊቀመናብርቱ መግለጫ ወቅት የተጠቀሰው በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚታወቀው የምርመራ ቦታ  ጉዳይ በዚህ ሳምንትም ሽፋን አግኝቷል፡፡ “ስቅይት ይፈጸምበታል” በሚባለው ማዕከላዊ ላይ ያጠነጠኑ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ውይይቱ እንዲቀጥል በእርሾነት አገልግለዋል፡፡ በመግለጫው ላይ ከተነሱ ጉዳዮች የሞቀ ውይይት የቀሰቀሰው ግን “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም ሆኑ ሶስቱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ሊቀመናብርት “የትግራይ ወይም የአንድ ብሔር የበላይነት የለም” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ደጋግመው ለማሳመን ቢታትሩም ጉዳዩ በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ክርክር መፍጠሩ አልቀረም፡፡ 

Äthiopien 40. Jahrestag TPLF (DW/T. Weldeyes)

ለክርክሩ ዋነኛውን ሚና የተጫወተው ደግሞ አቤቶኪቻው በሚባለው የብዕር ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው አበበ ቶላ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን በፌስ ቡክ ካሰፈረ በኋላ ነበር፡፡ የሊቀመናብርቱን ንግግር በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አድርጎ በፌስ ቡክ ያጋራው አቤቶኪቻው ከዚያ በመነሳት የራሱን ሀሳብ ዘርዝሯል፡፡ አስተያየቱን ብዙዎች የተቀባበሉት ሲሆን “የበላይነት አለ ወይስ የለም?” በሚል በሁለት ጎራ ለተከፈለ የጦፈ ክርክር መነሻ ሆኗል፡፡ የድጋፍ እና የነቀፌታ አስተያየቶች የተዥጎደጎዱለት አቤቶኪቻው በጉዳዩ ላይ ሀሳቡን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ በማሰብ አንድ ሰዓት ተኩል ርዝመት ያለው የቪዲዮ ማብራሪያ በፌስ ቡክ ገጹ ጭኗል፡፡ ቪዲዬው አርባ ሰባት ሺህ የሚጠጋ ጊዜ የመታየት ዕድል ቢያገኝም ክርክሩ ግን እስካሁንም ዘልቋል፡፡ ነዋሪነቱ በእንግሊዝ ሀገር የሆነውን አበበ ቶላ ስለ ፌስቡክ አስተያየቱ ይዘት እና ስለቀሰቀሰው ውይይት ጠይቄው ነበር፡፡ 

“ከዚህ በፊት የአማራ የበላይነት የሚባል ትርክት ነበር፡፡ እና ከእሱ ጋር አያይዤ ለማንሳት ሞከርኩኝ፡፡ በተለይ መገናኛ ብዙሃኖቻችን ይሄን ‘የትግራይ የበላይነት አለ’ የሚለውን ነገር በተደጋጋሚ ሲገልጹት ነበር፡፡ ‘አዎ አለ’ ሲሉ መገናኛ ብዙሃኖቻችን ሲገልጹ በማየቴ ይሄ ነገር አደጋው እንዴት አልታያቸውም የሚል ሀሳብ ያዘኝ፡፡ ይሄ ሀሳብ የመጣብኝ ከምንድነው? ህወሓት በተለይ በተደጋጋሚ በተሳሳተ መልኩ፣ በተሳሳተ አረዳድ የአማራ የበላይነት በሚል ሲያስፋፋው ወይም ሲናገረው የነበረው ንግግር ጭቁኑን የአማራ ህዝብ ምን ያህል ጉዳት ላይ እንደጣለው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤ የዕለት ተዕለት ልምዳችንም ጭምር ነው፡፡ ትላንትና ከጉራፈርዳ የተፈናቀሉ ሰዎችን ማየት እንችላለን፡፡ ቤንሻንጉሉን ማየት እንችላለን፡፡  አሁንም ቢሆን በተለያዩ ቦታዎች ኮሽ ባለ ቁጥር ምስኪን የአማራ ብሔረሰብ ተወላጅ በሞላ በስጋት ላይ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡ 

ትላንትና የአማራ የብሔር የበላይነት የለም እያልን ዛሬ ደግሞ እንዴት የትግራይ የበላይነት አለ እንላለን፡፡ እነዚህ ንግግሮች ለማህብረሰቡ አደገኛ ንግግሮች ናቸው፡፡ አደገኛ የቅስቀሳ መንገዶች ናቸው፡፡ ትላንት የአማራ የበላይነት አለ በመባሉ እያየን ያለነው ጦስ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ዛሬን የትግራይ የበላይት አለ እያልን ነገ የማንወጣው ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ መግባት አይገባንም፡፡ ብንችል እና ማድረግም ያለብን ይሄ የአማራ የበላይነት አለ የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ትክክለኛውን አቅጣጫ ማሳየት እና የህዝብ የበላይነት የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ እንደማያውቅ መሳየት ነው የሚል ሀሳብ ይዤ ነበር የመጣሁት፡፡ በተለይ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ እና ዘገባዎቻቸውን ሲያስተላልፉልን በኃላፊነት ስሜት ሊናገሩ እና ሊያስተላልፉን ይገባል የሚል መነሻ ይዤ ነበር ጽሁፍ ያሰፈርኩት፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች በጥሩም በመጥፎም መልኩ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተውበታል፡፡ ግማሾች ግንዛቤ ይዘውበታል፣ ግማሾች ደግሞ የያዙትን ግንዛቤ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን መወያያ ሆኖ ከርሞ ነበር የሚለው ግን እውነት ነው፡፡” 

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳያችን ተሻግረናል፡፡ የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን  በተለይ በምስራቅ ሐረርጌ የሚንቀሳቀሰው እና “ቄሮ” ተብሎ በሚታወቀው የወጣቶች ስብስብ ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ መዘገቡ በዚህ ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ነው፡፡ በርካቶች እርምጃውን ገዢው ፓርቲ በቅርቡ እወስዳቸዋለሁ ካላቸው ማሻሻያዎች ጋር የሚጣረስ ነው ሲሉ ነቅፈውታል፡፡ የተወሰኑ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ለወጣቶቹ ስብስብ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት የፌስ ቡክ “ከቨር ፎቷቸውን” “ቄሮ” የሚል ጽሁፍ በጉልህ በተጻፈበት ምስል ቀይረዋል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ኮሚሽኑ በቄሮ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ካሰበ ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን አስጠንቅቀዋል፡፡ 

ባቲ መገርሳ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ከኋለኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ተርታ ይሰለፋሉ፡፡ “የፌዴራል ፖሊስ ቄሮን ለማሳደድ የወሰነዉ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ እስር ቤቱ ባዶ እንዳይሆን ሰግቶ ይመስላል፡፡ እንግዲህ ይሞክራታ!” ሲሉ ዝተዋል፡፡ ሳምቤ ቦና ደግሞ “ከቄሮዎች ጋር አትሳፈጡ፡፡ እነርሱ እሳቶች ናቸው” የሚል ምክር በፌስ ቡክ አስተላልፈዋል፡፡ አበበ ጉተማ “ቄሮ ቢመረመር ምን ይመጣል?” በሚል ርዕስ ተከታዩን በፌስቡክ አጋርተዋል፡፡ 

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten (DW/Y. Gebregzihabher)

“ቄሮ የሚመረመረዉ ምን ስለሆነ ነዉ? ቄሮ ከዉጪ የመጣ አካል አይደለም፡፡ አሁን የተፈጠረም አይደለም፡፡ ቄሮ የህዝብ ልጅ ነዉ፡፡ ቄሮ ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙ ያላገባ ወጣት ወንድ ልጅ ማለት ነዉ፡፡ ይሄንን ከማንኛዉም የኦሮምኛ-አማርኛ-ኢንግሊዘኛ መዝገበ-ቃላት ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይሄ ክፍል በብዛት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በዩኒቨርሲቲዎች አከባቢ የሚገኝ ነዉ፡፡ ቡድን አይደለም፡፡ የተደራጀ አይደለም፡፡ የታጠቀ ሃይል አይደለም፡፡ በየቦታዉ በተለያዩ የተቃዉሞ ሰልፎች ላይ ባዶ እጃቸዉን አጣምረዉ የሚታዩ ወጣቶች ናቸዉ፡፡ ይህ የዕድሜ እኩዮች ተፈጥሯዊ ስብስብ እንጂ ሌላ መገለጫ የለዉም፡፡

አሁን ባለዉ ሁኔታ የተለየ መገለጫቸዉ ስራ አጥነት ነዉ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ነዉ፡፡ ይሄንን ያመጣዉ ደግሞ ዝርፊያ ነዉ እንጂ ሃገራችን ሃብት አጥታ አይደለም፡፡ ይሄ ስላሳሰበዉ የመብት ጥያቄ በማንሳት ላይ የሚገኝ ነዉ፡፡ ‘እኛም ዜጋ ነን፤ እኩል ተጠቃሚ እንሁን’ እያለ መብቱን እየጠየቀ ያለ የህዝብ አካል ነዉ፡፡ ህዝብን መመርመር ማንን ለመጥቀም ነዉ? ስለዚህ ምርመራ የተባለዉ ጉዳይ በአንድ በኩል ይሄንን የመብት ጥያቄ ለማፈን በሌላ በኩል ደግሞ የሰሞኑን የፖለቲካ ትኩሳት አቅጣጫ ለማስቀየር የተቀነባበረ ነዉ፡፡ ስለዚህ ትርፉ ድካም እንጂ ምንም ጠብ የሚል ነገር ስለማይኖር የሚያሳስብ ነገር የለዉም፡፡”

ጉደታ ገለልቻ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም “የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ አሁንም እንደቀጠለ ነው” በሚል ርዕስ ተመሳሳይ አስተያየት አስፍረዋል፡፡ “ከሳምንት በፊት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ‘ቄሮን መርመር ጀምረናል’ ማለታቸው ተሰማ፡፡ ቄሮ ማለት በአፋን ኦሮሞ ከ16 እስከ 24 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያለው ወጣት ማለት ነው፡፡ ታድያ ፌዴራል ፖሊስ በትንሹ ከሃያ ሚሊዮን በላይ የሆነውን ይህን የህብረተሰብ ክፍል እንዴት አድርጎ ነው ለመርመር የተዘጋጀው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጉደታ በዚያው ጽሁፋቸው በኢህአዴግ ተስፋ መቁረጣቸውን እንዲህ ገልጸውታል፡፡ “ከእንግዲህ ከኢህአዴግ መንደር የፈውስ መድኃኒት ይገኛል ብሎ መጠበቅ ማለት እድሜው ገፍቶ የሞት አፋፍ ላይ ከደረሰው አዛውንት ወደ ኋላ ተመልሰህ የቄሮን ሥራ ሥራ ብሎ እንደ መጠበቅ ነው” ብለዋል ጉደታ፡፡  

Filed in: Amharic