>

በግሌ የሕገመንግሰቱ ድንጋጌ እንዲከበር፤ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሻር እጠይቃለሁ!!! (ግርማ ሠይፉ ማሩ)

ፓርላማ ማለት እንደ እኛ አገር የጥያቄና መልስ መድረክ ባልሆነባቸው አገሮች፤ ፓርላማ የሃሣብ ፍጭት ማድረጊያ መድረክ ነው፡፡ የፖለቲካ ስንክሳር ማወራረጃ መድረክ ነው፡፡ ውጤቱ ደግሞ የሚታወቀው ከሃሣብ ፍጭት በኋላ በሚደረግ ድምጽ አሰጣጥ ሰነስርዓት ነው፡፡ በድምፅ መሸነፍና ማሻነፍ የክበር ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ መድረክ ላይ አብላጫ ድምፅ ማግኘትም ያለመግኘትም የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ሃሣቡ ለጊዜውም ቢሆን ተቀባይነት አላገኝም ማለት ነው መወራድ ማለት አይደለም፡፡ ማንኛውም ሃሣብ ትክክልም ቢሆን ተቀባይነት ካላገኘ፤ ለሌላ ጊዜ ይከርማል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በእኛ አገር ይህ ጉዳይ “ክብረ ነክ” ሆኖ እየታየ ነው፡፡ በምክር ቤት ሃሣብን በተቃውሞ ማሰማት እንደ ችግር ይታያል፡፡ መንግሰት ተብዬው ያመጣውን ማንኛውንም ሃሣብ ሁሉ ተቀባይነት ካላገኘ፤ ተደፈርኩ ብሎ ቡራ ከረዩ ይላል፡፡ ጂኒ ጅቡቲ (አፈንዲ ሰታይል) ያበዛል፡፡
አሁን ማን ይሙት አፈጉባዔ አባዱላ በዚህ ደረጃ ለመዋረድ ዝግጁ መሆን ነበረባቸው፡፡ ዛሬ በጠዋት አንድ ጋዜጠኛ ደውሎልኝ፤ ስብሰባው ሲጀመር በስበሰባ 490 አባላት ሰለተገኙ ስብሰባውን ማካሄድ ይቻላል ብለው አፈ ጉባዔው ሲናገሩ ሰምቻለሁ አለኝ፡፡ አላምንህም አልኩት፡፡ እንዳምንህ በድምፅ የተቀዳ መረጃ እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡ ይህ መረጃ ያለው ሰው መረጃውን ለህዝብ ይፋ ያድርግ፡፡ ይህም ቢሆን ግን የተፈጠረውን ስህተት ሊያርም አይችልም፡፡ በነጥብ በነጥብ ላስረዳ፤ ፍላጎት ላለው፡፡
በፓርላማ ስብሰባ የተገኙት ሰዎች 490 ከሆኑ እና ድምፅ ሲሰጥ የቁጥር ስህተት አለ ከተባለ፣ (395-346=49) 49 ድምፅ ስህተት የተፈጠረው ለደጋፍ ነው ለማለት ምንም መሰረተ የለውም፡፡ ሰለዚህ ሰህተቱ በተቃውሞ ለነበሩትም ሊሆን ይችላል (88+49=137 ተቃውሞ ሊሆን ይችላል)፡፡ መቼም በሰባት ድምፀ ተዓቅቦ 49 ሰህተት ሊሆን አይችለም በሚል ማለፍ ይቻላል፡፡ ወይም ደግሞ 49 ድምፅ ቆጠራ ሰህተቱ በድጋፍም በተቃውሞም በተሰጠው ቆጠራ ሊከፋፈል ይችላል፡፡
ሌላው ቁም ነገር ስብሰባው ሲጀመር 490 ሰው ተገኝቶ ነበር የሚለውን እንመን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰብሰባውን አጠናቆ ድምፅ ሰጥቶ ሊወጣ አይችልም፡፡ ይህ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በአጭሩ ያልቃል ያሉት ስብሰባ ሲራዘም ቀጠሮ ይዘው የመጡ ሌላ መስሪያ ቤት የሚሰሩ የምክር ቤት አባላት ስብሰባውን ጥለው ይወጣሉ፡፡ ሰለዚህ እነዚህ ሰዎች ድምፅ አልሰጡም፤ ድምፃቻ በስብሰባ ሰለተገኙ ብቻ አይቆጠርም፡፡ ሌላም ጉዳይ አለ፤ በምክር ቤት ውስጥ ያሉ አባላት በወቅቱ በድጋፍ፤ በተቃውሞም ወይም በተዓቅቦ ድምፅ ባለመስጠትም ላይሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ሲሆን ምክር ቤቱ ከመበተኑ በፊት ይህን አረጋግጦ ድጋሚ ቆጠራ በማድረግ ማስተካከል ነበረበት፡፡ ይህን አላደረገም፡፡ ሰለዚህ በዚህ ሁኔታ ድምፅ ያልሰጡ ሰዎች ሁኔታውን አወሳስበውት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ውጤቱ አዋጁ በሁለት ሶሰተኛ ድምፅ አልተደገፈም ከማስባል ውጭ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ ሰለዚህ በምክር ቤት 490 ሰዎች ተገኝተዋል በሚል በድጋፍ ድምፅ የሰጡትን አባላት ቁጥር በማሳደግ 395 ማድረስ በህግም በአሰራርም ተቀባይነት የለውም፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ “ማንኛውም ዜጋ፤ የመንግሰት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፤ ህገመንግሥቱን የማስከበርና ለህገ መንግስቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለበት” በሚለው አንቀጽ 9/2 መሰረት ሁሉም ዜጋ ምክር ቤቱም ሆነ መንግሰት ሕገመንግስቱን እንዲያከብሩ ጫና ማሳደር ይኖርበታል፡፡
በግሌ የሕገመንግሰቱ ድንጋጌ እንዲከበር፤ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሻር እጠይቃለሁ፡፡ ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒሰትር በሚሰይመው ምክር ቤት አሰፈላጊ ነው ተብሎ ከታመነበት በድጋሚ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ አማራጭ ሃሣቤን አቀርባለሁ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ይህን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር በእሳት እንደመጫወት የሚቆጠር አደገኛ ሙከራ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሕገ መንግሰት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የፓርቲን አጥር አልፈው ለህዝብ የለውጥ ፍላጎት ተገዢ ለመሆን የቆረጡ የምክር ቤተ አባላት “የተከበሩ” የሚለው ማዕረግ ደረጃ ለመድረስ እየሞከሩ መሆኑን በክብር እገልፃለሁ፡፡ ለህዝብ ክብር መሰጠት እና የተከበሩ መባል ትልቅ ነገር ነው፡፡ “የተከሩት i” በሚል ያዘጋጀሁትን መፅሃፍ በሸልማት የምሰጣችሁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እገልፃለሁ፡፡
Filed in: Amharic