የእህቴ ንግሥት ይርጋን የህይወት መንገድ በአዲስ አቅጣጫ የዘወሩት ተከታታይ ክስተቶች የተፈጠሩት በወርሃ ሐምሌ 2008 ዓ.ም ነው።
ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዝንባሌ ኖሯት የማታውቀው እህቴ ቀጣዮቹን ጥቂት ወራት በጎንደር ከተማ በነበሩ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በመሳተፍ፤በኋላም ሊይዟት ከሚፈልጓት የፀጥታ ኃይሎች በመሸሽ አሳልፋቸዋለች።
በመስከረም 2009 የትውልድ እና የመኖሪያ ከተማዋን የኋሊት ትታ ከተደበቀችበት የታች አርማጭሆ ገጠራማ አካባቢ በቁጥጥር ሥር ስትውል ሃያ አምስት ዓመቷ ነበር።
አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆና የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአማራ ክልል ተቀስቅሶ የነበረውን ሕዝባዊ አመፅ አስተባብረሻል፤ ከሕገ-ወጥ ድርጅት ጋርም ግንኙነት መስርተሻል በሚል የመሰረተባትን ክስ በመከታተል ላይ ስትሆን ለመጨረሻ ጊዜ በአካል ያየኋትም ከመታሰሯ ሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ነው።
ለአፍታ ያህል እንኳ ስቧት የማያውቀው የአካባቢዋ እና በአጠቃላይም የአገሪቷ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ እንደድንገት ቀልቧን ያጠመደው የወልቃይት ማንነት ኮሜቴ አመራሮች እና አባላት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡና በተለይም የኮሚቴው አስተባባሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሊይዟቸው የሞከሩትን የፀጥታ ኃይሎች በተኩስ ከመለሱ በኋላ ነው።
በወቅቱ ይህንን ጉዳይ በአትኩሮት መከታተል መጀመሯ የሚገርም አልነበረም፤ እጅግ ብዙ የከተማዋ ወጣቶች የኮሎኔሉን ሰፈር ማዘውተር የያዙት ከተኩስ ልውውጡ ማግስት አንስቶ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፀጥታ ኃይሎች ከወጣቶቹ ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውም አልቀረም። በአንድ አጋጣሚ አጠገቧ የነበረ አንድ ወጣት በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ ማየቷ ይበልጥ የነካት ይመስለኛል።
ፖለቲካ ጠገብ ያለመሆኗ እና ሰልፍን ከመሳሰሉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የጠለቀ ትውውቅ ያለማዳበሯ ከብዙሃን ጎልታ እንድትታይና ዓይን ውስጥ እንድትገባ አድርጎታል፤ ይህን በታላቅ ወንድም ዓይን ሳየው ምነው ጠንቀቅ ባለች ኖሮ እያልኩ አስባለሁ።
ሆኖም እንደዜጋ ሳጤነው ቁጭት ሳይሆን ኩራት ያሸንፈኛል፤ ላመነችበት ነገር ያላትን ሁሉ ያለምንም ቁጥብነት ፤ ያለምንም ማስመሰል መስጠቷ ያኮረኛል።
ከምግብ ቤት እስከማረሚያ ቤት
በአባት በኩል ብቻ የምዛመዳት ንግሥት ፤ በእናቷ በኩል ያሉ ሁለት እህቶቿን እና ከሐምሌው ክስተት በኋላ እንዲሁ ታስሮ የነበረ ወንድሟን ታስተዳድር ነበር።
በሃያዎቹ የመጀመሪያ ዕድሜዋ ወደአረብ አገር በማቅናት ዱባይ ውስጥ ጥቂት ዓመታትን አሳልፋለች። አዋጭ ሥራ ፍለጋ በአካባቢው ወዳለ ትንሽ ከተማ አቅንታም ነበር።
ከዚህ በኋላ ነው ወደጎንደር ከተማ ተመልሳ ተወዳጅ የሆነ የምግብ እና የመጠጥ መሸጫን የከፈተችው።
ምግብ ቤቷ በወጣቶች በተለይም በከተማዋ የመጓጓዣ አገልግሎት በሚሰጡ ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪ ሾፌሮች ይዘወተር የነበረ መሆኑ፤ እሷም ከብዙሃኑ ጋር መልካም ግንኙነት ማዳበር መቻሏ በኋላ ከተማዋ በተቃውሞ ሰልፎች ስትናጥ በብዙዎች እንድትከበብ አስችሏታል።
ከታሰረች በኋላ የንግድ ሥራዋ ሙሉ በሙሉ የቆመ ሲሆን ፤ ቤተሰቦቿም ኑሮን ለማሸነፍ በግቢያቸው ውስጥ ያሉ ሁለት ክፍሎችን ለማከራየት ተገድደዋል።
ከዘመድ ከሚገኝ ድጋፍ ባሻገር አሁን ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው ይኼው ነው።
የእርሷን ክስ እና ደህንነት በተቻለን መጠን ከመከታተል ባሻገር ለእናቷ የሚደርሱ መረጃዎችንም መቆጣጠር ሌላኛው ፈተናችን ነው።
ከተቃውሞዎቹ ጋር በተገናኘ ታስራ የነበረው እና በቅርቡ የተፈታችው አስቴር ስዩም እናት የልጃቸውን መፈታት ሳያዩ መሞታቸውን ማወቃችን ይበልጥ ጥንቁቅ እንድንሆን አስገድዶናል።
የአስቴር እናት ልጃቸውን ለመጠየቅ ወደአዲስ አበባ ካመሩ በኋላ፤ አስቴር ክፉኛ ተጎሳቁላ ስላዩዋት ሲመለሱ ወዲያውኑ ነበር ጤናቸው የታወከው።
እናም ንግሥት ጉስቁልቁል ብላ እንደነበር የተረዳን ሰሞን ሰውነቷ እስኪያገግም ድረስ የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን በመደርደር እናቷ ወደአዲስ አበባ እንዳትሄድ ከመከልከል ውጭ አማራጭ አልነበረንም።
አንዴ ደግሞ በምርመራ ወቅት ንግሥት እጅግ የከፉ አካላዊ ጉዳቶች እንደደረሰባት፤ ስብዕናን በሚነካ መልኩም ራቁቷን እንድትቆይ መደረጉን እንዲሁም ጥፍሮቿ ሁሉ መመንገላቸውን የሚናገሩ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጩበት ወቅት እናቷ ሙሉ በሙሉ አቅሏን አጥታ ወደአዲስ አበባ ስትከንፍ ሄዳለች። እዚያ ስትደርስ ግን የተባሉት ነገሮች የተጋነኑ መሆናቸውን ለመረዳት ትችላለች።
እርግጥ ንግሥት ማንነትን የሚነኩ ስድቦችን እንደምታስተናግድ እና ለረጅም ሰዓታት ቆማ እንደምትመረመር መረጃ አለን።
ሆኖም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ በግነት የተሞሉ መረጃዎች ለእናቷ እንዳይደርሱ መቆጣጠርም ሌላኛው ሥራችን ነው። በአንድ በኩል ሳየው ንግሥት ብቻዋን አይደለም የታሰረችው፤ እናቷንም ጨምራ እንጅ።
የእስረኞች መለቀቅ
የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዊን ጨርሶ ሊቀ መናብርቱ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ እስረኞች እንደሚለቀቁ መናገራቸውን ስንሰማ በመጀመሪያ እጅጉን ፈንድቀን ነበር። ነገር ግን ቀስ እያለ እውነታው ደስታችን እያተነነው መጣ።
እንደሚገባኝ እርምጃው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከማባበል የዘለለ ሚና የለውም።
መንግስት በአንድ በኩል እርቅና መግባባትን እፈልጋለሁ፤ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት እሻለሁ ይላል። በሌላ ሁሉንም ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ያሰራቸውን እስረኞች ላለመፍታት ሰበቦችና መስፈርቶች ይደረድራል።
እስካሁን ለናሙና ያህል የተወሰኑት ተፈቱ እንጅ ሁሉም ከእስር አልተለቀቁም፤ ከዚህ የተሻለ ነገር እንደማይኖር ስጋት አለኝ። እውነቱን ለመናገር ንግሥት በቅርብ ጊዜ የምትፈታ አይመስለኝም።
ከእኔ ጋር በጣም ነበር የምንቀራረበው። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪየን ስጨርስ እርሷው ናት መጥታ ያስመረቀችኝ።
ቤተሰባዊ ጉዳዮችንም የምማከረው ከእርሷው ጋር ነበር። ነገር ግን እስር ዕጣችን ሆነ። እኔ ከአንድ ወር በኋላ ብፈታም እርሷ ግን አሁንም ክሷ አላለቀም። ዘመዶች እና ጎረቤቶች አንዳንድ ጊዜ “ተይ አንገትሽን ደፍተሽ ኑሪ እያልናት አልሰማ ብላ እንዲህ ሆነች” ሲሉ እሰማለሁ።
እኔ ግን አንገቷን ያለመድፋቷ መቼም ሊያስፀፅተኝ አይችልም።