>
5:14 pm - Friday April 20, 1590

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የገጠማት ፈተና ኢትዮጵያን ከመታደግ ጋር ባንድነት የሚታይ ነው (ከይኄይስ እውነቱ)

ወያኔ ግንቦት 1983 ኢትዮጵያን ለግል ዓላማውና ጥቅሙ ሲቆጣጠር፣ ለጥፋት ዓላማው ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠራቸው መንፈሳዊ ተቋማት አንዷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (የኢኦተቤ/ክ) መሆኗ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በአንድ በኩል ሊቃውንቷን፣ ቅርሷን፣ አድባራቱን ገዳማቱን፣ ባጠቃላይ ቤተክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ኹለንተናዊ ሕይወት ያበረከተችውን ዕሤቶች እያጠፋ (የአገዛዙ ቁንጮዎች ይኽቺን የኢትዮጵያ ባለውለታ ቤተክርስቲያን ማጥፋት ከጥፋት ተልኳቸው መካከል አንዱ መሆኑን በጫካ መግለጫቸው በግልጽ ከማስቀመጥ አልፎ ኢትዮጵያ እጃቸው ላይ ከወደቀች በኋላ ይህንን እኩይ ተልእኮ እንዳሳኩ ያለምንም ኀፍረት በአደባባይ የሚደነፉበት ጉዳይ ነው)፣ በሌላ ወገን በሀብት በኩል የማትነጥፍ ‹ላም› ሆና ስላገኛት በጉልበት ሥልጣን የያዘበትን ሌላውን ዋነኛ ዓላማ (ዝርፊያ) መፈጸሚያ ማዕከልም ሆናለች፡፡ ለዚህም ወያኔ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን (ካድሬዎችን) በየአድባራቱና ገዳማቱ በጥምጣምና በቆብ ሽፋን አሰማርቷል፡፡ እነዚህ ተኩላዎች በከተማ የሚገኙና ገቢያቸው ከፍተኛ በሆኑ አድባራትና ገዳማት በተለይም ቊልፍ ቦታዎችን (አስተዳዳሪነት፣ ጸሐፊነት፣ ገንዘብ ያዥነት፣ ገንዘብና ንብረት ተቆጣጣሪነት ወዘተ.) ኹሉ በወረራ መልክ ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡ ለዛሬው አስተያየት መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በአ.አ. ሰዓሊተ ምሕረት ቤተክርስቲያን ከብልሹ አስተዳደርና ዝርፊያ ጋር ተያይዞ በአጥቢያው ምእመናን የተደረገው ተቃውሞ ነው፡፡ የጽሑፉ ትኩረት ግን የቤተክርስቲያንን ፈተና በጥቅሉ ለማየት ነው፡፡
የቤተክህነቱ አገዛዝ ወያኔ የተቆጣጠረው ቤተመንግሥት ግልባጭ መሆኑን እየዘነጋን 27 ዓመታት በሙሉ
እንግዳ መሆናችን ይገርመኛል፡፡ ከአናጕንስጢስ (ዝቅተኛው የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ መዓርግ) እስከ ጳጳስ በጉቦ ከተሰየሙባት የቤተክርስቲያን አገዛዝ ምንድነው የምንጠብቀው? ቤተክርስቲያኒቱ ድሮም ሆነ ዛሬ በዘመናዊ አስተዳደር (የሰው ሀብት፣ የፋይናንስ፣ የንብረት ወዘተ.) ድክመት የምትታማ አይደለችም፡፡ በዘርም ጉዳይ እንደዚሁ፡፡ (ክርስቲያን ዘር መቊጠር ካስፈለገው ኹሉም የክርስቶስ ዘር ነው፡፡) የኢኦተቤ/ክ በዓለማዊውና በመንፈሳዊው ትምህርት የሠለጠኑ ልጆችዋ እነሆ ደረስን አለንልሽ ሲሏት፣ ድብቅ ተልእኮ ያላቸው ተኩላዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የቤተክርስቲያኗ ልጆች ነን በሚሉ የቤተክህነቱ አገዛዝ አባላት (ድንቁርናና ንቅዘት) ጭምር ተቀባይነት አላገኙም፡፡ በመሆኑም በአስተዳደር ረገድ የኢኦተቤ/ክ ዘመኑን መዋጀት ያልቻለች ተቋም ሆናለች፡፡ እንዴት ይኽች ጥንታዊ ተቋም ከ1600 ዘመናት በላይ ስትለምን ትኖራለች? የዘመናዊ አስተዳደር ችግር (ድንቁርና) ካልሆነ በቀር በልማት ራሷን መቻል እንዴት ተሳናት?

ሥልጡን አሠራርን ከቅንነት ጋር አጣምሮ የያዘ አስተዳደር ቢኖራት ከራሷ ተርፋ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ‹‹የኔ ቢጤ››/ እና ጎዳና ተዳዳሪ መኖር ነበረበት? ከዓላማዎቿ አንዱና ዋናው ምስካየ ኅዙናን (የችግረኞች መጠገያ) መሆን አይደለምን? የአዘቦቱን ትተን ምእመኑ በየንግሡ በዓላት ጥሬ ገንዘቡን፣ ወርቁን፣ ከብቱን፣ ወዘተ. በመባዕ እና በስእለት መልክ ይሰጣል፡፡ ይኽ በየዓመቱ የሚገኘው በቢሊዮን የሚቆጠር የምእመናን ሀብት (ለአገልጋዮች የሚፈጸም ክፍያና አስተዳደራዊ ወጪን ግምት ውስጥ አስገብተን) የት ነው የሚውለው? የኢኦተቤ/ክ ምእመን በተቀራረበ ግምት የኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሹ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የእምነት ጉዳይ ስለሆነ ገቢ ያለው ብቻ ሳይሆን ለምነው ለቤተክርስቲያን የሚሰጡ እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የቤተክርስቲያኑ ተቋማት በጥናት ሊያሳውቁን ይችላሉ፡፡ እስከ መቼ ነው ምእመኑ በራሱ ጉዳይ ዳር ሆኖ ገንዘቡን/ሀብቱን ለሌቦችና ወንበዴዎች እየወረወረ እግዚአብሔርን እንዳገለገለ የሚቆጥረው፡፡ ይህ መንፈሳዊነት አይደለም፡፡ ጽድቅም አይደለም፡፡ የዋህነትም ልለው አልችልም፡፡ ግድየለሽነትና ድንቁርና ሞኝነት እንጂ፡፡

ክርስትናው የሚያስተምረን እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ እንድንሆን ነው፡፡ ቢያንስ ይህ የወያኔ አገዛዝ እስኪወገድ በከተማ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት የሚገኙ አገልጋዮችን (እውነተኛውን ከተኩላው በመለየት) ምእመናን ኃላፊነቱን ወስደን ለአገልጋዮች ወርኃዊ ክፍያቸውን መፈጸም እንችላለን፡፡ ከዚህ ውጭ በሙዳየ ምጽዋትም ሆነ በተለያየ መልኩ የሚደረገውን በገንዘብ፣ በወርቅና በከበት የሚደረገውን መባዕ ለዘራፊዎች ሲሳይ ከማድረግ መቆጠብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ በየአጥቢያችን ያሉ ቅርሶችና ንብረቶችን (ከዘራፊዎች የተረፈ ካለ) ጠንቅቀን እንወቅ እንጠብቅ፡፡ ያለነው በድህነት ‹ሀብታም› የሆነ አገር ውስጥ
በመሆኑ አካሉ የጎደለውን ‹የኔ ብጤ› ብቻ ሳይሆን መለመን አፍሮ ከነ ልጆች ቤቱን ዘግቶ ወይም አገዛዙ ከቤት ንብረቱ አፈናቅሎት በየላስቲክ መጠለያው ለሚገኝ ወገናችን ብንደርስለት ከጽድቅም ታላቅ ጽድቅ ነው፡፡ ሕንፃ እግዚአብሔር (ክቡሩ የሰው ልጅ) እየፈረሰ ሕንፃ ቤተክርስቲያን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰስን (ለዛውም አብዛኛው ለዘራፊዎቹ ሲሳይ የሚሆን) ለመገንባት መጨነቅ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባንን አለማወቅ ነው፡፡

ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንረዳውና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም እንደሚያስተምሩን ቤተክርስቲያን ማለት
ዋና ፍቺው የምእመናን አንድነት/ኅብረት ነው፡፡ ቤተ መቅደስም ቀዳሚ ፍቺው የእያንዳንዳችን ሰውነት መሆኑን ባለቤቱ ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው (ሥጋ ለብሶ በሰውነት በተመላለሰበት ዘመን) አስተምሯል፡፡ በመሆኑም ሕንፃ
ቤተክርስቲያኑም ሆነ ቤተክህነት እንደ ተቋም ከምእመናን ውጭ ትርጕም የላቸውም፡፡ የቤተክርስቲያን ገንዘብም
ሀብትም ምእመናን ናቸው፡፡ ማነው በምእመናን ገንዘብ/ሀብት ላይ የሚያዘው? መንፈሳዊነትና መንፈሳውያን
ተመናምነው በምትኩ ገንዘብ በሠለጠነበት በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን የወንበዴዎችና ዘራፊዎች ዋሻ ሆናለች፡፡ ዛሬ የኢኦተቤ/ክ ባለቤት ቢኖራት ታላቁ የዋልድባ ገዳም ባልተደፈረ ነበር፡፡ ለምን ተደፈረ ብለው የተቃወሙት መነኮሳት በአገዛዙ ወህኒ ቤት ተጥለው ግፍና በደል ሲፈጸምባቸው ተገቢ አይደለም፣ ልቀቋቸው ብሎ የሚሟገት እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያለ መንፈሳዊ አርበኛ አባት ባላጡ ነበር፡፡ የሚገርመው ምእመኑም ለእነዚህ የሃይማኖት አባቶች ድምፁን አላሰማም፡፡ ይህም እምነታችን በአለት ወይስ በአሸዋ ላይ የተመሠረተ ነው የሚለውን አጠያያቂ አድርጎታል፡፡

ኹላችን ተካክለን ስለበደልን ይሆን – የኢየሩሳሌም ሰማያዊት አምሳል፤ የኀጢአት ማስተሥርያ፣ ለፈጣሪ
ልመና የማቅረቢያና የመስገጃ፤ የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ መፈተቻ፤ የበረከት፣ የጸሎትና የንጽሕና፤
የሰላምና የፍቅር አደባባይ የሆነችው ቤተክርስቲያን – በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ ሰው የሚገደልባት፣ታጣቂ ‹አገልጋዮች› የተሠማሩባት፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት በጉልበት እንዲወጣ የሚደረግባትና የሚዘረፍባት፣ ርጕም የሆኑ የአገዛዙ ታጣቂዎች ምእመናንን ለመደብደብ እንደፈለጉ የሚፈነጩባት፣ የጥይት ድምፅ የሚሰማባት፣ሌሎችም ተዋርዶዎች ወዘተ. የሚታዩባት?

ለማጠቃለል የኢኦተቤ/ክ በውስጥም በውጭም የገጠማት ፈተና የወያኔ አገዛዝ በመላው ኢትዮጵያ እየፈጸመ
ያለው ጥፋት አካል ነው፡፡ ችግሩ የአንድ ሰዓሊተ ምሕረት ቤተክርስቲያን ብቻ አይደለም፡፡ በመሆኑም እንቅስቃሴያችንን በማቀናጀት በኅብረት መነሳት ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያንን ከአገዛዙ ጋር ካበሩ ወንበዴዎችና ዘራፊዎች ለመታደግ የምንፈልግ ኹሉ፣ የኢትዮጵያ አገራችንን ህልውና እየተፈታተነ ያለውን የወያኔ አገዛዝ አስወግዶ ለነፃነት፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ በሚደረገው ሕዝባዊ ዓመጽ ውስጥ ከጸሎት ባለፈ በተግባር መሳተፍ ይጠበቅብናል፡፡ ለጽድቅ ብለን የምናደርገው ምጽዋት በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ላለፉት 27 ዓመታት እያደሙ ላሉ ወያኔዎች አሳልፈን እየሰጠን መሆኑን እንወቅ፡፡ አገር ስትኖር ነው በማኅበር አምልኮታችንን በሥርዓትና በነፃነት መፈጸም የምንችለው፡፡

ማስተዋሉን ይስጠን፡፡

Filed in: Amharic