>

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል? (በተክሉ አባተ - ክፍል 1ና 2)

ከበርካታ ሳምንታት በፊት ከጓደኞቼ ጋር ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እየተወያየን ነበር:: ሁሉም ተሳታፊ የተስማማበት ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ ከምንም ጊዜ በላይ እጅግ ከባድ ማኅበራዊ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ነበር:: ለዚህም በግንባር ቀደምነት ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ ቢሰመርበትም ህዝቡም ላለንበት ሁኔታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ታላቅ አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሚገኝ ተወስቷል::
እንዲያውም ኢትዮጵያውያን ለአገርና ለለውጥ ያላቸው ስሜት እንደ በረዶ የቀዘቀዘ እንደሆነ ተነገረ:: ለዬት ያለና ታላቅ አገራዊና ወገናዊ ጉዳይ ሲነገር ህዝቡ ጸጥ ረጭ ብሎ ሰምቶ ሃሳቡን ሳይሰጥ ሹልክ እያለ እንደሚወጣ ሁሉም የታዘበውን እያነሳ ተናገረ:: ብዙዎች ለወገናቸው ጥልቅ ስሜት ስለሌላቸውና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በንቃት ስለማይሳተፉም መንግስት በጭቆናው እንዲቀጥል ሞራልና ጉልበት እየሰጡት እንደሆነም ተጨመረበት::

ከቀናት በኋላ በሌላ መድረክ ፋንታው የሚባል ወንድሜ ለኦስሎ ነዋሪዎች ከላከው ጾዳቤ ውስጥ “ለነገሩ ብዙ ኢትዮጵያዊ ሰው ለብዙ ነገር ስሜት የለውም” የሚል ትችት አገኘሁ:: ይህ በቀላሉ የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነና ውይይት እንደሚያስፈልገው በማመን ጸሃፊውን ቀጥለው በተዘረዘሩት ጥያቄዎች ዙሪያ ልምዱንና እውቀቱን እንዲያካፍለን ተማጸንኩት::
ሰው ስሜት የለውም ስንል ምን ማለታችን ነው?
የስሜት አለመኖር ምክንያቱና መንስዔው ምንድን ነው?
የስሜት አለመኖር የሚያስከትለው ጉዳት ወይም ጣጣ ምንድን ነው?
ስሜት-አልባነትን እንዴት ማጥፋት ወይም መቀነስ ይቻላል?
ስሜት-አልባነትን ለማጥፋት ወይም ለመቀነስ በሚደረግ ትግል ዋና ተዋንያን እነማን ናቸው?

የስሜት ያለህ!
አቶ ፋንታውም “የኢትዮጵያዊ ስራና ጥልቅ ስሜት አቅም” በሚል ርዕስ ይበል የሚያሰኝ ትንታኔ አቀረበ:: ስሜትን በሁለት ከፍሎ አብራራ:: ሃሳባዊ ስሜት “ከልባችን ለመውደድና በአእምሮአችን ለመረዳት በዙሪያችን በሚከሰቱ ነገሮች ላይ የምናሳየው ጥልቅ ፍላጎትና የምናደርገው ግንኙነት ነው”
(http://www.ethiopiawakeup.net/maindr/passion):: ስሜት በልብ ወይም በአእምሮ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሥራ እንደሚገለጥም ምሳሌ እያነሳ አብራርቷል:: የስሜት አለመኖር የሚያስከትለውን መዘዝም ከእድገትና ለውጥ ካለመኖር አኳያ አጠር አድርጎ አንስቷል::

እኔም ፋንታው ባነሳቸው ባብዛኞች ሃሳቦች እስማማለሁ:: በዚህ ጽሁፍ አገባብ ስሜት ማለት በአካባቢያችንና በአገራችን ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በነቃ አእምሮ ተከታትሎና መርምሮ የራስን ግንዛቤ መውሰድ ከዚያም የሚገባውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሆነም እስማማለሁ:: በስብሰባዎችና የውይይትመድረኮች መሳተፍ: የፖለቲካ ወይም የሲቪል ተቋማትን መምራት ወይም አባል መሆን: የራሱና የሌላ ሰው መብት ሲጣስ መቃወም: እድገትና ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጄክቶች መሳተፍ ወዘተ አገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚገለጥባቸው መንገዶች ናቸው::

ምናልባት ጥያቄ ቢኖረኝ ስሜት በሌለው ኢትዮጵያዊ ብዛት ላይ ነው:: እንደ ፋንታው አመለካከት ከሆነ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቂ ስሜት የለውም:: ይህ ቁጥር እንዴት ታወቀ? አገር ቤት ያለው ወይስ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ነው ስሜት የሌለው? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል::

ዳሩ ግን ከምናየውና ከምንሰማው መገመት አይከብድም:: ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቶ የሚወጣው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች የሚገኘው ህዝብ ከበቂና ከተጠበቀው በታች ነው:: ምክንያቱ ደግሞ መንግስትን ከመደገፍ ወይም የጭቆና አለመኖር ሊሆን እንደማይችል ለማንም ግልጽ ነው:: በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንም በዘመናዊ ማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን ስለአገራቸው የሚጽፉና የሚያነቡ ጥቂቱ ናቸው:: ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት የውይይትና ክርክር መድረኮች ተዘጋጅተው የሚሳተፉት ጥቂቶች ናቸው:: በሰላማዊ ሰልፍ የሚሳተፉትም እንዲሁ:: በአንጻሩ ደግሞ የሙዚቃ ምሽት ወይም የስፖርት ዝግጅቶች እንዲሁም ሰርግና ልደት በሚደረግበት ጊዜ ያረፍዳል እንጅ የተጠራው ሁሉ ሽክ ብሎ ይገኛል:: ያልተጋበዘውም ባለመጋበዙ ይሰማዋል::

ለመሆኑ አገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚጎድለን ለምንድን ነው? ይህ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሌ የሚያነሱት ጥያቄ ነው:: በዝግጅቶቻቸው በቂ ሰው አይገኝምና:: ይህ ጥያቄ ባንድም በሌላም መንገድ ቢነሳም አጥጋቢ መልስ አላገኘም:: አንዳንዶች የዚህ ሁሉ ችግር ህዝቡ ያለው ፍርሃት እንደሆነ ተናግረዋል:: ሌሎች ደግሞ ይህ ዝምታ የኢትዮጵያ ህዝብ የትዕግስቱ መለኪያ እንደሆነ ጽፈዋል:: ነገር ግን እነዚህ ምክንያቶች ችግሩን በፍጹም አይገልጹትም:: የሁሉም ሰው ምክንያቶች ሊሆኑም አይችሉም:: የተጠናከረ ውይይት ቢካሄድ ይህን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል በማመን በዚህ ጽሁፍና በተከታታይ ጽሁፎች አገራዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እንዳንከታተልና በሚገባ እንዳንሳተፍ የሚያደርጉ መንስኤዎችንና ምክንያቶችን በዝርዝር ለማየት እሞክራለሁ::

መንስኤዎችና ምክንያቶች

ለአገራዊ ስሜት አለመኖር መንስኤዎችን ከምክንያቶች ለመለየት የተደራጀ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል:: በዚህ ጽሁፍ ግን ሁለቱን አንድ ላይ አድርጌ አቀርባለሁ:: ይህን ማድረጌም የጽሁፌን ዓላማ ከመምታት አያግደኝም:: ይልቁንም አላስፈላጊ ክብደትን ያስወግድልኛል ብዬ አምናለሁ::

በቂ ስሜት ያለመኖር መንስኤዎቹና ምክንያቶቹ ከሰው ሰው ከጊዜ ጊዜ ሊለያዩ ይችላሉ:: ቢሆንም ግን ዋና ሊባሉ የሚችሉትን መገመቱ አይከብድም:: ከማኅበራዊ ህይወቴ ጋር በተያያዘ ከተመለከትኳቸውና ከታዘብኳቸው የስሜት አልባነት መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ዋናዎቹ ናቸው::

ዝንባሌና ፍላጎት

ሰዎች በተፈጥሮአቸውና በህይወት ተሞክሮአቸው የተነሳ ለተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ልዩ ፍላጎትና ዝንባሌ አላቸው:: በመሆኑም ለአገራዊ ጉዳዮች ምንም ደንታ የሌላቸው ሰዎች ይኖራሉ:: ሌላው ቀርቶ በግል ህይወታቸውም ሲበደሉና መብታቸው ሲጣስም አይገዳቸውም እጅጉን የሚያሳስባቸውና መስዋዕት የሚከፍሉለት ብቸኛው ጉዳይ ሥራቸውና የቤታቸው ነገር ነው:: የተሰማሩበትንም ሥራ የሚመለከቱት ለአገር በሚያደርገው አስተዋጽዖ ጭምር ሳይሆን የደመዎዛቸው መገኛና ማግኛ መሳሪያ በመሆኑ ብቻ ነው::

በዚህ ምድብ ውስጥ በርካታ በትምህርት ብዙም ያልገፉ ሰዎች: ቴክኒሽያኖች: መሃንዲሶች: ፕሮፌሰሮች: ዶክተሮች እና ሌላ ትልቅ ማዕረግና ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችም ይገኛሉ:: እነዚህን ሰዎች አይደለም በማስታወቂያ በአማላጅም ቢሆን ወደ አገራዊ ውይይት መድረክ ማምጣት ከባድ ነው:: ያለው አማራጭ እነዚህ ሰዎች በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ላቅ ያሉና ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብቻ ነው:: በፖለቲካዊ ውይይት ወይም መድረክ እንዲሳተፉ ማስገደድ ከአለት ላይ ውኃ ለማፍለቅ እንደመሞከር ነው:: በአገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፍ የሁሉም ሰው ምርጫ ሊሆን አይችልም::

የአቅም ጉዳይ
ቀላል የማይባሉ ሰዎች ደግሞ በአገራዊ ጉዳዮች ለመሳተፍ እምቅ ኃይል ቢኖራቸውም ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ ግምት አስተዋጽዖ እንዳያደርጉ ያደርጋቸዋል:: ራሳቸውን ዝቅ አርገው ስለሚመለከቱ ወጣ ብለው ለመታየት አይፈልጉም:: ውይይቶች በሚካሄዱባቸው ጊዜ ጥሩ ሃሳቦች ቢኖራቸውም ለመጠየቅ ያመነታሉ:: አልፎ አልፎም ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ:: ከብዙ ሰዎች የሚያበረታታ ምላሽ ካላገኙ በሰው እንደተጠሉና እንደተናቁ በመገመት ራሳቸውን ያስጨንቃሉ:: ከሰዎች የሚያገኙት ግምት አበረታች ስለማይሆን ተሳትፎአቸውን ለመግታት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ:: አገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አስተዋጽዖ ለማድረግ ይህ ነው የሚባል አቅም እንደሌላቸው ራሳቸውን ያሳምናሉ:: በመሆኑም ቀስ በቀስ በታዳሚነት ከሚገኙባቸው መድረኮች ይርቃሉ::

ሌሎቹ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት ሰዎች ተቃራኒ ናቸው:: በእውነትም ጥሩ ሃሳብና ተሞክሮ ቢኖራቸውም የሌላውን ለመቀበል ይቸገራሉ:: ሁሌ የራሳቸው ሃሳብ ብቻ እንዲያሸንፍ ይከራከራሉ:: ይህ ሳይሆን ቢቀር ስብሰባው ወይም ውይይቱ እርባና እንደሌለውና ችሎታ በሌላቸው ሰዎች እንደሚመራ ያወራሉ:: ያስወራሉ:: እንደምንም ብለው ለሚቀጥለው ጊዜ የመሪነቱን ቦታ ለመያዝ ይሯሯጣሉ:: ካልተሳካላቸውም ሙከራቸውን እንደ ሽንፈት ቆጥረው ከሱታፌ ይታቀባሉ:: ከተሳካላቸው መድረኩ ወይም ፓርቲው የግል ንብረታቸው እስኪመስላቸው ይቆጣጠሩታል:: ሥልጣን እንዲለቁ ወይም እንዲያካፍሉ ወይም የሌላውንም ሰው አስተዋጽዖ ቦታ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ያኮርፋሉ:: ያደረጉት አስተዋጽዖ የተረሳባቸው ይመስላቸዋል:: የመገለል ስሜት ያጠቃቸውና እንቅስቃሴአቸውን ቀስ በቀስ ያቋርጡና በትዝታ መኖር ይጀምራሉ:: ከቻሉም ሲሳተፉባቸው የነበሩትን መድረኮች ወይም ድርጅቶች ይኮንናሉ:: ለማዳከምም ይጥራሉ:: አንዳንዶችም የራሳቸውን ተስፈንጣሪ ድርጅቶች ይፈጥራሉ:: የባሰባቸው ደግሞ የመንግስት ደጋፊና አባል በመሆን ብቸኝነታቸውን ለመቋቋምና ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር ይጥራሉ::

////////// ይቀጥላል ////////

በክፍል አንድ ጽሁፌ ብዙ ኢትዮጵያዊ በቂ የአገር ስሜት እንደሌለው ሞግቻለሁ:: አገራዊ ስሜት ማለትም አገራችንን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮችን በነቃ አእምሮ ተከታትሎና መርምሮ የራስን ግንዛቤ መውሰድ ከዚያም የሚገባውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሆነም ጠቁሜአለሁ:: በስብሰባዎችና የውይይት መድረኮች መሳተፍ: የፖለቲካ ወይም የሲቪል ተቋማትን መምራት ወይም አባል መሆን: የራሱና የሌላ ሰው መብት ሲጣስ መቃወም: እድገትና ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጄክቶች መሳተፍ ወዘተ የአገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚገለጥባቸው መንገዶች እንደሆኑም ለምሳሌነት አንስቻለሁ:: ከዚያም አገራዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እንዳንከታተልና በሚገባ እንዳንሳተፍ የሚያደርጉ መንስኤዎችንና ምክንያቶችን በዝርዝር ማንሳትና መወያየት ፖለቲካዊ ንቃተ ኅሊናን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሳስቤአለሁ:: በዚህ ጽሁፍ ሁለት ለአገራዊ ስሜት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ተጠቃሽ መንስኤዎችን ወይም ምክንያቶችን ለውይይት አቅርቤአለሁ::

ባህላዊ አስተምህሮአችን

ባህላችን የማንነታችንና ምንነታችን መገለጫ ነው:: ይሁን እንጅ ባህል ሁሌ ጠቃሚ እሴችን ብቻ ሊይዝ ሊያስተላልፍ አይችልም:: በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ጎጅ ትምህርቶች ልምዶችና ወጎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ:: በመሪና በተመሪ መካከል ስላለው ግንኙነት ብንመለከት ብዙ ጎጅ የሆኑ አመለካከቶችን እናገኛለን::

ማንኛውም ዜጋ ለመሪው ወይም ለመንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መታዘዝና መገዛት እንዳለበት ለበርካታ መቶ ዓመታት ተሰብኳል:: መሪዎች ወይም መንግስታት ህግ ቢተላለፉ ማንም መጠየቅ እንደማይችል በአንድም በሌላም ዘዴ ተነግሯል:: ለዚህም “ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” የሚለው አባባል ጥሩ ምሳሌ ነው:: እንዲያውም ህዝቡ ወይም ተመሪው ለመሪው ያለመታተክ የመገዛት ሃይማኖታዊና ተፈጥሮአዊ ግዴታ እንዳለበት ይነገረዋል:: መንግስት ጌታ ሲሆን ህዝብ ደግሞ ባሪያ ነው:: ባሪያ የሚፈቀድለት ነገር ቢኖር የጌታውን ደህንነት መጠበቅና የሚፈልገውን ማድረግ ነው:: ህግጋትና ሥርዓታት ሁሉ የተዘጋጁት ለባሪያው እንጅ ለጌታው አይደለም:: ጌታው ከህግ በላይ ነው:: ጌታው የህዝቡን ንብረት የመውሰድ መብት አለው:: ፖሊሱ ሚሊሻው የደህንነት ሠራተኛው ወታደሩ አልፎ አልፎ የውጭ ጠላት ካልመጣ በስተቀር በዋናነት የሚያገለግለው ጌታውን ነው:: ይህንን ያልተጻፈ ህግ ከወላጆቻችን እየሰማን በአይናችንም እያየን አድገናል:: አውቀንም ሳናውቅም ህጉን እንፈጽማለን:: አንድ መንግስት የፈለገውን ያህል ጨቋኝ ቢሆን የእኛ መልስ ጸጥታ ነው:: መንግስቱ ለ17 ዓመታት እንደ ሰም አቅልጦ ሲገዛን ምላሻችን ዝምታ ነበር.: የአሁኑ መንግስትም ራሱ ያወጣውን ህግና መመሪያ ለእኛ ባሪያዎቹ ጥሎ እርሱ ከህግ በላይ ከሆነ ሁለት ዓስርት ዓመታት አለፉ:: ጥረን ተጣጥረን ያደረግነው ቢኖር በጣት የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረግ ብቻ ነው:: አብዛኛው ሰው በጸጥታ ባሪያነቱን ተቀብሎ እንደሚኖር ለማሳየት ነው እንጅ የተወሰኑት ቆራጦች ዕለት ከዕለት ያደረጉትን ትግል እረስቼ ግን አይደለም::

ለዚህ ጎጅ ባህል መዳበር በግንባር ቀደምትነት የሃይማኖት ተቋማትን ተገን ያደረጉ ልሂቃን ተጠቃሽ ናቸው:: በክርስትናውም በእስልምናውም ሃይማኖቶች ይህ ጉዳይ አለ:: የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ለመከላከል በተደረጉ መራራ ትግሎች ወሳኝ ሚና ተጫውታለች:: ኢትዮጵያዊ ወኔ እንዲዳብርም ሁሌ ትሰብካለች:: ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጨቋኝ መንግስታትና መሪዎች ህግን እንዲያከብሩና ህዝቡን በማስተዋል እንዲመሩ ግን ያደረገችው አስተዋጽዖ የጎላ አይደለም:: እንዲያውም አንዳንድ መምህራን ወቅቱ ላመጣው የመንግስት ሥርዓት ሁሉ ህዝቡ በአንክሮ መገዛት እንዳለባቸው ያስተምራሉ:: በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አማኙ ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ስለሳውዲ ዓረቢያ እንዲያስብና እንዲብከነከን ያስተምራሉ:: ከፕሮቴስታንት አስተማሪዎች የሚሰማው ደግሞ ስለጌታ አዳኝነት ብቻ እንጅ ስለኢትዮጵያ ህዝብና ችግሩ አይደለም::

በአጠቃላይ ሲታይ ህዝቡ በየጊዜው በለስ ለሚቀናቸው መንግስታት እና መሪዎች ያለምንም ጥያቄ እንዲታዘዝ ተነግሮታል:: የፖለቲካ መሪዎች በህዝቡ ላይ በደልና ግፍ ሲፈጽሙ የትኛውም የሃይማኖት ተቋም ተቃውሞ አያነሳም:: ህግና እውነት እንዲጠበቅ ከመስበክ ይልቅ ህዝቡ መሪዎችን አፍሮና ፈርቶ እንዲኖር ይነገረዋል:: እንዲያውም ከበዳይ መሪዎች ጎን በመቆም ህዝባቸውን የሚያሳዝኑም የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች አሉ:: አሁንማ ይባስ ብሎ ጨቋኝ የሃይማኖት መሪዎችንም እያየን ነው:: ይህ ጎጅ ባህል ለዘመናት እየተንከባለለ 21ኛው ክፍለ ዘመን ደርሷል:: ብዙ ሰው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርግ በተለያዩ መንገዶች አሉታዊ ተጽእኖ እያደረገ ይገኛል:: ይህን ስል ግን የተጠቀሱት የሃማኖት ተቋማት ጭቆናን በአቋም ደረጃ ይደግፋሉ ማለቴ አይደለም:: እነሱን ተገን ያደረጉ አስተማሪዎችንና መሪዎች የሚሰሩት ሥራ እንደሆነ ግን ይሰመርበት::

ፍርሃትና ስጋት

የኢትዮጵያን ህዝብ ጀግንነት መላው ዓለም ጠንቅቆ ያውቀዋል:: የዓረብና የአውሮፓ ወራሪዎችን ቅስም ሰብሮ አባሯል:: ኢትዮጵያ በማንም አገር ቅኝ እንዳትገዛ አድርገዋል:: ይህ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ከሚያስችሉን ታሪኮቻችን ውስጥ ትልቁ ነው:: ወደፊትም ይህን አይበገሬነታችንን ይዘን እንደምንቀጥል ተስፋዬ ነው::

ነገር ግን የህዝቡ ጀግንነት ጎልቶ የሚታየው ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር በሚደረገው ግብግብ ብቻ ይመስላል:: ከባእዳን ያልተናነሱ ግን በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጨቋኝ መሪዎቻቸውን ግን የሚፋለሙበት ወኔ የሚያንሳቸው ይመስላል:: ለዘመናት በነጻነት ኖረናል ይባላል እንጅ ለአፍታም ቢሆን እያንዳንዱ ዜጋ መብቱና ጥቅሙ ተከብሮለት ኖሮ አያውቅም:: ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ህዝቡ ለመንግስታቱ ያለው ፍርሃት ግን ዋናው ነው:: ውስጥ ለውስጥ በጥንቃቄ ከሚነገር ሃሜት አልፎ ጨቋኝ መሪዎችን በይፋ የሚያወግዝበትና የሚጠይቅበት ድፍረት ያጣ ይመስላል:: በአገር ቤትም ይሁን በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ድፍረትና ግልጽነት ባለው መልኩ አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢና አሳፋሪ ሁኔታ መናገር ሲያሸማቅቃቸው ይታያል:: ለምን ያለውን የመብት መጣስና ቅጥ ያጣ ድህነት መናገር እንደማይፈልጉ ሲጠየቁ የብዙዎች መልስ “እባክህ ልኑርበት” ሆኗል:: በስብሰባዎችና በውይይቶች መሳተፍ ባድሜና ዛላንበሳ እንደመዝመት አስፈሪ እየሆነ ነው:: ብዙዎች በፍቅርና በተመስጦ የሚወያዩባቸው ጉዳዮች ስፖርትና ሙዚቃ እንዱሁም አገር ቤት ህንጻ ስለመገንባት ሆነዋል::

ብዙዎች ፍርሃታቸው መጠን ከማጣቱ የተነሳ የራሳቸው መብትና ጥቅም ሲነካ እንኳን አይቃወሙም:: ስለህዝባቸው መቸገርና መጨቆን የሚታገሉትን ሳይቀር ፈርተው ለማስፈራት ይጥራሉ:: ተቆርቋሪ ወገን በመሆን ለመብት የሚታገሉትን ያስጠነቅቃሉ:: “አገር ቤት የጀመርከውን ቤት ሰርተህ ብትጨርስና በሰላም ብትኖርበት ይሻልሃል” የሚል ምክር ጣል ያደርጋሉ:: መንግስት ያለውን የካድሬ ብዛትና የስለላ መረብ እንዲሁም እየሰጠ ያለውን ጽኑ ቅጣት ለማስፈራሪያነት ያነሳሉ:: በአንድ ወቅት አርቲስት ታማኝ በየነ እንዳለው ሌሎች ለሚጽፉትና ለሚናገሩት የሚያነቡትና የሚሰሙት እየፈሩ ነው:: አንድ በስድሳዎቹ የእድሜ ክልል ያሉ አባት ይህን ቅጥ ያጣ ፍርሃት በተመለከተ ያጫወቱኝን ላካፍልና የዛሬውን ጽሁፌን ላጠቃልል::

በፈታኙ የደርግ ጊዜ ነው:: እኒህ የሃይማኖት ሊቅ የሆኑ አባት ኢሰፓዎችን ሳይፈሩ በህዝብ ፊት ይገስጹ ነበር:: አገዛዛቸውን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር:: በዚህም የተነሳ አብዮታዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ተወስኖም ነበር:: ይህን ሁኔታ የሚያውቁ ሌላ የሃይማኖት አባት በአንድ ወቅት እኒህን አባት አዲስ አበባ መንገድ ላይ ያገኟቸዋል:: ሰላምታ ከተለዋወጡና ጥቂት ከተነጋገሩ በኋላ “ይህን ድፍረትዎን አልወደድኩልዎትም ይጠንቀቁ” ይሏቸዋል:: እኒህ ሊቅ አባትም “እኔ ደግሞ የእርስዎ ፍርሃት ያስጠላኛል” ብለዋቸው ተለያዩ:: እስካሁን ድረስ እኒህ ጀግና አባት ለእውነት ሲታገሉ አሉ:: ስንቶቻችን ፈርተን ስንቶችን አስፈርተን ይሆን? ስንቶቻችንስ በፈሪዎች ምክር መሳይ ንግግር ተደናግጠን ሩጫችንን አቁመን ይሆን?

///////////////// ይቀጥላል ////////////////

Filed in: Amharic