በደርግም ይሁን አሁን ባለው ሥርዓት ይበደሉ እንጂ ተስፋቸውን፣በጎ በጎውን አሳቢነታቸውን፣ቀናነታቸውን ከዚያም አልፎ አዛኝነታቸው ወደር እንደሌለው በተወሰኑ ደቂቃዎች ቆይታዬ ተረድቻለሁ፡፡ ስለተበደሉት ሳይሆን ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ነው የሚናገሩት፡፡
በዕለቱ የተገነዘብኩት ደግሞ ዶ/ር መረራ ከእስር የተለቀቁት ረቡእ ቢሆንም እሁድም ላይ ሊጎበኛቸው የሚመጣው ሰው ብዛት አስደናቂ ነበር፡፡ የሕዝብ ፍቅር ማግኘት መታደል ነው፡፡ በእርግጥ እሳቸው ለሕዝባቸው ባላቸው ተቆርቋሪነት የመጣ እንጂ በዕድል የተገኘ አይደለም፡፡ አንድ ሰው መንግሥትም ሕዝብም ቢወደው እጅግ በጣም መታደል ነው፡፡ መንግሥት ቢጠላውም ሕዝቡ ከወደደው ደግሞ እንደ ዶ/ር መረራ መሆን ነው፡፡
ሌላው የተገኘዘብኩት ደግሞ ስለእሳቸው ሳይሆን ማረሚያ ቤት ስላሉት መጨነቃቸውን እና ማሰባቸውን ነው፡፡ በተጨማሪም፣ እሳቸውን ልንጠይቅ ሔደን ሳለ፤ እሳቸው ስለ ዶ/ር ዳኛቸው መልሰው ጠያቂ ሆኑ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለታቸውንም ጡረታ ሳያራዝም አባሯቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ዶ/ር ዳኛቸው ከዩኒቨርሲቲው የጡረታ ክፍያ ስለማያገኙ እንዴት እንደሚኖሩ ተጨንቀው ሲጠይቁ ነበር፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ ሁለቱ ዶክተሮች ብዙም ቅርርቦሽ የላቸውም፡፡ ነገር ግን አንዱ ለአንዱ ሲያደርጉት የነበረው መተዛዘን እጅግ የሚገርም ነበር፡፡ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ገደማ በእስር ቆይተው ሲወጡ እኛ ስለሳቸው ስናስብ እሳቸው ግን ያራሳቸውን ነገር ቀለል አድርገው በመመልከት የዶ/ር ዳኛቸው ጉዳይ ነው ያሳሰባቸው፡፡ እሳቸው ይሄን ይሄን በሚጠይቁበት በዚያች ቅጽበት የዶ/ር ዳኛቸው እምባ መምጣቱንና ያንን ለመቆጣጠር ተነስተው በወቅቱ እሳቸውን ሊጠይቅ ከመጣው ሕዝብ ጋር በመቀላቀል ዘወር ዘወር ብለው ሲመለሱ ነው፡፡
ሁኔታው፣የደበበ ሰይፉን “አክሱም ጫፍ አቅማዳ” ግጥም ውስጥ እነዚህን ስንኞች አስታወሰኝ፡፡
“እኔና ወንድሞቼ ሁላችን….. ሁላችን
ከባዶ አቅማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን፡፡”