>
5:18 pm - Saturday June 15, 3101

<አዬ ጉድ>ን አታበላሽ ለባሰ ቀን ይሆንሃል!!! (ደረጀ ደስታ)

ኢትዮጵያ ውስጥ ድሮ ጽሑፍ ሳንሱር ይደረግ ነበር። አሁን ግን ቀርቷል። ምክንያቱም ዛሬ ሳንሱር የሚደረገው ጸሐፊው ወይም ሰውየው ራሱ ነው። ብዙ ብንሞክርም ሳንሱር የወደቅን ሰዎች ለመረጃ ቅርበት የሌለን በመሆናችን አንዳንዴ ላልተጨበጠና ላልተረጋገጠ ወሬ እንጋለጣለን። መረጃን ከምንጩ አጣርተን ለመመዘን ይቸግረንና ጋዜጠኝነት ያልተከፈለ እዳ ይሆንብናል። በዚህ የተነሳ ከባለሥልጣናቱ አረቄና ከትፎ ቤት ሰበር ዜና እሚቀበሉ ተቺዎቻችን አሉባልታ ታወራላችሁ ይሉናል። እውነታቸውን ነው። እውነታቸውም እውነት መስሎን አሉባልታስ ከመጻፍ ብለን አርፈን ተቀምጠን ነበር። አርፈንም በተቀመጥንበት እያቃጠሉ አንገበገቡን። ግን አሁን ስናየው ለካ መንግሥት ራሱ አገር እሚመራው በአሉባልታ ኖሯል። ውሸቱማ ጆሮ ቆርጦ ይጥላል። እኛን ትዋሻላችሁ ሲሉን ከርመው ታዲያ አሁን እነሱም ሽምጥጥ ማድረጋቸው ለምንድነው? ወይስ ውሸትም እንጀራ ሆና በእንጀራችን መግባታቸው ነው? ይህን ማለታችን ዝምብለን አይደለም። ኢህአዴጎቹ ለሁለት ተከፍለዋል ሲባል ለካ በእውነትና በውሸት ነው። አንዳቸው ለምተናል ሲሉ ሌሎቹ ወድመናል እያሉ ነው። አንዳቸው ጠግበናል ሲሉ ሌሎቹ ርቦናል እያሉን ነው። አልቀናልና መጥቀናልም አለበት። አንዳቸውን ማመን የግድ ከሆነ መቸም ከሁለት አንዳቸው ውሸታቸውን ነው። ግን እንዲታወቅልንና እንደኛው ሳንሱር የወደቁ ጓደኞቻችን ማወቅ ያለብን ነገር፣ ይህን ወሮ የበላ መንግሥት ለማጋለጥ ውሸት መናገር እማያስፈልግ መሆኑን ነው። እንኳን ያልሆነውን ጨምረን የሆነውን ራሱ ተናግረን እሚያምነን ብናገኝ ጥሩ ነው። ምክንያቱም አንዳንዱ እውነት ከመዘግነኑ፣ ከማሳቁ፣ ከማሸማቀቁ የተነሳ አሁን ይህን ብናገር ይህን ብጽፍ ማን ያምነኛል ያሰኛል። ስለዚህ ምርጫችን ከውሸትና ከእውነት ሳይሆን፣ ሊታመን ከሚችል እና ከማይችለው እውነት ሊሆን ነው ማለት ነው። እሱ ባልከፋ ነበር። ግን ይሄን በዘበዛ መንግሥት ከአናታችን ማውረድ ያቃተን ለምን ይሆን እሚለውን እውነትና ውሸት አጥርተን ይዘን ይሆን? ወይስ እሱ ነገር እውነት ወይስ ሐሰት – ብለው እሚገላገሉት ቀላል ጨዋታ አይደለም። በጠቅላላው ነገረ ፖለቲካችን ሁሉም የየራሱን እውነት ይዞብን ከመጣ ግን ምን ይኮናል? እውነት ዓይን አዋጅ ሲሆንኮ ግራና ቀኝ ማየት ነው እንጂ አስቸኳይ አዋጅ አይገላግለውም። “አዬ ጉድን አታባለሽ ለባሰው ቀን ይሆነሃል!” ማለት ይሄ ነው።

Filed in: Amharic