>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1960

የትግራይ ፖለቲካ፡ የአጥር ላይ ትግል (ቢልልኝ ሃብታሙ) 

የትግራይ ፖለቲካና የአጥር ላይ ትግል አንድ ናቸው፡፡ ሁለቱም ትክክል የሚሆኑት በራሳቸው አይደለም፡፡ ሁለቱም ትክክል ለመሆን ጊዜ የሚፈጥረውን እድል የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ጎልቶ የወጣውን ሁለት ገፅታ ያለው ትግል በማየት ነው፡፡ የትግራይ ፖለቲካ ስንል የትግራይ ልሂቃን ነን ወይም የብሔሩ ተወካዮች ነን በሚል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚያራምዱትን የፖለቲካ ትግል ማለታችን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ ፖለቲካ የለውም፡፡ የአማራንም የትግሬንም ፖለቲካ ካየህ በውክልና የሚከናወን ፖለቲካ እንጂ የብዙሀኑን ራሽናል ተሳትፎ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ የለም፡፡ እዚህ አገር የህዝብ ፖለቲካ አድረገን የምንወስደው በጥቂት ኃይሎች የሚነዳውን የመንጋ ፖለቲካ ነው፡፡ የመንጋ ፖለቲካና ህዝብ ፖለቲካ ግን ይለያያሉ፡፡ ስለዚህ ያለፉት ስርዓቶች የፈፀሙትን ስህተት ዛሬም ተደግሞ እያየን ነው፡፡

በዚህ መሰረት የትግራይ ፖለቲካ ከአጥር ላይ ትግል ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የኢትዮጵያውንን ጭቆና ለመፍታት ትግሉን በተነሳሽነት የመጀመሩ ጉዳይ አንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የፖለቲካ ባህል የመጣው ግራና ቀኝ እያጣቀሰ አመቺ የሆነውን በመጨበጥ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ፡፡ ሲጀመር የትግራይ ፖለቲካ የነፃነት ትግሉን የጀመረው በሽፍታ ትግልና በአብዮት ትግል መካከል የመሆኑን ያሀል አሁንም በጋራ ጉዳይ ላይ የሚንቀሳቀሰው ይቺኑ የአጥር ትግል እያጣቀሰ ነው፡፡ በአንድ በኩል ወያኔ የሚባለው የፖለቲካ ትግል በአብዛኛው ራሽናል ያልሆነ ስሜትን ለገዥዎች በጊዜያዊነት መግለጥ ላይ የተመሰረተ የሽፍታ አይነት ትግል መሆኑን መውሰድ አንችላለን፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት አሁኑ ህወሀት/ኢህአዴግ መነሻ የሆኑት ግገሐት የመሳሰሉ የሽፍታ አይነት ትግል የነበራቸው ናቸው ፡፡ በሌላ በኩል ወቅቱ የፈጠረው የማርከስ ሌኒንዝም አብዮትን መነሻ በማድረግ ትግሉን ራሽናል ለማድረግ የተደረገው ጥረት ተሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ የተነሳ የትግራይ ፖለቲካ አሁንም ድረስ ከዚሁ የሽፍታ አባዜ ተላቋል ማለት አይቻልም፡፡

ሌላው ጉዳይ የትግራይ ፖለቲካ መገንጠልን በአንድነት ከመቀጠል አማራጭ ጋር እያጣቀሰ የመጣ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ኃይል ከመጀመሪያውም የተነሳው የትግራይን ነፃነት ለማረጋገጥ የመሆኑን ያህል ዛሬም ድረስ ይሄን የመገንጠል ጉዳይ ረስቶታል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከሰሞኑ የተንፀባረቀችው አንቀፅ 39ን የመጠቀም ፍላጎትም የምትነሳው ከዚሁ ካልጠራ የፌዴራሊዝም አመለካከት ነው፡፡ የትግራይ ፖለቲካ ለስርዓቱ የከፈለውን የላቀ የትግል ድርሻ ተገን በማድረግ ከሌሎች ህዝቦች በላይ ከስርዓቱ ለመጠቀም የሚፈልግ በመሆኑ የመጀመሪያ ፍላጎቱ የአገሪቱን ፖለቲካ በበላይነት መቆጣጠር ነው፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ በበላይነት የመቆጣጠር ፍላጎቱ ካልተሳካ የእንገንጠል ጥያቄውን ማስተጋባቱ አይቀርም፡፡ በዚህ ስስታም የፖለቲካ ስሜቱ ስርዓቱን ለመጨምደድ ባደረገው ጥረት በርካታ የፖለቲካ ኃይሎችን የትግራይ ህዝብ ጠላት አንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ስርዓቱን በበላይነት ለመቆጣጠር ባለው ስግብግብ ፍላጎት የተነሳ የሌሎችን ድርሻ እየነጠቀ በመምጣቱ በስርዓቱና በትግራይ ማንነት መካከል ያለው ድንበር አንዲደበዝዝ አድርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ ስርዓቱን ለሚታገሉ ወገኖች የትግል ብዥታ በመፍጠር ለትግሬ የበላይነት አመለካከት መነሻ ሆኗል፡፡

የትግራይ ፖለቲካ ህዝባዊነትን ከጥገኛ አጀንዳ ጋር እያጣቀሰ የመጣ በመሆኑ ጥገኛ አላማውን ለማስፈፀም ህዝብን አንደ ዋሻ የሚጠቀምበት አካሄዱ አንዱ መለያው ነው፡፡ በዚህ የአጥር ላይ ትግሉ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ከትምክህተኝነት የሚነሳውን ጥገኛ አጀንዳ ማራመድ ሲነቃበት ደግሞ በትግራይ ህዝብ የመነገድ ጨዋታን እየተከተለ መጥቷል፡፡ ይህ የፖለቲካ ባህል ለረጅም ጊዜ የነበረውን የትግል አቅም በመጠቀም ለብዙሀን የሚንቀሳቀስን ስርዓት በመጨፍለቅ ፖለቲካውን የሀብት ምንጭ ለማደረግ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚህም በትግራይ ፖለቲካ ታፔላ ከተቻለ ጥቂቶች ብቻ የሚጠቀሙበት የሀብት ምንጭ ፈጥሮ በጥቅም ሰንሰለት ማስፋት ይሄ ሲነቃ ደግሞ የሚሰራው ለትግራይ ልማት መሆኑን በመወትወት አንደተገፋ አድርጎ ያቀርባል፡፡ በዚህ መንታ ባህሪው ከታቻለ ጥገኛ አላማውን ማራመድ ካልተቻለ ህዝብን ለስህተቱ መከታ በማድረግ ሁለት አይነት ካርድ የሚጫወት የፖለቲካ ባህል ነው፡፡ የትግራይ ፖለቲካ ወቅቱ የሚጠይቀውን የአስተሳሰብ ትግል ለመጋፈጥ አቅም ስሌለው ሁሉንም ችግሮች በሀይል ለመጨፍለቅ የሚፈልግ ይህ ካልተሳካ እነገንጠል ካርዱን የሚመዝ ነው፡፡ በብዙ ትግል ሂደቶች ያለፈ ቢሆንም ካለው ደረቅ ባህሪ የተነሳ ራሱን ለማረም የሄደበት ርቀት ውጤታማ አልሆነም፡፡ በዚህ የተነሳ የትግራይ ፖለቲካ አሁንም ለአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር መባባስ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው፡፡ስለዚህ አገራዊ ስሜት ያለው ዜጋ አንዲጠፋ መታገል ያለበት ፖለቲካ ቢኖር ይህን የመሰለውን የትግራይ ፖለቲካ ነው፡፡

Filed in: Amharic