>
6:46 pm - Tuesday October 19, 2021

"በስርዓት ያልተመራ ህዝብ የመሪውን ባህሪ ይወርሳል" (አብዮት ሙላቱ)

በጥንት ዘመን በዓለም መድረክ ታፍራና ተከብራ የኖረችን አገር ለማስተዳደር ዕድልና አጋጣሚ ያነሳው ንጉስ በፀሀይ መውጫ አገር በሩቅ ምስራቅ ይኖር ነበር። ‘ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ’ በሚባል ብሂል አገሩን ያስተዳድር ነበርና ንጉሱ ከአባቶቹ ይልቅ በህዝብ የተፈራም የተጠላም ነበር።አባቶቹ ከህግ በታች ነገሱ ።እሱ በህግ ላይ ነገሰ።የሚገዳደረውንም ሁሉ እንደ እሳት በላ።ህዝቡም ሰጥ ለጥ ብሎ ተገዛለት።ንጉሱም “ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት” ባይ ህዝብ በጉልበቱ መቅረጹ ጠላቶቹን ሁሉ እንደመደምሰስ ቆጥሮ ከወይን ምርጡን፤ ከሴት ቆነጃጂቱን ፤ ምድሪቱ ካፈራቻቸው ፍሬ ሁሉ የተሻለውን እየመረጠ ቢጎድል ከህዝብ አፍ እየነጠቀም በተድላ ይኖር ጀመር።መጉደል በማያውቀው የተድላ ኑሮ በተዘናጋ ጊዜ ግን ያልጠበቀው ሁኔታ በገዛ አገሩ ላይ ይፈጠር ጀመር።ለይስሙላ “ህዝቤ”ይለው የነበር ” ህዝብ” ሁሉ የጉሱን አምባገነን ስርዓት ለመገርሰስ አምፁን አፋፉሞታል።’በፈላጭ ቆራጭ ስልጣኔ አንበረከኩት’ ያለው ህዝብ ንጉሱን ራሱን ከህግ እና ከህዝብ በታች ሊያንበረክከው ለካ በየጏዳው እየመከረ ኖሯል።ለካ ውስጥ ውስጡን ህዝብ በህቡዕ ተደራጅቷል።ለካ በየመንደሩ የጎበዝ አለቃ ሾሟል_ቄሮ።ለካ ድሮ ገና ንጉሱ አባቶቹ ባስቀመጡለት ወግ እና ስርዓት መሰረት መጏዝ በተወ ጊዜ፤ለካ ራሱን ከህግ በላይ አድርጎ በሾመ ጊዜ፤ ለካ ገና ድሮ አገሩን ከክብር መድረክ ገፍቶ በጣለ ጊዜ፤ ለካ ንጉሱም ከአገሩ ክብር ጋር አብሮ ወድቋል። ገና ድሮ ኢፍትሃዊ ስርአት በገነባ ጊዜ ለካ ገና ድሮ ንጉሱ ከህዝቡ ልብ ተገፍትሮ ወጥቷል~በጉልበቱ የሰውን ልብ የገዛ የለምና ለካ ገና ድሮ ንጉሱ ከዙፋኑ ወርዷል።በዚሁ ምክንያት ባባቶቹ ዘመን የአገሩ አንድ የግዛት አካል የነበሩ ክልሎች ጡንቻ እያበቀሉ አልታዘዝ አሉ።በየጦር አበጋዞቹ ሽኩቻ ምክንያት የንጉሱ አገር የጦር ቀጠና ሆነ።የአገር አንድነት ተናጋ።በመላው አገሪቱ በጉልበቱ አደሪ እና ነጥቆ አደሪ በዛ።በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደ ቤት መመለስ በመላው አገሪቱ አስቸጋሪ ሆነ።የአገሩ ዜጋ በሀይማኖት በዘር በመንደር በጎጥ እየተቧደነ በሚያደርገው ፍቲጊያ በዚያች በጸሀይ መውጪያዋ አገር መኖር ፈተና ሆነ።አገሩን አገሬ ብሎ መጥራት በዚያች አገር እንደነውር ተቆጠረ።የአንድነት አቀንቃኞች ከመናፍቅ ተቆጥረው በየ የጦር አበጋዙ በረት እንደ ከብት ታጎሩ ታሰሩ ተሰደዱ ተገደሉ። በመላው አገሪቱ የጦር አበጋዞች የአንድነት መታወቂያቸውን እየጣሉ የራሳቸውን መታወቂያ በማወጃቸው አንዱ የሌላውን መታወቂያ ሳይዝ ካንዱ ወደ ሌላው ክልል እንደ ድሮው ያለፍቃድ ዘው ማለት ቀረ።እንደ ድሮ ህዝብ ባሻው ቦታ መስራት ደስ ባለው ቦታ ኑሮ መመስራት የማይቻል ሆነበት።ንጉሱ ከእንቅልፉ ሲባንን ከዙፋኑ እና ከቤተ መንግስቱ በቀር ባዶ እጁን መቅረቱን አየ።ህዝብ እንደ ባቢሎን ሊበተን ቋፍ ላይ ነው።የአባቶቹ አገር ሊፈራርስ ሆነ።
ንጉሱም የአባቶቹ አገር ተረት ከመሆኑ በፊት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ወሰነ። ከህዝብ ተነጥሎ በአንድ በታወቀ ተራራ አናት ብቻውን ይኖር ወደ ነበር ወደ አንድ ጥበበኛ ሰውም ምክር ፍለጋ ተጏዘ።ጥበበኛውንም ባገኘ ጊዜ”ያባቶቼ አገር መጥፋቱ ነውና ምን ይሻላል ? “ሲል ንጉሱ ጠየቀ።
ጥበበኛውም የንጉሱን እጅ ይዞ ወደ አንድ ወንዝ ዳርቻ ወሰደው።የወንዙንም ዳርቻ ተከትለው ቁልቁል ወደ ወንዙ መዳረሻ ቃል ሳይተነፍሱ ወረዱ።የወንዞንም ፍሰት በጥሞና ሲያደምጡ ውለው አመሻሽ ላይም ጥበበኛው ከወንዙ ዳርቻ ወጣ ብሎ ወዳለ ጥሻ ንጉሱን ይዞ ገባ።ጥሻውንም በእሳት ካያያዘ በኃላ በአንድ አመቺ ስፍራ ተቀምጠው የሚሆነውን በጥሞና ይከታተሉ ጀመር።እጥሻው ውስጥ አንድ ቦታ የወደቀ እሳት ሃይል እየጨመረ መንገዱ ላይ የቆመን ሁሉ በሃይል ወደራሱ እየጠቀለለ ለሊቱን ሙሉ ሲነድ እና ሲንቀለቀል አደረ።እሳቱ ከልፍስፍሶቹ እና ከደቃቃዎቹ የሳር ዝርያ እስከ ጠንካራ የዛፍ ዝርያዎች ሁሉንም በላ።በመጨረሻም በራሱ ጊዜ ጠፋ።ንጉሱ እና ጥበበኛውም ሰው ባይናቸው እያዩት እሳቱ አመድ ሆኖ ጠፋ።
“አገርህ ለምን አደጋ እንደተጋረጠባት ገባህ ? ” ጥበበኛው ጠየቀ።ከንጉሱ ከተገናኘ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መናገሩ ነበር።
“እንዲያውም።ጭራሽ ተወሳሰበብኝ እንጂ”ሲል መለሰ የጥበበኛውን የምክር አኪያሄድ ባለማወቁ እና ባለመረዳቱ እየተሸማቀቀ።
“በስርዓት የማይመራ አገር የመሪውን ባህሪ ይወርሳል”አለ ጥበበኛው ወደ ወንዙ በአገጩ እየጠቆመ።” ይሄ ወንዝ ከተራራው አናት ጉዞ ሲጀምር ትንሽ ነበር።አሁን ግን ብዙ ነው።ይሄ ወንዝ ጉዞ ሲጀምር ግዛቱ ጠባብ ነበር። አሁን ግን ሰፊ ነው።ውሃ የትኛውንም ጠላት በትዕግስት ግን በረዢም ጊዜ እቅድ እንደሚጥል ያውቃል።ለውሃ እማይመች ነገር ቢገጥመው ለምሳሌ ጠንካራ ድንጋ ፊቱ ቢገተር ለጊዜው መንገድ ቀይሶ ያልፋል።የኃላ ኃላ ግዛቱን እና አቅሙን አስተባብሮ እንደሚያሸንፈው ፍጹም እርግጠኛ በሆነ ጊዜ እንደሚያፈራርሰው ያውቃል።ድንጋይ ፈጽሞ መንገድ ቢነሳው፥ውሃ ተጣጥፎ ማለፍ ቢሳነው ከድንጋይ በታች ለማለፍ ይጥራል እንጂ ከድንጋይ ጋር አይታገልም።ውሃ ማለፊያ ቢያጣ በለስላሳ እጆቹ በፍቅር እየነካካ ድንጋይ አናቱ ላይ መንገድ ይሰራል።ባገኘው መንገድ ሁሉ ይጏዛል።ባገኘው ንቃቃት ሁሉ ይሰርጋል።ሲገባም ሲወጣም ለስላሳ እጁቹ ህመም አይፈጥሩም።ከድንጋይ ሲጋጭ እንኳ ጥዑም ዜማን ያወጣልና ዜማውን እንጂ ህመሙን አስታዋሽ የለም።በገባበት ሁሉ ተስማምቶ ይኖራል።የቆሸሸን ገላ ያጥባል።አጠበን እንጂ ሸረሸረን የሚለው የለም። የተጠማን ያጠጣል።ጥማችንን ቆረጠልን እንጂ ግዛቱን በውስጣችን አስፋፋ የሚለው የለም። በደረሰበት ሁሉ ጎጆ ይቀልሳል።አባቶችህ ወሃ ነበሩ።አንት ግን እሳት ነህ።እሳት የገዛ ሃይሉ ታደኝ ነው።ከማንም ጋር መኖር አይችልም።በሃይል ሁሉንም ወደራሱ ይስባል።በጉልበቱ ቀጥቅጦ ነገሮችን ሁሉ በራሱ አምሳል ይፈጥራል።ሳራ ቅጠሉ እሳት ይሆናል።እሳት ባለበት ከእሳት ማንነት ውጪ በራስ መቆም የለመ።ዛፉ ድንጋዩ ብረቱ ሁሉም እሳት ይሆናሉ።በመጨረሻም በገዛ ሃይሉ ተጠልፎ አመድ ሆኖ ይጠናቀቃል።አንተ እሳት ነህ።እሳት የገዛ ሃይሉ ታዳኝ ነው።እሳት ጭረሃልና አመድ መሆንህ አይቀርም።አባቶቻችን ያወረሱንን አገር ግን አንተ በለኮስከው እሳት ነደው ይበልጥ በጠነከሩት ጡቦች መልሰን እንገነባለንለ።ለዚህ ግዳጅ ዝግጁ ከሆንክ ወደ ከተማህ ውጣ።አንተም አገርህም ተለውጣችኃልና እንደ ንጉስ ሳይሆን ተራ ሰው ሆኖ ለመኖር ጏዝህን ሸክፍ”በማለት ጥበበኛው ንጉሱን በተቀመጠበት ትቶት ወደ ተራራው አናት ወጣ።

Filed in: Amharic