>
5:18 pm - Tuesday June 15, 9328

‹‹ሥልጣንን መግራት!›› ( ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

 

በአሰፋ ሃይሉ

– የፕሮፌሰሩን ድንቅ ምክር ሁልጊዜም እናስታውስ
– ትልልቅ ሰዎች የማይበቅሉበት ሃገር ትልቅ ሃገር ሊሆን አይችልም።

ስለሥልጣን ወንበር ካነሳን ላይቀር በዚሁ ሳናነሳው እንዳናልፍ ብዬ ነው፡፡ ይህ የምታዩት ፎቶ የአፄ ምኒልክ የንግስና ወንበር ነው፡፡ ይህ ወንበር ከአውሮፓ የመጣ ነው፡፡ አውሮፓ ውስጥ ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች በዚህ ወንበር ላይ ተቀምጠው በራስ ቅላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚተላለፍለት የብረት ባርኔጣ ይገባላቸውና ፈጣን ሞታቸውን ይቀበሉበታል፡፡ ይህ ወንበር አውሮፓ ጥቅም ላይ በዋለ በጥቂት ወራት እኔም ሃገር ወንጀለኛ ከሚሰቀል ዘመናዊ የሆነ አውሮፓዊ ሞት ይሙት አሉና – ዘመናዊ የሆነ የሞት መቀመጫ አስመጡ፡፡ ያኔ ለአድዋ ገና ስድስት ዓመታት ይቀሩታል፡፡ ወንበሩ አውሮፓ ጥቅም ለይ ከዋለ ገና ወራት አልሞሉትም፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ ሳንሆን አንቀርም በዚህም ወንበር፡፡

ሶስት ወንበሮች ናቸው ወዳገራችን የመጡት፡፡ ምኒልክም የወንበሩን ግርማ ሞገስና ሁናቴ እንዲሁም የሞት ወንበር ስለሆነ እንዳይጎትተን እያለ ሁሉም ባለሟል ሊጠጋው ራሱ መፍራቱን ሁሉ አስተዋሉ፡፡ እና እጅግ ወደዱት፡፡ ማለፊያ ነው በሉ ሥራ ይጀምርልኝ አሉ፡፡ ከዚያ ግን ጉድ ፈላ! ለካንስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያኔ የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም፡፡ እና ወንበሩ መግደል አልችል አለ፡፡ ግን ሰው ዝናውን ሰምቶ እንደታቦት የሚነካው ጠፋ፡፡ በሉ አምጡልኝ አሉ እምዬ ምኒልክ፡፡ አንዱን ለዙፋኔ ወንበር አድርጉልኝ፤ ሁለቱን ደግሞ በወይኑና በጥዱ ጥላዎች ሥር አኑሩልኝ፤ እኔ ብቻ የምቀመጥባቸው፤ የነካቸውን የሚቀስፉ የንጉሠ-ነገሥት መንበሮች ይሆናሉ – ሲሉ አዘዙ፡፡ ያሉትም ሆነ፡፡

እኚህ ሞትን የደፈሩ ጀግና ሞት እስኪቀድማቸው በዚያ የሞት ወንበር ነበር የሚቀመጡት፡፡ ምናልባት ዘወትር ሟች፣ ኃላፊ መሆናቸውን እንዲያስታውሳቸው ይሆን? ወይስ የሥልጣንን ምንነት እንዲያስታውሳቸው ይሆን? ወይስ የተከተሉት ትውልዶቻቸው ሁሉ በሥልጣኑ ሙጭጭ ብለው እንደሚሟሟቱ በድርጊት የተገለጸ የሆነ አስፈሪ ክፉ ንግርት ይሆን? ወይስ ምን? አንድዬ ይወቅ እንግዲህ! እውነታው ግን ያ የምኒልክ ቤተመንግሥት ወንበር እስከዛሬም በጥቂቱም ቢሆን ያን ባህርዩን አለመተዉ ነው፡፡ እና ደግሞ ከዚህ በታች ላለው ጽሑፍ እንደዓይነተኛ ምስልም መግቢያም ሆኖ ያገለገለኝ በመሆኑ ተመችቶኝ ነው ማካፈሌ፡፡ ሞትን ለደፈሩት የኢትዮጵያ ጀግና ንጉሥ ታላቅ ክብርና የነፍስ ሰላምን ተመኝቼ አሁን ወደአሁኑ ጉዳያችን ልግባ፡፡

ይህ ከዚህ በታች የሰፈረው – አሁን ለአራተኛ ጊዜ የለጠፍኩት – የኢትዮጵያዊው አዛውንት ፕሮፌሰር – የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እጅግ የማደንቀውም የማከብረውም ድንቅ ጽሑፍ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ጽሑፉን ካሳተሙት 8 ዓመት ይሆነዋል፡፡ አሁን ለ4ኛ ጊዜ ስለጥፈው ነው፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ እስረኞች ሲፈቱ እርሳቸውም እንደተፈቱ ነበር – ለአጋቾቻቸውም ሲታገቱ ላስተዋላቸው ሕዝብም ለሁሉም መጪ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ይበጃል ብለው የተናገሩት፡፡ በእውነት ከታሰረና ከተንገላታ ሰው አንደበት የወጣ ቃል አይመስልም የፕሮፌሰሩ አነጋገራቸው፡፡ ሊቅ መሆን ማለት እንዲህ በተገራ አገራዊ አመለካከት ለሁሉም ጊዜ የማያልፍበትን መልዕክት ማስተላለፍ ነው እንላለን በእውነቱ ጽሑፋቸውን ካነበብን፡፡

በእውነት አሁን ከሥልጣን መንበር ላይም፤ ከሥልጣን በላይም፤ ከሥልጣን በታችም ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁሉ፤ ይህን የፕሮፌሰሩን መልዕክት ልብ ብለን ብናደምጥ፤ የእውነት ከተደቀነብን ፈተና፤ ከተደገሰልን አስከፊ ድግስ፤ በላያችን ላይ ከሚያንዣብበው አስከፊ አሞራ፤ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፈወስ እንችላለን፡፡ ይህ የፕሮፌሰሩ ድምፅ ነው፡፡ ይህ የአንድ አዛውንት ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ድንቅና በሳል ምክር ነው፡፡

የሥልጣን ወንበር እንዳይገድል፤ ተቀማጩን እንዳይዝ፤ እንዳያጋድል ከተፈለገ፤ ብቸኛው መፍትሄ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በላያችን ያነገስነውንም ሆነ፤ በልባችን ይዘነው የምንዞረውን የሥልጣን እሳቤ መግራት ብቻ ነው ይሉናል ፕሮፌሰሩ፡፡ ያ ነው ዘላቂው መፍትሄ ይሉናል እኚህ ከግራዚያኒ እስከ ዘውዲቱ፤ ከተፈሪ መኮንን እስከ ተፈሪ በንቲ፤ ከመንግስቱ ንዋይ እስከ መንግስቱ ኃይለማርያም፤ ከአማን አንዶም እስከ መለስ፤ ከኃይለማርያም እስከ አሁን ስንትና ስንት ባለተራዎች በሥልጣን ወንበር ሲቀያየሩ ያዩ አንጋፋ ምሁር፡፡ እና በሚከተለው ጽሑፋቸው ስልጣንን ስለመግራት እማኝነታቸውንም፤ ምክራቸውንም፤ ዕውቀታቸውንም፤ ቁጭታቸውንም፤ መከተል ያለብንም የአስተዋይ መንገድ እንዲህ ሲሉ ያንበለብሉታል፡፡ ለእሳቸው ከዕድሜ ይስጥዎት ምርቃትና ምስጋና ጋር- መልካም ንባብ ለሁላችን፡፡ ይኸውና-

‹‹ሥልጣንን መግራት!››

— ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፤ ከአገቱኒ መጽሐፍ፤ 2002 ዓ. ም. ፡፡

‹‹ ትልልቅ ፡ ሰዎች ፡ የማይበቅሉበት ፡ አገር ፡ ትልቅ ፡ አገር ፡ ሊሆን ፡ አይችልም ›› 
(— ከመጽሐፉ)

‹‹ ሥልጣንን ፡ ለመግራት ፡ እንድንችል ፡ በመጀመሪያ ፡ ራሳችንን ፡ መግራት ፡ አለብን ፤ ስለሥልጣን ፡ በነፍሳችን ፡ ውስጥ ፡ ሳይቀር ፡ ሳናውቀው ፡ ቋጥረን ፡ የሸሸግነው ፡ የባህል ፡ ውራጅ ፡ አለ ፤ ከመከበርና ፡ ከመክበር ፡ ጋር ፡ የተያያዘ ፡ የሥልጣን ፡ ምኞት ፣ ‹ ሲሾም ፡ ያልበላ ፡ ሲሻር ፡ ይቆጨዋል › ፡ የሚያቃጭልበት ፡ የንቅዘት ፡ ዝንባሌ ፣ ከሰው ፡ በላይ ፡ ለመሆን ፣ ያለምንም ፡ ተጠያቂነት ፡ ለመገላመጥ ፣ ለመሳደብ ፣ ለመግረፍ ፣ ለማሰር ፣ ለመግደል ፣ እጅ ፡ ለማስነሳት ፣ ያለምንም ፡ ተጠያቂነት ፡ ለመዝረፍና ፡ ለመቀማት ፣ ሕግንና ፡ ደንብን ፡ እንደፈለጉና ፡ እንደተመቸ ፡ እየለዋወጡ ፡ የግል ፡ መሣሪያ ፡ ለማድረግ ፣ — ይህንን ፡ ሁሉ ፡ የባህል ፡ ውራጅ ፡ ከውስጣችን ፡ ማራገፍ ፡ በግድ ፡ ያስፈልገናል ፤ ‹ የህግ ፡ አምላክ › ን ፡ ( ፈረንጆቹ ፡ ‹ the rule of law › ፡ የሚሉትን ፡ ‹ ለሕግ ፡ ተገዢነት › ) ፡ ማጠናከር ፡ አለብን ፤ አንድ ፡ አጥንታችንን ፡ ዘልቆ ፡ ነፍሳችን ፡ ውስጥ ፡ እንዲገባ ፡ ማድረግ ፡ ያለብን ፡ ቁም-ነገር ፡ ደንብና ፡ ሕግ ፡ የሚመሠረቱት ፡ ከጥፋት ፡ እንዲጠብቁን ፡ ነው ፡ እንጂ ፡ ለጥፋት ፡ እንዲያበረታቱን ፡ አለመሆኑን ፡ ነው ፤ …

‹‹ ስለሥልጣን ፡ ያለንን ፡ አስተሳሰብ ፡ ወደ ፡ ዘመናዊነት ፡ መለወጥ ፡ የሚያስፈልገን ፡ ይመስለኛል ፤ … በወንበሩ ፡ ላይ ፡ ያለውን ፡ ሰው ፣ ወይም ፡ ያሉትን ፡ ሰዎች ፡ መለወጥ ፡ ብቻ ፡ የሥልጣን ፡ ለውጥን ፡ አያመጣልንም ፤ የሥልጣን ፡ ወንበሩ ፡ ባሕርይ ፡ አብሮ ፡ መለወጥ ፡ አለበት ፤ የሥልጣን ፡ ወንበር ፡ በሠይፍ ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ በሕጋዊ ፡ ሥርዓት ፡ የተወጠረ ፡ እንዲሆን ፡ ያስፈልጋል ፤ ለማንም ፡ እይታና ፡ ትችት ፡ ክፍት ፡ ሆኖ ፡ ከወንበሩ ፡ ውጭና ፡ ከወንበሩ ፡ በላይ ፡ የበለጠ ፡ ኃይል ፡ መኖሩን ፡ ማመንና ፡ መቀበል ፡ ያስፈልጋል ፤ ሥልጣን ፡ በአንድ ፡ ሰው ፡ እጅ ፡ በተቋጠረ ፡ መጠን ፡ ሥልጣን ፡ ለሕዝብ ፡ የሚሰጠው ፡ ጥቅም ፡ ይቀንሳል ፤ ሕዝብን ፡ በድንቁርና ፡ ማፈን ፡ በተቻለ ፡ መጠን ፡ የሥልጣን ፡ ብልግና ፡ ሥር ፡ እየሰደደ ፡ ይሄዳል ፤ … ሥልጣን ፡ ርስት ፡ ወይም ፡ ርስተ-ጉልት ፡ አይደለም ፤ የሚነቀልና ፡ የሚተከል ፣ የሚለዋወጥ ፡ ነው ፤ የሥልጣን ፡ ምንጭ ፡ ሕዝብ ፡ ነው … ፤ የሥልጣን ፡ ባህርይ ፡ ምንጊዜም ፡ ሕጋዊ ፡ መሆን ፡ ያስፈልገዋል … ፤ ሥልጣን ፡ ወደፊት ፡ እያየ ፡ የሕዝብን ፡ ኑሮ ፡ ለማሻሻል ፡ የሚጥር ፡ እንጂ ፡ ወደኋላ ፡ እየተመለከተ ፡ በበቀልና ፡ በጥላቻ ፡ ጊዜንና ፡ ጉልበትን ፡ የሚጨርስ ፡ መሆን ፡ የለበትም ፡፡

‹‹ አንድ ፡ ነገር ፡ መረዳት ፡ ያለብን ፡ ኢትዮጵያውያን ፡ ለሥልጣን ፡ ያደረብን ፡ ምኞት ፡ ሥር ፡ የሰደደ ፡ በመሆኑ ፡ ለእኩልነት ፡ የመጣውን ፡ ቁም ፡ ነገርም ፡ ወደ ፡ ሥልጣን ፡ መለኪያ ፡ እንለውጠዋለን ፤ ለምሳሌ ፡ በደርግ ፡ ዘመን ፡ ‹ ጓድ › ፡ የሚለው ፡ ቃል ፡ ከሶቭየት ፡ ኅብረት ፡ ተተርጉሞ ፡ የመጣልን ፡ ሁላችንንም ፡ ለማስተካከል ፡ ነበር ፤ ነገር ፡ ግን ፡ አንዳንድ ፡ የቀበሌ ፡ ሎሌዎች ፡ ደብዳቤ ፡ ሲጽፉ ፡ ከፊርማቸው ፡ ሥር ፡ ‹‹ጓድ›› ፡ ይሉ ፡ ጀመር ፤ ትንሽ ፡ ቆይቶም ፡ ‹‹ ጓድነትዎ ›› ፡ ማለት ፡ ተጀምሮ ፡ ነበር ፤ በዚህም ፡ ምክንያት ፡ ጓድ ፡ የሚለው ፡ ቃል ፡ ዓላማ ፡ ፈጽሞ ፡ ተበላሸ ፡፡

<<አንድ ፡ ጊዜ ፡ ሬስቶራንት ፡ ውስጥ ፡ አሳላፊውን ፡ ለመጥራት ፡ ድምፄን ፡ ከፍ ፡ አድርጌ ፡ ‹‹ጓድ!›› ፡ ብዬ ፡ ስጠራ ፡ የነበሩት ፡ [የሥርዓቱ] ፡ ሎሌዎች ፡ በሙሉ ፡ ወደኔ ፡ ዞር ፡ አሉ ፤ በኋላ ፡ አንዱ ፡ የማውቀው ፡ መጥቶ ፡ ‹‹ አውቀህ ፡ እኛን ፡ ለማዋረድ ፡ ብለህ ፡ አይደለም ፡ አሳላፊውን ፡ ‹‹ ጓድ ›› ፡ ያልከው ? ›› ፡ በማለት ፡ ጥርጣሬዬን ፡ አረጋገጠልኝ ፤ በሱ ፡ ቤት ፡ አሳላፊውን ፡ ‹‹ ጓድ ›› ፡ በማለቴ ፡ ከፍ ፡ ሳደርገው ፡ ‹ የክብር ፡ ወይም ፡ የሥልጣን ፡ ስማቸውን › ፡ ለሌላ ፡ በእሱ ፡ ግምት ፡ ለማይገባው ፡ ሰው ፡ በመስጠቴ ፡ ሎሌዎቹን ፡ ደግሞ ፡ አዋርጃለሁ ፡ ማለት ፡ ነው ! ይህ ፡ የበሽታ ፡ መግለጫ ፡ አይደለም ?

‹‹ … አሁን ፡ ሥልጣንን ፡ ወደ ፡ መግራቱ ፡ ሀሳቤ ፡ ልመለስ — አንደኛው ፡ ዋና ፡ ነገር ፡ ራሳችንን ፡ መግራት ፡ ነው ፡ ብያለሁ ፤ ሁለተኛ ፡ ሥልጣንን ፡ የመግራቱ ፡ ዘዴ ፡ ወይም ፡ ሥልት ፡ ሲቀየስ ፡ ያለፈውን ፡ የሥልጣን ፡ ብልግና ፡ የምንነቅፍበትና ፡ ከአለፈው ፡ ወደ ፡ አዲሱ ፡ የሚተላለፍ ፡ ምንም ፡ የቂምና ፡ የክፋት ፡ ነገር ፡ እንዳይኖር ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ በክብሩ ፡ ዋስትና ፡ የሚሰጥበት ፡ ፍፁም ፡ አዲስ ፡ ምዕራፍ ፡ እንዲሆን ፡ ያስፈልጋል ፤ ጥላቻን ፡ አቅፈን ፡ ወደ ፡ ፍቅር ፡ ልንደርስ ፡ አንችልም ፤ ጥፋትን ፡ እያሰብን ፡ ልማትን ፡ ማካሄድ ፡ አንችልም ፤ ያለፉት ፡ ሠላሳ ፡ ዓመታት ፡ ይህንን ፡ ካላስተማሩን ፡ ከባድ ፡ ችግር ፡ አለብን ፡ ማለት ፡ ነው ፡፡

‹‹ እንደሚመስለኝ ፡ ሥልጣንን ፡ የመግራቱን ፡ አስፈላጊነት ፡ የሚቃወም ፡ የለም ፤ ችግሩ ፡ ያለው ፡ እንዴት ፡ ሥልጣንን ፡ እንግራ ? በሚለው ፡ ዘዴ ፡ ላይ ፡ ነው ፤ እንደሚመስለኝ ፡ በዚህም ፡ ላይ ፡ ቢሆን ፡ ችግሩ ፡ ያለው ፡ በዘዴው ፡ ላይ ፡ ሳይሆን ፡ ባለመተማመን ፡ ላይ ፡ ነው ፤ ወይ ፡ እንደደቡብ ፡ አፍሪካ ፡ ታላላቅ ፡ ሰዎች ፡ የሌሉበት ፡ ማኅበረሰብ ፣ ወይም ፡ ( በአፍሪካ ፡ ሌላ ፡ አገር ፡ መጥራት ፡ ስለሚያስቸግር ) ፡ እንደደቡብ ፡ አፍሪካ ፡ ታላላቅ ፡ መንፈሳዊ ፡ መሪዎች ፡ የሌሉበት ፡ ማህበረሰብ ፣ ወይም ፡ እንደምዕራባውያን ፡ አገሮች ፡ ጋዜጠኞችና ፡ ምሁራን ፡ ነቅተው ፡ እየተጠባበቁ ፡ ሕዝቡን ፡ የሚያነቁበት ፡ ማኅበረሰባዊ ፡ መዋቅር ፡ በሌለበት ፡ የሥልጣን ፡ ተቀናቃኞችን ፡ ጥርጣሬና ፡ ሥጋት ፡ ለማስወገድ ፡ ያስቸግራል ፤ በአሁኑ ፡ ጊዜ ፡ ትልቅ ፡ ሰውነትን ፡ በተመለከተ ፡ ኢትዮጵያ ፡ ምድረ-በዳ ፡ ሆናለች ፡ ለማለት ፡ ይቻላል ፤ … ፡፡

‹‹ […] ፍላጎቱ ፡ ካለን ፡ ግን ፡ ትልልቅ ፡ ሰዎችን ፡ ማፍራት ፡ እንችላለን ፤ ከአሉን ፡ አንዳንድ ፡ ሰዎች ፡ ውስጥ ፡ የተደበቀ ፡ ትልቅነትን ፡ ማውጣት ፡ እንችላለን ፤ እምነታችንን ፡ ልንጥልባቸው ፡ የምንችልባቸው ፡ ሰዎች ፡ ጥቂት ፡ አይደሉም ፤ … በማንኛውም ፡ የፖሊቲካ ፡ አመለካከት ፡ ውስጥ ፡ ያሉ ፡ ሊታመኑና ፡ ሊከበሩ ፡ የሚችሉ ፡ ሰዎች ፡ በኢትዮጵያም ፡ ውስጥ ፡ በውጭ ፡ አገሮችም ፡ አሉ ፤ ልባችንን ፡ ለርህራኄና ፡ አዕምሮአችንን ፡ ለቀና ፡ አስተሳሰብ ፡ ከአዘጋጀን ፡ ትልልቅ ፡ ሰዎችን ፡ በማፍራት ፡ ኢትዮጵያን ፡ የትልልቅ ፡ ሰዎች ፡ አገር ፡ እናደርጋታለን ፤ ትልልቅ ፡ ሰዎች ፡ የማይበቅሉበት ፡ አገር ፡ ትልቅ ፡ አገር ፡ ሊሆን ፡ አይችልም ፤ ትልቅነት ፡ በመወለድ ፡ መሆኑ ፡ ቀርቷል ፤ አሁን ፡ ደግሞ ፡ ትልቅነት ፡ በሥልጣን ፡ መሆኑን ፡ እናስቀረው ፤ እነዚህ ፡ ትልልቅ ፡ ሰዎች ፡ ሌሎቻችንን ፡ እንድንደማመጥ ፣ እንድንከባበርና ፡ እንድንተማመን ፡ በጣም ፡ ይረዱናል ፤ ነገር ፡ ግን ፡ ትልቁና ፡ ዋናው ፡ ነገር ፡ ለእነዚህ ፡ ትልልቅ ፡ ሰዎች … ፡ የሚሰጠው ፡ ልባዊ ፡ ክብር ፡ ነው ፤ […] ፡፡

‹‹ ኢትዮጵያ ፡ እጆችዋን ፡ ወደእግዚአብሔር ፡ ታደርሳለች ፤ እርስበርሳችሁ ፡ ከመዋደድ ፡ በቀር ፡ ለማንም ፡ ዕዳ ፡ አይኑርባችሁ ፤ ሌላውን ፡ የሚወድ ፡ ሕግን ፈጽሞታልና ፤ ስለዚህ ፡ ፍቅር ፡ የሕግ ፡ ፍጻሜ ፡ ነው ፡፡ ›› ( — ሮሜ ፡ 13 ፥ 8 )››

— የጽሑፉ ምንጭ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡- ‹‹አገቱኒ – ተምረን ወጣን››፤ ገጽ 134-138፣ እና ገጽ 3 የተወሰደ፤ ደራሲው፡- መስፍን ወልደ ማርያም (ፕ/ር)፤ ታተመ፡- አዲስ አበባ፤ 2002፡፡ ዓ.ም.

— የምስሉ ምንጭ (አሁንም እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡- የኢትዮጵያ ንጉሥ መንበረ-ዘውድ፤ <<The Emperor’s Electric Chair, 1890>>፡፡

ሥልጣንን እኛው ራሳችን በቅን ልቦና ተነስተን እንግራው፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን በምህረቱ በቸርነቱ አብዝቶ ይባርክልን፡፡ ኢትዮጵያ እናታችን ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ለፕሮፌሰሩ ረዥም እድሜን ይስጥልን፡፡ አበቃሁ፡፡

Filed in: Amharic