>

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌው ህገወጥነትና የፓርላማው ሀላፊነት (ከ”anonymous”)

ስዩም ተሾመ

ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል። መከላከያ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ከሆነ በህገ መንግስቱ የተጠበቁ የተለያዩ የግለሰብና የወል መብቶች ይታገዳሉ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አዋጁን የሚያስፍጽም ኮማንድ ፖስት ይቋቋማል፤ አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆነው በመላ ሀገሪቱ ነው ተብሏል።
በዚህች አጭር ጽሁፍ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጌ ሁለት ነገሮችን ማሳየት እፈልጋለሁ። በመጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌው ህገ መንግስቱን የሚጥስ ስለሆነ ህገወጥና ተፈጻሚነት ሊኖርው እንደማይገባ አሳያለሁ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከዚህ ድንጋጌ ጋር በተያያዘ የፓርላማው ሀላፊነት ምን እንደሆነ አብራራለሁ።

1 – የድንጋጌው ህገ ወጥነት

የድንጋጌውን ህገወጥነት ለማሳየት ሁለት ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። የመጀመሪው ምክንያት የህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መጣሱ ነው። አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነገገው ከዚህ በታች በጥቅል የተቀመጡት ሁለት ነገሮች ሲከሰቱ ወይም ከሁለቱ አንዱ ሲከሰት ብቻ ነው ይላል፤

  • ሀ) የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሀገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ወይም
  • ለ) ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብ ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣

መከላከያ ሚኒስትሩ ሲናገሩ አዋጁ የተደነገገው ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ስለተከሰተና ይህን አደገኛ ሁኔታ በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት ለመቋቋም የማይቻል ስለሆነ ነው ብለዋል። ይህ አደገኛ ሁኔታ ምን እንደሆነ፣ የትና መቼ እንደተከሰተ፣ በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት ለመቋቋም የተወሰዱት እርምጃዎች ምን እንደሆኑና በማን እንደተወሰዱ የተናገሩት ነገር የለም። ነገር ግን ሁሉም እንደሚያውቀው ባለፈው ሳምንት አዋጁ በተደነገገበት ወቅት ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በሀገሪቱ ውስጥ አልተከሰተም። በኦሮምያ የተደረገውን የስራ ማቆም አድማ ማለታቸው ከሆነ፣ ስራ ማቆም በህገ መንግስቱ የተጠበቀው ሀሳብን በነጻ የመግልጽ መብት አካል እንጂ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ መጣል ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። ለዚያውም በስራ ማቆም አድማው ወቅት በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት ለመቋቋም የማይቻል ከክልሉ ፖሊስ ቁጥጥር ውጪ የሆነ አደገኛ ሁኔታ ወይም ሁከት አለተከሰተም። በተጨማሪ አንድ ክልል ውስጥ በተደረገ የስራ ማቆም አድማ ምክንያት ሌሎቹ 13 ክልልሎችና አዲስ አበባ ላይ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚደነገግበት በህግ ተቀባይነት ያለው ምክንያት የለም። ስለዚህ የሚኒስትሮች ምከር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ የሚያስፈልጉት በህገ መንግስቱ የተቀመጡት ቅድመ-ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የደነገገው በመሆኑ ከስልጣኑ በላይ (ultra vires) ሄዷል። ድርጊቱ ህገወጥ ነው። ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌው በህግ ፊት እንዳልተደነገገ ይቆጠራል (null and void ab initio)::

ሁለተኛው ምክንያት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን የማስፈጸም ሃላፊነትን ኮማንድ ፖስት ለሚባል ምንም ህገ መንግስታዊ መሰረት ለሌለው አካል አሳልፎ መስጠቱ ነው። ህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቅጽ 4(ሀ) ስር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወስጥ የተደነገገውን የማስፈጸሙ ስልጣን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው ይላል። ይህ ስልጣን ለሌላ አካል ተላልፎ ሊሰጥ አይችልም (it is not delegable)። ይህን የህገ መንግስቱን አንቀጽ የሚጻረር ማናቸውም ህግ (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ) ተፈጻሚ እንደማይሆን የህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 ይደነግጋል። ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌው በዚህ ሁለተኛ ምክንያትም በህግ ፊት እንዳልተደነገገ ይቆጠራል (null and void ab initio)።

2 – የፓርላማው ሀላፊነት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌው በ15 ቀናት ውስጥ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሁለት-ሶስተኛ ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ እንደሚሻር ህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ) ስር አስቀምጦታል። ስለዚህ ምክር ቤቱ ይህን ህገ መንግስቱን የጣሰ ድንጋጌ ውድቅ አድርጎ የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ይጠበቃል። የተውካዮች ምክር ቤት ከፍተኛው የሀገሪቱ ህግ አውጪ አካል ሲሆን ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 55 ስር ለተውካዮች ምክር ቤት እጅግ ብዙ ስልጣን (sweeping powers) ይሰጣል። የተውካዮች ምክር ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንቃት እየተገበረው ስለሆነ አሁንም ይህንኑ እንደሚተገብር ብዙዎች ተስፋ ያደርጋሉ።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ህገ መንግስቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ከሚሰጠው እጅግ ጠቃሚ (important) ስልጣን ውስጥ አንዱ በአንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 5 እና 6 ስር የተቀመጠው የአዋጁን አፈጻጸም የሚመረምር ከአባላቱና ከህግ ባለሙያዎች የተውጣጡ 7 አባላት ያሉት ተቆጣጣሪ ቦርድ የማቋቋም ስልጣኑ ነው። ክቦርዱ ስልጣንና ሀላፊነቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፤

  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፡
  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብአዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፡
  • ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብአዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ማድረግ፡

ሁላችንም እንደምናውቀው ከዚህ ቀደም የኢህአዴግ መንግስት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን አውጆ ነበር። ከአዋጆቹ ጋር ተያይዞ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ዘግናኝና ለቁጥር የሚታክቱ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙባቸው የተወካዮች ምክር ቤት ከላይ የተዘረዘሩትን ስልጣናት ተጠቅሞ የእነዚህን ዜጎች ደህንነትና ሰብአዊ መብት ሲያስጠብቅ አልታየም። በዚህ ምክንያት የተጣለበትን ሀላፊነት ሳይወጣ ቀርቶ ህዝቡን በድሏል። ይህ መስተካክል አለበት።

ለማጠቃለል፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሕገ መንግስቱን መከበር የማረጋገጥ ሀላፊነት አለባችሁ። የሕገ መንግስቱ መጣስ፣ የህዝብ መበደል፣ የኢትዮጵያ አደጋ ላይ መውደቅ ሊያስጨንቃችሁ ይገባል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌው ህገ መንግስቱን ስለሚጥስ ውድቅ አድርጉት።

Filed in: Amharic