>
8:21 am - Sunday January 29, 2023

ከካሳ እስከ ቴዎድሮስ (አፈንዲ ሙተቂ)

በጎንደር ቤተ መንግስት እልፍኝ ውስጥ ከባድ ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ የተገኙት እቴጌ መነን (ትልቋ)፣ ራስ አሊ፣ አንድ መነኩሴ እና ሌሎች ሹማምንት ነበሩ (ደጃች ወንድይራድ ደግሞ ወደ ኋላ ላይ ውይይቱን ይቀላቀላል)።

1ኛ ተናጋሪ (እቴጌ መነን)

አረ ለመሆኑ ምን ይሆን አሳቡ
ሸፍቶ የሄደው ከነቤተሰቡ?

2ኛ ተናጋሪ (ራስ ዓሊ)

ሰውዬው ኩሩ ነው የተነፋ ልቡ
ይዞ ማዋረድ ነው ይበርዳል ጥጋቡ::

3ኛ ተናጋሪ (አንድ መነኩሴ)

ሰውዬው ብርቱ ነው ስሙ የተጠራ
ጎበዝ እኔ ነኝ ባይ ሀይልን የማይፈራ
በዘዴ በትዕግስት ማባበል ይሻላል
በሀይል ብንለው በጣም ያውከናል፡፡
—-
4ኛ (እቴጌ መነን)

እንዲህ ስትሉ ነው ስሙ የገነነው
የፈራነው መስሎት አገር የሚያብጠው
ዘዴ መላ አታብዙ ጦር ይታዘዝና 
ቢቻል ከነነፍሱ ይምጣ ይያዝና
እምቢ ካለም ይሙት በገዛ ጥፋቱ
ላንድ ወንበዴ ሽፍታ አይስጋ መንግሥቱ፡፡
——
ይህ ጭውውት የተቀነጨበው “ቴዎድሮስ” ከተሰኘው የደጃች ግርማቸው ተክለሃሪያት መጽሐፍ ሲሆን በጭውውቱ ውስጥ “ለምን ሸፈተ” ተብሎ እንደ አጀንዳ የቀረበው ደግሞ የያኔው ደጃች ካሳ ሀይሉ የኋለኛው ዳግማዊ ቴዎድሮስ መሆኑ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ካሳ ሀይሉ ከተራ ቤተሰብ ተወልዶ በአስገራሚ ሁኔታ የቤተ መንግሥቱ አባል ሆኖ ነበር፡፡ ታሪክ አለው፡፡

ደጃች ካሳ በወጣትነቱ ሽፍታ ሆኖ በቋራና በደምቢያ ይዘዋወር ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ሱዳንን ከሚቆጣጠሩት የቱርክ/ግብጽ ገዥዎች ጋር የድንበር ላይ ውጊያ ያካሄዱ ነበር፡፡ ታዲያ በአንዱ ውጊያ ላይ የዘመኑ ዋና መስፍን የነበሩት የራስ ዓሊ ልጅ የሆነችው ወይዘሪት ተዋበች ተማረከች፡፡ ይህም ወሬ ለካሳ ጆሮ ደረሰ፡፡ ካሳ በወቅቱ ሽፍታ ቢሆንም የኢትዮጵያዊያን መሸነፍና በምርኮ መጋዝ በጣም አበሳጨው፡፡ በመሆኑም በቱርኮች ላይ ድንገተኛ አደጋ ጥሎ አተረማመሳቸው፡፡

ካሳ ይህንን ሲያደርግ ተዋበች ምርኮኛ መሆኗ በቁጭት ውስጥ ጥሎአት በመርዝ ጩቤ ሰውነቷን ወግታ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ በማድረግ ላይ ነበረች፡፡ ይሁንና ካሳ በቦታው ደርሶ መርዙ ወደ ሰውነቷ ጠልቆ ሳይገባ ከደሟ ውስጥ መጥጦ ተፋው፡፡ በዚህም የተዋበች ህይወት ተረፈች፡፡ ካሳም ተዋበችን በጀርባው አዝሎ ከውጊያው እየሮጠ ወጣ፡፡ ወታደሮቹም በቶሎ እንዲያፈገፍጉ ትዕዛዝ ሰጣቸው፡፡

ካሳ ነፍሲያዋን ያተረፈላትን ተዋበችን ለአባቷ ለራስ ዓሊ አስረከባት፡፡ ራስ ዓሊም በጀግንነቱ ተደስተው እሷኑ ዳሩለት፡፡ ሽፍትነቱን ትቶ በቤተመንግሥት እንዲኖርም አደረጉት፡፡ ይሁንና የቤተመንግሥቱ ህይወት በነጻነት መኖርን ለለመደው ካሳ የግዞት ያህል ሆነበት፡፡ በዚያ ላይ መኳንንቱ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” እያሉ የሚያሳዩት ንቀት በጣም አቃጠለው፡፡ ተዋበችም በባሏ ላይ በሚደርሰው ንቀትና ማሽሟጠጥ በገነች፡፡ እናም በአንድ ውድቅት ላይ “አንተ ካሳ! ጎራዴህን ታጠቅና ተነሳ፤ ምንጊዜም ከጎንህ ነኝ” አለችው፡፡ ካሳም ሸፈተ፡፡
—-
እንግዲህ ከላይ የቀረበው ጭውውት ካሳ በሸፈተ በማግስቱ የተደረገ ነው፡፡ በዚያ ቀን በተደረገው ምክክር ደጃች ወንድይራድ የካሳን እጅ ይዞ እንዲመጣ ታዘዘ፡፡ ወንድይራድም ከቤተመንግሥቱ ቀርቦ እየጎረነነ ትዕዛዝ መቀበሉን አረጋገጠላቸው፡፡ ይሁንና የወንድይራድ ከልክ ያለፈ ጉራ ያልጣማቸው ራስ ዓሊ “አንተ ወንድይራድ! ካሳ እንደ ሌላው ሽፍታ አይምሰልህ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አደገኛ ተዋጊ ነው” በማለት ምክር ቢጤ ቢወርውሩለት ዳጃች ወንድይራድ እንዲህ የሚል የንቀት መልስ ሰጣቸው፡፡

አይስሙ ጌታዬ ሰው የሚለውን
አያስፈራም ካሳ ይንዛ ጉራውን
ገና መጣ ሲሉት አገር ጥሎ ይሸሻል
ወይንም ካንዱ ደብር ገብቶ ይደውላል፡፡
እንኳን አንድ ሽፍታ ቀማኛ ወንበዴ
ብዙ እመልሳለሁ በጦር በጎራዴ
እኔ ነኝ ወንድይራድ ታማኝ አሽከርሽ
ያን የኮሶ ሻጭ ልጅ የምቀጣልሽ፡፡

የወንድይራድ ፉከራና ድንፋታ ከካሳ ጆሮ ገባ፡፡ ካሳም “እናቴን እንዲህ የሰደበውን ባለጌ ባላሳየው እኔ ካሳ አይደለሁም” በማለት መሃላውን ሰጠ፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ተገናኙ፡፡ ውጊያው ገና ከመጀመሩ የወንድይራድ ፉከራ የአሸዋ ላይ ቤት ሆኖ ፈረሰ፡፡ እቴጌ መነን (የራስ ዓሊ እናት) የተመኩበት ዳጃች ወንድይራድም ተማረከ፡፡ ካሳም መሃላውን ተግባራዊ አደረገ፡፡ ወንድይራድን ቀንና ማታ ኮሶ እያጠጣው ገደለው፡፡

ከዚያ በኋላ ካሳ በሀገሩ ላይ ገነነ፡፡ ማን ይቻለው? ደጃች ውቤም ሆኑ ራስ ዓሊ፣ ደጃች ተድላ ጓሉም ሆኑ ደጃች ጎሹ ሁሉም ተራ በተራ ተሸነፉ፡፡ ካሳን ያሸንፋሉ ተብለው የተጠበቁት እቴጌ መነንም በናቁት አማቻቸው እጅ ምርኮኛ ሆነው ወደቁ፡፡ የጥንቱ የቋራ ሽፍታም ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ ነገሠ፡፡ ንጉሥ ለስሙ ብቻ ቤተመንግሥት የሚቀመጥበት ዘመነ መሳፍንትም አበቃ፡፡ ኢትዮጵያም አዲስ ታሪካዊ ጉዞዋን ተያያዘችው፡፡
—–
(ግንቦት 2006 ከጻፍኩት “ጎንደር እንዴት ነሽ” የተሰኘ የኢትኖግራፊ ወግ የተቀነጨበ ነው)።

Filed in: Amharic