>

‹‹የደረሰብህን በደልና ግፍ መቁጠር ከጀመርክ ቁስልህ ያመረቅዛል›› አቶ አንዱዓለም አራጌ

 ከእስር ተፈቺዎች ብሔር ተኮር ጥቃትና የንብረት ውድመት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆም አሳሰቡ
  • ‹‹ቂም ይዤ ስላልወጣሁ መሄድ የምፈልገው ወደፊት እንጂ ወደኃላ አይደለም››

አቶ እስክንድር ነጋ

  • ‹‹የደረሰብህን በደልና ግፍ መቁጠር ከጀመርክ ቁስልህ ያመረቅዛል››

አቶ አንዱዓለም አራጌ

  • ‹‹ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ ለማምጣት እታገላለሁ››

አቶ በቀለ ገርባ

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ብሔር ተኮር ጥቃትና የንብረት ውድመት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም እንዳለበት፣ ሰሞኑን በይቅርታና ክስ በማቋረጥ ከእስር የተለቀቁ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አሳሰቡ፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከተከሰቱ ግጭቶችና ሁከቶች ጋር በተገናኘ ብሔር ተኮር ዕርምጃ በመውሰድ ሕይወት እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስና ንብረት በቃጠሎና በተለያዩ ምክንያቶች እንዲወድም ማድረግ ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጽና የሚያመጣውም አመርቂ ውጤት ስለማይኖር፣ መወገዝ ያለበት ድርጊት መሆኑን አክለዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች ከዚህ ተግባር ተቆጥበው ትግላቸውን ያለምንም ሁከት፣ ብጥብጥና ጥፋት እንዲያካሂዱ፣ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራር የነበረው አቶ አንዱዓለም አራጌና እስክንድር ነጋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እስክንድር ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ስድስት ዓመታት ከስድስት ወራት የታሰረው ባልሠራው ወንጀል በሐሰት ተከሶ ነው፡፡ ከሕይወቱ፣ ከልጁና ከባለቤቱ የጠቀሰውን ያህል ዕድሜ መቀነሱንና በአጠቃላይ በእስር ቤት ብዙ ነገሮችን ያሳለፈ ቢሆንም፣ ስላለፉት ጊዜያት ማንሳትና ቀደም ብሎ የተናገራቸውን መድገም እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡

‹‹ለአገራችን የሚበጃት ወደኋላ መመልከት ሳይሆን ወደፊት ማየት ነው፤›› የሚለው እስክንድር፣ እሱ ምንም ደረሰበት ምን የሚያስበው ስለድሮው ሳይሆን በቀጣይ ተስፋ በሚያደርገው ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከእስር ሲለቀቅ በኢሕአዴግ ላይ ጥላቻና ቂም በቀል ይዞ አለመውጣቱን የሚናገረው እስክንድር፣ ኢሕአዴግ ወደፊት በሚመጣው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ አንድ አካል ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳለው አስረድቷል፡፡

ኢሕአዴግ በእሱ ላይ በደል ስላደረሰበት ቂም በቀል ይዞ እንደ ኢሠፓ ይበተን የሚል አቋም እንደሌለው ወይም እንዲበተን እንደማይፈልግ የሚናገረው እስክንድር፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የሚጠቅም ሥራ እንዲሠራና ከስህተቶቹ እንዲማር ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

በአውሮፓና በአፍሪካ አገሮች በተለይ በቦትስዋና፣ በጋና፣ በማላዊና በደቡብ አፍሪካ የታየው ብሩህ ተስፋ፣ በኢትዮጵያም የማይኖርበት ምክንያት እንደሌለ የሚናገረው እስክንድር፣ እነዚህ አገሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት የገነቡ በመሆናቸው፣ ለኢትዮጵያ ዓይነተኛ ምሳሌዎች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ በተጨባጭ ምን መደረግ እንዳለበት የሚያስተምሩ ምሳሌዎች መሆናቸውንም አክሏል፡፡

በደቡብ አፍሪካ አምባገነኖች በሕዝብ ላይ በደል ማድረሳቸውን የጠቆመው እስክንድር፣ ናሽናል ፓርቲ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት በተደረገው ሽግግር የኮሻና የዙሉ ጎሳዎች መጨራረሳቸውን ጠቁሟል፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውንም አክሏል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲገነቡና ከገነቡ በኋላ ግን ወደ ኋላ ተመልሰው ያንን ግፍና በደል መመልከት አለመፈለጋቸውን አውስቶ፣ ኢትዮጵያም ውስጥ ስለተፈጸመው ግፍና በደል ወደኋላ መመልከት ተገቢና አስፈላጊ ባለመሆኑ፣ ወደፊት የሚታየውንና ያለውን በሰላም፣ በዴሞክራሲ፣ በወንድማማችነት፣ በፍቅርና በአንድነት ተስፋ ላይ መሥራት ተገቢ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የብሔር ጥቃት እየታየ መሆኑን የገለጸው እስክንድር፣ ‹‹የብሔር ጥቃት፣ የፋብሪካና ሌሎች ቃጠሎዎች፣ በንብረትና በሕዝብ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም አለባቸው፤›› ብሏል፡፡ የሕዝብ ትግል ግቡ ለጥሩ ነገር ስለሆነ፣ ሥልቱም ጥሩ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ሥልቱ ከተበላሸ ግቡን ማስተካከል ስለማይቻል፣ በተለይ ወጣቱ ሥልቱ ላይ መጠንቀቅ እንዳለበት ምክሩን አስተላልፏል፡፡ ለግቡ ያለውን ራዕይ በሥልቱ ማሳየት እንዳለበትም አክሏል፡፡ በኢትዮጵያ የብሔር ጥቃት በመታየቱ መፍራት ተገቢ አለመሆኑንን የገለጸው እስክንድር፣ በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞከራሲ ሥርዓት በሚደረግ ሽግግር ተመሳሳይ ጥቃት የተፈጸመ ቢሆንም፣ ያንን ሁሉ ችግር አልፈው የዴሞክራሲ አገር ለመገንባት መቻላቸውን አስረድቷል፡፡ በኢትዮጵያ ግን የብሔር ጥቃት መፈጠርም ሆነ መታሰብ እንደሌለበትና ችግሩን በትክክል የማወቅ ግዴታ የኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ሕዝብ በመሆኑ በጋራና በአንድነት ተባብሮ በሰላማዊ መንገድ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታዩትን ግጭቶች ከምንጩ ለማድረቅ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሕጋዊ መድረክና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ጋር መደራደር እንዳለበት የተናገረው እስክንድር፣ ኢሕአዴግ ቀደም ብሎ የሚያስቀምጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ትቶ ካልተደራደረ ግጭቶች እየተባባሱና ሥር እየሰደዱ ሄደው አገር አደጋ ላይ እንደምትወድቅ ጠቁሟል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ፓርቲ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰና እየተበላሸ መሄዱን ሲያይ ከኤኤንሲ (ANC) በመደራደሩ ለውጤት መብቃቱን ጠቁሞ፣ ‹‹ይኼንን ጥበብ ኢሕአዴግም መማር አለበት፤›› ብሏል፡፡

ኢሕአዴግ በመርህ ደረጃ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተደራደረ መሆኑን እየገለጸ ቢሆንም፣ ‹‹ግን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? ቢሆንም እንኳን ግማሽ መንገድ ይቀረዋል፤›› የሚለው እስክንድር፣ ጊዜው አሁን ስለሆነ ከሁሉም ጋር በመደራደር የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቁ ሰዎች እንዳሉ ስለሚታወቅ፣ ፓርቲያቸው ወደ ሰላም አቅጣጫ እንዲሄድ መታገል እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች የማይኖሩባት አገርና ሥርዓት መገንባት እንዳለበት የጠቆመው እስክንድር፣ የታሰሩ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈትቶ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው አካል መሆን እንዲችሉ ማድረግ ተገቢና የግድ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ሰሞኑን ከተፈቱት ፍርደኞች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራር የነበረው አቶ አንዱዓለም አራጌ በበኩሉ እንደተናገረው፣ ‹‹እስር ቤት ያሳለፍኩትን የግፍ፣ የመከራና፣ የስቃይ ዓመታት ወደኋላ ሄጄ ማሰብ አልፈልግም፤›› ይላል፡፡

‹‹በደሌን መቁጠር ከጀመርኩ ቁስሌ ያመረቅዛል፣ ሕመሜን ማዳመጥ አልፈልግም፤›› የሚለው አቶ አንዱዓለም፣ ብዙ የተጎዳም ቢሆን ፈጣሪው ፀጋውን አብዝቶለት እስሩንና የደረሰበትን በደል ተቋቁሞ መፈታቱን ተናግሯል፡፡

በተለይ በመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ተኩል አይደለም በአገር ዜጋ ላይ ቀርቶ በሌላ አገር ዜጋ ላይም ቢሆን ሊፈጸም የማይገባ በደል እንደተፈጸመበት ገልጾ፣ እስከ መጨረሻው የእስር ዘመን (ስድስት ዓመታት ከስድስት ወራት) የደረሰበት በደል የሚሰቀጥጥ በመሆኑ ማንሳት እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡ ግን ያ መስዋዕትነት እንደሚፈጸምበት አስቀድሞ ስለሚያውቅ ለመሞት ጭምር ተዘጋጅቶ እንደነበር አስረድቷል፡፡

ወንጀል ሳይሠራ ነፃ ሆኖ መወያየትና መከራከር ኢሕአዴግን እንደ መድፈርና አልገዛምና የበላይነትን እንደ ማስፋፋት ስለሚቆጠር፣ ጥቃት እንደሚደርስበት ያውቅ እንደነበር ገልጾ፣ ለነፃነት የከፈለው መስዋዕት በመሆኑ እንደማይበዛ ተናግሯል፡፡ በእሱ ላይ የደረሰው እስራት፣ በደልና ስቃይ በቀለ ገርባና ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ በሌሎችም ወገኖች ላይ የደረሰ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከማዕከላዊ ወደ ማረሚያ ቤት ሲወርድ የታሰረው አገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ አደገኛ እስረኞች በሚታሰሩበት ‹‹ቅጣት ቤት›› በሚባል ማሰቃያ ቦታ መሆኑን ጠቁሞ፣ መዳፍ በምታክል ቦታ ላይ እስከ በር ድረስ በተነጠፈ ፍራሽ ላይ በወንጀል የማይመሳሰሉ 18 ታሳሪዎች እርስ በርስ ተደራርበው፣ በተለይ ለሁለት ዓመት ተኩል መቆየቱን አስታውቋል፡፡

አቶ አንዱዓለም ወደፊት በምን ሁኔታ እንደሚቀጥል ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ስለወደፊቱ ለመናገር ገና ነኝ፡፡ ታስሬ የነበረው ምንም መረጃ በሌለበት ቦታ ነው፡፡ መጀመርያ ጆሮና ዓይኔን ከፍቼ አካባቢውን መረዳት አለብኝ፡፡ እኔ ባልነበርኩበት ጊዜ የተፈጠረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበርና የአገሪቱን ሁኔታ በጥሞና ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ፤›› ከዚያ በኋላ የራሴን ትንተና ሠርቼ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ፤›› ብሏል፡፡

አቶ አንዱዓለም እንደሚለው ሕይወት ማለት ነፃነት ነው፡፡ ነፃነት የሌለበት ሕይወት ብዙም ትርጉም እንደማይሰጠውና ህሊናው እየወቀሰው ራሱን ሳይሆን ‹‹ቀንበር›› እየሳበ በአገሩ ላይ መኖር እንደማይፈልግም ተናግሯል፡፡ ‹‹ታሪካችን ሁሉ የአገዛዝ ነው፤›› የሚለው አቶ አንዱዓለም፣ ከእነ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ ድረስ የሚደረገው ትግል፣ በተለያየ መንገድ ይገለጽ እንጂ የዴሞክራሲ ትግል መሆኑን አብራርቷል፡፡ ብዙ መስዋዕትነት መክፈሉንና አገሪቱ በአንጡራ ሀብቷ ያስተማረቻቸውን ልጆቿዋን ማጣቷን አክሏል፡፡ በዚያ ጊዜ የተጀመረው የዴሞክራሲ ምጥ አለመወለዱና አገሪቱ አሁንም ጭንቅ ላይ በመሆኗ፣ መገላገልና ታሪኳን መቀየር እንዳለባትም ተናግሯል፡፡ ያ ደግሞ የሚሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲመጣ ነው ብሏል፡፡ አንድ ሕዝብ ትልቅ ነው የሚባለው ሉዓላዊ ሲሆንና አገርም ሉዓላዊ የሚባለው ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት ሲሆን መሆኑን አቶ አንዱዓለም አስረድቷል፡፡

ከነፃነትና ዴሞክራሲ ውጪ በሚመረተው ስንዴ ብዛት ወይም ሌላ ቁሳቁስ ሕዝብን ታላቅ ማድረግ ስለማይቻል፣ ሉዓላዊነቱ መከበር እንዳለበትም አውስቷል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ ሉዓላዊነታችን ተከብሮ አያውቅም፡፡ ይኼ ትልቅ ጎደሎነትና ክፍተት ነው፡፡ አሁን ዘመን ተቀይሯል፡፡ በዚህ ዘመን አሳክተን ማለፍ አለብን፡፡ ይኼንን ለማሳካት ደግሞ ሰላማዊ ትግል ሁነኛው መንገድ ነው፤›› ብሏል፡፡ ዋጋ ቢያስከፍልም ከተመጣበት አዙሪት ተወጥቶ በሰላማዊ መንገድ መታገል አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን አክሏል፡፡ ለማሰርና ለመግደል መዘጋጀት እንደማያስፈልግ አክሏል፡፡

መንግሥት አሁን እስረኞችን መፍታቱንና ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት አቶ አንዱዓለም፣ ‹‹ኢሕአዴግ የዴሞክራሲን ነገር ዙሪያውን ሲዞረው ነበር፡፡ ከ26 ዓመታት በኋላ ግን የዴሞክራሲ እንቅፋት መሆኑን አምኗል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቹ ላይ ችግር መፍጠሩን በመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል፤›› በማለት ይኼንን ያከብርለታል፣ ያደንቅለታል፡፡ ‹‹እየገደለ ራሱን እንደ መላዕክት ከመቁጠር ስህተቱን በትክክል ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ እስረኞችንም ለመልቀቅ የመጣበት ሒደት የሚበረታታ በመሆኑ ጥሩ ነው፤›› ሲል አቶ አንዱዓለም ተናግሯል፡፡ ‹‹አሸባሪ፣ አገር ከጂና ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን መናገር ትርጉም የለውም፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከችግር መውጣት አለብን፤›› ብሏል፡፡

አንዱ እየገነባ ሌላው እያፈረሰ፣ አንዱ እየተናገረ ሌላው እየተቃወመ፣ መደማመጥና መናበብ ሳይኖር ይችህን አገር እንገነባታለንና በርቀት እናስጉዛታለን ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑንም አክሏል፡፡

ኦሮሚያ ላይ ተጀመሩት ነገሮች ጥሩ መሆናቸውንና በሌሎችም ክልሎች ‹‹የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል፤›› የሚል አስተሳሰብ መምጣት እንዳለበት የተናገረው አቶ አንዱዓለም፣ በውጭው ዓለም ያደጉት አገሮችም የፖለቲካ ልዩነት የላቸውም ማለት ሳይሆን፣ ተቻችለውና በያገባኛል መንፈስ ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ባለሥልጣናት ላይ የታየው ሆደ ሰፊነት በኢሕአዴግም ላይ ሊተገበር እንደሚገባ አክሏል፡፡

ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ አብረውት እንዲመክሩና እንዲሠለፉ ቆራጥነት እንደሚስፈልገውና ከዚህም የሚበልጥ ዕድል እንደሌለ ተናግሯል፡፡ ‹‹ከተወሰኑ አሥርት ዓመታት በኃላ ሁላችንም የለንም፤›› የሚለው አቶ አንዱዓለም፣ ግን ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የተሻለ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ መንበርከክና ማንበርከክን ትቶ ሆደ ሰፊ ሆኖ ለሁሉም የሚበጅ ነገር መሥራት ተገቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ የተፈጠረን ችግር ለማክሸፍ ብሎ ኢሕአዴግ ማሰር መፍታቱን ከቀጠለ፣ የባሰ ነገር ውስጥ እንደሚገባና አደገኛ መሆኑንም አሳስቧል፡፡ አዲሱ ትውልድ ዝም ብሎ የሚቀበል ሳይሆን ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚለወጥና ፈጥኖ አሳቢ በመሆኑ፣ በአገሪቱም ላይ አዲስ ዘመን እንዲመጣ ተባብሮና ፈጥኖ የሚያስብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መሪ አስፈላጊ መሆኑን አቶ አንዱዓለም አስረድቷል፡፡

ወጣቱ ምን ማድረግ እንዳለበት ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ ወጣቱ ንብረት ማቃጠል የለበትም፡፡ ሥርዓቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም፣ ወጣቱ ግን መጠንቀቅና ከጥፋት መራቅ አለበት፡፡ በተለይ ወጣቱ፣ ‹‹ዘረኝነት የሚሉትን ነቀርሳ መቋቋምና ማስወገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያንን ዘረኝነት አይገልጸንም፣ አይወክለንምም፤›› ብሏል፡፡ ‹‹አባቶች የዓድዋን ድል የተቀዳጁት፣ ከየአቅጣጫው ተጠራርተውና አንድ ሆነው ባደረጉት ተጋድሎ በመሆኑ፣ አብረው ሞተው አብረው የተቀበሩ እንጂ ዘር ቆጥረው አለመሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፤›› ሲል አውስቷል፡፡ ከመቶ ዓመታት በኋላ ፍቅርና ታሪክ መሥራት ይገባል እንጂ፣ ሰው ዘሩ ተቆጥሮ ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀትና ማሰብ ፀያፍ መሆኑን አክሏል፡፡ ከዘረኝነት ታቅቦ ለሰላማዊ ትግል በመሠለፍ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ተቀዳሚና ዋናው ተግባር የወጣቱ መሆን እንዳለበት አቶ አንዱዓለም አብራርቷል፡፡

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው፣ በሌሎች አገሮች የሚታየውን ዓይነት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ ለማምጣት እንደሚታገሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አዳማ (ናዝሬት) በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተገኝቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ በቀለ እንደገለጹት፣ ምንም እንኳን እሳቸው ከእስር የተፈቱ ቢሆንም በርካቶች ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለብልፅግናና ለአገር አንድነት በመጻፋቸው፣ በመናገራቸውና በመከራከራቸው ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ እስረኞች ባለመፈታታቸው የእሳቸው መፈታት ብቻ ደስታቸውን ሙሉ እንደማያደርገው ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡ ራሱን በራሱ የሚስተዳደርበት ፍትሐዊ ምርጫ መካሄድ እንዳለበትና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ጥሪም አቅርበዋል፡፡ በአገሪቱ ፖለቲካ ያገባኛል የሚሉና እምብዛም ቦታ ያልተሰጣቸው በውጭ የሚገኙ ኃይሎች፣ ወደ አገር ውስጥ ገብተው በፖለቲካው እንዲሳተፉ ጥሩ እንዲደረግላቸው አቶ በቀለ አሳስበዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ናሆም ተስፋዬ አስተዋጽኦ አድርጓል)

ሪፖርተር

Filed in: Amharic